Sunday, October 17, 2010

የመናፍቃን ጭፈራ በእኛ ነዋያተ ቅዱሳት

“የቀደሙት ኢትዮጵያውያን የተዋሕዶ አበው ለኢትዮጵያ ሀገራችን ብሎም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘማናት የማይሽሩዋቸው ሀብቶችን አውርሰውን አልፈዋል። ከእነዚህም መሀከል በጥቂቱ  ፊደል ከነ ሙሉ አግባቡ፣ የዘመን አቆጣተር፣ የሀገር ድንበር ጠብቆ መኖር፣ ሥነ ጽሑፍን፣ሥነ ኅንፃን እናም ሌሎችም የሚጠቀሱ ናቸው” (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ )። እነዚህ አበው በተለየ ሁኔታ ሐዋርያዊት ለሆነችው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በደማቸው ቀለም በጥብጠው ቅዱሳት መፃህፍት ደርሰው እንዲሁም ተርጉመው፤ የዜማ መሳሪያዎች ከነ ሚስጥራቸው እና ትርጓሜያቸው፤ እንዲሁም ንዋያተ ቅድሳትን በየዘርፉ ለያየተው አስቀምጠውልን አልፈዋል። ለእነዚህ ቅዱሳን አበው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅድስናን ሰጥታ ለዘላለም ስታዘክራቸው ትኖራለች።

ዛሬ ይኅን ጽሑፍ ለመፃፍ ያስገደደኝ ኢትዮ ትዩብ በሚለው ድህረ ገጽ http://www.blogger.com/%28http://www.ethiotube.net/video/8669/Yetsidiq-Tsehay-Ethiopian-Gospel-Singers%29%20ላይ መናፍቃኑ ቅዱሳን አበው ያስረክቡን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለተለያዩ አገልግሎት የምትጠቀምባቸው ንዋያተ ቅድሳት እና የዜማ መሳሪያዎችን ይዘው ሲጨፍሩ በማየቴ ነው። እነዚህ መናፍቃን ባገኙት አጋጣሚ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያንቋሽሹ ሰምተናቸዋል እየሰማንም ነው። እንዲሁም የቅርብ ግዜ ትዝታችን “ አቡነ ያሬድ” ነኝ በማለት አንድ መናፍቅ በጵጵስናን ማዕረግ ላይ ሲቀልድ እና ሲያንቋሽሽ አይተናል። ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮያ ያበረከተችውን አስተጽኦ ከምንም ሳይቆጥሩ ለኢትዮጵያ ድህነት ተጠያቂዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ናት ሲሉም በዝምታ አልፈናቸዋል።

ታዲያ እነሱ የሚያንቁሽሹዋቸው አባቶቻችን የሰሩልን የዜማ መሳሪያዎችን እና ንዋያተ ቅዱሳቱን ይዘው ለጭፈራ ሲጠቀሙባቸው አይቶ ዝም ማለቱ የሚያስችል አይደለም። ለቅዱሳን ክብር የማይሰጡ እነዚህ “የእፉኝት ልጆች”፤ ዛሬ ከበሮውን፣ ፀናጽሉን፣መፆረ መስቀሉን፣ጽናውን፣ ቃጭሉን፣ መቋሚያውን ካባ ላንቃውን ይዘው ሲጨፍሩ አይተናቸዋል። ነገስ ታቦተ ህጉን ይዘው ሲጨፍሩ እያየን ዝም ልንላቸው ነውን? መልሱን ለእናንተ ትቼዋለሁ።

አንድ መምህር ሲያስተምሩ “እኛ በምናከብራቸው የጌታ አብይ በዓላት ላይ በቴሌቭዥንና በሬድዮ የምናያቸው ሌሎቹን ነው፤ በመሰረቱ በዓላቱ የእኛ ቤተ ክርስቲያን በዓላት ናቸው። እኛ ካላንደሩን ወይም ዘመን አቆጣጠሩን አንሰጥም ብንላቸው እኮ መቼ እንደሚከበር አያውቁትም ነበር” በማለት ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ታዲያ ከሉተር የወረሱት መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ነው እንዴ? ዘመን አቆጣተሩም የሙዚቃ መሳሪያውም ቢወስዱ ይሻላቸዋል። ለምን ይቅበዘበዛሉ?

የዜማ መሳሪያዎቻችን እኮ እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ የተቀመረ የሚያስተላልፉት ሚስጥር አላቸው።  ታዲያ እነዚህ የዜማ መሳሪያዎቻቻን እና ንዋያተ ቅድሳቱ ከሙሉ ሚስጥርና ትርጉማቸው ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፉ የእኛ ሀላፊነት ነው። አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱን በማስተዳደር ላይ ያለው  አካል የቤተ ክርስቲያኒቷን መብቶች የማስጠበቅ ግዴታ አለበት። ካልሆነ ግን ያው እንደ አስተዳደሩም ብልሹነት ታሪክ ሲወቅሰውና ሲያወግዘው ለዘላለም ይኖራል ማለት ነው። እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት እና ይመለከተናል የምንል ወገኖች ሁሉ በያለንበት የቤተ ክርስቲያኒቱ መብቶች ለማስጠበቅ በንቃት መንቀሳቀስ መቻል አለብን። የኮቲ ራይት በተጠበቀበት ዘመን የቤተ ክርስቲያኒቱን አንጡራ ሀብት የሆኑት ንዋያተ ቅድሳት በእኛ ዘመን ለጭፈራ አገልግሎት ሲውሉ ማየቱ አለመታደል ነው።

1 comment:

raguel orto said...

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 10:10 ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም.............ተው፡ሊባሉ፡ይገባል፡፡ፀበልን፡ሊያስተው፡ፀበል፡ያዝ፡የነበረ፡ክፉ፡መንፈስ፡እራሱን፡ቀይሮ፡የማያምንበትን፡ንዋያተ፡ቅዱሳን፡ይዞ፡መታየቱ፡
ለምን፡ይሆን?እውን፡ሊጠቀምበት፡ነው?ሌባ፡ነውና------ቅዱስ፡ሲኖዶስ፡የቤተክርስቲያንን፡መብት፡ማስከበር፡አለበት