Friday, February 18, 2011

መንፈሳዊ አስተዳደር መቼ ተጀመረ? ማንስ ጀመረው? ክፍል አንድ

“መንፈሳዊ አስተዳደር ከእግዚአብሔር የተግኘ፤ነገደ መላእክት የተመሩበት፤የቀደሙ አባቶች በሕገ ልቦና የተገለገሉበት፤በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል በተግባርና በፅሑፍ የተገለጠ ነው”። (የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ገጽ ፩)
፩    መንፈሳዊ አስተዳደር በዓለመ መላእክት
 •   ሰማያዊውን የእግዚአብሔር ዙፋን የሚሸከሙ ኪሩቤል/ዐርባዕቱ እንስሳ/፤ መንበሩ የሚያጥኑ ሱራፌል/ሃያ ዐራቱ ካህናተ ሰማይ/ መንፈሳዊ አስተዳደር ተለይቶ ተሰጥቶአቸዋል።
 •  ኃይላት በመንፈሳዊ ሕይወት የደከሙ ክርስቲያኖችን እንዲያበረታቱ በአመላካዊ ጥበብ ታዘዋል::
 •   አርባብ(የሚጋርዱ) የእግዚአብሔርን መንበር በክንፋቸው ይሽፍናሉ::
 •   ሥልጣናት ፍጥረተ ዓለምን እንዲጠብቱ የምጽአት አዋጅ እንዲያበስሩ ተወስኖላቸዋል::
 •   የሥልጣን ተዋረድን በሚያመለክት ሁኔታ ለዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት አለቃ ተሹሞላቸዋል::  “ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጣሁ” ኢያሱ 5፤14 
 •   የሥራ ክፍፍልና አለቅነት ብቻ ሳይሆን ስያሜ ሰጥቶ፤ ቦታ ለይቶ አስፍሮአችዋል:: “ ኪሩቤልን ሱራፌልንና ኃይላትን በኢዮር፤አርባብን መናብርትንና ሥልጣናትን በራማ፤ መኳንንትንና ሊቃናትን በኤረር” አክሲማሮስ  
 •    በአጠቃላይ ከአለመ መላእክት የስራ ክፍፍልን የስልጣን ተዋረድን የአገልግሎት ሥራዓትን ተጠያቂነት ባለው መልኩ መማር ይቻላል::
 •   በአንድ አስተዳደር ዙርያ የሚታዩ ጉልህ ተግባራትን ከዓለመ መላእክት ማንበብ ይቻላል::
፪   መንፈሳዊ አስተዳደር በሕገ ልቦና
 •  በወረቀት የተጻፈ ሕግ ሳይኖር ሰው ራሱንና ፍጥረተ ዓለሙን ለማስተዳደር ይችል ዘንድ በእግዚአብሔር ተሹሞዋል::   “ምድርን ግዙአት …በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ግዙአቸው…” ዘፍ 1፤28
 •   በዚህም መሰረት እስከ ሕገ ኦሪት የነበሩ ደጋግ አባቶች ንጉስ ካህን ነቢይ በመሆን ቤተሰባቸውና ወገናቸውን መርተዋል::
 •     በሕገ ልቦና የነበረው መንፈሳዊ አስተዳደር ራስን፤ ቤተሰብን በህገ እግዚአብሔር ከማስተዳደር ጀምሮ እስከ ብሔራዊ አስተዳደር የዘለቀ ነበር። ለምሳሌ የሳሌም ንጉሥ መልከ ፤ጼዴቅ ዘፍ 14፤18
፫    የደብተራ ኦሪት አስተዳደር በሕገ ኦሪት
 •  በዘመነ ሙሴ የነበረው መንፈሳዊ አስተዳደር ከቤተመቅደስ አልፎ አሁን በዓለም ላለው ዘመናዊ የአስተዳደር ትምህርት መሠረት ሆኗል። “እግዚአብሔር ሙሴን አለው ከእስራአኤል ሽማግሌዎችና አለቆች ይሆኑ ዘንድ የምታውቃቸውን ሰባ ሰዎችን ሰብስብልኝ    ወደ መገናኛ ድንኳን አምጣቸው።… ከአንተ ጋር የሕዝቡን ሸክም ይሸከማሉ” ዘኁ 11፤24 
 •  ከዚህም በላይ የማስተዳደር ጸጋ ከአባቶች ለልጆች ከትልቁ ለትንሹ በፈቃደ እግዚአብሔር እንደሚሰጥ ያረጋግጣል::  
 •  ዛሬም በቤተክርስቲያን የአስተዳደር ሥራ ላይ የሚሾሙ ጳጳሳት ከእነርሱ በቀደሙት ጳጳሳት የተመረጡና በፓትርያርክ የተሾሙ ናቸው::
 •     በሕገ ኦሪት በነበረው መንፈሳዊ አስተዳደር ችሎታን ያገናዘበ ምርጫ፤ የስልጣን ተዋረድና የሥራ ክፍፍል ፍንትው ብሎ ይታይበት እንደነበረ በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቧል::  “ሙሴም  ከእስራኤል ሁሉ አዋቂዎችን መረጠ” ዘጸ 18፤17
 •    የደብተራ ኦሪት የመስዋእት አቀራረብ፤የካህናት አሻሻም እና አለባበስ ሙሴ ከእግዚአብሔር ባግኘው ጸጋ ደንግጓል::
 •  የቤተመቅደስ አስተዳደር በሊቀ ካህናት በሚመራ ሸንጎ አማካይነት እስከ ሕገ ወንጌል አገልግሎቱን ቀጥሎ ነበር
 •   በሊቀ ካህናቱ የሚመራው ሸንጎ ከሰባው ሽማግሌዎች ሲያያዝ በመጣው ትውፊት ይመራ ነበር። ዘኁ 11፤17
፬.    የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በሕገ ወንጌል
 •  በሐዲስ ኪዳን የቤተክርስቲያን አስተዳደር መሥራች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው::
 •   የቤተክርስቲያን አስተዳደር ሥልጣን የክርስቶስ ስልጣን ነው:: “ሥልጣን ሁሉ በሰማይ በምድር ተሰጠኝ” ማቴ 23፤18
 •    መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥልጣኑ አስተማረ::: “እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር”
 •   ለቤተክርስቲያን አስተዳደርም በሐዋርያት በኩል ይህን የራሱን ሥልጣን ሰጠ::
 •    ቅዱሳን ሐዋርያትና በየዘመኑ የተነሱ የቤተክርስቲያን አባቶች በክርስቶስ ስለተላኩ የክርስቶስ ሥልጣን ነበራቸው:: ማቴ 28፤18-20
 •   ሐዋርያት በቤተክርስቲያን አስተዳደር መሪ በመሆን ካከናወኑአቸው ዐብይት አስተዳደራዊ ተግባራት የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል:-
        (ሀ) ትምህርተ ሃይማኖትንና የቤተክርስቲያን ሥራዓትን (ቀኖናን) ደንግገዋል። ሐዋ.ሥ 15፤29
        (ለ) ቢጽ ሐሳውያን ተመክረው ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ከቤተክርስቲያን ለይተዋል። ሐዋ.ሥ 5፤6
       (ሐ) የቤተክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የተሟላ ለማድረግ በሕዝብ ለተመረጡና በመልካም አገልግሎታቸው ለተመሰከረላቸው እጅ በመጫን ሹመት ሰጥተዋል። ሐዋ.ሥ 6፤16
 •   በኢየሩሳሌም የተጀመረው የቤተክርስቲያን አስተዳደር ሐዋርያት ዓለምን በእጣ ተከፋፍለው ማስተማር ሲጀምሩ ወንጌለ መንግስት ወደ ተለያዩ ክፍለ ዓለም ሊስፋፋ ችሏል::
 •   የአህጉረ ስብከት መብዛትም የቤተክርስቲያን አስተዳደር ሁለት ዓይነት ይዘት እንዲኖረው አድርገዋል::
1.    ዓለም አቀፋዊ ሲኖዶስ
 •     ስለ ቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት በአንድ የእምነት ጥላ ሥር የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት፤ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የሚያደርጉት ጉባኤ ነው::
 •     በኒቅያ በቁስጥንጥንያና በኤፌሶን የተደረጉ ታላላቅ ጉባኤዎች ዓለማቀፋዊ ሲኖዶስ ተብለው የሚጠቀሱ ናችው::
 •     በጉባኤያቱ የተደነገጉ ድንጋጌዎች፤የተጻፉ መጻሕፍት፤የተወገዙ መናፍቃን በአንዲት ቤተክርስቲያን ማእከላዊ አስተዳደር በሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ስለተወሰኑ የአንዲት ቤተክርስቲያን መገለጫዎች ነበሩ::
 •     በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የቤተክርስትያን  አባቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የቤተክርስቲያን አስተዳደር ለማሰናሰልና ሥራዓት ለማስያዝ ውሳኔ አስተላልፈዋል::
 •     በዚህም የነበረውን የቤተክርስቲያን አስተዳደር መስፋፋትና የፖለቲካ አስተዳደር ተከትለው በአራት ክፍሎች ከፍለውት ነበረ::  "ይህም በቀዳማዊ ደርጃ የቅዱስ ጴጥሮስ መንበር፤ በሁለተኛ ደረጃ የቅዱስ ማርቆስ መንበር፤በሦስተኛ ደረጃ የነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ መንበርና በአራተኛ ደረጃ የአንጾኪያው/የቅዱስ ጴጥሮስ ሁለተኛ/ መንበር እንደሆነ ነበር"ፍትሐ ነገስ አንቀጽ 4::
2.    ብሔራዊ ሲኖዶስ
 •     በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተዳደር በአንድ ፓትርያርክ ሊቀመንበርነት የሚመራ የሊቃነ ጳጳሳ፤ጳጳሳትና የኢጲስ ቆጶሳት ጉባኤ ነው::
 •     የግብጽ ሲኖዶስ፤ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ፤ የአርመን ሲኖዶስ… ብሔራዊ ሲኖዶስን ያመለክታል::
ይቀጥላል

No comments: