Monday, June 28, 2010

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዲያስጶራው ዓለም ለምትገኝበት ትርምስ ተጠያቂው ማን ይሆን?

  ጃኑዋሪ 5, 2010 በደጀ ሰላም  ላይ አቅርቤው የነበረ ጦማር “የእኔ እና የእናንተ አባቶች ንጽህት ሐይማኖት ከሙሉ ሥርዓቱ ጋር እንዲሁም ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሳያፋልሱ፤ ከቀደሙት አባቶቻቸው የተረከቡትን፤ ለእኛ አስረክበውናል። ለእኔ እና ለመሰሎቼ። በመንፈስ ቅዱስ ለምንወልዳቸው ልጆቻችን እናንተ ደግሞ በሥጋ ለምትወልዱዋቸው ልጆቻችሁ በዚህ በዲያስጶራው ዓለም ምን ዓይነት ቤተ ክርስቲያን አስረክበናቸው ልናልፍ ይሆን?”።

ይህንን ቃል የወሰድኩት ብፁዕ አቡነ አብርሃም የዋሽንግተን ዲሲ እና አከባቢዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በዓለ ልደት ንግስ ላይ በምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ውስጥ ካስተላለፉት መልዕክት ነው። እኔም ከዚህ በፊት በተለያዩ ርዕሶች በዚሁ በደጀ ሠላም አስታያየት መስጫ ቦታ ላይ ያነሳሁት ጥያቄ ስለሆነ፤ እንዲሁም ደግሞ ዛሬ እኔ የምኖርበት ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሀሳቡን ስለደገሙት በጣም ደስ ብሎኝ ለውይይት ይሆነን ዘንድ ለደጀ ሠላማውያን ላቀርበው ተገደድኩ። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዲያስጵራው ዓለም ለምትገኝበት ትርምስምስ ተጠያቂው ማን ይሆን? ይህ እንግዲ ብዙዎች እውነተኛ የተዋህዶ ልጆች የሚያነሱት ጥያቄ ነው። መልሱን ግን ሁላችንም ለራሳችን እንደሚመስለን ወይም እንደሰማነው ልንመልሰው እንችላለን። አንዳንዶች አቡነ ጳውሎስን ተጠያቂ ያደርጋሉ፤ ሌሎች ደግሞ አቡነ መርቆርዎስን ተጠያቂ ያደርጋሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ሁለቱን ኮሚስት መንግስታትን ማለትም ደርግ እና ኢሀዴግን ተጠያቂ ያደርጋሉ።አንዳንዶች ደግሞ እነዚህ የተጠቀሱት ሁሉንም ተጠያቂ የሚያደርጉም አሉ። የዚህ የመወያያ ሀሳቤ ዓላማ ለትርምስምሱ ተጠያቂዎች መልስ ለማግኘት አይደለም። መልሱን ለቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊዎች ሊቃውንት እተወዋለሁ።

በተለያዩ የመወያያ ርዕሶች በዚሁ በደጀ ሠላም እንደገለጽኩት እዚህ አካባቢ በኢ/ኦ/ተ/ቤ ሥም የሚጠሩ 18 (አስራ ስምንት) አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ። ከነዚህ 18ቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አንዱ የምስራቀ ፀሐይ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ከተቋቋመ ገና ሰባተኛ ወሩ መሆኑን በበዓሉ ላይ ተገልፆልናል። ዛሬ በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የምዕመናን ብዛት እና የበዓሉ ድምቀት ሲታይ ግን የሰባት ወር ዕድሜ ያለው አጥቢያ አይመስልም። ይህ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በመቃኞነት በኪራይ ቤት እንኳ ቢቋቋምም ነገር ግን የኢ/ት/ኦ/ተ/ቤ ቀኖና እና ቃለ ዓዋዲ እንደሚያዘው ለመጀመሪያ ግዜ በዚህ አካባቢ በኢ/ኦ/ተ/ቤ ስም እና ባለቤነት የተመዘገበ መሆኑንና በሀገረ ስብከት መተዳደሩ ከሌሎቹ አጥቢያ ልዩ ያደርገዋል። በዚህ አካባቢ ቆይታዬ የታዘብኩት ነገር ቢኖር በየ ዓመቱ የጥምቀት እና የመስቀል በዓል ሲደርሱ የአንዳንድ አጥቢያ አብያተ ከርስቲያናት አስተዳዳሪዎች እየተሰባሰቡ በዓሉን ለማክበር ብቻ ብለው ምዕመናንን ተታርቀናል፣ ሠላም ሰፍኖዋል፣ አንድ ሆነናል፣ አጨብጭቡ፣ እልል በሉ የተለመደ ሆኖዋል። ነገር ግን አንድነቱ ሲዘልቅ አናየውም። ዛሬም ከላይ በገለጽኩት ደብር ክብረ በዓል ላይም ሌሎች አጥቢያ አብያተክርስቲያናት እንደሚያደርጉት ሊቀ ጳጳሱ በዚሁ በዓል የተገኙት የተለያዩ አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ት ቤት እየዘረዘሩ ተናግረው ሳይጨርሱ እልልታውና ጭብጨባው ቀደመ። የየደብሩ ሰንበት ት/ት ቤት አባላት ተገናኝተው በአንድ ላይ መዘመራቸው ባልቃወምም ለአንድነታችን መሰረት ሊሆን ግን በፍፁ የሚችል አይመስለኝም። የአድነታችን መሰረት ሊሆን የሚችለው እያንዳንዱ ምዕመን እንዲሁም አገልጋዮች የጥንታዊቷ እና ሐዋርያዊቷ የኢ/ኦ/ተ/ቤ የቀደሙት አባቶች ያስረከቡንን አስተተዳደራዊ መዋቅር ጠንቅቀ ስናውቀው እና ስንተገብረው ብቻ ነው። አንድነታችን የሚመጣው በችግሮቻችን ተነጋግረን በተቀመጠልን መዋቅር ሥር ስንጠለል ነው። አለበደዚያ ግን የተወሳሰበ እና የተበጣጠሰ የፕሮቴስታንቱን ዓይነት ቤ/ክ በግለሶቦች እና በድርጅቶ ስም እንዲሁም ባለቤት ለልጆቻችን አስተላልፈንላቸው እናልፋለን። እኛ የፈጠርነው ችግር ልጆቻችንስ ይፈቱት ይሆን?። ወይስ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚለውን አባባል እየተገበርነው ያለው ተግባር ከቀጠለ፤ ይኼኛውም ዳግም አጥፊው ትውልድ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከወቀሳም ከውገዛም የሚያልፍ አይመስለኝም።

ይህ የቤተ ክርስቲያናችን የአስተዳደር መዋቅር ት/ት የተለያዩ ሰባኪያን ወንጌል እዚህ እኔ የምኖርበት አካባቢ አያነሱትም፤ እንዲሁም እንደ ጦር የሚፈሩትም ይመስለኛል። ግን አስከ መቼ ፈርተነው ልንኖር?። እንግዲህ ይህ በማለቴ አንዳንዶች እንደተለመደው ቅጥያ ስም በማውጣት “ወያኔ የአባ ጳውሎስ ደጋፊ” እንደሚሉኝ አልጠራጠርም ምክንያቱም እዚህ ሀገር ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንዲሁም ስለ ቀኖና ቤተክርስቲያን መናገር “የወያኔነት” ተቀጽላ ስም ማግኘት የተለመደ ሆኖዋል። እንዲሁ በተመሳሳይ በሀገራችን በኢዮጵያም በቤተ ክርቲያኒቱ ላይ እየተፈፀሙ ያሉት በደሎች መናገር ደግሞ “ጽንፈኛ ተቃዋሚ” የሚል ቅጥያ ሥም ከማስገኘትም አልፎ በወንጀል ያስፈርዳልም። ስለዚህ ወገኖቼ ዓይናችን ወደ እውነት ያለመሸነጋገል እየተያየን ከመጥፎ ታሪክ ተጠያቂነትም እንድንድን የእውነቱን መሰረት ይዘን ብንወያይበት መልካም ይመስለኛል።

6 comments:

Wongelawi Birhanu said...

Bravo Abel Kedamawi! This is a great start. we all are besides you and insist you use this blog only and only for the benefit of our mother church Hawaryawit, Alemakefawit, One(ahati) and Kidist Orthodox tewahedo church

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የቅድስት አርሴማ ቤ/ክ said...

+ + +

Dear our brother! thank U very much! for your initiation to start the blog and all the issues are really true, Let God help you to be the light in the darkness around us.

Unknown said...

Dear brother,

I appreciate your effort to give us some insight about what is going on in the name of our church in the DC area. You tried to present the facts and raise legitimate and logical questions. I would also be happy if those brothers and sisters, who did the reported thing, to give us their perspective so that we can have a clear and balanced understanding of what happened and why that happened before we make our own judgements and decisions. According to what you wrote here it is a clear violation of the biblical teaching and law of our church to establish a new church without a blessing from a bishop, which have been done for the last 2000 years even with hard times, like the problem we have with Coptic Church. We might have disagreements and differences with the adminstration and some people on top positions, but I believe that we all believe in one church established by our Lord and built by His deciples and saints. This church has been kept alive by the sacrifice of millions of Martyres and our ancestors. We all accept the dogma and kenona of this Holy Church. So the question here is why are we doing this terrible thing which has the potential to distract our unity and sprituality? I believe not matter what happened in the adminstration or whoever the Church is the Church, in other words, the laws are still right and important and we need to abide by the law.Individuals might be wrong but the rules and the laws of the church are right. We do not need to break a law to correct mistake done by somebody else. We need to focus on how to keep our unity and protect our church from its antagonists rather than distracting. Dear brothers and sisters in DC area, especially those who establish a new "church" in a wrong way, please try to think about tomorrow, try to think about our kids, and grand kids, try think abour the quensequence of our actions. Please try to have a good heart for our mother church and not always forget the sacrifices of our ancestors. The way you are going and doing things will not solve our problems, it would rather fuel the fire to burn more and cause more damage. Lets try not to follow our instinct but our heart, not our emotions but our Lord, not our personal ambitions but our kids and grand kids. I would like to remind you that these days will pass and all the curses will pass together. And yet there is another day, another year, another century, another time to come and lets focus on how to make that time more bright and less problematic than today. Let us stop condemening eachother and start a healthy and constructive discussion. Let us put aside our diffeerences and start praying together. Let us stop our personal egos and listen to what other fathers, brothers, and sisters are saying. Then will come a prosperous and blessed part of our time. Otherwise it is even hard to imagine the future.

May God bless all of us and give us a good heart
Amen

Your little brother

Unknown said...

እንደ እኔ አመለካከት

ችግሩን እየፈጠረ , እያባበሰና እያወሳሰበ ያለው :
ማኅበረ ቅዱሳን ነው ብዬ በጽኑ አምናለሁ ::

ምክንያቶችም

1. ብዙዎቹ አባላቱ የቤተ ክርስቲያን ዕውቀታቸው ለብ ለብ ስለሆነና : ሁሉንም ነገር እንደሚያውቁ አድርገው ራሳቸውን ስለሚቆጥሩ
በዚህም ሰበብ ሊቃውንቱን ሁሉ በነሱ ጠባብ ዓይን ብቻ በመወሰን : ይህንም የጎላ ድክመት : ለአባላቱ ሁሉ ስለሚያስተላልፉ ::

2. አንዳንድ አባላቱ : ሳይማሩና ሳይበቁ ቄስና ዲያቆን እየተባሉ :
ከነሱ አባላት ውጭ የሆኑ ሌሎች ካህናትን : በአድማና በስም ማጥፋት እያሳደዱ : ቤተ ክርስቲያንን ለብቻቸው ለመቆጣጠር በሚያደርጉት የተሳሳተ አካሄድ ምክንያት ::

3. ከነሱ አባላት ወይም ከማኅበሩ ዕውቅና ውጭ አንድ ሰው ምንም ዓይነት ሥራ ለመሥራት ሲነሳ : የተለያዩ የመጠላለፊያ ደንቃራዎችን በመፍጠር : ምንም ዓይነት እንቅስቃሴዎች እንዳይደረጉ : ሁሉንም ጠቅልሎና ገድቦ ለመያዝ በሚያደርጉት የቡድን ተቃውሞና : ጭፍን ድጋፍ

4. አራት ኪሎ ላይ ለሚገነቡት ፓላስ ማሰሪያ በማለት : የተለያዩ አባሎቻቸውን በየአብያተ ክርስቲያናቱ : አስርገው በማስገባት : የሚሸጡ ንዋያተ ቅድሳቱንም ሆነ ሁሉንም የገቢ /የልማት ምንጮች ሁሉ ለመቆጣጠር በሚያደርጉት የስግብግብ ሩጫ ::
በመሠረቱ የሚሠራው ህንጻ ; ከቤተ ክርስትያኗ ዕውቅና ውጭ የሚካሄድና ባለቤቱም በግልጽ የማይታወቅ : የጥቂት ብልጦች የግል ንብረት መሆኑ ግልጽ ነው ::

5. ማኅበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ :
በውጭ አገራትም ይሁን : በአገር ውስጥ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ (በሲኖዶሱ መካከልም ይሁን በየአጥቢያዎቹ ) ለሚፈጠረው ብጥብጥም ትርምስ : ጠንሳሹና ተንኳሹ : ራሱ ማኅበሩ ነው :

ለምሳሌ : በሁለቱ አባቶች ምክንያት በተከፈለው የቤተ ክርስቲያን መካከል የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ : ከወዲያ ከወዲህ ወሬ እያመላለሱ ለውግዘት እንዲደርሱ ለማድረግ ብዙ እንደ ደከሙ ራሳቸው አባላቱና ጽ /ቤቱ በሚገባ ያውቀዋል

ከሰሞኑ አንዳንድ ቅን አሳቢ ሰዎች በቅንነት ተነሳስተው በአባቶች መካከል እርቅ እንዲፈጠር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን በመቃወም በደጀ ሰላም ላይ የተከተበውና የማኅበረ ቅዱሳንን አቋም የሚያንጸባርቀውን ጽሑ አንብበናል ::
ምክንያቱም :
እርቅ ከተደረገ : ራሳቸውን ደብቀው ሲሰሩት የነበረው ተንኮል እንዳይጋልጥባቸው በመስጋት ;

እርቁ ከተካሄደም : በመሃል ሆነው የሚያምታቱት ቅሰጣ ስለሚገታባቸውና : ከጨዋታ ውችጭ እንደሚሆኑ በሚገባ ስለሚገነዘቡ መሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው ::

በአጠቃላይ :
የቤተ ክርስቲያንን ችግር ለመፍታትና ሰላማዊ አገልግሎት እንዲካሄድ ከተፈለገ
ማኅበሩ ; ጣቱን በሌሎች ላይ በመቀሰር ሳይሆን : ራሱን በመርመርና ; ስህተቱ እያረመ በማስተካከል ምሳሌ እየሆነ መሆን አለበት ::

እውነተኛ ውይይት ከፈለጋችሁም : ይህን ዓይነቱን አስተይየት ለንባብ በማብቃትና ግልጽነታችሁን በማሳየት :
ስለሆነ :
የምታደርጉትን ለመታዘብ እንጠብቃለን ::

samueldag said...

በስመ፡አብ፡ወወልድ፡ወመንፈስቅዱስ
አሀዱ፡አምላክ
አሜን፡፡
ሀዋርያት፡በሰበሰብዋት፡በአንዲት፡ቤተክርስቲያን፡እናምናለን፡፡
ቤ/ክ፡ትምህርትዋ፡አገልግሎትዋ፡ሁሉ፡በየትም፡ቦታ፡ብትሆን፡አንድ፡ነው፡፡ባለቤትዋና፡መስራችዋ፡አካልዋ፡ልዑል፡አምላክ፡ኢየሱስ፡ክርስቶስ፡የማይለወጥ፡ዘላለማዊ፡ስለሆነ፡ጎርፍ፡ብጎረፈ፡ቁጥር፡እምነትዋ፡ስርዐትዋ፡ትውፊትዋ፡አይለወጥም፡፡ዕብ13:7-9 ማንም፡በልቡ፡ፈቃድ፡ሀሳቡን፡ሊጭንባት፡አይገባም፡፡
ቤ/ክ፡በሀገረ-አሜሪካ፡አሁን፡ያለበትን፡ሁኔታ፡መነጋገር፡መልካም፡ነው፡፡በስደት፡ሀገር፡ህዝቡን ፡የሰበሰቡት፡ሲያጽናኑት፡የነበሩት፡ካህናትና፡ዲያቆናት፡እንዲሁም፡ምእመናን፡ምስግና፡ይገባቸዋል፡፡ቅዱስ፡ዮሀንስ፡መንገዱን፡ጠርጎ፡ሙሽራው፡ሲመጣ፡ደስታው፡እንደተፈጸመ፡ነገረን፡፡ዮሀ 3፡28-30 እንጅ፡እኔ፡ብርሀን፡ነኝ፡አላለም፡፡ያከበረው፡አምላክ፡በ ማት 11፡11 ላይ፡መሰከረለት፡፡እኛም፡ለቀደሙት፡ምስጋናችን፡የሚቀጥለው፡የቀደመውን፡ተዋህዶ፡እምነትን፡እና፡የቤ/ክ፡አንድነት፡ይዘው፡እስከተገኙ፡ድረስ፡ብቻ፡ነው፡፡እዚህ፡ያሉ፡የቦርድ፡አባላትና፡ማህበረ፡ካህናት፡ለቤተክርስቲያን፡አንድነት፡ያለድርድር፡ያለቅድመሁኔታ፡በደስታ፡ሊታዘዙ፡ይገባል፡፡እንደዚህ፡ከሆኑ፡እንደ፣ቅዱስ፡ዮሀንስ፡ምስጋና፡ይገባቻዋል፡፡እኛ፡ምእመናን፡ከእናት፡ቤተክርስቲያንና፡አንድነትዋን፡ከማይቀበሉትና፣የሀዋርያትን፡አሰረፍኖት፡የሚይፋልሱትን፡ተው፡ልንላቸው፡ይገባል፡፡
በዚህ፡አገር፡ላደጉ፡ልጆቻችን፡ቦርዱ፡ይሆን፡ድቁና፡የሚሰጥልን? ወይስ፡ገለልተኛ፡ነን፡የሚሉት፡ዲያቆናት፡አገልግሎታቸው፡በዚሁ፡ተወስኖ፡ይቀራል? ወይስ፡ቦርዱ፡እንደደመወዛችው፡ሊወስን፡ይሻ፡ይሆን?
ለማጠቃለል፡ቤ/ክ፡አንድ፡ነች፡፡ይህችውም፡መንበርዋ፡በቅድስት፡ሀገር፡በኢትዮጵያ፡ያለችው፡ነች፡፡ምእመናን፡የሚመጣውን፡መዘዝ፡በእምነት፡መነጽር፡ተመልክተን፡ወደቤታችን፡ልባችን፡ሊመልስ፡ይገባል፡፡የእግዚአብሄር፡ቸርነት፡በእመቤታችን፡አማላጅነት፡አንዲቱን፡ተዋህዶ፡ሀይማኖታችንን፡ይጠብቅልን፡፡
ሀይለገብርኤል reston va

Anonymous said...

በስመዓብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድማችን ቃለ ህይወት ያሰማልን መንግስቱን ክብሩን ያውርስልን!!
ያነሳኸው ሃሳብ ወቅታዊ ነው በዚህ በሰሜን አሜሪካ የኃይማኖታችን መሰረት መናጋቱና እውነተኛዋ ቤተ-ክርስቲያን ሰሚ ማጣቷ አሳዛኝ ነው ። ለዚህ ተጠያቂዎቹ ደግሞ እኛ ልጆችዋ ነን። ዶግማዋ፣ ስርዓቷ፣ ቀኖናዋ፣ ትውፊቷ ሲበላሽ እያየን በማን አለብኝነት አስመስለን የምናልፍ ችግሯ ችግራችን ህመምዋ ህመማችን እንዳይደለ ሁሉ እውነትን መናገር ፈርተን ከሰው ጋር ለመኖር ጥሩ ለመባል ስንል በድፍረት መናገር ያቃተን ወኔ ቢስ ልጇቿ ነን። ምዕመናን እውነተኛዋ ቤተ-ክርስቲያን ማን እንደሆነች እንዳያውቁ ልዩነቱን የሚናገር ደፋር ከየት ይምጣ? ግለሰቦች ስርዓተ ቤተ-ክርስቲያን በመጣስ ምዕመናንን በማደናገር ፖለቲካዊ ጥማታቸውን የግል ፍላጎታቸውን ያረኩባታል አይ ይሄ ልክ አይደለም አልቀበልም ማለት ከመጣ ደግሞ ታቦቱ የኛ ቤተ-ክርስቲያኑ የኛ ለቀህ/ሽ ውጣ/ጪ ይመጣል አሊያም አድማና አሉባልታው ይበራከታል ታዲያ መቼነው ቤተ-ክርስቲያን ከግለሰቦች እጅ ወጥታ የክርስቲያኖች እንባ የሚታበሰው??? አዋቂዎች ነን የምንለውስ መቼነው ያወቅነውን አሳውቀን እራሳችንን አድነን ሌሎችን የምናድነው?? ጎበዝ ቤተ-ክርስቲያን የቁርጥ ልጆች የሚያስፈልጋት ዛሬ ነውና እንንቃ! አምላከ ቅዱሳን ከጎናችን ይሁን አሜን!!