Tuesday, August 31, 2010

አህጉረ ስብከቶቹ ዘመናዊ የአስተዳደር መርህ መከተል አለባቸው

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን  ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ በተዋረድ የሀገር ስብከት ቤተ ክህነት እና የወረዳ ቤተ ክህነት ትልቁ ችግራቸው ዘመናዊ የአስተዳደር መርህ መከተል አለመቻል ነው። ይህም ቤተ ክርስቲያን ዘመንን የዋጀ የአስተዳደር መርህ እንዳትከተል አድርጓታል። በዚህም ምክንያት የተባላሸ እና በጣም ኋላ ቀር የሆነ አስተዳደር በቤተ ክህነታችን ላይ ሰፍኖ ይታያል።

ጠቅላይ ቤተ ክህነታችን እና ሌሎችም በተዋረድ ያሉት ቤተ ክህነቶቻችን ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንደሚጎድላቸው በየአደባባይ እየተነገረ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ብሩህ የቤተ ክርስቲያን ራዕይ ያላቸው አንዳንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የለውጥ እንቅስቃሴ ቢጀምሩም በቅዱስ ፓትርያርኩና እና ከጎናቸው የቁሙት ጥቅመኞች አሻፈረኝ ባይነት ተግባራዊ ሊሆን አልተቻለም።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአሁን ወቅት አርባ አህጉረ ስብከት በሀገር ውስጥ እና ስምንት ደግሞ ከሀገር ውጪ በድምሩ አርባ ስምንት አህጉረ ስብከት እንዳላት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000ዓ.ም” የሚለው መጽሐፍ ይገልጻል።  ቤተ ክርስቲያናችን በውጪ ሀገር ከሚገኙት አህጉረ ስብከቶች መሀክል በሰሜን አሜሪካ(USA) ሦሶት  ሀገረ ስብከቶች ካቋቋመች አራት አመታትን አስቆጥራለች። በዚህ ጽሁፍ ላይ አንዳንድ ነጥቦች በሰሜን አሜሪካ ስላሉት አህጉረ ስብከቶቻችን እንመለከታለን።

የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ተግባር በቃለ አዋዲ በአንቀጽ ፵ እና ፵፪ “ሀገረ ስብከት በአንድ የተወሰነ ክልል ቤተ ክህነቱን ወክሎ የሚሠራ ተቋም ሲሆን፣ ሃይማኖቱን እና ቀኖናውን ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ፣ ከክርስቶስ ጀምሮ የመጣውን ሀብተ ክህነት ለመጠበቅ እና ለማስተላለፍ፣ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፣ ገዳማት እና አድባራት እንዲረዱ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲተከሉ፣ ምእመናን ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መብት እንዲከበር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ወጥ እና ሥርዓቱን የጠበቀ እንዲሆን፣ የካህናት አስተዳደር እና አገልግሎት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት እንዲሆን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት እና ንብረት በሕግ እና በሥርዓት መሠረት እንዲጠበቅ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እና እንዲሰጡ” ማድረግ የሚሉ  ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ታዲያ እነዚህ አህጉረ ስብከቶች ምንም እንኳ ከተመሰረቱ አጭር ግዜ ቢሆንም፤ ቤተ ክርስቲያን ህግ ደንግጋ የሰጠቻቸውን ትልቅ ኃላፊነት ለመወጣት ምን እየሰሩ ነው? ዘመናዊ የአስተደዳደር መርህስ ይከተላሉን? በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚታየው የተበላሸ አስተዳደር እዚህስ አንዳይደገም ምን እየተደረገ ነው? ይህ በተለያዩ አጋጣሚዎች የማገኛቸው ምእመናን የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ሲሆኑ መልስ የሚሹም ናቸው።

እንግዲህ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዘመናዊ የአሰዳደር መርህ ባለመከተሉ የተነሳ የቤተ ክርስቲይኒቱ ሀብትና ንብረት መባከን፣ ሰዎች በማይመጥናቸው ቦታ ላይ ማስቀመጥ በአጠቃላይ በገንዘብ አስተዳደር እና በሰው ሀይል አስተዳደር ላይ ከፍተኛ የሆኑ ችግሮች እንደሚታዩ ብዙ የህዝብ መገናኛ ብዙሀን ይናገራሉ።  እኛ ባለንበ ሀገር ስብከት ይህ ችግር እንዳይከሰት ገና ከጅምሩ የችግሩ ግንድ ሳያቆጠቁጥ ቆርጠን መጣል አለብን። ይህ ካልሆነ ግን ግንዱ አቆጥቁጦ ለመቁረጥ ስንጀምር ሌሎች ብዙ የችግር ግንዶች ስለሚፈጠሩ ለማጥፋት እንቸገራለን። የሚፈራው የተበላሸ አስተዳደር በአህጉረ ስብከቶቻችን ሳይከሰት ገና ከምንጩ ማድረቅ አለብን። ለዚህም መፍትሔው ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለው ዘመናዊ የአስተዳደር መርህ መከተል ነው።

በእርግጥ አህጉረ ስብከቱቹ ከተመሰረቱ ወዲህ  በተለይም የብፁዕ አቡነ አብረሃም ሀገረ ስብከት ከዚህ በፊት ያልነበሩ አንዳንድ በዓይን የሚታዩ ለውጦች አሉ፤ ለምሳሌ የሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መመስረት፣የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መኖሪያና ጽ/ቤት ግዢ መፈጸም የሚጠቀሱ ናቸው። ነገር ግን ከችግሩ ስፋት እና ሥር መሥደድ አንፃር ሲታይ ከተጠቀሱት ሥራዎች በተጨማሪ ሀገረ ስብከቱ ብዙ መሥራት ያለበት ይመስለኛል። የተጠበቀውን ያህል ሥራዎች ያልተሰራበት ምክንያት ምን ይሆን?  ብዙዎቻችን የተለያዩ መልሶች እንሰጥ ይሆናል ፤የብዙዎቻችን መልስ ግን ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግ ሲሆን የእኛን ድርሻ አለመወጣት አይታየንም።

ሦስትቱም ሊቃነ ጳጳሳት ያሉበት አህጉረ ስብከቶቻችን የወርዳ ቤተ ክህነት እንደሌላቸው ግልጽ ነው። ሀገረ ስብከቶቹ ግኑኝነታቸው ቃለ አዋዲ እንደሚያዘው ከወረዳ ቤተ ክህነት ጋር ሳይሆን በቀጥታ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ነው። እንደውም ሊቃነ ጳጳሳቱ ራሳቸው ዝቅ አድርገው የአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተደዳሪ ሆነው እየታዩ ነው። 

ስለዚህ የወርዳ በቤተ ክህነት እስኪቋቋም ድረስ የተበታተኑትን ለመሰብሰብ፣አሻፈረኝ ብለው ያፈነገጡትም በህግ ለመጠየቅ ያመች ዘንድ ዘመናዊ አስተዳደርን መርህ ያደረገ አንድ ቡድን ማቋቋም ግድ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። አህጉረ ስብከቶቹ የሌሎች አሃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ በመውሰድ የወረዳ ቤተ ክህነት እስኪያዋቅሩ ድረስ ከየ ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጋር የሚሰራ ሁሉንም ግዛቶች(እስቲቶች) ውስጥ የሚያካትት ግዚያዊ ኮሚቴ ማዋቀር ያለባቸው ይመስለአኛል። ይህ ኮሚቴ በሦስቱም ሀገረ ስብከቶች እንደየ አካባቢው ሁኔታ ተጠንቶ ቢዋቀር።
ለምሳሌ፦
፩. የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ጉዳይ አስተባባሪ ቡድን
፪. የህግ ጉዳይ አስተባባሪ ቡድን
፫. የሰው ሀይል አስተዳደር አስተባባሪ ቡድን
፬. የገንዘብ አስተዳደር አስተባባሪ ቡድን
እናም እነዚህ ቡድኖች ቃለ ዓዋዲ በማያፋልስ መልኩ የሥራ ድርሻ ተስጥቶዋቸው እንዲሁም ከዘመኑ ጋር የሚሄድ አሠራር ተከትለው እንዲሰሩ በተተመነ የግዜ ገደብ እንዲጨርሱ ቢደረግ።

2 comments:

Ewnetu said...

Thank you for the essue you raised it, but the problem is like 'menbere patryark'.The bishopes in US are not aproprate for the position i am sory to say this i belive that we have to pray more.offcorse i agree with your idea the fact is who lead us to do that? the church admenstration needs revolation not evoluation.

Anonymous said...

Mr. kedamawi, thank you for your comments, but in usa we respect law and regulation, your father, your church leader doesn't agree with law and regulation. even he doesn't follow the basic church rule. Mr. abba doesn't obey for the church and we don't follow him or respect him and we don't accept any order from him. Listen , a Leader lead by example not by dictating.