Friday, July 30, 2010

እምነታቸው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተሳሰባቸው የፕሮቴስታንት…….መጨረሻቸውስ?

በአውሮጵያውያን አቆጣጠር በ1517 አካባቢ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሮም ውስጥ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል መልሶ ግንባታ ስትጀምር በወቅቱ የሮማን ካቶሊክ መሪ የነበሩት ፖፕ ሊዮን ፲(Pope Leo X )፤ ዮሐን ቴትዝልን (Johann Tetzel) የመላው ጀርመን ኮሚሽነር በማድረግ ሾመውት ነበረ። ዮሐን ቲትዝል የዶመኒካ ተወላጅ ሲሆን፤ስርየተ ሀጥያት (selling indulgences) በገንዘብ  እንደሚገኝ አጥብቆ ያስተምር ነበር። ይህን አስተምህሮ ለታላቁ ካቲድራል ግንባታ አገልግሎት ገቢ ለማሰባሰብ እጅግ ጠቀሚታ ነበረው፤እንዲሁም በየ ዕለቱ በአደባባይ ለሀጥያት ስርየት በሚቀመጡ ሳጥኖች ብዙ ገንዘብ ይሰበሰብ እንደነበር መዛግብት ያትታሉ። በዚህ ጊዜ ነው የፕሮቲስታንቱ እምነት መስራች ማርቲን ሉተር በተቃውሞ የተነሳው። የማርቲን ሉተር ተቃውሞው በብዛት አስተዳደራዊ ጥያቄ ነበረ፤ለምሳሌ ለተቃውሞ በፃፈው በሰማንያ ስድስተኛ አንቀጹ (“Why does the pope, whose wealth today is greater than the wealth of the richest Crassus, build the basilica of St. Peter with the money of poor believers rather than with his own money? የፖፓው ሀብት ከባለሀብቱ ቄሳር በልጦ እያለ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል በራሱ ገንዘብ ማስገንባት ሲችል እንዴት የድሀው አማኝ ገንዘብ ይፈልጋል?”) በማለት ጠይቆ ነበረ።

ዓላማዬ የፕሮቲስታንትና የካቶሊክ ታሪክ ለመዘርዘር አይደለም ፤የኛው ቤተ ክርስቲያን ነባራዊ ሁኔታ ለመዳሰስ እንጂ። አሁን እኛ ባለንበት ዘመን በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ጉዳይ ላይ ጥያቄያችን አልተመለሰልንም የሚሉ ወገኖች ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር በመነጠል ራስችን ችለናል ወይም "ገለልተኞች ነን" (independent church) በማለት ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ከተገለሉ  ሁለት አስርት ዓመታትን አስቆጥረዋል። ታዲያ ይህ ራስን የመቻል አስተምህሮ በኦርቶዶክስ እምነት ውስጥ ከየት መጣ? አስተምህሮውስ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ እንዴት ይታያል? በእነዚህ ጥያቄዎች ዙርያ የተዋሕዶ ልጆች መወያየት ያለብን ይመስለኛል። አለበደዚያ ግን አስተሳሰቡ ወይም አስተምህሮው ሲውል ሲያድር ራሱ የቻለ ከኦርቶዶስ የተገነጠለ ሌላ ሀይማኖት እንዳይሆን ያሰጋል።

በኦሬንታል የእንኛን ቤተ ክርስትያን ጨምሮ  አሐት አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ደግሞ በምስራቁ ኦርቶዶክሳዎያን ዘንድ ራስን የመቻል ወይም የገለልተኝነት አስተምህሮ የላቸውም። ታድያ አሁን እየተስፋፋ ያለው ገለልተኝነት አስተሳሰብ (Independence) በቡድንም ሆነ በግል አስተምህሮው ከየት የመጣ ነው? ጳጳስ እንዲሁም ሊቀ ጳጳስ የማይቀበል ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ የለም።

በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ሰባቱንም ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን የመፈጸም ስልጣን ያላቸው ጳጳሳት እና ሊቀ ጳጳሳት ብቻ ናቸው። ታድያ የአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን የመጨረሻው የስልጣን አካል እንዴት ቦርድ ሊሆን ይችላል? የሃይማኖት እጸጽ ቢፈጠርስ አውጋዡ ማን ሊሆን ነው? ቦርዱ? መልሱን ለተመልካቹ ትቼዋለሁ።

አንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ወይም አንድ ሰባኪ ራሴን ችያልሁ፤ ከማንም ምንም አልፈልግም ካለ አስተሳሰቡ የፕሮቲስታንት ነው፤ ምክንያቱም ራስን የመቻል(Independence) አስተምህሮ የፕሮቴስታንት ነውና። ስለዚህ እምነት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተሳሰብ ደግሞ የፕሮቴስታንት ውሎ ሲያድር መጨረሻውስ ምን ይሆን?
    እግዚአብሔር ተዋሕዶ  ሃይማኖታችን ይጠብቅልን!!! አሜን

2 comments:

Anonymous said...

Very good brother, that is very true. May God give us the ears to listen and the mind to contemplate the message positively.

Anonymous said...

አቤል ያንተ ጽሁፍ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ደበደበው እንደሚሉት ተረት ይመስላል።
ከላይ በጻፍከው ጽሁፍ እንደገለጽከው በ 16ኛው ክፍለዘመን የነበሩት የተወሰኑ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ጉዳይ ላይ ጥያቄያችን አልተመለሰልንም በማለት ከካቶሊክ እምነት በመውጣት የፕሮቴስታንት እምነትን ገነቡ። በጊዜው ለነበረው ችግርና እሮሮ የካቶሊክ እምነት መሪዎች አይነተኛ መፍትሄ ቢፈልጉ ኖሮ ችግሩን በአጭር ቀጭተውት ህዝባቸውን ከብዙ መከራ ባዳኑት ነበረ። ነገር ግን ከእንቅልፋቸው ሲነቁ የካቶሊክ እምነት እንዳይፈራርስ ረጅም መሰናክሎችን እንዲያልፉ አስገድዷቸዋል።
አሁንም በዘመናችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ ጥያቄያችን አልተመለሰልንም የሚሉ ወገኖች ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር በመነጠል ራስችን ችለናል ወይም ገለልተኞች ነን (independent church) በማለት ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ራሳቸውን አግለዋል።
የእኔ ጥያቄ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪዎች (ፓትርያርኩና ተከታዮቻቸው) አካባቢ ችግር የለም ወይ?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪዎች (ፓትርያርኩና ተከታዮቻቸው) ከገለልተኛዎቹ አቢያተ ክርስቲያናት ለሚቀርበው አስተዳደራዊ ችግር መፍትሄ ለመፈለግ ፈቃደኞች ናቸው? እስከዛሬ ምን መፍትሄ አፈላልገዋል?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪዎች (ፓትርያርኩና ተከታዮቻቸው) ፍቅርንና አንድነትን ነው ወይንስ ጥላቻን ነው ለምእመኑ እያስተማሩ ያሉት?
አቤል እባክህ ጣትህን ወደችግሩ ምንጭ ቀስረው። ያኔ መፍትሄው ይገኛል።