Wednesday, December 29, 2010

“ቆሞስ አዲስ ቤተ ክርስቲያን መባረክ አይችልም” ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ

ቅዱስ ገብርኤል ሠለስቱ ደቂቅ(ሦስቱ ህፃናትን) ከእሳት ያወጣበት በቤተ ክርስቲያናችን የጊዜ ቀመር(አቆጣጠር) መሠረት በማድረግ ታህሣሥ ፲፱(19) ዓመታዊ የመታሰቢያ በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተለይም የቅዱስ ገብርኤል የመታሰቢያ ጽላት ባለበት አጥቢያ በደማቅ ተከብሮ ውሎዋል::

Saturday, December 11, 2010

ብፁዕ አቡነ ማትያስ አሜሪካ ገቡ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ እዚህ አሜሪካን ሀገር ገብተዋል:: ብፁዕነታቸው ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል ቤተ ከርስቲያን የገጠማትን ዘመን ያልዋጀ አሰራር በመተቸት የሚታወቁ ናቸው:: በባለፈው ዓመት ከአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደሰማናቸው ከሆነ ቤተ ክርስቲያን ዘመናዊ የአስተዳደር መርህ እንድትከተል እንዲሁም ደግሞ ቅዱስ ፓትርያኩ እየፈጸሙት ያለው ጥፋት እንዲያበቃ ጠንከር ያለ ትችት እና ተግሳጽ አሰምተው ነበረ::

Friday, December 3, 2010

“ነጭ እንቁ በአዳም ገላ” የተሰኘው መጽሐፍ የዲሲ ማኅበረ ካህናትን አጋለጠ

የዋሽንግተን ዲሲ ማኅበረ ካህናት ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያምን በተመለከተ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አስተምህሮ ጋር ያላቸው ልዩነት የገለጹበት መረጃ የያዘ መጽሐፍ በገበያ ላይ ዋለ:: “ነጭ እንቁ በአዳም ገላ” በሚል ርእስ በመምህር ሀብተ ማርያም ተድላ የተዘጋጀው መጽሐፍ የዛሬ ስድስ ዓመት በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ “በገለልተኛ አስተዳደር ሥር” ያሉት በወቅቱ ማኅበረ ካህናት ተብሎ ይጠራ የነበረው በእመቤታችን አስተምህሮ ከኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ጋር ያላቸውን ልዩነት የሚገልጽ የተፈራረሙበት ሙሉ መረጃ አካቶ ኢትዮጵያ ውስጥ በገበያ ላይ ውሎዋል::

Thursday, November 18, 2010

የዋሽንግተን ዲሲ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ውዝግብ ቀጥሎዋል

ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በአካባቢያችን በቁጥር 20 ከሚሆኑት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል “ገለልተኛ” አስተዳደር ሥር ነን ከሚባሉት መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል::  አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን አሁን በሚያስተዳድረው ቦርድ እና “የምእመናን ተቆርቋሪዎች ነን” በማለት ራሱን የሚጠራ ቡድን  መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን አሁንም ቀጥሎዋል::

Sunday, October 17, 2010

የመናፍቃን ጭፈራ በእኛ ነዋያተ ቅዱሳት

“የቀደሙት ኢትዮጵያውያን የተዋሕዶ አበው ለኢትዮጵያ ሀገራችን ብሎም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘማናት የማይሽሩዋቸው ሀብቶችን አውርሰውን አልፈዋል። ከእነዚህም መሀከል በጥቂቱ  ፊደል ከነ ሙሉ አግባቡ፣ የዘመን አቆጣተር፣ የሀገር ድንበር ጠብቆ መኖር፣ ሥነ ጽሑፍን፣ሥነ ኅንፃን እናም ሌሎችም የሚጠቀሱ ናቸው” (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ )። እነዚህ አበው በተለየ ሁኔታ ሐዋርያዊት ለሆነችው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በደማቸው ቀለም በጥብጠው ቅዱሳት መፃህፍት ደርሰው እንዲሁም ተርጉመው፤ የዜማ መሳሪያዎች ከነ ሚስጥራቸው እና ትርጓሜያቸው፤ እንዲሁም ንዋያተ ቅድሳትን በየዘርፉ ለያየተው አስቀምጠውልን አልፈዋል። ለእነዚህ ቅዱሳን አበው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅድስናን ሰጥታ ለዘላለም ስታዘክራቸው ትኖራለች።

ዛሬ ይኅን ጽሑፍ ለመፃፍ ያስገደደኝ ኢትዮ ትዩብ በሚለው ድህረ ገጽ http://www.blogger.com/%28http://www.ethiotube.net/video/8669/Yetsidiq-Tsehay-Ethiopian-Gospel-Singers%29%20ላይ መናፍቃኑ ቅዱሳን አበው ያስረክቡን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለተለያዩ አገልግሎት የምትጠቀምባቸው ንዋያተ ቅድሳት እና የዜማ መሳሪያዎችን ይዘው ሲጨፍሩ በማየቴ ነው። እነዚህ መናፍቃን ባገኙት አጋጣሚ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያንቋሽሹ ሰምተናቸዋል እየሰማንም ነው። እንዲሁም የቅርብ ግዜ ትዝታችን “ አቡነ ያሬድ” ነኝ በማለት አንድ መናፍቅ በጵጵስናን ማዕረግ ላይ ሲቀልድ እና ሲያንቋሽሽ አይተናል። ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮያ ያበረከተችውን አስተጽኦ ከምንም ሳይቆጥሩ ለኢትዮጵያ ድህነት ተጠያቂዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ናት ሲሉም በዝምታ አልፈናቸዋል።

Friday, October 15, 2010

ቅዱስ ሲኖዶስ

ኅበረ ቅዱሳን ድኅ ገጽ የተወሰደ::
በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባዔ ጌታ በሚያውቃት ዕለት ይህች ዓለም ታልፋለች፡፡ እንደ ቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ ይህ ዓለም ካለፈ በኋላ የማይጠፋ እና የማይለወጥ የዘለዓለም መኖሪያ የሆነ ሌላ ዓለም ደግሞ አለ፡፡ ያም የእግዚአብሔር መንግሥት ነው፡፡ የሰውን ልጆች ለእግዚአብሔር መንግሥት የምታበቃው እውነተኛዋ ፍኖት ደግሞ ክርስትና ናት፡፡ /ኤር 6.16/ እርሷም አንዲት ናት፡፡ የተሰጠችውም ፈጽማ አንድ ጊዜ ነው፡፡ /ይሁዳ 1-3/

Sunday, October 10, 2010

“ሐውልቱ” በመዲናችን በዋሽንግተን ዲሲም እየተሰራ ነው

በዋሽንግተን ዲሲ የምትገኘው ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዛሬ መስከረም 30፣ 2003 ዓ/ ም ከሥርዓተ ቅዳሴ በኋላ የሽልማት ስነስርዓት በዓል ተከብሮ ውሎዋል:: ተሸላሚዎቹም ከካህናት በኩል ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ኅይሌ ሲሆኑ ከምእመን ወገን ደግሞ ዶ/ር አክሊሉ ኀብቴ ናቸው:: ሽልማቱም የረዥም ግዜ አገልጋዮች በሚል ነው:: ሸላሚው በግንቦት ወር መጨረሻ አካባቢ ሊቀ ሊቃውንት በቨርጂኒያ ዉድ ብሪጅ ቤተ ክርስቲያን ባርከው የከፈቱለት ዲ/ን ጌታሁን ነው:: እንግዲህ የቅዱስ ፓትርያርኩ ሸላሚዎች እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፤ ሊ/ካህናት ጌታቸው ዶኔ ፤ዲ/ን በጋሻው ደሳለኝ እና ሌሎች የጥቅም አጋሮቻቸው ሲሆኑ፤ እዚህ ሀገር የግብር ጓዳቸው ሸላሚው ዲ/ን ጌታሁን እና ምን አልባትም ሌሎች የጥቅም አጋሮቹ ተባብረውታል::

Friday, September 24, 2010

"ቤተ ክርስቲያን የግሌ ናት ካሉ፤ ትንሽ ቆይተው አምላካችሁ እኔ ነኝ እንዳይሉ መፍራት ነው"

(ከአብነት ብርሃኔ)
እንደው የቤተ ክርሰቲያናችን ነገር ምን ቢደርግ ይሻላል፡፡ እኛም እያየን መቃጠል ሆነ፤ እነሱም "ምን ታመጣላችሁ"?  የሚል መንፈስ ልባቸውን ደፍኖት መጫወቻ አደረጉዋት እኮ፡፡ ደጆችሽ አይዘጉ የተባለችውን ቤተ ክርስቲያን የፈለኩት ይግባ፤ ያልፈለኩት አይግባ ተብሎ በፖሊስ የሚጠበቅበት ጊዜ ላይ ደረስን፡፡ ለነገሩ ኃይለኛ የገንዘብ ጥማት ያላቸው ምድራዊውን ብቻ የሚያስቡ ገብጋቦችና ራስ ወዳዶች ናቸው የተሰገሰጉባት፤ከውስጥ በልቶ የማይጠግብ መዥገር ተጣብቆ ይመጣታል፤ ከውጭ አረማውያን ያደሙዋታል፤መቼም የሚተኛላት አልተገኘም፡፡

Tuesday, September 21, 2010

በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የሐመረ ኖኅ ኪዳነምሕረት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እና አገልጋዮች ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በሙሉ የይድረሱልን ጥሪ አስተላለፉ


ይህች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በአካባቢያችን በገለልተኛ ስም ከተዋቀሩት አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት ምድብ ውስጥ ቢሆንም፤ ነገር ግን በአንድ ግለሰብ ባለቤትነትና ፈላጭ ቆራጭነት ይተዳደራል:: ይህንን ችግር ያስመረራቸው የአጥቢያው ምእመናን እና አገልጋዮች  በአካባቢው ለሚገኙት ምእመናን እንዲሁም ለተዋሕዶ ልጆች በሙሉ እሮሮዋቸውን ያሰሙበት ጽሑፍ በአካባቢያችን ተሰራጭቶ ነበር::   የጽሑፉ ሙሉ ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል::
+++

Tuesday, August 31, 2010

አህጉረ ስብከቶቹ ዘመናዊ የአስተዳደር መርህ መከተል አለባቸው

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን  ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ በተዋረድ የሀገር ስብከት ቤተ ክህነት እና የወረዳ ቤተ ክህነት ትልቁ ችግራቸው ዘመናዊ የአስተዳደር መርህ መከተል አለመቻል ነው። ይህም ቤተ ክርስቲያን ዘመንን የዋጀ የአስተዳደር መርህ እንዳትከተል አድርጓታል። በዚህም ምክንያት የተባላሸ እና በጣም ኋላ ቀር የሆነ አስተዳደር በቤተ ክህነታችን ላይ ሰፍኖ ይታያል።

Wednesday, August 11, 2010

መፍትሔዬ:- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዲያስጶራው ዓለም ለምትገኝበት ትርምስምስ

ይህ ጽሑፍ ከዚህ በፊት በደጀ ሰላም ላይ አቅርቤው ነበረ። አሁንም ወቅታዊ መስሎ ስለታየኝ እዚህ ላይ በድጋሚ ቀርቦዋል።
+++
ሰሞኑን ባቀረብኩት የቤተ ክርስቲያናችን ችግር ላይ አንዳንድ ጽሑፉን ያነበቡ ደጀ ሰላማውያን “የምናውቀውን ችግር ደግመህ ለምን ትነግረናለህ? መፍትሔው ነው የጠፋው” በማለት ስለጠየቁኝ፤መፍትሄ እንኳን ባይሆን ለመወያያ ይሆነን ዘንድ አንዳንድ ነጥቦች ለማስቀመጥ ተገድጃለሁ። በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እኛው የፈጠርነው ይህ ሁሉ ትርምስምስ በዘለቂው ለመፍታት “ከ40 ሚሊዮን የተዋህዶ ልጆች መሀከል በደጀ ሰላም ድረ ገጽ የምንወያይ ሰዎች ብቻ ልንፈታው አንችልም” የሚሉ ደጀ ሰላማውያን ሊኖሩ ይችላሉ፤ ለእግዚአብሔር ምን ይሳነዋል በቅንነት እና ለእውነት ከተወያየን እንፈታዋለን የሚል ተስፋ አለኝ። ለእኔ የታዩኝ አንዳንድ ለችግሮቹ መፍትሄ ይሆናሉ የምላቸው ነጥቦችን ለውይይት እንዲያመቸን አቅርቢያለሁ።

Monday, August 2, 2010

የማንም ደጋፊ አይደለሁም

አንተ የማን ወገን ነህ? የማንስ ደጋፊ ነህ? የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ደርሰውኛል። እኔ የማንም ደጋፊ ወይም የማንም ወገን አይደለሁም፤ ነገር ግን የተሰቀለውን ክርስቶስ አምነው ከተቀበሉ የተዋሕዶ ልጆች መሀከል አንዱ ነኝ። የቤተ ክርስቲያን ህጓ፣ ሥራዓቷ እና ቀኖናዋ ተጠብቆ ለትውልድ ይተላላፍ ብለው ከሚጮሁት ብዙ ተዋሕዶአውያንም መካከል አንዱ ነኝ። እስኪ ከዚህ በፊት በደጀ ሰላም ላይ ያቀረብኳቸው አንደንድ ጽሑፎች፦

Friday, July 30, 2010

እምነታቸው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተሳሰባቸው የፕሮቴስታንት…….መጨረሻቸውስ?

በአውሮጵያውያን አቆጣጠር በ1517 አካባቢ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሮም ውስጥ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል መልሶ ግንባታ ስትጀምር በወቅቱ የሮማን ካቶሊክ መሪ የነበሩት ፖፕ ሊዮን ፲(Pope Leo X )፤ ዮሐን ቴትዝልን (Johann Tetzel) የመላው ጀርመን ኮሚሽነር በማድረግ ሾመውት ነበረ። ዮሐን ቲትዝል የዶመኒካ ተወላጅ ሲሆን፤ስርየተ ሀጥያት (selling indulgences) በገንዘብ  እንደሚገኝ አጥብቆ ያስተምር ነበር። ይህን አስተምህሮ ለታላቁ ካቲድራል ግንባታ አገልግሎት ገቢ ለማሰባሰብ እጅግ ጠቀሚታ ነበረው፤እንዲሁም በየ ዕለቱ በአደባባይ ለሀጥያት ስርየት በሚቀመጡ ሳጥኖች ብዙ ገንዘብ ይሰበሰብ እንደነበር መዛግብት ያትታሉ። በዚህ ጊዜ ነው የፕሮቲስታንቱ እምነት መስራች ማርቲን ሉተር በተቃውሞ የተነሳው። የማርቲን ሉተር ተቃውሞው በብዛት አስተዳደራዊ ጥያቄ ነበረ፤ለምሳሌ ለተቃውሞ በፃፈው በሰማንያ ስድስተኛ አንቀጹ (“Why does the pope, whose wealth today is greater than the wealth of the richest Crassus, build the basilica of St. Peter with the money of poor believers rather than with his own money? የፖፓው ሀብት ከባለሀብቱ ቄሳር በልጦ እያለ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል በራሱ ገንዘብ ማስገንባት ሲችል እንዴት የድሀው አማኝ ገንዘብ ይፈልጋል?”) በማለት ጠይቆ ነበረ።

Thursday, July 29, 2010

የዲሲ ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማሪያም ቤተ ክርስቲያን የማን ናት?

የዳንኤል እይታዎች ድህረ ገጽ ላይ “የብርጭቆው ወይስ የምንጩ ውኃ” ሳነብ ብዙ ትዝታዎች ቀሰቀሰብኝ። እኔ ያለሁበት አካባቢ ዘመነ መሳፍታዊ የቤተ ክርስቲያን ክፍፍልም ተምልሼ እንዳየው አደረገኝ። ገጠመኜም አውጥቼ እንድናገር ተገደድኩኝ። ዲ/ን ዳንኤል የእኛ አካባቢ እንዲህ በማለት ገልጾታል “በውጭ ሀገር እየኖረ ይህንን እቃወማለሁ የሚለው ወገኔም ቢሆን ቤተ ክርስቲያኑን በታቦቱ ስም ከመጥራት ይልቅ በወንዙ እና በጎጡ መጥራት የሚቀናው ነው፡፡ «የነ እገሌ ቤተ ክርስቲያን» የሚባል ኑፋቄም፣ ዕብደትም የሆነ አመለካከት እንደልቡ እጁን ከትቶ የሚጓዘው እዚያው ባሕር ማዶ ነው”፡፡ ድንቅ ገለጻ! ።

Wednesday, July 21, 2010

ማንን እንምረጥ?

“የምን ምርጫ? የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ መሮታል” እንደምትሉኝ አልጠራጠርም። ይሄኛው ምርጫ ለየት ይላል። የምርጫው ተፎካካሪዎች የሚወዳደሩት መራጮችን መንግስተ ሰማያት ለማስገባት ነው። ምርጫው የሚካሄደው በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ነው። ይህ ምርጫ በሚገርም ሁኔታ ዘወትር ከሚደረገው የምርጫ ጫወታ ይለያል፤ ምክንያቱም የምርጫ ቦርድ የለውም። እንዲሁም የምርጫ ታዛቢም የለውም፤ ታዛቢው ግን የመራጮቹ ህሊና ብቻ ነው። መራጮቹም ማንን መምረጥ እንዳለባቸው የሚወስኑት በሚቀርብላቸው አገልግሎት ነው። አካባቢውን ለማያውቁ መራጮች(እንግዶች) ግን የመምረጥ እድል አያገኙም። እነዚህ እንግዶች የሚጓዙት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያገኙት ሰው በመረጠላቸው ምርጫ ነው። እናም መራጮቹ ግራ የተጋቡ ይመስላሉ፤ምክንያቱም የምርጫው ተፎክካሪዎች(ተወዳዳሪዎች) ሁሉም “እኔ ትክክል ነኝ” እያሉ መራጮቻቸውን ለመሳብ ይሯሯጣሉ፤ ፉክክሩም መራጮችን መንግስተ ሰማያት ለማስገባት ነው።

Friday, July 16, 2010

በስደት የትውልድ ሓላፊነት

 ይህ በአካባቢያችን ስለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን በተመለከተ በማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ ላይ የተገኘ ጽሑፍ ነው።
የማህበረ ቅዱሳን ድህረ ገጽ ፦የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሐዋርያት የፈጸሙትን ተግባር ቀዳሚ ሥራዋ አድርጋ የዘመናትን ድንበር እየተሻገረች አገልግሎቷን ስታከናውን ቆይታለች፡፡ የወንጌልን ብርሃን ላልደረሳቸው ሁሉ ታደርሳለች፡፡ ተምረው ያመኑትን፤ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቀች፤ የመንፈስ ቅዱስን ልጅነት እንዲያገኙ፣ በክርስቶስ ክርስቲያን እንዲሆኑ ታደርጋለች፡፡ በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪ በመላው ዓለም በዝርወት /በስደት/ ያሉ ልጆቿን እስከመጨረሻው ትጠብቃለች፡፡ የዘላለማዊው ሕይወት የሰማያዊው መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑም ታበቃለች፡፡

Wednesday, July 14, 2010

በእውነት የፓትርያርኩ ሥርዓት አልባ መሆነ እኛን ከእውነተኛ መንገድ እንድንወጣ አስተዋፆ አለውን?

 “እናንተ እኮ ዝም ብላችሁ ነው የምትለፉት፤ የእኛ አባቶች ይሄንን አውቀው ነው ገለልተኛ የሆኑት” በማለት አንዲት እህቴ በምታገለግልበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ካህናት እያመፃደቀች፤ እኔም በቤተ ክርስቲያን ላይ ያለኝን አቋም እንድቀይር ሽንጣን ገትራ ተከራከረችኝ።ይህ እንግዲህ ሰሞኑን በዜና  እየተሰራጨ ያለው የፓትርያርክ ጵውሎስ ሥርዓት አልበኝነት ምክንያት በማድረግ ነው ክርክሩ የመጣው። በእውነት የፓትርያርኩ ሥርዓት አልባ መሆነ እኛን ከእውነተኛ መንገድ እንድንወጣ አስተዋፆ አለውን? የሚለው ጥያቄም ተደጋግሞ ይነሳል።   ምንም እንኳ ፓትርያርኩ ከህግ ውጪ ሆነው ቢንቀሳቀሱም እኛም የእርሳቸው ፈለግ ተከትለን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጣስ ተገቢ ነውን? እንግዲህ ከላይ የጠቀስኳት እህቴ “የእኛ ገለልተኛ አባቶች ትክክል ናቸው” አለችኝ። እውነት ትክክል ናችውን? መልሱን ለአንባቢው ልተወው።

Friday, July 9, 2010

የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በዲሲ ምን ይመስላል?

በተለምዶ ዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ብላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ያዋቀረችው ወደ ፲፭ (አሥራ አምስት) ክፍለ ግዛቶችን (እስቴቶች) ይደርሳሉ ። ነገር ግን በሀገሩ መንግስት ስያሜ መሰረት ዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚባሉት ዲሲ፣ ቨርጂኒያ እና ሜሪ ላንድ ናቸው። ይህ ጽሑፍም የሚዳሥሰው በተዋቀረው ሀገረ ስብከት ሁሉ ሳይሆን በሀገርሩ መንግስት ስያሜ መሰረት በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ብቻ ይሆናል።

Friday, July 2, 2010

“ገለልተኛ ”፣ "ስደተኛ” ፣ ”እናት” ቤተ ክርስቲያን

“ገለልተኛ” ፣"ስደተኛ"፣ “እናት” ቤተ ክርስቲያን የሚሉ በወቅቱ እየተዘወተረ የሚነገሩ በቤተ ከርስቲያናችን ላይ ተቀጽላ ሥያሜዎች ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ለውይይት ሲቀርብ የማያስደስታችው ወገኖች አሉ፤ እንደውም "ሚስጥራቸን በአደባባይ ማውጣት ይሆናል" ብለውም ያስባሉ። ሚስጥርነቱ  ምን ላይ ነው?የተለያየ ቅዳሴ መቀደሳችን እንደሆነ ያመኑት የተርዋሕዶ ልጆች ቀርቶ ያላመኑትም ቢሆን አውቀውታል። ተቃውሞው ይህ ብቻ አይደለም ቤተክርስቲያን ስላለችበት ሁኔታ መነጋገር "ልዩነትን መስበክ ነው"፤ በማለትም የሚያስወሩ ወገኖችም አልጠፉ። ተለያይተናል እኮ ፤ከዚህ በላይ ልዩነት ምን ይመጣል? ጥያቄው “ምን ብናደርግ” ወደ አንድነት መምጣት ይቻላል?የሚል ነው። መለያየታችን ግን የአደባባይ ሚስጥር ነው።

Monday, June 28, 2010

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዲያስጶራው ዓለም ለምትገኝበት ትርምስ ተጠያቂው ማን ይሆን?

  ጃኑዋሪ 5, 2010 በደጀ ሰላም  ላይ አቅርቤው የነበረ ጦማር “የእኔ እና የእናንተ አባቶች ንጽህት ሐይማኖት ከሙሉ ሥርዓቱ ጋር እንዲሁም ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሳያፋልሱ፤ ከቀደሙት አባቶቻቸው የተረከቡትን፤ ለእኛ አስረክበውናል። ለእኔ እና ለመሰሎቼ። በመንፈስ ቅዱስ ለምንወልዳቸው ልጆቻችን እናንተ ደግሞ በሥጋ ለምትወልዱዋቸው ልጆቻችሁ በዚህ በዲያስጶራው ዓለም ምን ዓይነት ቤተ ክርስቲያን አስረክበናቸው ልናልፍ ይሆን?”።

“እስክንድር ከሆንክ እንደ እስክንድር ተዋጋ፤ ካልሆነ ደግሞ ስሙን መልስ”

December 23, 2009 በደጀ ሰላም  ላይ አቅርቤው የነበረ ጦማር ፦በሰሜን አሜሪካ የኢ/ኦ/ተ/ቤ ካህናትና ምዕመናን ጉባኤ መግለጫ ሳነብ የተዘበራረቀ ስሜት ተሰማኝ። ምክንያቱም በዘንድሮ ጉባኤአቸው ላይ ታሪካዊ ውሳኔ ያሳልፋሉ ብዬ ጠብቄ ነበረ። እነዚህ በተለያዩ ግዛት የሚገኙት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በአስተዳደር ብልሹነት ምክንያት የአቡነ ጳውሎስ አስተዳደር እንደማይቀበሉ፤ ነገር ግን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች እንደሚቀበሉ በተለያዩ መድረኮች ሲገልፁልን ቆይተዋል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ በአንዳንድ ብፁአን አባቶች አማላካችነት ቤተ ክርስቲያናችን ከብልሹ አስተዳደር እንድትፀዳ ጥያቄው ቀርቦዋል። ይህም ጥያቄ በሒደት ላይ መሆኑን በተለያዩ የህዝብ መገናኛ ብዙሀን ሰምተናል። ታዲያ ችግራቸው የአስተዳደር ብልሹነት ከሆነ ጥያቄው አሁን በውስጥም ስለተነሳ “እኛም ከዚህ በፊት ያነሳነው ጥያቄ ስለሆነ ከእናንተ ጋር ነን፣ አብረንም እንዋጋዋለን” በማለት ግልፅ የሆነ ውሳኔ ለምን አላሳለፉም?።

ዲ/ን ተስፋዬ መቆያ ለምን ተቆጣ?

ውድ እህትና ወንድሞቻችን እኛ በምኖርበርት በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሰሞኑን “የተከፈተው” ቤተ ክርስቲያን ላይ መነጋገሪያ እየሆነ ነው። በምድረ አሜሪካ ቤተ ክርስቲያን “መከፈት” አዲስ ነገር ባይሆንም፤ነገር ግን ይሄኛው ለየት ያደርገው በደጀ ሰላም የቤተ ክርስቲያን አመሰራረት በተመለከተ የሀሳብ ልውውጥ መጀመሩ ይመስለኛል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ሁለት ጎራዎችም በተለያየ መንገድ አቋማቸውን ፍንትው አድርገው እያሳወቁም ነው ። አንደኛው ወገን በማንኛውም መንገድ ቤተ ክርስቲያን “ይከፈት” እንጂ “የእግዚአብሔር ቃል ለምዕመን ከደርሰ ችግር የለውም” የሚል ሲሆን፤ሌላኛው ወገን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን መመስረት ያለባት “ሐዋርያዊ ትውፊት ጠብቃ የቀደሙት አባቶቻችን ባስቀመጡልን ህግ መሰረት መሆን አለበት” የሚል ነው። ታድያ የትኛው ነው ትክክል? መልሱን ለአንባብያን እንተወው።

የህንድ ቤተ ክርስቲያን ለእኛ ምሳሌ መሆን ትችላለችን?

December 19, 2009 በደጀ ሰላም   ላይ አቅርቤው የነበረ ጦማርአንድ አባት በምገለገልበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በመድረክ ቆመው የህንድ ቤተ ክርስቲያንን እድገት ምሳሌ እየጠቀሱ ስለ እኛ ቤተ ክርስቲያን እድገት ሲያስተምሩ በጥሞና ተመስጬ እያደመጥኩ አእምሮዬ ወዲያው ጥያቄ አቃጨለብኝ “የእኛ ቤተ ክርስቲያንስ የት ናት”?። እኚሁ አባት ስለምግባባቸው ከመድረክ በኋላ ጥያቄም አቀርብኩላቸው። “ለመሆኑ ዛሬ የተማርነው ትምህርት ለእኛ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ይመለከታታል ወይ?፤ እርሶ እንዲቴት የህንድ ቤተ ክርስቲያንን በምሳሌነት ሊጠቅሷት ቻሉ”? ብዬ በትህትና ጥያቄዬን ሰነዘርኩ። እሳቸውም “ልጄ ምን ማለትህ ነው?፤ የህንድ ቤተ ክርስቲያን እኮ ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር እህት ናት፤ ስለዚህ የህንድ ቤተ ክርስቲያን እድገት ለእኛ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ምሳሌ መሆን ትችላለች” አሉ። ጥያቄን በፈለኩት መልኩ ስላልመለሱልኝ በድጋሚ ማብራራት ጀመርኩ።

ኮሚኒስታዊው ኢትዮጵያዊ ትውልድ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን

ኖቬምበር 16/2009 በደጀ ሰላም ላይ አቅርቤው የነበረ ጦማር  ፦“የራሱን ሀብትና ማንነት የማያከብር ሕዝብና ተቋም በቁሙ የሞተ ነው” በሚል በነመራ ዋቀዮ ቶላ የቀረበውን ጽሑፍ ሳነብ ልቤ እጅጉን ተነክቷል። ይህንኑ የደጀ ሰላም ጦማሪ ሀሳብ መነሻ በማድረግ እኔም መጦመር እንኳ ባልችልም ስሜቴን ግን ለመግለጽ ብዕሬን ለማንሳት ተገድጃለሁ። ባለፉት 40 ዓመታት ቤተ ክርስቲያናችን የአስኳላውን ትምህርት ተምሬያለሁ በሚለው በማርክሳዊና በሌኒናዊ ትውልድ እጅጉን ተፈትናለች። እንዲሁም አሁንም ‘በተረፈ’ ኮሚኒስቶች እየተፈተነችም ትገኛለች።