Friday, January 21, 2011

"ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን" አዲሱ ተስፋዬ

ተሐድሶ ምንድ ነው? ቤተ ክርስቲያናችን የሃይማኖት ተሐድሶ ያስፈልጋታልን? እንግዲህ ተሀድሶያውያን “በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ Lutheran church እንመሰርታለን” የሚል አቋም እንዳላቸው ብዙ መረጃዎች ይመሰክራሉ:: ይህ እንቅስቃሴ በቀደሙ ግዜያት በስውር እንደነበረ ይታወቃል:: አሁን ግን ዓላማዎቻቸው እና ታሪካቸውንም ጭምር አቡጊዳ  በተባለው ድህረ ገጽ በማቅረብ ላይ ናቸው:: አቶ አዲሱ ተስፋዬ የተባሉ ሰው የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረተ እምነት እና ታሪክ ተመርኩዘው በድህረ ገጹ ላይ ተሀድሶያውያኑ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እና ማኅበረ ቅዱሳን በተመለከተ ለሚያወጡት ጽሑፍ ምላሽ ሰጥተውበታል:: መልካም ንባብ::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕህዶ ቤተክርስትያንን ለማፈራረስ በተለያዩ ግዜያት በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል። መሰረትዋ በዓለት ላይ የሆነው ተዋሕዶ ግን በማንም ሳትንበረከክና ሳትፈርስ ለሁለት ሺህ ዓመታት ተጉዛ እዚህ ደርሳለች። ፈተናው ግን አሁንም አልቆመም። የወቅቱ የቤተ ክርስትያን ፈታኞች ደግሞ በደጉ፣ በሊቁና በታላቁ የኢትዮጵያ ንጉስ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ላይ ዘምተዋል። በበርካታ ድረ ገጾች ላይ ስማቸውንና ክብራቸውን የሚያጎድፍ አዲስና ተለጣፊ መሰረተ ቢስ ታሪክ ከመለጠፍ አልፎ ፤ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ሥርዓትና ሃይማኖት ያበላሹ ንጉስ “ ብለው እስከመሳደብ ደርሰዋል። እነዚሁ የተረት ሊቃውንት፣ “ታምረ ማርያምን የጻፉ እሳቸው ናቸው፣ ገዳም ገብተው ያፈረሱ መነኩሴ ነበሩ” እና ወዘተ የሚሉ የፈጠራ ክሶችንም አስነብበዋል። እውን ግን የዐፄ ዳዊት ልጅ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ይህን አድርገው ይሆንን ? ኧረ በፍጹም። እንዲያውም በኢትዮጵያ ቤተ መንግስትም ሆነ ቤተ ክህነት ከፍተኛ ውለታ ሰርተው ያለፉ ደግና ምትክ የለሽ ነጉስ ነበሩ። አንቀጽ ባንቀጽ እንመልከት ፡:

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ፤ ሲነግሱ የተረከቡዋት ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ፈጠጋር በተባለው ቦታ (ባሁኑ ኦሮምያ ክልል አዋሽ ወንዝ አካባቢ) ተወለዱ።እንደ ንጉስ ልጅነታቸውም በቤተ መንግስት አደጉ። አባታቸው ዐፄ ዳዊት ሲሞቱ ታላላቅ ወንድሞቻቸው ዐፄ ቴዎድሮስ (ቀዳማዊ) እና ዐፄ ይስሐቅ ንግስናውን ተረክበው ኢትዮጵያን ለ20 ዓመታት ገዙ። ወንደሞቻቸው ነግሰው ሳለም አምባ ግሼን ላይ ለብዙ ዓመታት ታሰሩ። በኋላም እሳቸው ነገሱ። ከነገሱም በኋላ የሲዳሞ ሀድያ ንጉስ ልጅ ከእስልምና ወደ ክርስትና አስጠምቀው አገቡ።

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የተረከቧት ኢትዮጵያ ግን በቤተ መንግስቱም በቤተ ክህነቱም ወገን አሳሳቢ እና አስፈሪ ሁኔታ ላይ ነበረች። አባታቸው ዐፄ ዳዊት “አባይን እገድባለሁ” ብለው ግብፆችን አስፈራርተዋቸው ስለነበር፤ ግብፆችና ቱርኮች በአዳል በኩል ክርስትያኑን መንግስት ለመደምሰስ ተዘጋጅተዋል። በሰሜን የዮዲት ጉዲትን የአይሁድ ስርወ መንግስት መልሶ ለመትከል ቤተ እስራኤሎች( ፈላሾች) ጦር ሰብቀው ተነስተዋል። ቤተ ክህነቱም ውስጥም ውዝግቡና ልዩነቱ ሰፍቶ ነበር። ቤተ ተክለ ሃይማኖትና ቤተ ኤውስጣጥዮስ ልዩነታቸው ከሮ ሰፊ ክፍተት ተፈጠረ። ሚካኤላውያን ሚባሉቱ ሌሎች ደግሞ ራሳቸውን መለየት ጀመሩ።የአይክኖክላስትን የኑፋቄ መርዝ የሚረጨው የነእ እስጢፋኖስ ( የደቂቀ እስቲፋኖስ መነሻ) ቡድንም ሌላው ችግር ነበር። //

ጀግናው ፣ሐዋርያው እና ሊቁ ዘርዐ ያዕቆብ ግን በግብፅና በቱርክ ድጋፍ የክርስትያኑን መንግሰት አጥፍቶ የእስላም መንግስት ለመትከል አስቦ የተነሳውን እና የዮዲትን ያይሁድ መንግሰት ለመትከል የተነሱትን የፈላሻ እንቅስቃሴ በጦር ሀይል ድባቅ ከመቱ በኋላ ፤ በሃይማኖት የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት ፊታቸውን ወደ ቤተ ክህነት መለሱ ።

ቤተ ተክለ ሃማኖትና ቤተ ኤዎስጣጢዮስ፤ ሚካኤላውያን እና የአይክኖክላስት ኑፋቄ አራማጆች። ሶስቱንም በመጠኑ እንመልከት።

ቤተ ኤዎስጣጢዮስ እና ቤተ ተከለ ሃይማኖት

በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት ተነስቶ የነበረው ከባዱ የየሃይማኖት ውዝግብ የቤተ ተክለሃ ይማኖት እና በቤተ ኤዎስጣጢዎስ መካከል ሰንበትን በተመለከተ የተነሳው ልዪነት ነበር።የልዩነታቸውም ምክንያት የሰንበት አከባበር ሲሆን ፣ ቤተ ተክለሃይማኖቶች ትምህርታቸው ሰንበት እሁድ ብቻ ናት ሚል ሲሆን ፤ የቤተ ኤውስጣጢዮሶች አስተምህሮ ደግሞ ቅዳሜና እሁድ ( ቀዳሚት ሰንበት ቅዳሜ እና የሐዲስ ኪዳን ሰንበት እሁድ ) ሁለቱም ሰንበታት ስለሆኑ መከበር አለባቸው የሚል ነበር። ሁለቱም አመለካከቶች ይመሩ የነበሩት በወቅቱ ከፍተኛ ክብርና ዝና በነበራቸው ሊቃውንት አባቶች መሆኑ ሌላው ፈታኝ ነገር ነበር። ቤተ ተክለሃይማኖቶች በማእከላዊ ኢትዮጵያ ባሉ ክፍላተ ሀገራት ባሉ ገደማትና ምዕመናን ክፍተኛ ተከታይ ነበራቸው። ግብጻውአኑ ጳጳሳትም ቤተ ተክለሃይማኖትን የመደገፍ አዝማሚያ ማሳየታቸው ደግሞ ሌላው አበይት ጉዳይ ነበር።

ቤተ ኤውስጣጢዮሶች ደግሞ ከአስመራ( ኤርትራ) የሚገኘው የደብረ ቢዘን ገዳም ጀምሮ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባሉ ሌሎች ገዳማትና አድባራት በርካታ ተከታዮችና ደጋፊዎች ነበሯዋቸው።ይህም ራሱን የቻለ ፖለቲካዊ መዘዝ ነበረው። በወቅቱ ለንጉሰ ነገስት አጼ ዘርአያዕቆብ ከባድ ፈተና ነበር;; ይንንም ዝነኛው ታሪክ ፀሀፊ Adrian እንዲል ሲል ይገልጸዋል

“Debre Bizan, the greatest of Ewostotathian monastery lies on the Eastern edge of the plateau of Eritrea, only ten miles from the sea and overlooking the coast . The political value of supporting Sabbath observance with in Zera Yaikobs strategy is obvious enough. With out Ewostotathian loyality Eritrea , the coast , and even wider areas of the North might hardly be served . yet he waited pretty patiently before calling the council”

ይኸው በሊቃውንቱ መካከል የተፈጠረ ልዩነት ወደ አስከፊ ክፍፍል እያመራ በመሄዱና የሀገሪቱንም ህልውና ችግር ውስጥ እየከተተ እንደሆነ የተረዱት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የተባሉት ጳጳሳትን ከግብጽ ካስመጡ በሁዋላ በሁለቱ አስተምህሮዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት በተጉለት ቡልጋ ደብረ ምጥማቅ ገዳም ጉባኤ ዘረጉ። በዚሁ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤተ ክርስትያን ሊቃውንት በተገኙበት ጉባኤ ላይ መጠነ ሰፊ ክርክር ከተደረገ በሁዋላ ሊቃውንቱ ሰንበታት ማለትም ቀዳሚት ሰንበት ቅዳሜና የሐዲስ ኪዳን ሰንበት እሁድ ሰንበታት ተብለው መከበር እንደሚገባችው ፤ የቀዳሚት ሰንበት አከባበር ግን እንደ አይሁድ ባለ አከባር ሳይሆን ክርስቲያናዊ አከባበርን የተከተለ መሆን እንዳለበት የሁለቱም ወገኖች ሊቃውንት ተስማምተው ለ በርካታ አስርተ አመታት የቤተ ክርስትያን አባቶችን ሲያናቁር የነበረው የሰንበት አከባበር ጉዳይ በማያዳግም ሁኔታ ተወሰነ።ለዘመናት ሲንከባል የመጣው ልዩነት በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት መፍትሄ አገኘ።

ሚካኤላውያን

ሌላው በእኚሁ ንጉስ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ህዝቡን ያምስ የነበረው የሃይማኖት ውዝገብ ሚካኤላውያን የሚባለው ነበር። ይሕው “የዘሚካኤላውያን” በመባል ሚታወቀው እንቅስቃሴ ጊዮርጊስ በሚባል መነኩሴ ይመራ ነበር። ትምህርታቸውንም Church in EthiopiaAfrica በተባለው መፅሀፍ እንዲህ ሲል ሲገልፀው

“ Giorgis a monk who taught the unknowabilty of God and gave rise to the group known as The mikaelities “ ::ግብፃውያኑ የታሪክ ጸሀፊዎች ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አብራርተው ፅፈውታል።

“ .. compared the unity and trinity of God with three suns whose lights are united when they appear side by side, three suns (persons) with one light (divinity). The opponents of this view, proposed instead, as Fre Makhebar did, one sun with a disk (God the Father), light (God the Son), and heat (God the Holy Spirit). ‘

የዚህ ቡድን አባለት በርካታ የሚያነሳቸው ነጥቦች ቢኖሩም ዋናው የሚታወቁበት አጀንዳ ግን በምስጢረ ስላሴና ምስጢረ ስጋዌ ጉዳይ ነበር ፤፤ ጥቂቶቹ የክርክር ነጥቦቹም እነዚህ ነበሩ

• ስላሴ ጎን ለጎን ባሉ በሶስት ነገር ግን አንድ ብርሃን( መለኮት) ባላቸው ሶስት ጸሐይ ይመሰላሉ ። የለም ስላሴ ባንድ ጸሐይ ይመሰላሉ። የጸሐዩ ክበብ አብን ብርሀኑ ወልድን ሙቀቱ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን በሚለው ምሳሌ ይመሰላሉ …

• ወልድ ለፍርድ ሲመጣ አብና መንፈስ ቅዱስም ከጎኑ ሆነው በሰው አምሳል ይታያሉ እና ይህን መሰሎች ነበሩ።

ይህም ልዩነት ለመፍታትም በዘርአያቆብ ድካም ጉባኤ ተዘረጋ። ሊቃውንቱ ተቀምጠው ተወያይተው ትክክለኛው ትምሀርተ እንዲፀና አደረጉ።

ደቂቀ እስጢፋኖስ ( ኤኢክኖክላስቶች)

በሜድትራኒያን አካባቢ ከ 7-9ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ “ስዕላትን እና ቅርፃቅርፆችን ከቤተክርስትያን ይወገዱ” የሚል የኑፋቄ ውዝግብ ተነስቶ ነበር። Iconoclast የተባሉት ቡድኖች ስእላት በቤተክርስትያን አያስፈልጉም ብለው ስእላትን ካምልኮ ስፍራዎች በሙሉ ለማስወገድ ተነስተው ነበር {}። የሜዲትራንያኑን ዓለም ክርስትያኖች ያመሰው ይህ የኑፋቄ ትምሀርት ወደ ኢትዮጵያም በ 13ኛው ክፍለ ዘመን እየተንዃተተ መግባቱ አልቀረም። ባፄ ይግባ ፅዮን ዘመነ መንግስት( 1285-1294) አንዳንድ በ ኢትዮጵያ ቤተ ክህነት ውስጥ ይህንን ሐሳብ የሚያራምዱ አይክኖክላስቶች ( ፀረ ስእልና ቅርጻ ቅርጽ ) ተነስተው እንደነበረ የኮፕት ታሪክ ሊቃውንት በኮፕቲክ በመዛግብታቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል ።

“In Ethiopia it started during the reign of Yagbe’a Seyon (1285-1294), when a group of clergy maintained that the icon was mere slate and the cross a mere piece of wood from Golgotha. These dissidents created great schism in the church. Since Ethiopian leaders suppressed dissidence …”

እነዚሁ ኤክኖክላስቶችን የተበከለ ትምህርት ይዘው ስእልና መስቀል ከቤተ ክርስትያን መውጣት አለባቸው ብለው ቤተ ክርስትያንን ሲበጠብጡ የነበሩት አካላት በወቅቱ በነበሩ ሊቃውንትና በነገስታቱም ድጋፍ ከቤተ ክርስትያን ከኑፋቄያቸው አንዲታገሱ ቢደረግም ፤ ውስጥ ለውስጥ ግን መርዛቸውን ማግሳታቸው አልቀረም።በ15ኘው ክፍለ ዘመን ተነስቶ የነበረውም መናፍቁ እስጢፋኖስና ተከታዮቹ ደቂቀ እስጢፋኖስ በመስቀልና በመቤታችን ክብር ላይ ያነሳው ጥያቄ መነሻው ይሄ ከሜድትራኑ ዓለም በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ተነስቶ የነበረና በሁዋላ ባስራ ሶስተኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የገባ ፤ በወቅቱ የነበሩትም ንጉስ ዐፄ ግባጽዮንና በሊቃውንቱ ተወግዞና ታግሶ የነበረ ኑፋቄ ፤ በሁዋላም በዘመነ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት እስጢፋኖስ መልሶ ያነሳው ትምህርት ነው። ይህንንም ችግር ለመፍታት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ባደባባይ ጉባኤ ስለጠሩና ጉዳዩ ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብና ከእስጢፋኖስ ስም ጋር ይነሳል እንጂ የዚህ የኒፋቄ ትምሀርት መነሻ ኤክኖክላስቶች ናቸው( የዛሬው ጂሆባ መሰረቱ የጥንቱ አርዮስ እንደሆነው ሁሉ ) ።

በዘመናቸው የተነሳውን የሃይማኖት ውዝግብ መፍትሄ ካልሰጡ ለሀገር የሚተርፍ ችግርና መዘዝ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል የተረዱት አጼ ዘርአ ያእቆብ፤ አስጢፋኖስንም ለሌሎቾ ( ለቤ ተክለሃይማኦትና ለቤተ ኤውስጣጢዮሶች እንዲሁም ለሚካኤላውአን ) እናዳደረጉት ሁሉ ጉባኤ ሰርተው ሊቃውንቱን ሰብስበው አወያዩ;

አቡነ ጎርጎርዮስ የቤተ ክርስትያን ታሪክ በተባለው መጽሀፋቸው ገጽ 45 ላይ ሁኔታውን እንዲህ ገልጸውታል

“ ቤተ ክርስትያናችንን ስነ ጽሁፍና ኪነ ጥበብ አስፋፉት ፣አምልኮ ጣኦትን ከምድረ ኢትዮጵያ ለማጥፋት የታገሉት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ናቸው። ከዚህም ሌላ በዘመናቸው ዜና መዋእላቸው እንደሚለው ደቂቀ እሰጢፋ የሚባሉ ለእመቤታችንና ለመስቀል ስግደት አይገባም የሚሉ መናፍቃን እንደተነሱ ይጽፋል። ይኸውም ዜና መዋዕል እንደሚባለው እነዚህን መናፍቃን ንጉሱ ባሉበት ሊቃውንቱ ተከራክረው ረቱዋቸው. ከዚህ በሁዋላ እነ ደቂቀ እስጢፋኖስ ለፍርድ ወደ ንጉሱ ቀረቡ ። ንጉሱም ፍርዳቸውን ክምእመናን እንዲቀበሉ የተሰበሰቡትን ምእመናን ጠየቁ ሁሉም በሞት ቅጣት እንዲቀጡ በየነባቸው።

የዘርዐ ያዕቆብ መጻሕፍት

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በቀደሙት ግዜያት ተነስተው ሲንከባለሉ እሳቸው ዘመነ መንግስት ላይ ደርሰው ምእመናንና ቤተ ክርስትያንን ሲያውኩ የነበሩ ሶስቱንም ልዩነቶች ፣ ሊቃውንቱን ስብስበው አከራክረው ሰላም አወረዱ። ደብረ ምጥማቅ ቡልጋ በተካሄደው ጉባኤ ቤተ ተክለሃኢማኖትና ቤተ ኤውስጣጢዮሶች ለበርካታ ዘመናት የቆየውን የሰንበት አከባበር ልዩነታቸውን አስወግደው ተስማሙ።፡ ሚካኤላውያንም አንስተውት ነበረውን የሚስጥረ ስላሴ ና ስጋዌ አስተምሀሮ ልዩነት በጉባኤ ተፈታ። መናፍቁ እስጢፋኖስ ም ከሊቃውንቱ ጋር ተከራክሮ ተረታ።

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ችግሩ ተፈታ ብለው ግን አርፈው ቁጭ አላሉም። ከዚህ በፊት ተነስተው ነበሩ ችግሮች ወደፊትም እንዳይደገሙና በቃል የተደረገው ክርክር ቢረሳ በማለት ህዝባቸውን የሚመክር መጻህፍትን ማዘጋጀት ጀመሩ።የሚካኤላውያን የሃይማኖት ጉዳይ ከሚስጥረ ስላሴ ጋር የተያያዘ መሆኑን ተረዱት ነጉሰ ነገስት ዘርአያዕቆብ መጽሐፈ ስላሴ የሚባል መጽሀፍን ደረሱ። መናፍቁ እስጢፋኖስ በመቤታችን ክብር ላይ የኑፋቄ መርዝ እንደረጨ የተገነዘቡት ዘርአያዕቆብ መጽሀፈ ምእላድ የሚባል መጽሀፍን ደረሱ። ስለ ሰንበት አከባበርና ሌሎች ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የሚመክር መጽሀፈ ብርሃን ተሰኘ ሌላ አስደናቂ መጽሀፍ ደርሰው ለህዝባቸው መማርያና መጽናኛ ይሆን ዘንድ አበረከቱ።

ተአምረ ማርያምና ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ
አንዳንድ የተሳሳቱ ወገኖች ተአምረ ማርያምን የደረሱት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እንዲሆኑ አድርገው በሬ ወለደ አይነት ተረት ሲያወሩ ይደመጣሉ። ሌሎች ደግሞ “ታምረ ማርያምን ለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ያስተዋወቁት እንዲነበብም ያደረጉት እሳቸው ናቸው” በማለት የተሳሳተ ታሪክ ያወራሉ ይጽፋሉም። እውነቱ ግን ሌላ ነው።

ታምረ ማርያም ከጥንት ጀምሮ በ አትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ሲነበብ የነበረና በሊቃውንቱም ሆነ በምእመናኑ ዘንድ የተከበረ መጽሀፍ ነው። ለዚህም እንደከዋክብት የበዛ ማስራጀ ማቅረብ ቢቻልም ጥቂቱን እንመልከት ።

Jacques Mercier, “Ethiopian Art History” in Ethiopian Art: The Walters Museum (London: Third Millennium, 2001), በተባለው መጽሀፉ ገጽ 51ላይ ታምረ ማርያም ባጼ ዳዊት ዘመነ መንግስት ይነብብ እንደነበረና አረብኛውንም ታምረ ማርያም ያስተረጎሙት አጼ ዳዊት መሆናቸውን እነዲህ ሲል ይገልጣል።

“During his(Dawit) reign, two surviving examples of illustrated manuscripts were produced. One is a translation of the Miracles of Mary which had been written in Arabic, done at the command of Emperor Dawit; this is the oldest surviving illustrated book commissioned by an Ethiopian Emperor”

James bedinger , African kings በተባለ መጽሀፉ ላይም ዛግዌ ነገስታት በመቤታችን ስእል ስርኛ በመስቀል ስር ሰግደው ተንበርክከው ጸሎት ያደርሱ እንደነበረ ፤ታምረ ማርያምም በየሰንበቱ ይነብብ እንደነበር መስቀልንም ይስሙ ይሳለሙ እንደነበረ በማያሻማ ጽሁፍ ገልጾታል።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገድለ ዜና ማርቆስ የያዛቸው መረጃዎችና ሁነቶች በሚል ጥናታው ጽሁፉ ላይ አንዳቀረበው ገድለ ዜና ማርቆስ ብዙ ምስክርነቶችን የሚሰጥ ሲሆን … ጸሐፌ መንክራት ዮሐንስ ተአምረ ማርያምን በጻፈ ጊዜ እመቤታችን ያደረገችለትን ነገር /ገጽ.192/፡፡ ተአምረ ማርያም ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በፊት እንደ ነበረ መረጃ እንደሚሰጥ ይገልጣል።

የመቤታችን 33ቱ በ ኣላትም አፄ ዘርአያቆብ የፈለሰፉት ሳይሆን በወቅቱ ክግበፅ ቤተክርስትያን ( ሙአላቅ) የተወሰደ ስርአት እንደሆነ ይህንን በረከት በአልም ያስተማሩት ግብፃውያን እንደሆኑ ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ይናገራል።

“Many miracles that she worked in Spain, France, Italy, Syria, and Egypt were translated into Ge‘ez, the church language of Ethiopia. At that time, the rule from Mu‘allaqa, Masehafa ser‘at, ordaining thirty-three holidays in honor of the Virgin, was brought to Ethiopia.”

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ በርካታ ጉባኤያት እንዲካሄዱ በማድረግ ቤተ ክርስትያንን ትምህርት አፅንተዋል። በቤተክርስትያን አነጋገር ትምህርተ ሃይማኖት በጉባኤ ተወሰነ ሲባል፤ሰዎች ተሰባስበው የጋራ መግለጫ አወጡ ማለት ሳይሆን ፤ገበሬ እህሉ አጠገብ ወይም እህሉን መስሎ አዝመራውን የሚጎዳ አረም ሲበቅል ከህሉ መካከል ነቅሎ እንዲጥል ቤተክርስትያንም ባይኑዋ አይታ በጆሮዋ ሰምታ በጇ ዳሳ በምታውቀውና በምታምነው እውነት አጠገብ የራስዋን እውነት መስሎ የሚጎዳትን የመናፍቃንን አስተሳሰብ አረም ነቅላ ለመጣል ጉባኤ ታደርጋለች። አረሙንም ነቅላ ጥላ ትምህርተ አዝመራዋን ትተክላለች። ይህም ክጥንት ሐዋርያት የተገኘ ትውፊት ነው ( ጉባኤ ኒቅያ ፣ ኤፌሶን ወዘተ ) ። አፄ ዘርአያቆብም ያደረጉት ይህንን ነው።

አንድም ለቤተ ክርስትያን እንግዳ የሆነ አዲስ ትምህርት አላስማሩም። የነበረውንና በሊቃውንት የተወሰነውን እንዲፀና አደረጉ አንጂ። ታምረ ማርያምም በዛግዌ ነገስታት ዘመን ጀምሮ ይነብብ ይከበር የነበረ መጽሀፍ እንደነበረ ታሪክ ይመሰክራል። አረብኛውን ቅጂም ያስተረጎሙት አፄ ዳዊት መሆናቸውንነ አሁንም በርካታ መረጃዎች ይናገራሉ ። ግማደ መስቀል አፄ ዳዊት ዘመን ስለመጣ የመስቀል በ አልም በድምቀት መከበር የጀመረው በሳቸው ዘመን ሲሆን ቀጥሎም ልጆቻቸው በአጼ ቴዎድሮስ (ቀዳማዊ)ና በአጼ ይስሀቅ የቀጠለ ትውፊት እንደነበረ አሁንም ታሪክ ኢመሰክራል ። አፄ ዘርኤአቆብ ይሄንን ጥንታዊ ስርአት አስተብቆ መቀጠል እንጂ ሀዲስ ትምህርት አላመጡም ። አላስተማሩምም።

ሲጠቃለል

በዘመናችን ተለጣፊ አዲስ ታሪክ እየፃፉ፣ ደጋጎችን ነገስታት ፃድቃንና ሊቃውንት መሳደብ ፋሽን ሆኖዋል። ከዚህ በፊት ለብዙዎች አዲስ ታሪክ ተፅፎላቸው ፣በሙት ደብዳቢዎች ሲሰደቡ ሲወገዙ ከርመዋል፡፤አሁን ደግሞ ተረኛው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ሆነዋል። ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ግን በቤተ ከርስቲያን የታሪክ ሰማይ ላይ ፣ እንደንጋት ኮከብ የሚያበራ ታሪክ ሰርተው አልፈዋል። ለመላው የተዋህዶ ክርስትያን በሙሉ ጀግናና ፃድቅ ናቸው –አፄ ዘርአያቆብ ዳዊት ስመ መንግስቱ ቆስጠንጢኖሰ።

“To ZeraYakob …as he grew older he grew more e worried by the weakness in the faith of his people, the superstition, the ignorance, the pagan practice, the appeal of Judaism,the pastoral laziness, the theological deviation of the monks …were his prime concerns

በክርስቶስ መሰረት ላይ የታነፀችው የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም አንድም የሚታደስ ትምህርተ (ነገረ) ሃይማኖት የላትም ። የቤተ ክርስቲን ሥርአትም ሆነ ነገረ ሃይማኖት የተደነገገው ትናንት በሚሳሳት ዛሬ ደግሞ ስተቱን በሚአርም ሰው ሳይሆን ፤ ትናትም ዛሬም በማይሳሰተው ፍፁም በሆነው መንፈስ ቅዱስ መሪነት የተደነገገ ስለሆነ መታደስ ፣ምንም አይነት ነገረ ሃይማኖትም ሆነ ስርአተ ቤተ ክርስትያን መከለስ ፣መጨመር ፣መቀነስ አያስፈልገውም። ሃይማኖት እናዳባቶቻችን ፣ጥብብ እንደግዜአችን።ሃይማኖትን ተቀብለን ለማማን እንጂ ለመከለስ ስልጣኑም፣ ብቃቱም፣ መብቱም የለንም።

ቤተ ክርስቲያንም የራሷ ፣ በድንቅ ሊቃውቶችዋ የሚመራ የሊቃውንት ጉባኤ አላት። ይህም ጉባኤ የቤተ ክርስቲያን የሆኑ መጽሐፍትን መርምሮና ተመልክቶ ያሳትማል። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የሚከለስም ሆነ የሚታደስ መፃህፍት የሉዋትም። ያለ ሊቃውንት ጉባኤ እውቅና ግለሰብ ለሚያሳትሙት ( ተስፋ ዘብሄረ ምናምን ፣ ገብረስላሴ ዘብሄረ ምናምን፣ ዲያቆን እንትና፣ ዘማሪት እንትና ) መጻሕህፍት ግን ስህትት ካለባቸው ችግሩ ራሳቸው ግለሰቦቹን( አሳታሚዎቹን ) አንጂ ቤተ ክርስቲያንን አይመለከትም።

ስለዚህ ተሀድሶዎች ሌላ መጫዋቻ ካርታ ፈልጉ። ትናትና ቤተ ክርስቲያንን እናድሳለን ብለው የተነሱ ሰዎች ዋናው ጥያቄ አድርገው ሲያቀረቡ የነበረው “በኦርጋን በጊታር አንዘምር” ነበረ።፡በኋላም “ማርያም አታማልድም ፣ መላክት አያማልዱም ፣ ክርስቶስ ነው አማላጅ” ማለት ጀመሩና በመጨረሻ የመናፍቃኑን ጎራ ተቀላቀሉ። “ተሀድሶ ነን፣ መነኮሳት ነን” ሲሉ የነበሩት እነ አባ ዮናስ ፣ አባ ብእሴ መጨረሻቸው የት እንደሆነ እኮ እንተዋወቃለን። እነ ዲያቆን ግርማ፣ እነ ገረመው ፣ ስዪም ወዘተ “ቤተ ክርስቲያን ትታደስ “ብለው መጨረሻቸው ምን እነደሆነ እኮ የቅርብ ግዜ ታሪክ ነበር; “ዛሬም ቤተ ከርስትያን እናድስ” ሚለው ዘመቻ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ ነው። አራት ነጥብ።

No comments: