Wednesday, August 11, 2010

መፍትሔዬ:- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዲያስጶራው ዓለም ለምትገኝበት ትርምስምስ

ይህ ጽሑፍ ከዚህ በፊት በደጀ ሰላም ላይ አቅርቤው ነበረ። አሁንም ወቅታዊ መስሎ ስለታየኝ እዚህ ላይ በድጋሚ ቀርቦዋል።
+++
ሰሞኑን ባቀረብኩት የቤተ ክርስቲያናችን ችግር ላይ አንዳንድ ጽሑፉን ያነበቡ ደጀ ሰላማውያን “የምናውቀውን ችግር ደግመህ ለምን ትነግረናለህ? መፍትሔው ነው የጠፋው” በማለት ስለጠየቁኝ፤መፍትሄ እንኳን ባይሆን ለመወያያ ይሆነን ዘንድ አንዳንድ ነጥቦች ለማስቀመጥ ተገድጃለሁ። በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እኛው የፈጠርነው ይህ ሁሉ ትርምስምስ በዘለቂው ለመፍታት “ከ40 ሚሊዮን የተዋህዶ ልጆች መሀከል በደጀ ሰላም ድረ ገጽ የምንወያይ ሰዎች ብቻ ልንፈታው አንችልም” የሚሉ ደጀ ሰላማውያን ሊኖሩ ይችላሉ፤ ለእግዚአብሔር ምን ይሳነዋል በቅንነት እና ለእውነት ከተወያየን እንፈታዋለን የሚል ተስፋ አለኝ። ለእኔ የታዩኝ አንዳንድ ለችግሮቹ መፍትሄ ይሆናሉ የምላቸው ነጥቦችን ለውይይት እንዲያመቸን አቅርቢያለሁ።

እንግዲህ ስህተት ካለም እያረማቹኝ በጎደለውም እየሞላችሁበት፤ የሚከተሉትን ሀሳቦች በያለንበት እንድንወያይበት ለመጠቆም ሞክሬያለሁ፦
፩. ከእረኞቻችን ምን ይጠበቃል?
እዚህ ላይ ለውይይት እንዲያመቸን “ገለልተኛ” ነን የሚሉና በቦርድ የሚመሩት በተለያየ መልኩ በግለ-ሰዎች ሥር ያሉት፣ እንዲሁም ደግሞ “በኢ/ኦ/ተ/ቤ ሥር” ነን የሚሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉት ዕረኛቻችንን ብቻ ይመለከታል። “በስደተኛው ሲኖዶስ” አስተዳደር ውስጥ እንመራለን ለሚሉት ዕረኞቻችን በተመለከተ በሌላ ግዜ እመለስበታለሁ። እረኞቻን ብዬ እንደ መፍትሔ ሀሳብ ያስቀመጥኩት ከዲያቆናት እስከ ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ ነው። እንግዲህ ስለ ቤተ ክርስቲያን ስተዳደራዊ መዋቅር አስፈላጊነት፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊነት እና ሐዋርያዊ አመጣጥ ለዕረኛቼ መናገር “ለቀባሪ አረዱት” ሥለሚሆንብኝ ለእነሱ ትቼዋለሁ። ቤተ ክርስቲያን አንድነቷን ጠብቃ ለትውልድ እንድትተላለፍ አንድ አስተዳደራዊ መዋቅር መኖር ግድ ነው እንደምትሉኝ አልጠራጠርም። ስለዚህ በተለያየ ሁኔታ አሁን ላለንበት ትርምስምስ “በገለልተኛ” እና በግለስዎች ያሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ምክንያታቸው የአባ ጳውሎስ የአስተዳደር በደል መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህን የአስተዳደር በደል ፈርቶ መሸሽ ማለት ለእኔ ቤተ ክርስቲያን ስትበደል “እኔ ይመቸኝ እንጂ የሯሷ ጉዳይ” ማለት ይመስለኛል።

በእኛ ከአስተዳደሩ ሸሽቶ መውጣት አባ ጳውሎስ ምን ተጎዱ? ቤተ ክርስቲያናችንስ ምን ተጠቀመች? ይህ እንግዲህ ዕረኛቻችን በሚገባ መወያየት ያለባቸው ጉዳይ ይመስለኛል። ነፃነት ያለበት ሀገር ውስጥ ስለሆንን በመዋቅሩ ሥር እንኳን ሆንን አባ ጳውሎስን መቃወም አንችልም ወይ? እንደ ኢትዮጵያው እዚህ ሀገር ደብር አስተዳዳሪውን እንደተፈለግ ያለ ህጉ ማዘዋወር የሚችሉ ይመስሏችኋል? አይመስለኝም። ታድያ ምንድ ነው የሚያስፈራን? ነፃነት በሌለበት ሀገራችን እንኳ በቅርቡ በአርባ ምንጭ እና በአክሱም ከታማዎች ህግ በማያዘው መሰረት በተነሱት አስተዳዳሪዎች ምክንያንት የተከሰቱት የምዕመናን ተቃውሞዎች ማስታወስ ይቻላል። ስለዚህ “ሥጋችሁን እንጂ ነፍሳችሁ መግደል ለማይችሉት አትፍሩ” የሚለው አምላካዊ ትዕዛዝ የተዘነጋ ይመስለኛል። “ቦርድ ያባርረኛል” ብሎ መፍራት ቢያባርርስ፤ ዕረኞች ከተወያያችሁበት ቦርዱ አሐዱ አብ ቅዱስ አይልም እኮ። ስለዚህ ከላይ መጀመሪያ ላይ የጠቀስኳቸው ሦስቱንም አስተዳደር ሥር የሚገኙ ዕረኞቻችን ለእውነት ብለው ወደ ልባቸው መመለስ ያለባቸው ይመስለኛል። የመደራደሪያው ጊዜም አሁን መስሎ ይታየኛል። እኛው የፈጠርነው ችግር እኛው ካልፈታነው ልጆቻችን ይፈቱታል ብዬ አልጠብቅም። “የመቅደስ አገልግሎት እስከተሟላ ድረስ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር በዲያስጵራው ዓለም ለምን ያስፈልገናል”? የሚሉ ዕረኞች ብዙ ጊዜ ያጋጥሙኛል። ይህ ግን በቤተ ክርስቲያን ላይ መቀለድ ያስብላል። ድርድሩ እንዴት ይጀመር ለሚለው ለእናንተው እተወዋለሁ።
እዚህ እኛ ያለንበት ሀገር ላይ አስተዋዮቹ አባቶቻችን ያስረኩቡንን የቤተክርስቲያን የአስተዳደር መዋቅር ጠብቀን ብንሄድ ቤተ ከርስቲያናችን ምን ጠቀሜታ ታገኛለች? ቢባል፦

1. የቀደሙት አባቶቻችን በሀግራችን ኢትዮጵያ ላይ የአብነት መማሪያ ትምህርት ቤቶች ገንብተው እንዳስረከቡን ሁሉ፤ እኛም እዚሁ ሀገር ላይ ለሚቀጥለው ትውልድ ይሚሆን ዘንድ የአብነት ት/ት መማሪያ ሥፍራዎችን ገንብተን ማስቀመጥ እንችል ነበረ። እዚህ ሀገር ላይ ቤተ ክርስቲያናችን የ50 ዓመት ዕድሜን አስቆጥራለች፤ በዚህ ዕድሜዋ ግን በሳምት አንድ ቀን ከሚሰጠው የቅዳሴ አገልግሎት ውጪ ለትውልዱ የሚተላለፍ ምንም የተሰራ ነገር የለንም። አንዳንድ አካባቢዎች በብድር የተለያዩ ህንፃዎች ተገዝተው ሊሆን ይችላል፤ አንድ ላይ ብንሆን ግን በ50 ዓመት ዕድሜ ከዛ ያለፈ መስራት በቻልን ነበር።

2. በአንድነት ጥላ ሥር ብንሆን ሌሎች አሀት አብያተ ክርስቲያናት እንደሚያደርጉት እኛም ያላመኑት አፍሪካውያንን ወንድሞቻችን እያስተማርን የእግዚአብሔር መንግስት ለዓለም እንዲዳረስ በሚገባ መንቀሳቀስ እንችል ነበረ።
3. ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ቅርበት ላይ ስለሆንን ለሌሎች አህጉረ ስብከቶቻችን ምሳሌ መሆን እንችል ነበረ።
እረኞቻችን እነዚህን ሀሳቦች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ራሳቸው ለውይይት ማዘጋጀት ያለባቸው ይመስለኛል።

፪. ከሰንበት ት/ት ቤት ወጣቶች ምን ይጠበቃል?
ስንዱ እመቤት የሆነችው የኢ/ኦ/ተ/ቤ የሰንበት ትምህርት ቤት አስፈላጊነት እና ዓላማው በህግ ደንግጋ አስቀምጣልናለች። ቃለ ዓዋዲው ስለ ሰንበት ት/ት ቤት ዓላማ ሲገልጽ “የኢ/ኦ/ተ/ቤ እምነትና ሥርዓት ተጠብቆ ሳይለወጥ ሳይበረዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላልፍ ማድረግ” ይላል። ስለዚህ አንድ የሰንበት ት/ት ቤት አባል ይሄ ሁሉ የቤተ ክርስቲያን አደራ ተሸክሞ ይኖራል ማለት ነው። እዚህ ሀገር የምንኖር የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከቀደሙት አባቶቻችን የወረስነውን የቤተ ከርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር መጠበቅ ከእኛ ምን ይጠበቃል? ቢባል፦

1. ስለምናገለግልበት አጥቢያ አብያተ ቤተ ክርስቲያን በሚገባ ማወቅ፤ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ መተዳደሪያ ደንብ “ምን ይላል”? ብሎ በሚገባ መፈተሽና በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ከህገ ቤተ ከርስቲያን እና ከቃለ ዓዋዲው ጋር የሚጋጭ ነገር ካለ እንዲስተካከል ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ማንሳት።

2. በሳምንት አንድ ቀን ከምንዘምረው የመዝሙር አገልግሎት በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎችን ለመስራት በአካባቢያችን ከሚገኙት አሐት አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ጋር ልምድ በመቅሰም ለትውልድ የሚተላለፉ ሥራዎች ለመጀመር መዘጋጀት።

፫. ከምዕመናን ምን ይጠበቃል?
ቤተ ክርስቲያናችን ከቅዱስ ፓትርያርኩ እስከ ምዕመናን ድረስ በየደረጃው የሥራ ድርሻ ከሙሉ ሀላፊነት፤ መብት እና ግዴታ ጋር አስቀምጣለች። ሁሉም እኩል የሚዳኝበት በየደረጃው የሯሷ ህግም አላት። አለመታደል ሆኖ ግን እዚህ እኛ ያለንበት ሀገር ብቻም ሳሆን ሀገር ቤትም ጭምር ምዕመናኑ ቤተ ክርስቲያን የሰጠችን መብቶችና ግዴታዎች ብዙውን ግዜ እየተወጣን አይመስለኝም። የዲያስጶራው የቤተክርስቲያናችን ትርምስምስ በዘላቂ እንዲፈታ ከምዕመናን ምን ይጠበቃል?

1. የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ይመለከታል የሚለው አስተሳሰብ መላቀቅ ያለብን ይመስለኛል። ክርስቶስ በደሙ የመሰረታት የቤተ ክርትስቲያናችን ጉዳይ ለሁላችንም እኩል ይመለከተናል። ሥለዚህ ስለምንገለገልበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በሚገባ ማወቅ አለብን። መተዳደሪያ ደንቡ ምን ይላል? ቤተ ክርስቲያኑ በማን ሥም ነው ያለው? እስከ መቼ ድረስ ከቤተ ክርስቲያን ተገንጥሎ ይቆያል? የሚለው በሚገባ ማወቅ ያለብን ይመለኛል።

2. በኢትዮጵያ ሀገራችን ነፃነት ስለሌለ በየ ዘመኑ የሚነሱ ፖለቲከኞች እንድፈልጉት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ቢጫወቱም፤ እዚህ ሀገር ግን ነፃነት ሥላለን የምንገለገልበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የፖለቲከኞች ዓላም ማስፈፀሚይ እንዳትሆን መከላከል መቻል። የቤተ ክርስቲያኒቷን ቀኖና እና ሥርዓት እንዲተገበር የራስ ጥረት ማድረግ።
        እግዚአብሔር ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ይጠብቅልን!!! አሜን

2 comments:

Anonymous said...

ውድ ቀዳማዊ ሆይ! በቅድሚያ ስለጽሁፍህ መልካምነት ልገልጽ እወዳለሁ። በማስከተልም ብትችል ለሌላም ጊዜ እንዲህ በአንድነት ሊያነጋግሩን ሊያወያዪን የሚችሉ ጽሁፎችን መጻፍ ብትችል፤ወገንተኝነት ብሎም የመፍረድ መንፈስ ያለበትንና አንድና ተመሳሳየ ቅንአቱና መቆርቆሩ እያለ የተለያየን ያህል የሚያከፋፉንን ጽሁፎች ባትለጥፍ ምን ይመስልሀል?

Anonymous said...

ቃለ ሕይወት ያሰማልኝ ቀዳማዊ። የተሰጠው የመፍትሂ ሃሳብ በጣም ግሩም እና ገንቢ ነው። አንዳንድ አንባብያን ግን የአጥቢያዎችን ችግር ማቅረብ በታኝ (አፍራሽ) እንደመሆን ይቆጥሩታል። የምሳሌ፡
- አዲስ ቤተ ክርስትያን ሲመሰረት(ሲከብር) በሊቀ ጳጳስ መባረክ እንዳለበት መናገር
- የቦርድ አስተዳደር መቅረት እንዳለበት። በመሰረቱ የቦርድ አስተታደር ኢ-ቤተ ክርስትያናዊ ተግባር በሆኑን ማሳወቅ እና
የመሳተሉት ጠቃሚ እና መሰረታዊ የሆኑ ቀኖናዊ ጉዳዮችን መጥቀስ መወያየት በግልፅ ማንሳት የማይመቻቸው የቤተ ክርስትያን ሳይሆን የ ቦርድ ጠበቃ የሆኑ ግለሰቦች ብሎም ሰባኪያን እንዲሁም ካህናት አሉ።
ለንዚህ ሰዎች በግልጽ ሐሳባችንን፤ እውነታውን እና አቃማችንን ማሳወቅ አለብን። ቤተ ክርስትያንን የምንወድ ከሆነ በእርግጥ እኒህን ሰዎች መደገፍ የለብንም። እውነትን መምረጥ ፤ ሐሰትን ጥቅመኝነትን ማስወግድ፤ ለእውነት መጠላትን ይጠበቅብናል።

የሆነ ሆኖ ግን አስተሳሰባችን ውሱን(የተገደብ) ሆኖ ለአጥቢያ ብቻ ከማሰብ ባለፈ መልኩ አንዲት፤ቅድስት፤ሐዋርያዊት፤አለማቀፋዊት ስለሆነጭው ቅድስት ቤተ ክርስትያን ማሰብ፤መቆርቆር፤መጸለይ ያስፈልገናል።

ሌላ ላሰምርበት የምፈልገው ቢኖር፦ ትችትን መቀበል መልመድ አለብን። በአንዳንድ አጥቢያ እንዲህ አይነት ችግር አለ ከተባለ መጀመርያ መኖሩን አለመኖሩን ማረጋገጥ ካለ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲሰጥበት ማሳሰብ ተገቢነው። የተጠቀሰው ችግር ከሌለ ግን በሳደብ እና ማብጠልጠል ሳይሆን እውነታውን ማሳወቅ ሰዎች እንዲረዱት ማድረግ ነው።

እንግዲህ እንዳላበዛው እኔም የናንተን እሰማለሁ። እግዚአብሄር አምላክ ሁላችንም የምንሰማበት ጀሮ የምናስተውልበት አእምሮ ይስጠን። አሜን።

ወንድማችሀ ከ VA