Tuesday, September 21, 2010

በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የሐመረ ኖኅ ኪዳነምሕረት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እና አገልጋዮች ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በሙሉ የይድረሱልን ጥሪ አስተላለፉ


ይህች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በአካባቢያችን በገለልተኛ ስም ከተዋቀሩት አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት ምድብ ውስጥ ቢሆንም፤ ነገር ግን በአንድ ግለሰብ ባለቤትነትና ፈላጭ ቆራጭነት ይተዳደራል:: ይህንን ችግር ያስመረራቸው የአጥቢያው ምእመናን እና አገልጋዮች  በአካባቢው ለሚገኙት ምእመናን እንዲሁም ለተዋሕዶ ልጆች በሙሉ እሮሮዋቸውን ያሰሙበት ጽሑፍ በአካባቢያችን ተሰራጭቶ ነበር::   የጽሑፉ ሙሉ ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል::
+++


ለሐመረኖህ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ምእመንና ለኢቲዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በሙሉ
በስሜን አሜሪካ ካህናት ቅድስት ቤተክርስቲያን የግል ንብረት የማድረግ ጥረትንና ምእመንን በፖሊስ የማገድ ተግባርን ለማስቀረት የሚደረግ ታላቅ ሐይማኖታዊ ትንቅንቅ !!!!!!!!!!!!
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቅድስት ቤተክርስቲያን በነገሥታት፣ በመሳፍንታት፣ በባላባት፣ በመንፈሳዊ አባቶች፣ በግለሰቦችና በምእመናን በሕብረት ስትታነፅ ኖራለች። እየታነፅችም ነው። ለእምነት ሥርዓቷም ማከናወኛ የሆኑትን በርካታ ነዋየ ቅድሳትም በእምነቱ ተከታዮች ምእመናን በግልና በጋራ ሀብት ሲሟላ የቆየና እየተሟላም ይገኛል። በዚህ ሁኔታ የታነፁት አብያተ ክርስቲያናት በእግዚአብሔር ፀሎት ቤትነት ለእምነቱ ተካታዮች በሙሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ ቆይተዋል። ቤተክርስቲያናችን የፅሎት ቤት ብቻ ሳትሆን  እግዚአብሔርን ተስፋ ላደረጉ፣ መጠጊያ ለሌላችው አቅመ ደካሞች፣ ደሀዎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጠጊያና ከለላም ናት።
ነገር ግን ዛሬ በዚህ በስሜን አሜሪካ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ዶግማና ቀኖና ውጭ በምእመናን ጉልበትና ገንዝብ የታነፁትን ወይም የተገዙትን አብያተ ክርስትያናትን ያለምንም እፍረትና ፍርሀት “የግል ሀብቴ ነው” በማለት ከእግዚአብሔር የተሰጣችውን የክህነት ፀጋንና መንፈሳዊ ሀላፊነትን በምድራዊ ሥጋቸው ለውጠው አንዳንድ ካህናት በየፍርድ ቤቱ ቆመው የይገባኛል ክርክር ማቅረብ ጀምረዋል። የነርሱንም ስጋዊ ስሜትና ፍልጎት የሚፃረሩ ወይም ቤተክርስትያንዋ መንፍሳዊ በሆነ ደንብና ስርዓት እንድትመራ የሚጠይቁትን ምእመናንንም በፖሊስ ከአግዚአብሔር ቤት ማባረር ብቻ ሳይሆን ምእመኑን ከቤተክርስቲያን የማባረር መብትም እንዳላችው በድፍረት በየፍርድ ቤቱ በጽሑፍ በመግለፅ ይከራከራሉ። ይህም ካህናት የምእመኑ እረኛ ሆነው በእግዝአብሔር የተመረጡበትንና የእግዚአብሔርም በጎች ከመንጋቸው ቢጠፉ ፈልግው ከመንጋው እንዲቀላቅሏችው ከእግዝአብሔር የተስጣቸውን መንፈሳዊ ኃላፊነት የሚፃረር ብቻ ሳይሆን  ፈፅሞ መንፈሳዊ የሆነው ፀጋችው ከውስጣቸው ተሟጦ የእውነት፣ የፍቅር፣ የስላም ምልክት የሆነውን የጌታችን የመድሀኒታችን የእየሱስ ክርስቶስን መስቀል ይዘው፤ በክህነታቸውና በለበሱት ያሸበረቀ የክህነት ልብሳቸው ተከልለው፤ በዚያ በሰላ ምላሳችው ምእመኑን እየሸነገሉ የግል አለማዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሌት ተቀን ሲደክሙ ይታያሉ። እንደነዚህ ያሉትን የበግ ለምድ ለብሰው በእግዚአብሔር በጎች መካከል ያሉትን የካህን ቀበሮዎችን ከሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎትን ከሚሰጡ ከተከበሩ ካህናት አባቶቻችን ለይተን በማውጣት በረከስው ምግባራችው ከእግዚአብሔር ቤትና በጎች ተለይተው በሀላፊነትም እንዲጠየቁ በማድረግ የእግዚአብሔርን ቤት ማፅዳትና ቀደምት የሐይማኖት አባቶቻችን በደማቸውና በሕይወታቸው መሥዋዕትነትን ከፍለው ጎሳንና ብሔርን ሳይለይ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየውን ሐይማኖታችንንና ቤተክርስቲያናችንን ጠብቀን ለልጆቻችን ማስተላለፍ የእኛ የዚሁ እምነት ተከታዮች መንፈሳዊ ግዴታችን ነው። ይህንን ካላደረግን ግን እኛም ከነዚህ ምግባረ ብልሹ ካህናት ጎን ቆመን በእግዚአብሔር ቤትና በምእመናን ገንዘብ መንፈሳዊ ሳይሆን ዓለማዊ ፍላጎታችውን እንዲያሟሉ፣ እየተባበርናችው መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።
በዚሁ መሠረት እዚህ በስደት ላይ የሚገኘው የዚሁ እምነት ተከታይ ህዝብ በግል ወይም በሕብረት ጸሎትና ምህላ ከፈጣሪው ጋር ለመገናኘት እንዲችል፣ ከእትዮጵያ የመጡት ወይም እዚህ ባዕድ አገር የተወለዱት ልጆቻችን በሐይማኖታችን ታንፀው እንዲያድጉ፣ ሐይማኖታችንና የቤተክርስቲያናችን ቀኖናና ዶግማ በሚፈቅደው መሠረት የክርስትና፣ የቁርባን፣ የተክሊል ጋብቻ፣ የፍትሀት ፀሎት ውዘተሥርዕቶችን ለመፈጸም የሚያስችለውን  የሐመረ ኖህ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን በቨርጂንያ ስቴት .. 1995 ከዚሁ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ካህን ጋር ሆኖ መሥርቷል። ይህ በስደት አገር ሠርቶና ደክሞ ከሚያገኘው ገቢው እየቀነስ ቀደም ሲል ለካህናትና ለዲያቆናት እንዲሁም ለቤት ኪራይ ሲከፍል ቆይቶ አሁን ደግሞ ቤትና ቦታ ገዝቶ በየወሩ $ 15,000.00 - $ 20,000.00 ያላነስ ክፍያን እየሽፈነ  ቢሆንም ምእመኑ ስለ ቤተክርስቲያንዋ አስተዳደርና የአሰራር ሥርዐቶች ላይ ግን ምንም አይነት ተሳትፎ የለውም። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ቤተክርስትያንዋ ገና ስትመሠረት እኝሁ ካህንና አራት ስዎች ሆነው ፈርመው ያወጡትና ያለአንድ ማሻሻያ 15 ዓመታት በላይ የካህኑን ፈላጭ ቆራጭነት የሚያረጋግጥ የመተዳደሪያ ደንብ ሲሆን ይህ ደንብ ለካህኑ ብልሹ አሠራር እንዲመች ተደርጎ የወጣ ከመሆኑም በተጨማሪ፣
1.ደንቡ ምእመኑን በበላይነት ያላማከለና ያላሳተፈ፣ የቤተክርስቲያንዋን የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በአግባቡ ለመመዝገብና ለመቆጣጠር የማያመች፣ ለቤተክርስቲያንዋ መንፈሳዊም ሆነ ለመልካም አስተዳደር እንቅፋት የሆነ ከመሆኑም በላይ ምእመኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በቤተክርስቲያንዋ አስተዳደር ጉዳይ ላይ እንዳይሳተፍና ችግሩን እንዳያውቀው አድርጎታል።
2.ደንቡ ሥልጣን ሰጥቶኛል በማለት ቤተክርስቲያንዋ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ የሰበካ ጉባኤ አባላት የሚሻሩትና የሚመለመሉት በኝሁ ካህን ብቻ እንጂ በምዕመኑ አይደለም። ካህኑም የሚመለምሉአቸው አባላት ለቤተክርስቲያንዋ እድገትና መልካም አሠራር ይበጃሉ የሚሉአቸውን ሳይሆን  ከጥቂቶቹ በስተቀር አንደ ካህኑ ስሜትና ፍላጎት ይታዘዛሉ እንዲሁም ለተበላሸው አስራር ይመቻሉ የሚሏችውን ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ ግን እንደሌሎቹ አብያተ ክርስቲያን በምዕመናን የሚመረጡና የሚሻሩ ለካህኑ ሳይሆን ለምዕመኑ ተጠሪ የሆኑ የሰበካ ጉባኤ አባላት ይኖሩን ነበር።
3.በኚሁ ካህን የተመለመሉትም የሰበካ ጉባኤ አባላት በዚሁ ደንብ መሠረት ቁጥራችው ያልተሟላና የሥራ ዘመናቸውም ያበቃ ቢሆንም ለካህኑ እስከተመቹ ድረስ ግን ያገልግሎት ዘመን ገደብ ስለማይጣልባቸው አንዳንዶቹ 10 አስከ 13 አመታት እያገለገሉ ይገኛሉ።
4.ይህ ደንብ እንዲሻሻል ካህኑም ጭምር አምነውበት ረቂቅ የመተዳደሪያ ደንብ በሦስት የሰበካ ጉባኤ አባላት ቢቀርብም በኚሁ ካህን እንቢተኝነት ሥራ ላይ ሳይውል ቀርቷል። ምክንያቱም ይህ ደንብ የካህኑን ፈላጭ ቆርጭነትን የሚገድብ፣ ምዕመኑን በበላይነት የሚያማክል፣ ለቤተክርስቲያንዋ መልካም አስተዳደርና አሠራር የሚበጅ ሲሆን የካህኑንም አንዳንድ ሥልጣን የቤተክርስቲያንዋ ባለቤት ለሆነው ምእመን የሚሰጥ በመሆኑ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
በሌላ በኩልም ... ኖቬምበር 8/2009 ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ የቤተክርስቲያንዋ ተቆርቕሪ ምዕመናን ግፊት ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ስብሰባ ተደረጎ ነበር። ስብሰባውን በፅሎት የከፈቱትና በስብሳቢነት የመሩት እኚሁ ካህን ሲሆኑ በእለቱ አምስት ጊዚያዊ የስበካ ጉባኤ አባላት በምዕመኑ ተመርጠዋል። የተመረጡትም በኚሁ ካህን ጠያቂነት ይህችን ቤተክርስቲያን በእውነት ለማገልገል በኪዳነ ምሕረት ስም ቃል ገብተዋል። በቀጣዩ ሁለት ወራትም ለሚቀጥሉት አምስት አመታት የሚያገለግሉ የሰበካ ጉባኤ አባላትን ለማስመረጥ ተወስኖ በካህኑ ቡራኬ ስብስባው አበቃ። ነገር ግን በምዕመኑ የተመረጡት የሰበካ ጉባኤ አባላት እንደቀድሞዎቹ በካህኑ እንደተመረጡት የካህኑን የግል ፍላጎትና ጥቅም የማያስጠብቁና በገቢና ወጪ ገንዘብም ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ያደርጋሉ ብለው በመገመት በምዕመኑና በካህኑ ጭምር የተመረጡትን የሰበካ አባላት እኔ ምርጫውን በጽሑፍ እስካላፀደኩ ድረስ  ተፈፃሚነት የለውም በሚል የእብሪት አነጋገር የምዕመኑ ድምፅ በካህኑ የግል ጥቅምና ፍላጎት  ብቻ ተሽሯል። ካህኑ ይህንን የእግዚአብሔር ክህነት ካለው የማይጠበቅ ሥራችውን ለመሸፈን ሲሉ የሰበካ ጉባኤ አባላትን ምዕመኑ እንደሚመርጥና የሚመርጧቸውንም አባላት ከወዲሁ እያስበ እንዲቆይ በተደጋጋሚ በዓውደምህረቱ ለምዕመኑ ቢገልጹም በምዕመኑ የተመረጠ አንድም አባል የለም። በጣም የሚያሳዝነው ግን ካህኑ እንደልማዳቸው ይበጁኛል ያሉአችውንና የፍርፋሪው ተካፋይ ይሆናሉ ያሉዋቸውን ግለስቦች ከጉያቸው ሥር ያሉትን ቀደም ብልው መርጠው አስቀምጠዋል። በዚህ ሁኔታ የመረጡዋቸውን ግለስቦችን እንደአዲስ ተመራጮች አስመስለው ምዕመኑ በግድ እልል እንዲል አድርገዋል። ምዕመኑም የባሰ ይታዘበኛል ብለው የፈሩአቸውን ተመራጮችን ስም ዝርዝር ግን ለምዕመኑ ሳይገልጹ አልፈዋል ምዕመኑም የስበካ ጉባኤው አባላት በእኛ ይመረጣሉ ተብለን ከተነገርን በኃላ እንዴት በካህኑ ብቻ ሊመረጡ ቻሉ ? ብሎ በውጪ ተቃውሞውን በመግለፅ ያጉረመረመ ቢሆንም በወቅቱ የመምረጥ መብቱ ለምን እንደተነፈገ ያለመጠየቁ ከቤተክርስቲያንዋ አስተዳዳሪ የሚገባውን መድረክ ባለማግኘቱ መሆኑ የሚታመን ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ለቤተክርስቲያንዋ ግንባታ ለተገዛው አዲስ ቦታ በተደራጀና ለቁጥጥር አመቺ በሆነ መልኩ ለመሥራት እንዲያስችል ተብሎ የተዋቀሩትንና በዚሁ ሙያቸው ከፍተኛ ትምህርትና የሥራ ልምድ ያላቸውን የሕንጻንና የፋይናንስ ኮሚቴዎችን እኚሁ ካህን በትነዋቸዋል። ምክንያቱም እነዚህ ኮሚቴዎች ያወጡት የሥራ መመሪያ የካህኑን የተለመደና የቆየ የግል ፍላጎትንና ጥቅምን የሚቆጣጠርና ጨርሶም የሚያስቀር በመሆኑ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎአቸው በቤተ ክርስትያንዋ የአሰራርና የአስተዳደር ለውጥ እንዲኖር መሰረታዊ የሆኑ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን የሚያቀርቡትንና በጊዜያዊ የሰበካ አስተዳደር አባልነት የተመረጡትን ምዕመናን ጨምሮ ያልተፈጠረውን ፈጥረው፣ ያለስም ስም ሰጥተው የፖሊስ እርዳታ ጠይቀው .. . በኖቬምበር22/2009 ስድስት ምእመናንን ከቤተክርስቲያን እንዲታገዱ አድርገዋል። ቄስ ታደስ ሲሳይ ለፖሊስ የስጡት ምክንያት ቤተክርስቲያንዋ የግል ድርጅታችው ስልሆነች የፈልጉትን ማስገባት ያልፈለጉትን ደግሞ መከልከል መብታቸው አንደሆነ በመግለፅ ነው።ፖሊሱም ለታገዱት ምዕመናን የሰጠው ይህንኑ ምክንያት ነው። በእለቱ በር ላይ ቆመው ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገቡትንና የሚከለከሉትን ምዕመናን ለፖሊሱ ያመላክቱ የነበሩት ከካህኑ ጎን ተስልፎ ለመንፈሳዊ ሥራ ሳይሆን ለሥጋቸው የቆሙት የሰበካ ጉባኤ አባል ተብየው አቶ አቢይ እምሩ እና የሰበካው ጉባኤ አባል ያልነበሩት አቶ ሚኒሊክ ዘለቀ ናቸው። አቶ ሚኒሊክ ዘለቀም ለዚህ ትብብሩ ይመስለናል ካህኑ የሰበካ ጉባኤ አባል አድርገው መርጠውታል።
በዚህ ሁኔታ ከቤተክርስቲያን በተባረሩት ስዎች የተቆጣው ምዕመን የቤተክርስቲያንዋ አስተዳዳሪ እንዲያነጋግሩት በመጠየቁና ካህኑም በግፊት ቀርበውከውስጣችሁ ሽማግሌ መርጣችሁ ያነጋግሩኝባሉት መሠረት በእለቱ ከነበሩት ምዕመን ሽማግሌዎች ተመርጠው ካህኑም ሽምግልናውንና ሽማግሌዎችን ተቀበለው ሽምግልናው ተጀመረ። ሽማግሌዎችም ጉዳዩን በስላማዊ መንገድ ለመፍታት በርካታ ስብስባዎችን ያደረጉ ቢሆንም ካህኑ ግን እርቁ እንዳይሳካ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ምክንያቶችን ከመስጠታቸውም በላይ ሁለቱን ወገን በአንድ ላይ ለማነጋገር በተቀጠረው ቀንና ቦታ ላይ ለመገኘት ተስማምተው ሌላው ወገን ሲቀርቡ ካህኑ ግን ሳይቀርቡ በመቅረታቸው የሽማግሌዎቹም ድካም ከንቱ ሆኖ ቀርቷል። ይሁንና የሽምግልናው ቡድን ሁለቱንም ወገን ያወያየበትን ቃልጉባኤ፤ የግጭቶቹን መንስዔዎችንና የመፍትሔ ኃሳብ ያላቸውን 17 ገጽ ወረቀት ለሁለቱም ወገን በጽሁፍ ስጥቷል። ካህኑም ይህንን የሽምግልና ውጤት ካነበቡት በኃላ ከምዕመኑ ጋር እንደሚወያዩ በተደጋጋሚ በየእሁዱ ቢገልጹም እንደልማዳቸው ነገሩን አረሳስተው አልፈውታል።
የሽምግልና ቡድኑ እንደመፍትሔ ሃሳብ አድርጎ ያቀረባቸው ዋና ዋና ነጥቦች፤
1.    ቤተክርስቲያንዋ ከሲኖዶስ ውጭ በመሆንዋና ችግሮችም ሲፈጠሩ መሥመር የሚያስይዝ የበላይ አካል ባለመኖሩ ወይም በህዝብ የተመረጠ ጠንካራ ተጠሪነቱ ለምእመኑ/ለጠቅላላ ጉባኤ የሆነ የሰበካ ጉባኣኤ ወይም ቦርድ አለመኖሩ፣
2.   ቦርዱ/የስበካ ጉባኤው የሚመራበት ገዥ የሆነ ደንብ ባለመኖሩ፤ያለውም ደንብ ቢሆን የአንድ ካህንን ፈላጭ ቆራጭነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ፤
3.   የሰበካው/የቦርዱ አባላት በጠቅላላ ጉባኤ ምርጫ አለመሰየማቸውና እነዚህን አባላት የመሰየምና የመሻር መብት የጠቅላላ ጉባኤው ባለመሆኑ፣
4.   ግልጽነት የተሞላበት የገቢ አሰባሰብና የወጪ ሥርዓት አለመኖር ናቸው።
ከላይ እንደተገለፀው ችግሩን በስላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ በመቅረቱና ቤተክርስቲያንዋም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን የቤተክርስቲያንን አሠራርና ሥርዓትን በተወሰኑ ግለሰቦች መጣስ እንደሌለበትና ይህ በመንፈሳዊ አባቶችና በእምነቱ ተከታዮች ደምና ሕይወት ተጠብቆ የቆየውን ሀይማኖታችንና የቤተክርስቲያናችንን ሥርዓት ለልጆቻችን ለማቆየት እና በየቀኑ የሸረሪት ድር እየጠረጉ ከመኖር ሽረሪቷን ማስወገድ ዘላቂ መፍትኼ ነው በማለት ቆርጠው በተነሱ የቤተክርስቲያንዋ በርካታ ምዕመናን በቤተክርስቲያንዋ አስተዳዳሪና የሰበካ ጉባኤ አባላት ላይ ክስ መስርተዋል። ካህኑም  ምዕመኑን በማንኛውም ጊዜ የማባረርና ከሀይማኖቱና ከሕብረተስቡ የማግለል ሥልጣን አንዳላቸው እንዲሁም ፍርድ ቤቱ ይህንን ክስ የማየት ሥልጣን የለውም በማለት ለተከሰሱበት ክስ መልስ ቢሰጡም ፍርድ ቤቱ .. 8/14/2010 በዋለው ችሎት የካህኑን ከርክር ውድቅ አድርጎ በፍሬ ጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ተይዟል። ይህ ውሳኔ ለቤተክርስቲያናችን ብቻ ሳይሆን በዚህ አገር ላሉትም ተመሳሳይ አጉራ ዘለሎች ትምህርት ስጪ ነው ብለን እናምናለን።
በአጠቃላይ ዓላማችን ግለሰቦችን ያለበቂ ምክንያት ለመፃረር ሳይሆን ቤተክርስቲያናችን ሁሉንም በበላይነት የሚገዛ መተዳደሪያ ደንብ እንዲኖራት ለማድረግ ነው። ይህንንም ደንብ ተግባራዊ የሚያደርጉ ተጠሪነታቸው ለጠቅላላ ጉባኤው የሆነ በምዕመኑ የሚሾሙና የሚሻሩ የሰበካ ጉባኤ አባላት አንዲኖሩን ነው።ሥራን የሚያቀላጥፉ ብቃት ያላችው አባላት ያሉበት ንዑስ ኮሚቴዎች ተዋቅረው የአዲሱ ቤተክርስቲያናችን የገንዘብ አሰባሰብና የሕንፃ ግንባታ ሥራን ለማቀላጠፍ ነው። ከምዕመኑ የሚሰበሰበው ገንዘብና ወጪ  ምዕመኑ በየጊዜው ሊያውቀዉና ሊቆጣጠረው የሚያስችሉት የሂሳብ አያያዝ እንዲኖረን ነው። ይህንን የሚፃረር ካህን ወይም ምዕመን ካለ ዓላማው ግልፅ ስለሆነ እስከመጨረሻው ለመታገልና የእግዝአብሔርን ቤት ለማፅዳት ግን ዓላማችንና ግባችን ንው።
ስለዚህ ሀይማኖታችንና የቤተክርስትያናችንን ሥርዕት የመጠበቅና ለልጆቻችን የማስተላለፍ ኃላፊነት ለተወሰኑ ምዕመናን ብቻ የሚተው ጉዳይ ስላልሆነ በኪዳነ ምሕረት ስም የተስየመውን የእግዚአብሔርን የጸሎት ቤት የማጽዳትና ሥርዓት የማስያዝ መንፈሳዊ ግዴታና ኃላፊነት የሁላችንም የዚሁ እምነት ተካታዮች እንደሆነ እናምናለን። በመሆኑም እስካሁን ድረስ ከነዚህ ምዕመናን ጎን ያልተስለፋችሁ ካላችሁ ዛሬ ነገ ሳትሉ የትግሉ አጋር በመሆን ቡድኑን በሀሳብ፣ በእውቀት እና በገንዘብ እንድትረዱት በልዑል እግዚአብሔር እና በእናቱ በኪዳነምሕረት ስም ጥሪአችንን እናቀርባለን።
አስተባባሪ ኮሚቴ
አስተያየትና ጥያቄ   bege1026t@yahoo.com   
            

  

 
       


No comments: