Sunday, February 27, 2011

"የመጽሐፍ ሂስ ወይስ የዶሮ ኩስ" ይድረስ ለቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

እዚህ ሀገረ አሜሪካ ውስጥ ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ እና አባ መዓዛ በየነ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአዳም ኃጥያት ወርሳለች” የሚል አስተምህሮ እያስፋፉ ናቸው:: ሁለቱንም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስም የየራሳቸው የሆነ በግል የሚያስተዳድሩት ቤተ ክርስቲያን አላቸው:: ይህንን አስተምህሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደማትቀበለው ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ የዛሬ ስድስት አካባቢ ምላሽ ሰጥተውበት ነበር:: የእነዚህን ሰዎች አስተምህሮ በመቃወም በ2002ዓ/ም መምህር ሀብተ ማርያም ተድላ የተባሉ አንጋፋ አባት “ነጭ እንቁ በአዳም ገላ” በሚል ርእስ የመልስ መጽሐፍ ጽፈውበታል:: እንዲሁም ደግሞ ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው በበኩላቸው የእነዚህ ግለሰዎች አስተምህሮ የቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ እንዳልሆነ በጽሑፍ ምላሽ ሰጥተውበት ነበረ:: በቅርቡ ደግሞ በቀሲስ አብረሃም ኅ/ሥላሴ “ማርያማዊ ሕገ ሃይማኖትና ተማኅጽኖ” በሚል ርእስ የአስተራየ አስተምህሮ በመቃወም መጽሐፍ ጽፈዋል:: ቀሲስ አስተራየ ጽጌ የቀሲስ አብረሃም ኅ/ሥላሴ መጽሐፍ በመቃወም 32 ገጽ ያለው ጽሑፍ “ኢትዮ ሚድያ” ድህረ ገጽ ላይ ጽፈው ነበረ:: የሚከተለው ጽሑፍ ለአስተርአየ ጽጌ ምላሽ የሚል ደርሶኛል:: መልካም ንባብ::

የመጽሐፍ ሂስ ወይስ የዶሮ ኩስ
ይድረስ ለ “ጠልሰም በዲሲ ደብተራ” ጨንቋሪ
ከደብተራ እሳቱ ቦጋለ


መግቢያ
“ማርያማዊ ሕገ ሃይማኖትና ተማኅጽኖ” የተባለውን የነገረ ማርያም መጽሐፍ በአድናቆትና በምስጋና ካነበብኩ በኋላ አንተ ይህን መጽሐፍ ለመንቀፍ “ጠልሰም በዲሲ ደፍተራ” ብለህ የጨነቈርከውን ድርሳነ ዘለፋ አነበብኩት። ጽሑፉህ የፈጀውን ወረቀትና ቀለም ያህል እንኳን ዋጋ የሌለው ዝባዝንኬ መሆኑን አንባቢ ሁሉ ሳይረዳው እንዳልቀረ እርግጠኛ ነኝ። ከክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ እንደማይገኝ ሁሉ እንዳንተ ካለው ከሣራም ከስድብና ከብልግና በስተቀር ምንም ቁምነገር እንደማይገኝ በተደጋጋሚ በምትለቀልቀው ጽሑፍህ ለማረጋገጥ ችያለሁ። “ከልጅ አትጫወት ይወጋሃል በእንጨት” እንደተባለው አንተን ከመሰለ ፍሬ ቢስ ከሆነ ሥራ ፈት ጋር እንካ ሰላንቲያ መጫወት ራስን ወደ አንተ የመንፈስ ደረጃ ዝቅ ከማድረግ በስተቀር ሌላ ፋይዳ እንደሌለው በመገንዘብ መልሴን በጅምር ትቼው ነበር። ታዲያ አንተ ለከት-የለሽ ባለጌ የመጀመሪያው አልበቃህ አለና ሌላ ሁለተኛ ድርሳነ ዘለፋ ጨንቁረህ በማየቴ ውሸት ሲደጋገም እውነት ሊመስል ሰለሚችል ጨመዳድጄ የጣልኩትን ወረቀት እንደገና አነሣሁና ይህን አጭር መልእክት ጻፍኩልህ።

የአንተ የጨንቋሪው ማንነት

ለመሆኑ አንተ የድርሳነ ዘለፋው ባለቤት ማነህ? ጽሑፌን እንደ ጀመርኩ፣ መጻሕፍትን መርምሬአለሁ ስትል ስለምሰማ ምን ዓይነት ሰው እንደ ሆንክ በዓይነ ልቡናዬ ስገመግም የሚከተለው ጥቅስ ከፊቴ ድቅን ብሎ ታየኝ፤

“ወፈድፋደሰ ለእመ ኮንከ ዘነሣእከ ኃይለ እመጻሕፍት አምላካውያት ወአጥረይከ ትጋሀ ዘየሐበርቶ ለልብ፣ እስመ ነጽሮ ዘዘልፍ ውስተ መጻሕፍት ቅዱሳት ይመልዓ ለነፍስ አንክሮተ ዘኢይትነገር ወትፍስሕተ አምላካዌ” (ማር ይስሐቅ ምዕ 1)

“ይልቁንስ ከአምላካውያት መጻሕፍት ኃይልን ብታገኝ፣ ልብንም (እንደ ወርቅ) የሚወለውለውን ትጋትን ገንዘብ ብታደርግ፣ አዘውትሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን መመልከት ነፍስን በማይነገር መደነቅና በአምላካዊ ደስታ ይሞላታል” (ማር ይስሐቅ 1)

መጻሕፍትን የሚመረምር ሰው ትሁት ሰብእና ያለው፣ ልቡ ቅን፣ አንደበቱ የታረመ፣ እግዚአብሔርን ፈሪ፣ ሰውን አክባሪ፣ ሊሆን እንደሚገባው ይህ ጥቅስ ያስገነዝበናል። አንተ ግን አነበብኩ በምትለው ቃለ እግዚአብሔር የመንፈስ ለውጥ ያላገኘህ፣ በቃልህ የያዝከውን ያለ አንዳች ማስተዋልና ሚዛናዊነት የምትለፈልፍ፣ በትክክል ከምትጮኸው ይልቅ የሚያዳልጥህ ጊዜ የሚበዛ አሮጌ ቴፕ ነህ።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአዳም ኃጢኣት አለባት እያልክ በቤተ ክርስቲያናችን የሌለ አዲስ ነገር መናገር ስትጀምር የሰሙ አንዳንድ ምሁራን፣ የምትሰማና የምትታረም መስሎአቸው፣ ትክክለኛውን ነገረ ማርያም የሚያንፀባርቅ፣ በማስረጃ የተደገፈና ጨዋነትን የተላበሰ መልስ ቢልኩልህ አንዱን “ቡድሐ” ሌላውን “ደደብ” እያልክ ሰደብካቸው። እኔም ከመጻሕፍት እየጠቀስኩ የተሳሳትካቸውን ነጥቦች ሁሉ በዝርዝር ባስረዳሁህ እወድ ነበር፣ ነገር ግን ቈልህ ቅሌት እንጂ መልካም ነገር ስለማይወድ ወንጌል “ኢተሀቡ ቅድስተ ለከለባት ወኢትደዩ ባሕርየክሙ ቅድመ አርሕው ከመ ኢይኪድዎሙ በእገሪሆሙ ወተመይጦሙ ይንፅኁክሙ / በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሷችሁ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፣ ዕንቍአችሁንም በዕሪያዎች ፊት አታኑሩ”(ማቴ. 7:6) እንዲል፣ አንባቢን ታላቅ ይቅርታ እየጠየቅሁ በሚገባህ ቋንቋ ማንነትህን ልገልጥልህ ወሰንኩ። እንደ ጥንቱ፣ እንደ አገር ቤቱ ቢሆንማ “ለቀጣፊ ይደልዎ ጥፊ፣ ለቀልቃላ ይደልዎ ዱላ፣ ለመናጢ ይደልዎ ቡጢ” በተባለልህ ነበር!!
በመጀመሪያ ማንነትህን በሚገባ የሚገልጹ ሁለት ስሞች አግኝቼልሃለሁ፤

1/ እንደራስህ አገላለጽ ከሆነ ያልሰበሰብከው እውቀት፣ ማወቅም ብቻ ሳይሆን ተጠያቂ ያልሆንክበት ክፍለ ትምህርት ፈጽሞ አይገኝም። አህያ “እኔ ያልፈሳሁበት ዳገት የለም” ብላ የለ! እውነቱ ግን አንተ ጨንቋሪ ጥቂት ቁምነገር በመያዝ ፋንታ “የኔታ እገሌ ዘንድ ነበርኩ፣ መምህር እገሌ ዘንድ ይህን ቀጸልኩ” እያልክ ተረትና የጎመን ጥቅስ ስታጠና ዕድሜህን የፈጀህ ዘዋሪ ስለሆንክ “እግረ ተማሪ” መባል ይስማማሃል።

2/ ድፍረት እንጂ ብልሃት ስለሌለህ “እስመ ንጽሕት ፈድፋደ ምስብዒተ እምነ ፀሐይ” እንደተባለው፣ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራውን እመቤት ድንግል ማርያምን የእምነት መነጽር ሳታደርግ በደረቁ የክሕደት ዓይንህ ለማየት ስትሞክር የፀሐይዋ ብርሃን ዓይንህን (ዓይነ ልቡናህን) እልም ድርግም አድርጎ ስላጠፋው ጠምባሳ ዕውር ነህና “ጤሜዎስ” ትባላለህ።

አንተ እገረ ተማሪ! በጨነቈርካቸው ሁለት የስድብ ድርሳናት “ማርያማዊ ሕገ ሃይማኖትና ተማኅጽኖ” በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ከሰፈሩት አያሌ ቁምነገሮች በአንዱ እንኳ ላይ አግባብ ያለው ሂስ መወርወር ባለመቻልህ፣ በክርክር መርታት ያቃተውን ዲዳ ዱላ እንደሚቀናው ሁሉ አንተም የዘለፋ አረንቋህን ያረፈበት ላይ ይረፍ ብለህ ዓይንህን ጨፍነህ ለድፈኸዋል። አንተ አንደኛውን የለየልህ የሰይጣን ቁራጭ ነህ፣ እኔ የማዝነው ሳያውቁና ሳይገባቸው አንተን ካህን ነህ ብለው ሥራ ፈትተህ ጸጉር በመሰንጠቅ፣ ነገር በማራቀቅና፣ አሠስ ገሰሱን በመለቅለቅ ጊዜህን እንድታባክን ድጎማ በማድረግ ለሚረዱህ ጥቂት የዋሃን ምእመናን ነው። ነገር ግን የማይታወቅ የተሰወረ የለምና እነዚህ የዋሃን አንድ ቀን ከክንብንባቸው ይገለጡና እውነተኛውን ማንነትህን ሲገነዘቡ አሽቀንጥረው እንደሚጥሉህና የተለመደውን ዙረትህን እንደምትቀጥል እርግጠኛ ነኝ።

ጤሜዎስ ሆይ! መቼም ብዙ ታወራለህ፣ ወሬህም ራስን ክበህ ክበህ ራስ ዳሸንን ከማሳከል፣ ሌላውን ግን ከመንቀፍና ከማዋረድ ያለፈ አይደለም። ትንሽ ሕሊናህ የሚወቅስህ ሰው ብትሆን ኖሮ እውነተኛው ማንነትህን አጠገብህ ሆነው ለሚረዱህ የዋሃን እንኳን መግለጥ ይገባህ ነበር። እንግዲህ “አይጥ ሞቷን ስትሻ የድመት አፍንጫ ታሸታለች” እንደተባለው አላርፍ በማለትህ ጉድህ ቁልጭ ብሎ ወጥቶ ሰው ሁሉ ሊሰማው ነው።

ኢትዮጵያ ሳለህ “እኔ ከሁሉ በላይ አዋቂ ነኝ” እያልክ ስትሸልል ይህን ሽለላህን ደርግ ሰምቶ “የለውጥ ሐዋርያ” ብሎ ሾመህና በየቤተ ክርስቲያኑና በየገዳሙ እየዞርክ ስለ ኮሙኒዝም እንድትሰብክ አሰማራህ። ነገር ግን የአንተና የመሰሎችህ ስብከት ጥንታዊት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን ከእምነቷና ከትውፊቷ ሊያናውጻት ባለመቻሉ “የፍየል ወጠጤ” እንዳይዘፈንብህ በመፍራት የደርግ ተቃዋሚ መስለህ ወደ ኬንያ ተሰደድክ። አንተ ግን ቤተ ክርስቲያኔ ለከፍተኛ ትምሕርት ላከቺኝ እያልክ ታወራለህ! ለመሆኑ በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያ (ሱማሌና ጅቡቲስ ለምን ቀሩ?) ስማር ቆይቻለሁ ብለህ የምትወሸክተው በየትኛው ዩኒቨርሲቲ በየትኛው የትምህርት ዓይነት ተመርቀህ የትኛውን ዲግሪ አግኝተሃል? ሰው አይቶአቸው ጸሐይ ሞቆአቸው በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እውቀታቸው የተረጋገጠላቸውን ሰዎች ግን እየዘረጠጥክ ስታዋርድ ትንሽ የማይከብድህ ጉድ ነህ።

ከኬንያ ስፖንሰር አድርገው ወደ አሜሪካ ያመጡህ ብጹእ አቡነ ማትያስ ነበሩ ይባላል፣ አንተ ግን ምንስ ውለታ ቢስ ብትሆን ውለታቸውን የምትከፍላቸው “ካቶሊክ ነዎት” ብለህ በመዝለፍ መሆን ይገባ ነበር?

እዚህ አሜሪካ ከመጣህ በኋላም በዋሺንግተን ዲ.ሲ. መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ጥቂት ጊዜ እንደቆየህ ጠባይህ ከሰው ጋር የማያኖርህ መንቻካ ነገረኛ ከመሆንህ በላይ፣ እዚያ ለሚገኘው የተማረ ሕዝበ-ክርስቲያን የመንፈስ ደረጃውን የሚመጥን አገልግሎት መስጠት ስለተሳነህ እንደ አሮጌ ጥብቆ አውልቀው ጣሉህ።

መቼም በሀገረ አሜሪካ አንድ ትልቅ ችግር አለ፣ ይኸውም አንድ ካህን ከነበረበት ቤተ ክርስቲያን ተባርሮ ወደ ሌላ ስፍራ ሲሄድ የተባረረበትን ምክንያት በመጠየቅ ፋንታ ቄስ አገኘን ብሎ አብሮ መክነፍ የተለመደ ሆኖአል። አንተም እውነተኛ ካህን የመሰልካቸውን ሰዎች አግኝተህ አሁን ካቴድራል በተባለው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተብዬ መስጠት ጀመርክ። ከእነዚህም ጋር ተስማምተህ መሥራት አቅቶህ ስላባረሩህ ወደ ሲያትል ዋሺንግተን ተሰደድክ። “ጅብ በማያውቁት አገር ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል” እንደሚባለው አንድ ቦታ ሲነቃብህ መፍትሔህ ወደ ሌላ አገር መፈርጠጥ ነው። መጥፎ ጠባይ አገር በመለዋወጥ አይድንምና ሲያትልም የተለመደውን እንክርዳድህን ስትዘራ ያገኙህ ምእመናን ቦታቸውን እንድትለቅላቸው ስለጠየቁህ ሽሽትህን ወደ ሴይንት ሉዊስ ሚዙሪ አደረግህ። ሚዙሪ እያለህም ተመሳሳይ ችግር ተፈጠረና ምእመናኑ በአንተ የክህነት ጥላ ስር ሆነን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ከምንባል ይልቅ እምነታችንን ጠብቀን ያለ ቤተ ክርስቲያን ብንቆይ ይሻላል ብለው ስለሸሹህ ተነሥተህ ወደ ካንሳስ ኪዳነ ምሕረት ሄደህ ተሸነቀርክ።
እውነተኛ ማንነትህ መገለጥ የጀመረው በካንሳስ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ነው። መቼም ካንተ በላይ እውቀት ላሳር ሆነና የራስህን ኃጢኣት እንደማሰብ ሰው ሁሉ “ንጽሕተ ንጹሓን፣ ቅድስተ ቅዱሳን” እያለ የሚያከብራትንና የሚማፀናትን እመቤታችን ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክን “ኃጢኣት አለባት” እያልክ መለፈፍ ስትጀምር ታላቅ ተቃውሞ ተነሣብህ። ለመሆኑ የካንሳስ ኪዳነ ምሕረት ምእመናን አሥራ አንድ (11) የተለያዩ ክሶች እንዳቀረቡብህ ታስታውሳለህ? ጥቂቱን እኔ ላስታውስህና
 1/ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአዳም ኃጢኣት ነበረባት ማለትህ ዋናው ክስ ነው::
2/ ከነጫማህ ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባትህና ምእመናንም ጫማቸውን ሳያወልቁ እንዲገቡ ማደፋፈርህ ነው::
3/ ስትጸልይ እንደ ጰንጤዎች ዓይንህን መጨፈንህ ነው::
4/ ጳጳስ ብቻ ማድረግ የሚገባውን ሢመተ ዲቁና በድፍረት መስጠትህ ነው።

የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ቦርድ በሁለት ምክንያቶች ሊመሰገን ይገባዋል፤ አንደኛ ችግሩ የዶግማና የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ መሆኑን ተገንዝቦ የበላይ አካል ተመልክቶት ውሳኔ እንዲያሳልፍበት በማድረጉ ሲሆን ሁለተኛ አንተ የለየልህ መናፍቅና ዓመፀኛ መሆንህ ሲረጋገጥ ክህነትህን ሽፋን በማድረግ ሌሎችን በተለይም ወጣቶችን እንዳትበክል ከዚያ መንቅሮ በማስወጣቱ ነው።
ትልቁ ክስ ከቀረቡብህ ክሶች ዋናው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ ነበረባት ማለትህ ሲሆን ብጹእ አቡነ ማትያስ አንተ ከዚህ ከኑፋቄህ እንድትመለስ በቂ ዕድል ከሰጡህ በኋላ እምቢተኛ ሆነህ ስለተገኝህ ሥልጣነ ክህነትህን በመያዛቸው ኃላፊነታቸውን በሚገባ ተወጥተዋል። ለመሆኑ ወደ ላይ ተንጠራርተህ ብጹዕነታቸውን በመዝለፍህ “የኔ ናት፣ አስተምራኛለች” የምትላትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በምእመናን ፊት ማዋረድህ እንደሆነ እንዴት አልተገለጸልህም? እነዚያ ደጋግመህ የምትጠቅሳቸውና አስተማሩኝ የምትላቸው ኁልቈ መሳፍርት የሌላቸው መምሕራን ስድብ ነው ያስተማሩህ? ወዲያው ደግሞ ጳጳሴ አቡነ ይስሐቅ እንጂ አቡነ ማትያስ አይደሉም ማለት ጀመርክ። በጣም የምታስገረም ነህ! መጀመሪያውኑ “አቡነ ማትያስን አልቀበልም፣ በእሳቸው አልዳኝም፣ ጳጳሴ አቡነ ይስሐቅ ስለሆኑ እሳቸው ጉዳዩን ይመልከቱልኝ” እንዳትል ማን ከለከለህ? ይፈርዱልኛል ብለህ ያሰብካቸው አባት ሲፈርዱብህ ጊዜ ቀለምህን ለውጠህ የዋሁን አቡነ ይስሐቅን የሙጥኝ አልክ።

ዕረፍተ ነፍስ ያድላቸውና ብጹዕ አቡነ ይስሐቅ በዚያ ጊዜ በየዋህነታቸው ላይ ከአገራቸው ከወጡ ከ50 ዓመት በላይ ስለሆናቸው ብዙ ነገር ተዘንግቶአቸው እንደነበረ ራሳቸው ያመኑት ሐቅ ነው። በተጨማሪም በአካባቢአችን የተከሠተው የሥልጣን ችግርም ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉ አይካድም። “የቤተሰብ ግርግር ለሌባ ይመቻል” እንደሚባለው የጳጳሳቱን መለያየት ተገን አድርገህ “አቡነ ይስሐቅ ሥልጣነ ክህነቴን መልሰውልኛል” እያልክ ሕዝበ ክርስቲያኑን በማታለል ላይ ትገኛለህ። ለመሆኑ አንዱ ጳጳስ ያገደውን ክህነት በሥልጣን እኩል የሆነው ሌላው ጳጳስ ሊመልስ የሚችለው በየትኛው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው? እርግጥ አንድ ካህን ቢወገዝ ያለ አግባብ ተወግዣለሁና ይታይልኝ ሲል ለሲኖዶስ ማመልከት ይችላል። ቢያንስ ሦስት ጳጳሳት ሆነው ጉዳዩን አጥንተው ውግዘቱ ሕገወጥ መሆኑን ካመኑበት ካህኑን ከውግዘቱ ፈተው ወደ ሥራው ሊመልሱት ይችላሉ። አለዚያ ግን አንተ እግረ ተማሪው እንዳደረግኸው ቦታ እየለዋወጡ ካህን ነኝ ብሎ ግብረ ክህነት መፈጸም እንደ አሁኑ ባለው የውዥንብር ጊዜና ተመልካች በሌለበት በስደት አገር ካልሆነ በስተቀር በሰላም ጊዜና የቤተ ክርስቲያን ሕግ በሚከበርበት ቦታ የማይሞከር ትልቅ ሸፍጥ ነው።

“ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም” እንደተባለው፣ የተንኮል ገድልህ የማያልቅ ፍጡር ነህና ኑፋቄህ እዚያው በካንሳስ ተወስኖ እንዳይቀር ደብረ ሰላም በሚገኘው የትሮይ ፈረስህ ወደ ዋሺንግተን አምጥተህ ነዛኸው። በዲ.ሲ. ማኅበረ ካህናት ስም በመጀመሪያ ተሰብስበው ባንተ ጉዳይ ላይ ከተወያዩት ሰዎች መካከል ጥቂቱን ይዘህ ራስህ የጫርከውን ደብዳቤ እነሱን አስፈርመህ ከቃለ ጉባኤ ተብዬው ጋር ወደ ሲኖዶስ ላክህ።

የደብዳቤህ አጻጻፍ በብዙ መንገድ ሕግን ያልተከተለ የሸፍጥ ሥራ ነው። አንደኛ “እመቤታችንን ጥንተ አብሶ አላገኛትም” የሚለው ዶግማ የተበየነና የተወሰነ፣ ያለቀና የደቀቀ ጉዳይ ሆኖ ሳለ እንደ አዲስ ነገር አድርጎ ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ትክክል አይደለም፣ መናፍቅ ያሰኛል እንጂ የቤተ ክርስቲያኗን ውሳኔ ሊያስለውጥ አይችልም። ሁለተኛ አጻጻፉ አቅዋምን በትክክል የሚገልጽ ቀጥተኛ መሆን ሲገባው አንተ እግረ ተማሪው ሆነ ብለህ ያጣመምከው አወናባጅና አሳሳች አጻጻፍ መሆኑ ያንተን የጉደኛ ጭንቈራዎች በማወዳደር ብቻ በቀላሉ ይታወቃል። ክርክሩ የተነሣው፣ ትላለህ እግረ ተማሪው፣

“አንጺሖ ሥጋሃ ቀዲሶ ኪያሃ ኀደረ ላዕሌሃ የሚለውን ይዘው እመቤታችን በሐልዮ በነቢብ በገቢር ከሚሠራው ኃጢኣት ንጽሕት እንደሆነች አምነው በአዳም ዘር በኩል ከሚተላለፈው የውርስ ኃጢኣት መንፈስ ቅዱስ አነጻት በሚሉትና በአዳም ዘር በኩል ከሚተላለፈው የውርስ ኃጢኣት መንፈስ ቅዱስ አላነጻትም” በሚሉት መካከል ነው”።

በደንብ ላስተዋለው ሰው ይህ አባባልህ ሁለቱም ወገኖች ከአዳም የሚወረሰው ኃጢኣት በእመቤታችን እንደተላለፈባት አምነው አንደኛው ክፍል ማለትም ያንተ ወገን ከውርስ ኃጢኣት መንፈስ ቅዱስ አነጻት ሲል ሁለተኛው ማለትም ተቃዋሚው ወገን “የለም መንፈስ ቅዱስ አላነጻትም፣ እንደተሸከመችው ቀርታለች” እንደሚል አስመስሎ የተቀመጠ አባባል ነው። እንዲህ ያለ ተንኮል (ያውም በመንፈሳዊ ጉዳይ ላይ) ታይቶ አይታወቅም። እውነተኛው ክርክር ግን አንተ “ከአዳም የሚወረሰው ኃጢኣት በማንኛውም ሰው እንደሚተላለፍ በእመቤታችንም ተላልፎባታል፣ የነጻችው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል መንፈስ ቅዱስ በላይሽ ይመጣል ሲላት ነው” ስትል፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በይፋ ያወጣውን መክሥተ ሃይማኖት የሚቀበሉ ወገኖች ግን ከአዳም የሚወረሰው ኃጢኣት ወይም ጥንተ አብሶ በእመቤታችን እንዳይተላለፍባት መንፈስ ቅዱስ ጠብቆአታል ማለታቸው ነው።

ጤሜዎስ ሆይ! እንግዲህ አንተና ጓደኞችህ የተንጠላጠላችሁባት “አነጻት” የምትለው ቃል ናት። ይቺን ቃል መነሻ በማድረግ “አነጻት” ማለቱ ከውርስ ኃጢኣት ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል የሚል አመለካከት አላችሁ። እግረ ተማሪ ሆይ! “ለራስ ሲቈርሱ አያሳንሱ” እንደተባለው የቤተ ክርስቲያናችንን የአንድምታ ትርጓሜ ጠንቅቄ አውቃለሁ የምትል ከሆንክ “መጽሐፍ ምሥጢር እንጂ ዘይቤ አይጠነቅቅም” እንደሚባለው ምሥጢር ለመጠበቅ ንባብ ማቃናት እንደሚያስፈልግ እንዴት መገንዘብ ተሳነህ? እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ እንጥቀስና አርዮስ “ወልድ ፍጡር በባሕርየ መለኮቱ” ለማለት ማስረጃ ያደረገው “ትቤ ጥበብ ፈጠረኒ መቅድመ ኵሉ ተግባሩ” የሚለውን ኃይለ ቃል ነው። “ፈጠረኒ” የሚለው ቃል በገጸ ንባቡ ከተወሰደ አርዮስ እንዳለው “ወልድ ፍጡር” ስለሚያሰኝ አባቶች “ፈጠረኒ ያለው ወለደኒ ሲል ነው” በማለት ተርጉመዉታል። እመቤታችንንም በሚመለከት “አነጻት” ማለት “ጠበቃት”፣ ከጥንተ አብሶ ሰወራት ተብሎ ይተረጐማል። ታዲያ እመቤታችን አምላክን ለመውለድ የተመረጠች ንጽሕት ድንግል መሆኗን ካመንህ የግድ እንደ ተራ ሰው የአዳምን ኃጢኣት ካልተሸከመች ብለህ ድርቅ ማለትህ ለምን ይሆን? እውነት ተሳስታ እንኳን በአፍህ ስለማትገባ የኑፋቄው ምንጭ አንተ ስትሆን “በአሜሪካ የአቡነ ጳውሎስ ተወካይ የነበሩት አቡነ ማትያስ የፈጠሩት የነገረ መለኮት ችግር” የሚል ሐሰት መጻፍህ ያሳዝናል።

ወደ ጭንቈራህ ስገባ እግረ ተማሪው ምን ዓይነት የማይሰለች ዝግንትላም ነው? ነው ያልኩት። መጽሐፍ “ለጻድቅሰ ኅዳጥ ቃል ይበቁዖ” እንዳለው የምታስተላልፈው እውነት ቢኖርህ በጥቂት ቃላት ልትገልጸው በቻልክ ነበር፤ አረፍተ ነገር በመደራረብና ካብ አይገባ ድንጋይ ዓይነት ጥቅስህን በማዥጎድጎድ አዋቂ ለመምሰልና አንባቢን ለማደናገር መሞከር እንዳንተ ካለ አታላይ እግረ ተማሪ የሚጠበቅ ነው። በአንተ ቤት ተራቀህና የምሁር ጽሑፍ ጽፈህ ሞተሃል። ነገሩ ግን “የሚሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ” ነው። እንዲሁም “ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው” እንደሚባለው ያለማቋረጥ እንደ ቆርቆሮ ስትንኳኳ ሰው የሚለውን መስማት ባያቅትህ ኖሮ ያንተን ጭንቈራ ያነበቡ ስዎች “ምን ዓይነት ቀውስ ነው” እያሉ የታዘቡህን ትዝብት አውቀህ ትንሽ በታገሥክ ነበር።

“ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” ነውና “ማርያማዊ ሕገ ሃይማኖትና ተማኅፅኖ” ለተባለው የነገረ ማርያም መጽሐፍ አቃቂር አወጣለሁ ብለህ እንደ ሕልም እዣት ባወረድከው ድርሳነ ዘለፋህ ውሸታምና ቀባዣሪ መሆንህን ብቻ ሳይሆን አውቀህም ሆነ አብደህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠላት መሆንህን በትክክል አሳይተሃል። ሥራ ፈተህ በጨነቈርከው በእያንዳንዱ አረፍተ ነገር ላይ በመተቸት ጽሑፍህ ቁም ነገር የሌለው የቃላት ጋጋታ መሆኑንና ሐሳብህም እፍ ቢሉት እንደሚፈራርስ ልጆች እንደሚሠሩት የወረቀት ቤት መሆኑን ለአንባብያን ማሳየቱ ቀላል ሲህን፣ እኔ ግን እንዳንተ በከንቱ የማባክነው ጊዜ ስለሌለኝ ዋና ዋናዎቹን ውሸቶችህን፣ ክሕደቶችህን፣ ውንጀላዎችህንና ስድቦችህን በመጠቈም እወሰናለሁ።
ድርሳነ ዘለፋ ቀዳማዊ ዘጤሜዎስ

1. ደብተሮች ጠንቋዮች ናቸው፣ ቅኔ ማኅሌቱም የጠንቋዮች መሰብሰቢያ ነው ብለሃል።

ደብተራ” የሚለውን “ደፍተራ” በማለትህ አዋቂ ነኝ ባይ ነገር ግን አላዋቂ ደንቆሮ ማይም መሆንህን አረጋገጥክ እንጂ ያሻሻልከው ነገር የለም። “ደብተራ” ማለት የዜማና የቅኔ ሊቅ ማለት ነው። ስያሜው የተወሰደው ከብሉይ ኪዳን ነው። ሌዋውያን የእግዚአብሔር ታቦተ ሕግ በሚያድርበት በደብተራ ኦሪት ሆነው በዝማሬና በሽብሸባ ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑ ነበር። በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በቅኔ ማኅሌት ቆሞ ለረጅም ሰዓታት ቃለ እግዚአብሔር እየተናገረ ሳይደክምና ሳይሰለች ፈጣሪውን በዜማና በቅኔ የሚያመሰግን ሊቅ ደብተራ ይባላል። ሰነፍ ሰው ላልደከመበትና ለማያውቀው ሙያ ካለመጨነቁ በላይ ማጥላላትና ማንቋሸሽ ልማዱ ነው። አንተ እግረ ተማሪም የደብተራ ሙያ ስለሌለህ ደብተራ ይጥፋ፣ ቅኔ ማኅሌቱም ይፍረስ ብለህ ፈርጀሃል።

አንተ ጤሜዎስ እንደምትቃዠው ሳይሆን ድብትርና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጥንታዊነት ከሚያረጋግጡ ባሕሎች አንዱ መሆኑን፣ እንኳን ኢትዮጵያዊ ፈረንጆችም በደንብ የሚያውቁት ሐቅ ነው። ባዕዳን እንኳን ያከበሩትንና ዋጋ የሰጡትን የሥርዓተ አምልኮታችን ዋነኛ ክፍል የሆነውን የቅኔ ማኅሌት አገልግሎት እንደ አንተ ያለ ደፋር እግረ ተማሪ ሲያንቋሽሸው መስማት እጅግ ያበሳጫል። ታሪኩን አታውቀውም እንጂ እንደ ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ ያነገበ ሰባኬ ወንጌል እምብዛም ባልነበረበት ዘመን መጽሐፍ ቅዱሱን በዜማ አስገብቶ ለሕዝብ በማሰማት ሃይማኖት እንዲስፋፋ ያደረገ ደብተራ ነው። ዜማውንም ቅዱስ ያሬድ በመንፈስ ቅዱስ ወደ መንበረ ፀባዖት አርያም ተመስጦ፣ ከመላእክት ተምሮ ለቤተ ክርስቲያናችን ያበረከተልን፣ ለኢትዮጵያ እንጂ ለሌላ ለማንም ያልተሰጠ በረከት መሆኑ እየታወቀ የዝነኛው የቤተ ክርስቲያን አባት የቅዱስ ያሬድ ሙያ በአንተ በደጎባው አፍ መነቀፉ ያሳዝናል። አንተ የተሳሳትከው አንሶህ እንደ ሸርጣን ሌላውንም ጎትተህ ከአንተ ጋር ጉድጓድ መክተት ስለምትወድ በሊቅነታቸው ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባራቸው የታወቁን አባት የኔታ ብርሃኑን (በኋላ አቡነ በርናባስ) የቅዱስ ያሬድ ዜማና የቅኔ ማኅሌት ጠላት ናቸው ማለትህ ትልቅ ወንጀል ነው። በስደት አገር ሆነና ነው እንጂ አገር ቤት ቢሆንማ እንዳንተ ያለው አፉ እንዳመጣ እየለፈለፈ የሰው ስም የሚያጠፋ ወንጀለኛ ምሱን ሊቀምስ፣ ዋጋውን ሊቀበል በተገባ ነበር።

“ማርያማዊ ሕገ ሃይማኖትና ተማኅፅኖ” የተባለውን መጽሐፍ ያነበቡ ብዙ ሰዎች በአጠቃላይ ይዘቱም ሆነ ውስጡ በሰፈረው ቁምነገር አድንቀዉታል። አንተ ግን መጽሐፉን ጠልሰም፣ ጸሐፊውን ጠልሳሚ ማለትህ አንተን መጥፎ ግምት ውስጥ ሲያስገባህ መጽሐፉን ያልሰማው ሁሉ ሰምቶ እንዲፈልገው አድርጎታል። ጥንቆላውና ቡዳነቱማ ከምትነቅፈው ደራሲ ይልቅ አንተን እንደሚመለከት ልቡናህ ስለሚያውቀው በዚሁ አልፈዋለሁ።

2. የ"ማርያማዊ ሕገ ሃይማኖትና ተማኅፅኖ" ደራሲ (ከእንግዲህ ወዲህ ባጭሩ “ደራሲው” እለዋለሁ) “የላቲንን ትምህርትና እምነት እንቀበል” አለ እያልክ ትዋሻለህ።

ደራሲው በመጽሐፉ ውስጥ እንዲህ ያለ አንዲት አረፍተ ነገር አላሰፈረም። ነገር ግን እመቤታችንን የአዳም ኃጢኣት አላገኛትም በማለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አንድ ዓይነት ትውፊት እንዳላቸው ገለጸ እንጂ “የላቲንን እምነት እንቀበል” አላለም። መቼም አረፍተ ነገር እንደ ሽንኩርት እየከታተፍክ በማቅረብ ደራሲው ያላለውን ብሎአል እያልክ የምትዋሸው ማኅለቅት የሌለው ውሸት ሕሊናህ የማይወቅስህ ሸፍጠኛ መሆንህን ከማሳየቱ በላይ አንባብያንን ለራሳቸው የማያስቡ በአንተ ጠማማ አቀራረብ የሚመሩ ጅሎች አድርገህ ማሰብህን ያረጋግጣል።

ለማለት የፈለግኸው ቀላል ነገር ሆኖ ሳለ የማትዘልበት ሜዳ፣ የማትንጠላጠለው ዛፍ የለም። የለቃቀምከውን ታሪክና ጥቅስ በሙሉ በመዘርገፍ ሊቅነትህን አሳያለሁ ብለህ አስበህ ከሆነ ሐሳብህ ግቡን አልመታም። አይ ሊቁ! ግሪኮችና ኢትዮጵያውያን በክርስቶስ ባሕርይ ላይ የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም በሐልዎተ እግዚአብሔር አንድ ናቸው ትለናለህ። “እግዚአብሔር አለ” በማለትማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ ብቻ ሳይሆን ከእስላምም ጋር ትስማማለች። እንግዲህ ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ አኀት ናቸው በለና!

እቅጩን ለምን አትናገርም? ቤተ ክርስቲያናችን እንደ መምህሯ እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ "አንድ ሥግው ባሕርይ ነው" በማለቷ ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትለያለች፣ በአንጻሩ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን (ግሪክ፣ ራሺያ ወዘተ) ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ ነው በማለቷ ከሮማ ቤተ ክርስቲያን ጋር ፍጹም አንድ ናት። ሐቁ ይህ ስለሆነ የማምታታት ሱስህን ለማርካት ካልሆነ በስተቀር የፈለግኸውን መጽሐፍ ብትጠቅስ አንድ ባሕርይ የምትለውን ቤተ ክርስቲያናችንን ሁለት ባሕርይ ከምትለው ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር አንድ ልታደርጋት አትችልም።

የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን (ግሪክ፣ ራሺያ፣ ወዘተ) ቀደም ባለው ዘመን በእመቤታችን ጥንተ አብሶ እንደሌለባት ያምኑ ይጽፉም ነበር፣ በኋላ ግን በቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ ምክንያት ማለትም ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ባላቸው የሥልጣን ፍልሚያ የጥንቱን አቅዋማቸውን ትተው “ድንግል ማርያም የአዳምን ኃጢኣት ወርሳለች” ማለት ጀመሩ። ይህም በራሳቸው የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ጸሐፊዎች የተመሰከረ እውነት ነው። እንዲሁ በራስህ ምናብ ከምትነዳ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ካሊስቶስ ዌይር የጻፈውን “The Orthodox Church” የተባለውን መጽሐፍ አንብበህ ሐቁን እወቅ። ከባለቤት ያወቀ ቡዳ ነውና (no pun intended) ባለቤቶቹ የሚሉትን ከመቀበል ይልቅ የራስህን መላምት መደንቀር ደንቆሮ ያስብልሃል እንጂ አዋቂ አያሰኝህም።

ለነፍስህ ባታስብስ እንኳ እንደው ውሸት አይሰለችህም? ደራሲው እመቤታችን ያለጥንተ አብሶ ተጸነሰች ማለት አዲስ ዘመን አመጣሽ ትምህርት ነው አለ የምትለው ምን ዓይነት ቀጣፊ ብትሆን ነው? ደራሲውን ቀጣፊ ትላለህ እንጂ ካንተ የበለጠ ቆርጦ ቀጥል የለም። ቀጣፊው እግረ ተማሪ ሆይ! ደራሲውማ ጥንታዊውን የያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ አንድምታ ትርጓሜ በመጥቀስ እመቤታችን ያለጥንተ አብሶ ተጸነሰች ማለት የቤተ ክርስቲያናችን ነባር እምነት መሆኑን በሚገባ አስረድቶአል። የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን እንኳን ካቶሊክን ለመቃወም ስትል ብቻ ነባር እምነቷን እስክትቀይር ድረስ በእመቤታችን ንጽሐ-ጽንሰት ታምን እንደነበር ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ ጽሑፍ በመጥቀስ ማስረጃ አቅርቦአል። አንተ ነህ “ይህ እምነትና ትምህርት አሁን የመጣ ነው፣ ጥንት ያልነበረ ነው” የምትለው። ይህንን ካልክ ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ እምነት አንተ እንደምትለው ለመሆኑ በማያሻማ ቃል የተጻፈ ማስረጃ እስቲ አምጣ! “እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት” የሚል ዶግማ በቤተ ክርስቲያናችን መቼ ታውጆ መቼ ተሻረ? ሊቃውንቱ ያላሉትን “እንዲህ ማለታቸው ነው” እያልክ የምትዘባርቀውን ማንም አይቀበልህም። ምእመናኑም ቢሆኑ የነገረ መለኮት እውቀት አይኑራቸው እንጂ ክፍትና ሚዛናዊ በሆነ አእምሮ የተጻፈውን አንብበው የሚረዱ ስለሆነ ያንተን ገደል የሚከት ምሪት አይፈልጉም። የድፍረትህ ብዛት የነአለቃ አያሌውንና የነመልአከ ብርሃን አድማሱን ጽሑፍ እንደ ልማድህ እየተለተልህ አንዱን ሐረግ ከአጠቃላይ ሐሳቡ (ኮንቴክስት) ነጥለህ በማውጣት ለኑፋቄህ መጠቀሚያ በማድረግህ አጭበርባሪነትህን አስመስክረሃል። ለመሆኑ በዚህ አንቀጽ ውስጥ ከባስልዮስና ከዲዮናስዮስ የጠቀስከው ምን ዓይነት ነጥብ ለማስቈጠር ነው? “ቀበሮ ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንደተባለው ያለ ነው! መቼም ብልሁ አንባቢ ባንተ ጠማማ ድርሳነ ዘለፋ የሚመራ አይደለም እንጂ አንተ እውነቱን ሐሰት፣ እምነቱን ክሕደት ለማድረግ ያልፈነቀልከው ድንጋይ የለም፣ ያወጣኸው ግን ትል ብቻ ነው።

ቀጣፊው ጤሜዎስ ሆይ! እስቲ ማለባበሱን ተወውና እውነተኛ እምነትህን ተናገር። “በእመቤታችን የአዳም ኃጢኣት ተላልፎባታል” ባይ ነህ፣ የተወገዝከውም በዚህ ነው። ታዲያ ዳር ዳሩን ከምትዞርና “ጥንተ አብሶ የለባትም” የሚሉትን ከምትኰንን የራስህን እምነት በቀጥታ ለመግለጽ እንዴት ወኔ አጣህ?

ደጋግመህ የምትጠቅሰው “immaculate conception” የሚለውን ሐረግ ነው። ይህ ማለት “እመቤታችን ያለ ውርስ ኃጢኣት ተጸንሳለች” ማለት ነው እንጂ ስለደጋገምከው ሌላ ምትሃታዊ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። አቡነ ማትያስ “እኛም እንደሱ ነው የምንለው” ያሉትን አንተ እንደ ልማድህ አጣመህ “እንደነሱ ነው የምንለው አሉ” አልክ። እንደዚያም ቢሆን የጋራ እምነት መኖሩን ያሳያል እንጂ አንተ እንደምትለው አንዱ ከአንዱ መዋስን አያሳይም። ለምሳሌ የቅዱስ ቁርባንን አማናዊነት ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ይቀበላሉ፣ ታዲያ ማን ከማን ተዋሰ ብለህ ልትኰንን ነው? ባታውቀው ነው እንጂ ይህ የቤተ ክርስቲያን የጋራ ትውፊት ይባላል።

መቼም የደራሲው መጽሐፍ ያንተን ኑፋቄ ከማጋለጡና የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርት ቁልጭ አድርጎ ከማሳየቱ ሌላ ምንም ሃይማኖታዊም ሆነ ሌላ ዓቢይ ጉድለት እንደሌለበት ልቡናህ እያወቀው መጽሐፉን ለማጥላላትና ለማስጠላት ያደረግኸው ርኩስ ጥረት ግቡን አልመታልህም። ከዚህ አልፈህ ተርፈህ ደግሞ የደብረ ሰላምን ካህናትና የአስተዳደር ቦርድ በስም እየጠራህ የደራሲው መጽሐፍ እዚያ እንዳይሸጥ ያቀረብከው ማስፈራሪያ እንዴት ያለህ ዓይን አውጣ ባለጌ መሆንህን ያረጋግጣል። ለመሆኑ ደብረ ሰላምን በሪሞት ኮንትሮል መቆጣጠር ትችላለህ ያለህ ማነው? አንተ ትቀላለህ እንጂ የመጽሐፉ ፈላጊ ብዙ ስለሆነ በቅርቡ ሁለተኛው እትም ሳይወጣ አይቀርም ብዬ እገምታለሁ። ስለዚህ እንግሊዞች እንደሚሉት “Eat your heart out”. አንድ ነገር ግን እንድታውቅ ያስፈልጋል፤ አስተሳሰብህ እንደሚያመለክተው አንተ ከ500 ዓመት በፊት መወለድ የሚገባህ የጨለማው ዘመን ሰው ነህ። መጽሐፍ ይከልከል፣ ይቃጠል፣ ወዘተ የሚል ሰው የእውቀት ፀር ስለሆነ በየትኛውም የከፍተኛ ትምሕርት ተቅዋም እንዲማርም ሆነ እንዲያስተምር አይፈቀድለትም። አንተ ግን የነገር እንጂ የትምሕርት ሰው ስላልሆንክ ጉዳዩ ብዙም አይመለከትህም።

3. “የኦርቶዶክሶችን ትምህርት በጭፍን መቀበል አንችልም። አይገባንምም” ብሎ ሊመክረን ይዳዳል ስትል ደራሲውን ከሠሃል።

ብዙ የሚቀባጥር ሰው ራሱን ችግር ላይ እንደሚጥል ባንተ እየታየ ነው። አንተ ሳይገባህ በጭፍን በሃይማኖተ አበውና በሌሎችም መጻሕፍተ ሊቃውንት ውስጥ እንደምትዳክረው ሌላውም ሳይረዳና ምሥጢሩን ሳያውቅ በጭፍን ይቀበል ማለትህ ነው። ይህን ምክር አንተን መሰል ገልቱ ካልሆነ በስተቀር አእምሮ ያለው ሰው አይቀበልህም።

እግረ ተማሪ ሆይ! በዚህ አንቀጽ ካቀረብከው አሠስ ገሰስ መካከል ዋናዎቹ ክሶች የሚከተሉት ናቸው፤

ሀ/ ደራሲው “ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በሚናገሩት ሁሉ ፍጹማን አይደሉም፣ አንዳንድ ሕፀፅ አለባቸው” አለ ብለህ ከሰኸዋል። ፍጡር ሆኖ የማይሳሳት አለ የምትል ከሆነ ክስህ ትክክል ነው። ታዲያ የሮማው ፓፓ አይሳሳትም ብለህ ታምናለሃ! ደራሲው የጻፈው ግን አንተ እንዳጣመምከው አይደለም። ከየቦታው ቃርመህ ሳይገባህ በቃልህ ካጠናኸው ሌላ የነገረ መለኮት ታሪክ ስላላነበብክ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በሰብአዊ ቋንቋ ሊገለጽ የማይችለውን ነገረ መለኮት በብቃት ገልጸነዋል የሚል ግብዝነት እንዳለባቸው በማድረግህ ያመሰገንኻቸው መስሎህ እንዳዋረድካቸው አልተረዳኸውም። እነሱ ግን ፍጹማን ነን ብለው አያውቁም፣ እንዳንተ ግብዞች አይደሉማ!

ጥንታውያን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከአያሌ መናፍቃን ጋር ባደረጉት ትግል ብዙ ጽፈዋል፣ ብዙ ተናግረዋል። አመለካከታቸውም ሁልጊዜ ፍጹም ነው ማለት ጉንጭ አልፋ ክርክር ነው። የተቃና ትርጓሜ ያስፈለገበት አንዱ ምክንያትም ይህ ነው። ሊቃውንቱ የተናገሩትን ከመሠረታውያን ዶግማዎች ጋር ማስማማት ያስፈልጋል። ይህም አዲስ ነገር ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ሲሠሩበት የኖሩት ነው። በተለይ አንተ እግረ ተማሪው እንደ ትልቅ ወንጀል ቆጥረህ የጠቀስከው ዮሐንስ አፈ ወርቅ በቃና ዘገሊላ ስለተፈጸመው ተአምር በቃለ ምእዳኑ መካከል የሰጠውን አስተያየት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ይህን ለማለቱ ደራሲው ማስረጃ አለው። አንተ ግን "እኔ ካላወቅሁት የለም ማለት ነው" ብለህ ስለደመደምክ የተለመደውን ግብዝነትህን ገልጸሃል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እመቤታችንን በተዋቡ ቃላት ካመሰገኗት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አንዱ ነው፣ ደራሲውም ይህንን በመጽሐፉ በሚገባ ገልጾታል። የሊቃውንቱንም ድርሳናት የእምነታችን መሠረት ከሆኑትና በሦስቱ ጉባኤያት ከተወሰኑት ዶግማዎች ጋር በማገናዘብ እንቀበል አለ እንጂ ሊቃውንቱን በጅምላ አንቀበል አላለም። ጠዋይነትንና ውስልትናን እንጂ እውነትንና ሚዛናዊነትን ካንተ መጠበቅ ስለማይቻል ላንተ ምንም ነገር ማስረዳት ከንቱ ልፋት ነው። በተረፈ ደራሲው የጻፈውን የሚያስተባብል ማስረጃ ካለህ ማቅረብ ነው።

ስለ ቀጰዶቅያውያን አባቶችና ስለ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ደራሲው ያቀረበው ሁሉ በማስረጃ የተደገፈ ነው። ዋናው ጥያቄ ብለዋል ወይስ አላሉም? የሚል ሊሆን ይገባዋል። በጊዜና በቦታ ተወስኖ በተፈጸመ ጉዳይ (በፋክት) መከራከር አስፈላጊ አይደለም። እኔ ካላወቅሁት የለም ወይም ትክክል አይደለም ብሎ ማሰብ ኢ-ምሁራዊ ነው። እነ ባስልዮስ፣ ጎርጎርዮስ፣ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ወዘተ በስፋት በምልአት የጻፉት ስለ ምሥጢረ ሥላሴና ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ ነው፣ ስለ እመቤታችን ግን አንዳንድ ነገሮችን እግረ መንገዳቸውን ጠቃቅሰው ማለፋቸው አይካድም። ሆኖም በግሪኮች ዘንድ ነገረ ማርያም በምሥጢረ ሥጋዌ የሚጠቃለል እንጂ ለብቻው የሚሰጥ ትምህርት አለመሆኑን ደራሲው በሚገባ ገልጾታል። እነዚህ ሊቃውንት ነገረ ማርያምን መደበኛ ከፍለ ትምህርት አድርገው ቢጽፉ ኖሮ ያልተብራራው ሁሉ ግልጽና የማያሻማ ይሆን ነበር። ይህ ባለመሆኑ እንዳንተ ያለ ወስላታ አንዲት ቃል “አነፃት” ማለትን ተንተርሶ የሌለ ኑፋቄ ለመፍጠር ችሎአል። አንተ እንደምታደርገው የግል ትርጓሜ አደገኛነት እዚህ ላይ ነው።

ሊቃውንት በተለይም የቀደሙት ቅዱሳን አባቶች የተናገሩትንና የጻፉትን በሁለት ከፍለን ልናየው እንችላለን፤ አንደኛው ስለታወቁት ዶግማዎች (ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ ወዘተ) የጻፉት ነው፡ ይህ በዓለም አቀፍ ጉባኤያት ከተወሰኑት ውሳኔዎች ጋር የሚስማሙና በማስረጃነት የሚቀርቡ ሐሳቦቻቸውን ያዘለ ሥራቸው ነው። ሁለተኛው ለምእመናን ገለጻ ሲያደርጉ፣ ከአይሁድና ከአረማውያን ጋር ሲከራከሩ፣ ስብከት ሲሰብኩ፣ ትምህርት ሲያስተምሩ፣ ኃይለ ቃል ሲተረጉሙ ብዙ የግል አመለካከታቸውን አንጸባርቀዋል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ምናልባት በዐውደ ምሕረቱ ላይ ቆሞ በመስበክ ላይ እንዳለ በቃና ዘገሊላ የተፈጸመውን ታሪክ በስብከቱ መካከል ጠቅሶ ሲያስረዳ ደራሲው የጠቀሰውን አስተያየት መናገሩ ተመዝግቦአል። የተወሰነ ዶግማን መካድና ዓቢይ ባልሆነ ነጥብ ላይ የግል ሐሳብን መግለጽ ሁለቱ እኩል በአንድ ዕርከን የሚታዩ አይደሉም። ሐዋርያው ጳውሎስም እንኳ የራሱን የግል አስተያየት ከክርስቶስ ከተቀበለው ትምህርት ለይቶ ተናግሮአል። ማንኛውም ሰው ቢሆን ከስሕተት ነፃና ፍጹም እንዳልሆነ እናውቃለን። አንድ ሊቅ ታላላቆቹን ዶግማዎች በሚመለከት ያስተማረው ትምህርት ትክክል እስከ ሆነ ድረስ በሌሎች በጥቃቅን ነገሮች ላይ የግል አስተያየቱን ቢሰነዝርና በአጠቃላይ ከሚታመነው እምነት ጋር ተስማምቶ ባይገኝ፣ አጠቃላይ እምነቱን የሚያፈርስ አይሆንም፣ የእሱንም ክብርና ተፈላጊነት የሚቀንስ አይደለም። ይህንም ሐቅ አንተ ባታውቀው የዶግማን ትምህርት በቅጡ የተከታተለ ሁሉ ያውቀዋል።

ጤሜዎስ ሆይ! አንተ ሃይማኖተ አበው የተባለው ምእላድ ለቅምሻ ያህል የተዘጋጀ ትንሽ መዝገበ ሃይማኖት እንጂ የሊቃውንቱን ታላላቅ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ የማይወክል መሆኑን ሳትገነዘብ አንዱን አረፍተ ነገር ራሱን የቻለ የጸሐፊውን አጠቃላይ ሐሳብ ያካተተ አድርገህ በመውሰድ ወይም በማስመል "ጎርጎርዮስ እንዲህ አለ፣ ባስልዮስ ይህን ተናገረ" እያልክ ቅዱሳኑን የኑፋቄህ ተባባሪዎች ልታደርጋቸው ትሻለህ፣ በእውነቱ ይህ ትልቅ ኃጢኣት ነው። የቤተ ክርስቲያናችንንም ሊቃውንት አንድም ሳይቀር ደጋግመህ የምትጠቅሰው ልታከብራቸውና ልታመሰግናቸው ሳይሆን ሊቅ ተብለህ ከእነሱ ጋር እንድትደመር በማሰብ መሆኑን አንባቢ ሁሉ ተገንዝቦታል። አንተ ግን ከእግራቸው እጣቢ እንደማትደርስ የታወቀ ነው። ምናል! ተሰንጥቀህ እስክትሞት ድረስ ተንጠራራ!

ለ/ ደራሲው “እመቤታችን ስጋት ነበረባት” አለ ብለህ ትልቅ ክሕደት አስመስለህ ከሰኸዋል።

ያንተ ዋነኛና ቀዳሚ ዓላማ ነቀፋና ትችት ስለሆነ መጽሐፉን በንጹሕ ልቡና አላነበብከውም እንጂ ደራሲው በዶግማ መልክ ስለእመቤታችን የሚታመኑትን ማለትም፣ ንጽሐ ጽንሰቷን፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋን፣ ወላዲተ አምላክ መሆኗን፣ አማላጅነቷን፣ ዕረፍቷን፣ ትንሣኤዋን፣ ዕርገቷን፣ በሚገባ ገልጿል። ከዚህ የተረፈው ትውፊታዊ ታሪክ ነው።

ወደ ዝርዝሩ እንግባና ቅዱስ ገብርኤል ድንግል ማርያምን ሲያበስራት “ሰላም ለኪ” ባላት ጊዜ ደንግጣ ነበር፣ ፈርታም ነበር። መልአኩ ግን አትፍሪ ብሎ አረጋግቶአት ወላዲተ አምላክ ለመሆን የመመረጧን ዜና በሚገባ በዝርዝር ነግሮአት ተሰውሮአል። አንተ ግን ለክስ ስለምትቸኩል የምትጽፈውን በደንብ አታጤነውም። ከጽንሰቷ በኋላ ግን የሚሆነውን ሁሉ ታውቅ ነበር በማለት ከሰብአዊነት ልታወጣት ትሞክራለህ። ለምሳሌ እመቤታችንና ጠባቂዋ ቅዱስ ዮሴፍ በዓል አክብረው ከኢየሩሳሌም ወደ ገሊላ ሲመለሱ የአሥራ ሁለት ዓመቱ ብላቴና ኢየሱስ ጠፍቶባቸው ሲፈልጉት አልነበረምን? በመቅደስ ተቀምጦ “ባዩትም ጊዜ ደነገጡ” (ሉቃ. 2:48) የሚለውን ቃል አላነበብክምን? እመቤታችንም ልጇን “እነሆ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው። እርሱም፦ ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው። እነሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም።”

እንግዲህ እግረ ተማሪውን የምጠይቅህ፣ እመቤታችንና ዮሴፍ ጌታን ሲፈልጉት መጨነቃቸውን፣ የነበረበትን ስፍራ አለማወቃቸውን፣ ባዩትም ጊዜ መደንገጣቸውን፣ የተናገራቸውን አለመረዳታቸውን፣ ትክዳለህ ወይስ ታሪኩን እመቤታችን ክርስቶስን ከመጽነሷ በፊት የሆነ ልታደርገው ነው!

ደግሞስ ዮሴፍ እጮኛው ማርያምን ያለፍርሃት እንዲወስዳት ከመልአኩ እስኪረዳ ድረስ ስጋት ነበረበት ቢባል ይህን ያህል አካኪ ዘራፍ የምትለው “ መልአ ከርሣ ለድንግል ወተሀውከ ልቡ ለዮሴፍ ሶበ ርእየ ልሕቀተ ከርሣ ለእንተ እንበለ ርኵስ ሐለየ ፍጹመ ምሥጢራ ለንጽሕት ወረከባ ጽንስተ በምሥጢር ዘኢየአምሮ ወወድቀ ውስተ ጽኑዕ መዋግደ ሕሊና... ወነጸራ እንዘ ጽንስት ወሐለየ ከመ ይእቲ ኮነት ውስተ ርኵስ” (ሃ.አ. ዘኤራቅሊስ ገጽ 157-8) የሚለውን ቃል አላነበብክምን?

እመቤታችንና ቅዱስ ዮሴፍ ፍጡራን ናቸው፣ አምላከ አማልክት እግዚአብሔር ወልድ ግን አምላክ ሆኖ ሳለ ጽዋዐ ሞቱ በቀረበ ጊዜ ኀዘን፣ ትካዜ፣ ፍርሃት እንደ ደረሰበት፣ “ተከዘት ነፍስየ እስከ ለሞት” በማለት መስክሮአል። መለኮቱ ከሰውነቱ ለአንዲት ቅጽበት እንኳን እንዳልተለየ እየታወቀ “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ” ብሎ መጮሁም ተመዝግቦአል(ሉቃ. 22:44፤ ማቴ. 26)። ወንጌሉ “ፈራ!” ይላል።

ስጋት፣ ጭንቀት፣ ፍርሃት፣ ድንጋጤ፣ ወዘተ የሰብአዊ ባሕርይ ምልክት እንጂ የእመቤታችንንና የዮሴፍን ክብር የሚያዋርድ፣ የክርስቶስን አምላክነት የሚቀነስ አይደለም። እግረ ተማሪው ማወቅ ያለብህ እግዚአብሔር በሰው አድሮ ሲሠራ ሰብአዊ ባሕርዩን ገፎ እንደ ማሺን በመጠቀም አይደለም። እንዲያውም የሰውን ድክመት ወደ በጎ ነገር ለውጦ እንደሚጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል። እመቤታችንም ሰማይና ምድር የማይችሉትን አምላክ በማኅፀኗ መሸከምን ያህል የተአምራት ተአምር ሲፈጸምባት ሳትሰጋ፣ ሳትጨነቅ፣ እንዲሁ እንደ ዋዛ ተቀበለችው ማለት መለኮታዊውን ተአምር መካድ፣ እመቤታችንንም ማዋረድ እንጂ ማክበር አይደለም። ይልቅስ እሷን ከሰብአዊ ባሕርይ የምታወጣ፣ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የመውለዷን ተአምር የምታቃልልና “ጥንተ አብሶ እንዳያገኛት እግዚአብሔር በከሃሊነቱ በመጠበቅ ለዚህ ታላቅ አገልግሎት አላዘጋጃትም” የምትል አንተ እግረ ተማሪው ነህ።

በአጠቃላይ በዚህ አንቀጽ ያቀረብከው ክስ ሁሉ ያንተን አላዋቂነትና ችኩልነት ያሳያል እንጂ ደራሲውን የሚያስወቅስ ካለመሆኑ በላይ ደራሲው ተጽፎ ያላገኘውን ከራሱ አንቅቶ አንተ እንደምታደርገው በመፈላሰፍ የተናገረው ምንም ነገር እንደሌለ ልታውቅና ልታምን ይገባሃል። የእመቤታችንን ጥንተ ታሪክ ለማወቅ ከፈለግህ ቅዱስ ያዕቆብ ኤጲስቆጶስ ዘኢየሩሳሌም የጻፈውን ነገረ ማርያም አንብብ። የውጭ ነው፣ የግቢ ነው እያልክ ማደናገሩን ተወው።

4. የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶች ሊቃውንትን ያዋረድክ አንተ እግረ ተማሪው ነህ እንጂ ደራሲው አይደለም።

እግረ ተማሪ ሆይ! እንዳንተ አባባል የኢትዮጵያ አባቶች ሊቃውንት የተባሉት ቅዱሳት መጻሕፍትን አስማምተው በመተርጐማቸው ሳይሆን እናት ንባቡ ብቻ ሳይሆን ትርጉሙም ጭምር ከውጭ መጥቶላቸው በቃላቸው ስላጠኑት ብቻ መሆኑ ነዋ! ታዲያ እነ አለቃ ወልደ አብን እነ መምህር ኤስድሮስን ምን ልታደርጋቸው ነው? አንተስ ሃይማኖት ለመጠበቅ ከመምሕራን አደራ ተሰጥቶኛል እያልክ የምትወሸክተውና የምትኩራራው ከውጭ የመጣውን እንዳለ በቃልህ በመሸምደድህ ነውን?

እንግዲህ አስመሳይ፣ አታላይ፣ መቀጣት የሚገባህ አንተ ነህ እንጂ ደራሲው አይደለም። የኢትዮጵያ ሊቃውንት ከውጭ የመጣውን እንዳለ ወረሱ እንጂ የራሳቸው የሆነ አስተዋጽኦ የላቸውም ስትል አታፍርም? አንተ ከሥረህ ለክርስትና ትውፊት ታላቅ አስተዋጽኦ ያላትን ቤተ ክርስቲያናችንን ለማክሰር በመከጀልህና ባዕዳን ያልነፈጓትን ድርሻ ልትከለክላት በመነሣትህ ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን ጠላት ነህና ለፍርድ ልትቀርብ ይገባሃል። ደራሲው የቤተ ክርስቲያናችንን ሊቃውንት ችሎታና ታላቅነት በመመስከሩ ዲግሪውን ይከልከል ማለትህ ዲግሪ ለማግኘት የሚያስፈልገውን ድካም ስለማታውቀው ነው። አንተማ የሌለህን ዲግሪ ምኑን ትከለከለዋለህ! ባንተ አነጋገር ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የውጪዎቹን ሰርቀው የራሳቸው በማድረግ ባልደከሙበት ባለቤቶች ሆኑ እንጂ የራሳቸው ድርሻ የላቸውም ማለት ነው። አዬ! አስተማሩኝ እያልክ መምሕራኑን በስም እየጠቀስክ ከምታስወቅሳቸው ብትሞት ይሻልህ ነበር። ለመሆኑ አለቃ ወልደ አብን፣ እንዲሁም “ረከብናሁ ለበትር ዘያደክማ ለሮሜ፣ ጽሩበ በንባብ ወቅሩጸ በትርጓሜ” የተባለላቸው እጨጌ በትሩን፣ እንዲሁም አንተ የጠቀስካቸው እነ አራት ዓይና ጎሹንና ሌሎቹንም አገር በቀል ሊቃውንት ሁሉ ኮራጆች (plagerist) አደረግኻቸው ማለት ነው?

መቼም ግብጾች ለኑፋቄህ ድጋፍ ከመስጠት ሌላ ያደረጉልህ ምን እንደ ሆነ አላውቅም፣ ጥብቅና ቆመህላቸዋል። በደላቸውንም ልትደብቅላቸው ትሞክራለህ። "የግብጽን ቤተ ክርስቲያን ልንወቅሳት የሚገባን በኢየሩሳሌም ገዳም ብቻ ነው" ማለትህ ታሪክ ባለማወቅህ ነው? ወይስ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን "ወሰብአ ኢትዮጵያሰ ኢይሲሙ ጳጳሰ እምሊቃውንቲሆሙ/ የኢትዮጵያ ሰዎች ግን ከሊቃውንታቸው መካከል ጳጳስ አይሹሙ" የሚል የሐሰት ሕግ በሠለስቱ ምእት ቀኖና ላይ ስርዋጽ አስገብተው ለአንድ ሺ ስድስት መቶ ዓመት ሲያታልሉን መኖራቸውን ልትክድ ነው?

መቼም ያንተ ጉድ አያልቅም፣ "አቡነ ጳውሎስንም ቢሆን መውቀስና መክሰስ የሚገባን በሚፈጽሙት በደል ብቻ መሆን" ይገባል ትልና በሌላ ቦታ ደግሞ ቀኖናዊ አይደሉም እያልክ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ የሆነ ንግግር ትናገራለህ፣ ይህን በቦታው እንመጣበታለን። አሁን ወደሚቀጥለው ክስህ እናመራለን።

5/ "የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ለጣሊያን ቤተ ክርስቲያን ጠላት ናት" ብለህ የምትከሰው አንተ ነህ እንጂ ደራሲው አይደለም።

እግረ ተማሪ ሆይ! እባክህ “እውነቱን ተናግሮ እመሸበት ያድሯል” ተብሎአልና በካንሳስ ስለተፈጸመው እውነቱን ተናገር! ለመሆኑ አባ መቃርዮስ የሚባል ግብጻዊ ጳጳስ ባንተ ግብዣ ካንሳስ ላይ “በእመቤታችን ጥንተ አብሶ ነበረባት” ብሎ ሴሚናር ከማካሄዱ በፊት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ስለዚህ ጉዳይ በይፋ ተነጋግራ ያወጣችው ዶግማ የት አለ? እስቲ ንገረን? ነገር የሚምታታብህና ሐሳብ የሚጋጭብህስ ደራሲው ሳይሆን አንተ መሆንህ ነጥቡን እየለቀቅህ አራምባና ቆቦ በመርገጥህ ተገልጦአል። እባብ የዋጠች ፍየል ማርከሻውን እስክታገኝ ድረስ እንደምትቅበዘበዝ አንተም ቁምነገሩ ጠፍቶብህ ጥቅስ እንደ ቅጠል ስትቀነጣጥብ ትታያለህ። "እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት" የሚል አዲስ እምነት ያወጀች የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ይህን ኑፋቄ ከረሜላ እንዳገኘ ሕፃን ፈንድቀህ ኢንተርኔት ላይ የሰቀልከው አንተ ነህ። በዚህ ጉዳይ ላይ ግብጽ ፀረ-ካቶሊክ ናት፣ ካቶሊክ ፀረ-ግብጽ ናት ቢባልም ያው ነው፤ ስልቻና ቀልቀሎ እንደማለት ነው። አንተ ግን ነቀፋ እንደ ውሃ የሚጠማህ ጸዋግ ስለሆንክ የሰውን ሥራ መተቸትና ማጥላላት እንጂ ምንም የምታሳየው አዎንታዊ አስተዋጽዖ የሌለህ ምስኪን ነህ። እንዲሁ ሰው እንደተሳደብክና እንደነቀፍክ ወደ መቃብር ልትወርድ በመሆንህ ሊታዘንልህ ይገባል።

በዚህ አንቀጽ የዘበዘብከው ቅዠት እግርና እጁ ስለማይታወቅ መተዉን መርጬ ነበር፣ ነገር ግን ደራሲው ለጣሊያን እንደሚሟገት አድርገህ ያቀረብከው ሐተታ በተለመደው ተንኰልህ ለማሳጣት ያቀረብከው እንጂ አንድም እውነት እንደሌለበት ግልጽ ማድረግ አለብኝ። ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው በደል የታወቀ ነው፣ በታወቁ ጸሐፍት የተዘጋጁ የታሪክ መዛግብት ስላሉ ያንተ ሌክቸር ሁሉን አዋቂ እንድትባል ከምታደርገው ሙከራ የማያልፍ ፍሬ ቢስ ሐተታ ነው። ዋናው ቁም ነገር ግብጾች ላንተ ድጋፍ መስጠታቸውና አንተም ሽንጥህን ገትረህ ለእነሱ መሟገትህ መታወቁ ነው። “ውሻ በበላበት ይጮኻል” ይባል የለ! አንባቢዎች ማወቅ ያለባቸው አስተማረችኝ የምትላትና ሥልጣነ ክህነት የሰጠችህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን እሷን እየነቀፍህ፣ ባለሥልጣኖቿን እየተሳደብክ፣ ባሕሏንና ትውፊቷን እያጥላላህ ቄስ ነኝ እያልክ ማታለልህ የወጣልህ ከሐዲ ብትሆን እንጂ አዙሮ ማየት የሚችል ባለአእምሮ አለመሆንህ ከታወቀ ቆይቶአል።

አባ አየለ የተባለው ካቶሊካዊ መነኩሴ በጻፈው መጽሐፍ የተነሣ እነአለቃ አያሌው፣ እነመልአከ ብርሃን አድማሱ፣ እነአቡነ መቃርዮስ (አንተ ባታውቃቸውም እነአፈ ሊቅ አክሊሉም አሉ) የጻፉት መልስ ከጥንተ አብሶ ጋር ምን አገናኘው? “የ... ማደናገሪያ ቆዳ” እንደተባለው ዋናውን ነጥብ ለማድበስበስና አንባቢን ለማደናገር ግንኙነት የሌለውን የቃላት ክምር መቆለልህ አዘውትረህ ከምታሳየው ሸፍጥ ጋር የተያያዘ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፣ ታዲያ ደግሞ የተነቃብህ መሆኑን ማወቅ ያባት ነው። የማይገናኙ ነገሮችን በግድ ስበህ ለማገናኘት የምታደርገው ሙከራ አንባቢን ለማደናገርና ከዋናው ኢላማ ማለትም በእመቤታችን ጥንተ አብሶ ነበረባት ከምትለው ኑፋቄህ ላይ ዓይኑን እንዲያነሣ የምትጠቀምበት ዘዴ መሆኑ ታውቆአል።

ሁለት ነጥቦችን ላንሣና ይህን ክፍል እደመድማለሁ። አንደኛ እላይ እንደተገለጸው “ፀረ-ካቶሊክ” ማለት ከካቶሊክ ጋር በሐሳብ የማይጣጣም ለማለት ጥቅም ላይ የዋለ፣ የተለመደ አገላለጽ እንጂ በጦር መሣሪያ ካቶሊክን የሚዋጋ ጠላት ማለት አይደለም። ታሪክ ልንገርህና አንድ የትምህርት ተቈጣጣሪ አንደኛ ክፍል ገብቶ የአስተማሪውን የማስተማር ችሎታ ለመገምገም ከኋላ ተቀመጠ። አስተማሪው ዓለም ትዞራለች እያለ ሲያስተምር ተቈጣጣሪው “እንዴት ነው የምትዞረው?” እያለ ጠየቀ፤ አስተማሪው ደጋግሞ ቢያስረዳም ተቈጣጣሪው እንዳልገባው ሆኖ ያንኑ ጥያቄ መላልሶ በመጠየቁ አስተማሪው እሱን ለማጥመድ እንጂ በእውነት ትምህርቱን አለመረዳት እንዳልሆነ አውቆና የመጣ ይምጣ ብሎ “ዱሮስ አንደኛ ክፍል መቼ ይገባዋል፣ ዝም ብለህ አዳምጥ ብሎ” ተቈጣጣሪውን ገሠፀው። አሁንም የአንተ ጥረት ለመረዳት ሳይሆን ለማጥመድና ነገር እሰው ላይ ለመተብተብ ስለሆነ ቢገባህ ይግባህ ባይገባህ ተወው እንጂ ቀጥተኛውን ነገር ለአንተ ለማስረዳት ሲደጋግም የሚውል ሥራ ፈት የለም።

ግብጾቹ ፀረ-ካቶሊክ አቅዋም ለመያዝ ባንተ ግብዣ ካንሳስ ላይ እንደ ተሰበሰቡ ራስህ ኢንተርኔት ላይ የለጠፍከው መጣጥፍ ምስክር ነው። ካቶሊኮችን ቢፈልጉ ለራሳቸው እንዲከራከሩ ልተዋቸውና በራሴ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ ላተኩር። በካንሳሱ ስብሰባ አንተን ልክ ነህ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን ተሳስታለች ማለታቸውን ትክዳለህ? አንተም የነሱን ድጋፍ ካገኘህ በኋላ ደረትህን ነፍተህ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተሳስታለች፣ እኔ ግን ትክክለኛ ነኝ” እያልክ መታበይ ጀመርክ። ለመሆኑ ያ ግብጻዊ ጳጳስ “ኢትዮጵያና ግብጽ በነገረ መለኮት አንድ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በተወሰነ ጊዜ እየተገናኙ ይወያያሉ” የሚለውን የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት የጋራ ፕሮቶኮል ጥሶ በአንተ የግል ጎራ፣ መደበቂያ ዋሻ ውስጥ ገብቶ ከፕሮቶኮሉ ውጭ ኦፊሺያል ያልሆነ ስብሰባ ካንተ ጋር ለማካሄድ ማን ሥልጣን ሰጠው? ለነገሩ አንተ የምትፈልገውን ካገኘህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብትዋረድ ምን አግዶህ!

ሁለተኛ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ፀረ-ካቶሊክ አቅዋም አልፈጠረችም የምትል ከሆነ፣ እመቤታችን የውርስ ኃጢኣት ነበረባት የሚል ዶግማ ጥንት እንደነበራት ምን የምታቀርበው ማስረጃ አለህ? በነገራችን ላይ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተራቀቀና ራሱን የቻለ የዶግማ አካለ ትምህርት እንደሌላት ፓፓው አቡነ ሸኑዳ እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት ለማለት ማስረጃ አድርገው ያቀረቡት “ወትትሐሠይ መንፈስየ በአምላኪየ ወመድኃኒየ” የሚለው ቃል መሆኑ በቂ ምስክር ነው።

አዲስ የበቀለ ትምህርት “ማርያም ጥንተ አብሶ አለባት” ማለት እንጂ “እመቤታችን በንጽሕና ተፀነሰች” ማለትማ ነባር እምነት ነው። “ውዳሴ አምላክ” የተባለው ጸሎት በትክክል መቼ እንደተጻፈ አላውቅም። ከቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ እንደ ተገኘ መጽሐፉ ራሱ ይናገራል። እንዲህ የሚል ቃል አገኘሁበት፤

“ አንቺ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት እንድትሆኚ ሌላ ኃጢኣት በሰው ሁሉ የደረሰ የአዳም ኃጢኣት እንኳ አልደረሰብሽም“።

ከብረ ነገሥትም

" ለመድኃኒቱ ተወልደት ዘእንበለ ጥልቀት። እስመ ግብራ ለንጽሕት ዘእንበለ ርስሐት።"

" ያለኃጢኣት ለመድኃኒት ተወለደች፣ የንጽሕት ተፈጥሮ ያለነውር ነውና።" ይላል (96:16)።

እነዚህ ሁለቱ መጻሕፍት የጸሎትና የታሪክ እንጂ የዶግማ መጻሕፍት ባይሆኑም "እመቤታችንን ጥንተ አብሶ አላገኛትም ማለት ጥንታዊ እምነት ለመሆኑ ታሪካዊ መረጃ ናቸው።

6/ ስለቅዱስ ሲኖዶስ

እግረ ተማሪ ሆይ! ቅዱስ ሲኖዶስ እምነትን ጠብቆ የማስጠበቅ ኃላፊነት የለውም በማለትህ በበላይ አካል የማታምን፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የጣስክ ዘላን መሆንህን ታስመሰክራለህ። “በአቡነ ጳውሎስ ስለሚመራው ሲኖዶስ የሚነግረን ከሆነ ስለሲኖዶስ ምንም ግንዛቤ የለውም” ስትል አታፍርም? ደራሲው የሲኖዶስን ኃላፊነት በአጠቃላይ ተናገረ እንጂ ይኸኛው ሲኖዶስ ወይም ያኛው ሲኖዶስ አላለም። አንተ ሸፍጠኛ ባንድ በኩል በፖለቲከኞቹ በኩል እንዳትወቀስ አቡነ ጳውሎስንና እሳቸው የሚመሩትን ሲኖዶስ ታጥላላለህ፣ በሌላ በኩል ደግሞ “ብጹእ ወቅዱስ” እርስዎ ከሾሟቸው ጳጳሳት ጋር አብሬ ተምሬአለሁ እያልክ እያሞካሸህ የጫርከውን ደብዳቤ አየር ላይ ለጥፈኸዋል። ለመሆኑ እንዲህ የምትጠላቸውና የምትቃወማቸው ከሆነ ማንም ለሚያውቀው ለፕሮቴስታንት ሴሚናሪ የጻፉትን ቲስስ ለኑፋቄህ ማስረጃ አድርገህ ለምን አቀረብህ? መጀመሪያ ተለማመጥካቸው፣ ካንተ ጋር ሳይስማሙ ሲቀሩ ደግሞ የጭቃ ጅራፍህን አዞርክባቸው። እንግዲህ ከሳቸው ጋር ያለህን ችግር እዛው ተወጣው። መጥፎ ግምት ላይ የወደቅኸው ግን አንተ ነህ፣ ምክንያቱም ያንተን ጎን የደገፉ ይመስልህና ካሞካሸህ በኋላ እንዳሰብከው ሳይሆን ሲቀር የጥላቻ ጦርህን ትወረውራለህ።

ቅዱስ ሲኖዶስ ሃይማኖት ጠብቆ ለማስጠበቅ አይበቃም ባልክበት አፍህ መምሕራኖቼ ሃይማኖት የመጠበቁን አደራ በኔ ላይ ጥለዉታል ትላለህ። አሁን ደግሞ ከሲኖዶስ በላይ ሆንክ! ስለዚህ የተወሰደብህን ሥልጣን በራስህ ለራስህ መስጠት ትችላለህ ማለት ነዋ!

ደራሲውን ወደሚመለከተው ነጥብ እንለፍና “እመቤታችን ወደ ኩነት ሳትመጣ ተቀደሰች አይባልም” ስትል እንደልብህ ወደምትሳደብበት ወደ ነፃው አገር እንድትገባ የረዱህን ብጽእ አቡነ ማትያስን ትንሽ ሳይቀፍህ አፍህን ከፍተህ ከመዝለፍ በስተቀር የረባ ምክንያት ኖሮህ ያቀረብከው የለም። “ቀደሰ” ማለት ለየ ማለት መሆኑን ካወቅህ ወደ ሕልውና ወይም ኩነት ሳትመጣ አስቀድሞ ስለተመረጠች “እግዝእትነ ማርያም ነበረት በሕሊና አምላክ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም” እንደተባለላት አትገነዘብምን? ወይስ እሷን ለእናትነት የመረጠ አምላክ የወደፊቱን አያውቅም ለማለት ትከጅላለህ? አንተ በእርግጥ ለእመቤታችን በሚሰጠው ክብር ችግር እንዳለብህ በግልጽ ይታያል፣ ሆኖም እላይ "ወደ ሕልውና ሳትመጣ ተቀደሰች" የማለት ዋና ነጥብ እግዚአብሔር የወደፊቱን አስቀድሞ እንደሚያውቅና ከፍጥረት በፊት ለማዳን ሥራው እቅድ እንዳወጣ፣ በዚህ መለኮታዊ እቅድ ውስጥም ድንግል ማርያም ታላቅ ሚና እንዳላት መናገር ነው። ወይም ወደ ኩነት ሳትመጣ ልትቀደስ የማትችለው እግዚአብሔር እሷን በግዘፈ ሥጋ ሳያያት በሕሊና ሊያያትና ሊቀድሳት ማለትም ለእናትነት ከቀሩት ሴቶች ሊለያት አይችልም ብለህ እረፈዋ!!

እንደ ቀበሮ ከአንድ ነገር ወደ ሌላው በመዝለል ነገረ መለኮት አያድግም፣ ወዘተ በማለትህ የነገረ መለኮትን ታሪክ ስላላነበብክ የተለመደውን ቅዠትህን ትቃዣለህ። አባቶች በስንት መሥዋዕትነት አዳብረው፣ አጎልምሰው፣ አንተን ከመሰሉ ከሐድያን ታግለው፣ በመጨረሻም በጉባኤ አስወስነው ያቆዩንን ነገረ መለኮት ለእነሱ ዋጋ ላለመስጠት ስትልና እፊትህ የተደቀነችውን ጠባብ ሐሳብህን ለማራመድ ስትል ድካማቸውን ሁሉ ገደል ለመክተት ሞከርክ። በምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ወዘተ የተካተተው ነገረ መለኮት አባቶች ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቅዱስ ትውፊት ጨምቀው በተመረጡ ቃላት ገልጸው ያቆዩት ባይሆን ኖሮ ወንጌላውያንማ የክርስቶስን ትምህርትና የማዳን ሥራ ተረኩ እንጂ ነገረ መለኮትን አሁን ከጉባኤ ኒቅያ ጀምሮ በሚታወቀው መልኩ እንዳልጻፉ የታወቀ ነው። ይህን እንኳን ሳታውቅ ነገረ መለኮት ለማስተማርና ለመጠበቅ ከመምሕራኖቼ ኃላፊነት ተቀብያለሁ ማለትህ እጅግ ያሳፍራል።

7/ “ያቡነ ጳውሎስ ሲመተ ብትርክና ቀኖናዊ መሆኑን ለማሳመን ደራሲው የደጅ መጥኛ ሰንካላ መረጃ አቀረበ” የምትለው እንደተለመደው እግር አውጥቶ የሚሄድ ውሸት ነው።

እግረ ተማሪ ሆይ! በአራተኛው አንቀጽ “አቡነ ጳውሎስንም ቢሆን መውቀስና መክሰስ የሚገባን በሚፈጽሙት በደል ብቻ መሆን” ይገባል ያልከውን ረሳህና አሁን ደግሞ ሢመታቸው ቀኖናዊ አይደለም እያልክ ትጨፍራለህ። አለቃ ገብረ ሃና ልጅቷን “የኔ ልጅ! ዝንጀሮ ትጠብቂያለሽ?” ቢሏት “እኔ የምጠብቀው ከመሰለዎ ገመሬ ገመሬውን እየመረጡ ይበሉት” እንዳለችው፣ የአቡነ ጳውሎስን ቀኖናዊነት ብትቀበል ወይም ባትቀበል ከደራሲው ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። አንተ ግን ባንድ ራስ ሁለት ምላስ መሆንህን ከማሳየት አትቦዝንም። ለመሆኑ ደብዳቤ የጻፍክላቸው ፓትርያርክ ብለህ አይደለምን? ብትርክናቸውን ከተቀበልክ በኋላ አሁን ብትርክናቸውን ለመቀበል የሚያስገድደኝ ምክንያት የለም እያልክ የምትዘላብደው ለምንድነው? ቀድሞውኑ እንድትቀበላቸውና ብጽእ ወቅዱስ ብለህ እንድትጽፍላቸው ማን አስገደደህ?

የአቡነ ጳውሎስ ሢመተ ብትርክና ቀኖናዊ ነው ብለው የተቀበሉትና ኢትዮጵያ ድረስ ሄደው መቀበላቸውን ያጸደቁት አንተ የምታመልካቸው አባ ሲኖዳ ናቸው። አንተ ግን ደራሲውን በማይመለከተው ጉዳይ ልትኰንነው ትፈልጋለህ። መቼም ታሪክ ነውና አቡነ ጳውሎስ በአቡነ ቴዎፍሎስ አንብሮተ እድ እንደተሾሙ የምትክድ አይመስለኝም። ሢመተ ብትርክናቸው የተፈጸመው አቡነ መርቆሬዎስ መንበሩን ለቀው ለአሥር ወር ያህል ባዶውን ከቆየ በኋላ መሆኑ ዓለም ያወቀው ነው። ከዚህ በተረፈ ግን ግብጾችን በአንድ በኩል በኑፋቄህ ስለደገፉህ ታመሰግናቸውና ዞር ብለህ ደግሞ አቡነ ጳውሎስን ስለተቀበሉ እነሱኑ መውቀስ ሲገባህ የደርግ ባለሥልጣኖችን በስም እየጠቀስክ በመሳደብ ፖለቲከኞችንና የስደት ሲኖዶስን ለማስደሰት ትሞክራለህ። ለአንዴ እንኳን እባክህ እውነት ተናገርና እስቲ ለመሆኑ በደርግ ጊዜ የት ነበርክ? ኢትዮጵያ ውስጥ እንደነበርክ መቼም አትክድም! በወቅቱ ምን ያሰማኸው ተቃውሞ አለ? ተቃውሞ ይቅርና “የለውጥ ሐዋርያ” ተብለህ በየአድባራቱ፣ በየገዳማቱ እየዞርክ ከመሰሎችህ ጋር “በስመ ማርክስ ወኤንግልስ ወሌኒን ይትባረክ” እያልክ ለሃይማኖት-የለሹ የደርግ መንግሥት ስታሽቃብጥ መኖርህን ትክዳለህ? ለማንኛውም አንተ ከቅንነትና ከአርቆ አስተዋይነት ፍጹም የተራቆትክ ስለሆንክ ለወደፊቱ ገንቢ ሐሳብ ሳይኖርህ ስላለፈው ዘመን የሆነ ያልሆነውን ብትቀባጥር “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” ይሆንብሃል። የደርግ ዘመን እንዳበቃ ያንተም ከንቱ ድንፋታ ቢያበቃ ጥሩ ነበር።

ደራሲው የአቡነ ቴዎፍሎስን ታሪክ አበላሸ ስትል፣ አቡነ ቴዎፍሎስ አቡነ ጳውሎስን ጵጵስና በመሾማቸው ታሪካቸው ተበላሸ ማለትህ ነውን? ደግሞ ተሿሚውን ስታቃልል ሿሚውን ማቃለልህ መሆኑ እንዴት አልታወቀህም? አቡነ ቴዎፍሎስ በመጀመሪያ አንተ በጠቀስካቸው ግለሰቦች ተውንጅለው እንዲታሰሩ ምክንያት የሆነው ጊዜያዊ መንፈሳዊ ጉባኤን ሳያስፈቅዱ እነአቡነ ጳውሎስን ሾሙ ተብለው እንደሆነ ትክዳለህ? እንግዲህ አልገባህም እንጂ የአቡነ ጳውሎስን ቀኖናዊነት ስትክድ አቡነ ቴዎፍሎስ ሦስቱን ሰዎች ከቀኖና ውጭ ሾመዋል ማለትህ እንደሆነና አቡነ ቴዎፍሎስን መወንጀልህን ልታውቅ ይገባል። በአንድ በኩል ዘረኛነትህን ታንፀባርቃለህ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሰማዕቱን ያመሰገንህ መስለህ ትወቅሳቸዋለህ።

በዚህ ድርሳነ ዘለፋህ ውስጥ ከጥንተ አብሶ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ሙታንንም ሕያዋንንም ጠቅሰሃል። ሙታኑ “ሙት ወቃሽ” ያሰኙሃል እንጂ በነፍስህ ካልሆነ በሥጋህ የሚያመጡብህ ጉዳት የሚኖር አይመስለኝም። በሕይወት ያሉትን ግን አፍህ እንዳመጣ ዘልፈህ በኋላ የማትወጣው ችግር ውስጥ እንዳትገባ እፈራልሃለሁ። በስም ማጥፋት ወንጀል ከጠበቃ ቢሮ አንድ ደብዳቤ ቢደርስህ በፍርሃት ተንቦቅቡቀህ ትሞታለህ፣ ከተጋለጥክ ደግሞ ፉከራህም ሆነ የትሮይ ፈረስህ አያድንሁም።

8/ የደራሲው መጽሐፍ ጸያፍ ንግግሮችን እንደተጠቀመ የምታቀርበው ሁሉ ፍጹም ሐሰት ነው።

እግረ ተማሪ ሆይ! ለመሆኑ የደራሲውን የቃላት አጠቃቀም ለመንቀፍ የሚያስችል ምን እውቀት አለህ? ነገረ መለኮቱን አገባደህ አሁን ደግሞ የቋንቋ ሊቅ ነኝ ብለሃል። ያንተ ሊቅነት ተዝቆ እንደማያልቅ ጎተራ ሆኖአል። ዋናው ቁምነገር የጠቀስካቸው ቃላት ከግእዝና ከአማርኛ ውጭ አለመሆናቸውን አለመካድህ ነው። በቃላት አመራረጥ በኩልስ ወደፊት ጸሐፊ ሁሉ አንተን እያስፈቀደ ይጽፋል።

ጸያፍ ማለት አለስልቱ ወይም አለአገባቡ የተጻፈ ማለት ነው። ቃላት በራሳቸው ጸያፍ አይደሉም፣ አንድ ቃል ጸያፍ የሚሆነው አጠቃቀሙ ሲበላሽ ነው። ደራሲው አንዳንድ እንግዳ ቃላት የተጠቀመው ሐሳቡን በዝርዝር ለመግለጽና ግእዝ ለማያውቁ አንባብያን ለማብራራት ነው እንጂ አንተ የዘረዘርካቸውን የተለመዱ ቃላት መደጋገም አቅቶት አይመስለኝም።

ለምሳሌ "መናፍቅ" የሚለውን ቃል በምንም በኩል ብትተረጉመው ማንነትህን በትክክል የሚገልጽ ቃል ነው። "ናፈቀ ተጠራጠረ" ብትለውም አንተ ተጠራጣሪ ብቻ ሳትሆን ከሐዲ ነህ። "ነፈቀ ከፈለ" ብትልም ክሕደትህን እያራባህ አብረው የሚያገለግሉትን የምትከፋፍል የአንድነትና የሰላም ጠላት ነህ። መልካም ሥራ እንሥራ የሚል ጥቅስ ስትጠቅስ አታፍርም? በዞርክበት ቦታ ሁሉ ኑፋቄና ሐከክ የምትዘራ ስለሆንክ አዋቂ ለመምሰል ጥቅስህን ታዥጎደጉዳለህ እንጂ አንድ መልካም ምግባር የሌለህ ወሬኛ ነህ።

“ገለፈት” የሚለውን ቃል ደራሲው በመጠቀሙ ትልቅ ስሕተት የፈጸመ ወይም ክብረ ነክ ነገር የተናገረ መስሎህ ለመተቸት ሞክረሃል። ሁሉም የሰውነት ክፍሎች ተፈጥሮአዊ አገልግሎትና ክብር አላቸው፤ ያንተ ገለፈት ግን ከልብህና ከአፍህ ላይ ስለሆነ መላ ፈልገህ ብታስወግደው መልካም ነው።

ደራሲው በማስረጃነት የጠቀሳቸውን ዋቢዎች በመንቀፍ እኔ የማላውቀውን ለምን ጠቀሰ ብለህ አካኪ ዘራፍ ማለትህ ጠባብነትህን ያሳያል። አንተ በቃልህ ከሸመደድከው ውጭ አዲስ ነገር ካየህ ካብህ ስለሚናድብህ ይህ በአገራችን አይታወቅም፣ ይህን አባባል እነእገሌ አልተጠቀሙበትም፣ “ማርያማዊ ሕገ ሃይማኖት” በሚል ርእስ ከዚህ ቀደም የጻፈ የለም ወዘተ እያልክ ትጮኻለህ። በእውነቱ ያንተ ችግር የእውቀት ማነስ ብቻ አይደለም፣ ልበ-ቈላፍነት ጭምር ነው እንጂ! አንድን መጽሐፍ በይዘቱም ሆነ በሚያራምደው ፅንሰ ሐሳብ የሚቃወም ሰው ችሎታ ካለው የተሻለ ሐሳብ በተሻለ አቀራረብ አቀናጅቶ መጽሐፍ ይጽፋል፣ አለዚያም እንደ አቅሙ በመወያያ ርእሱ ላይ ያተኰረ ሂስ ያቀርባል እንጂ መስመር አልፎ የሰውን ሰብእና የሚያጎድፍ ቀቲለ-ባሕርይ (character assassination) ዓይነት ዝባዝንኬ ለመጨንቈር ይህን ያህል ጊዜ የሚያባክን ከአንተ በስተቀር አላየሁም፣ አልሰማሁም። በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠረን ሰው ውሻ ትላለህ፣ የራሱን ትቶ ሌላ ቦታ ሄዶ የሚያነፈንፍ ውሻስ አንተ ነህ።

አንተ እግረ ተማሪ! እነጎርጎርዮስ እነዮሐንስ አፈወርቅ ሌሎችም አባቶች የጻፏቸው አንተ በሃይማኖተ አበው የሚገኘው እስትጉቡእና ወደ ግእዝ ተተርጉመው ያየሃቸው ጥቂት መጻሕፍት ብቻ መስሎህ አዲስ ነገር ለምን ሰምቼ ብለህ ትዘላለህ። እነዚህ አባቶች አንተ የማታውቃቸው ብዙ ቅጾች ያሏቸው ሥራዎች አውርሰዉን አልፈዋል። ትንሽ አእምሮህ ክፍት ቢሆን ኖሮ እነዚህን መጻሕፍት ፈልገህ በማጥናት ራስህ አውቀህ ለሌሎች ለማሳወቅ ትሞክር ነበር። በዚህ አጋጣሚ የምጠቅሰው ሊቁ አለቃ አያሌው ዕረፍተ ነፍስ ይስጣቸውና እንግሊዝኛና ሌላም የውጪ ቋንቋ ባለማወቃቸው እጅግ ይቆጩ እንደነበር ሲናገሩ መስማቴን ነው። እኒህ ሊቅ እንዲህ ያለ ስሜት ያደረባቸው የአገሩን የውስጥ ትምህርት አኝከውና አጣጥመው ካንንሸራሸሩት በኋላ በቂ አለመሆኑን ስለተገነዘቡ ነው። አንተ ግን ጥራዝ ነጠቅ ስለሆንክ ያችኑ የያዝካትን አትንኩብኝ ስትል ትኖራለህ። በነገራችን ላይ የ"ጥራዝ ነጠቅ" ትርጉም አስቸግሮህ ስትታገል አይቻለሁ፤ ጥራዝ ነጠቅ ማለት መጽሐፉን አንብቦ ሳይዘልቅ አንዷን ጥራዝ ብቻ ይዞ እፍኝ ቆሎውን እንዳይነጥቁት እንደሚሮጥ ሕፃን ያለ ነው። ለምሳሌ በሃይማኖተ አበው ውስጥ ያለውን የአትናቴዎስን ቅንጭብ አንብቦ የአትናቴዎስን ድርሰት ወሰንኩ የሚል ካለ ጥራዝ ነጠቅ ነው። ያንተም ችግር የዚህ ዓይነት ስለሆነ ዋናውና እናቱ ከአገር ውጭ እያለ አገር ወዳድ ለመምሰል "የአገር ውስጥ" እያልክ ትጮኻለህ። እውነት የትም፣ ከየትም ብትሆን ያው ናት፣ እንዳንተ ያለ ጠምዛዥ ሊጠመዝዛት ቢሻም ትክክለኛ መልኳ የኋላ ኋላ መገለጧ አይቀርም።

“ጠልሰመኞች ስለሚጽፉት ነገር በቂ እውቀትና የመግለጽ ችሎታ ሳይኖራቸው ከዚህም ከዚያም የሰሙትን ደበላልቀው የሚጠለስሙ ጥራዝ ነጠቆች ይባላሉ” ያልከው ስለራስህ እንጂ ስለሌላ ስለማንም እንዳልሆነ ይህን መያዣውና መጨበጫው የማይታወቅ ውጥንቅጥ ድርሳነ ዘለፋህን ያነበቡ ሁሉ ይገነዘቡታል። የእምዬን ወደ አብዬ አዙረህ መላከክ ትወዳለህ!

እንደተለመደው ዙሪያ ዙሪያውን ዞረህ ሲደክምህ ወደ ዋናው ርእስ ትመለሳለህ። በተለይ ሁለት ነገሮችን እጠቅሳለሁ፤

ሀ/ እመቤታችንን ጥንተ አብሶ አላገኛትም ማለት ከሮማ የተኮረጀ ነው ብለሃል። የእምነት መመሳሰል መኮራረጅን የሚያመለክት ነው ካልክ የጥምቀትና የቅዱስ ቁርባን አማናዊነትንስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከሮማ ኮረጀች ትላለህን? ዋ! ይህ በጭፍን የምትጓዝበት መንገድ ስለማያዛልቅህ ብትገታ ይሻልሃል።

ለ/ እመቤታችንን ጥንተ አብሶ አላገኛትም ማለት ሰውነቷን መካድ ነው ብለሃል። በአንተ አመለካከት ሰው የተፈጠረው ከኃጢኣት ጋር ነው ማለት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር የኃጢኣት ምንጭ ነው ማለት ነው! ደግሞም ክርስቶስ ከኃጢኣት በስተቀር ሰው ሆነ እንላለን። እንግዲህ ክርስቶስ ኃጢኣት ስለሌለበት በሰውነቱ ፍጹም አይደለም ልትል ነው? ወይስ በሰውነቱ ፍጹም ስለሆነ ኃጢኣት ነበረበት ልትል ነው? ችግሩ እኮ የሚያመጣውን መዘዝ ሳታስብ አፍህ እንዳመጣ መለፍለፍህ ነው።

9/ ስለደራሲው የትምህርት ደረጃ ብዙ ነቀፋ ተናግረሃል።

ደራሲውን ለማንቋሸሽና የትምህርት ደረጃውን ዝቅ ለማድረግ ያወረድከው ስድብና ነቀፋ ራስህን ያስገምትሃል እንጂ ደራሲውን ስለማይጎዳው ለዚህ መልስ በመስጠት የምናጠፋው ጊዜ አይኖርም። ይህን ብዬ ወደሚቀጥለው ክፍል ላልፍ ስል ዓይኔ አንድ አረፍተ ነገር ላይ ተተከለ። “ፓብሊክ ኢኮኖሚክስ አጥንቻለሁ ይላል” ትልና “ይህም መስክ ብዙ ዘርፍ አለው” ትላለህ። ድፍረትህ ወሰን የለውም። ግእዙን ጨረስክና ወደ ፓብሊክ ኢኮኖሚክስ ገባህ። ለመሆኑ ፓብሊክ ኢኮኖሚክስ የተረጐሙልህ የኔታ ማናቸው? የሞተም ይሁን ያለ አንዱን ጥቀስልኛ! ወይስ አንዱ የዋህ አሽቃባጭህ ጉግል አድርጎ የሰጠህን ይዘህ ነው ስለፓብሊክ ኢኮኖሚክስ ያወቅህ የመሰለህ? The most important research themes are the economics of taxation and the analysis of social programs” እንዲል፤ አልክ! ለመሆኑ ማነው ያለው? አንተ ነህ ወይስ ያገርህ የደምቢያ ገበሬ? ይህን እንግሊዝኛ የገለበጥኩት ጨርሶ ምንም ዓይነት ፍንጭ በሌለህ ትምህርት እንኳን ገብተህ ለመቀላመድ ወደ ኋላ የማትል ግብዝ መሆንህን አንባቢ እንዲያይልህ ነው። ብልህ ተማሪ (ያውም የሒሳብና የእስታቲስቲክስ/ ኢኮኖሜትሪክስ ባግራውንድ ያለው) በትጋት ተከታትሎ ዲግሪ በሚቀበልበት ትምህርት አንተ አንዲት ተባራሪ አረፍተ ነገር አነበብክና ድንገት ኤክስፐርትነት ተሰማህ!

አንተን ሳያስፈቅድ ለደራሲው ዲግሪ የሰጠ ዩኒቨርሲቲ በእውነት ቅጣት ይገባዋል ወይም መዘጋት አለበት!! ዝነኛው ፈላስፋ ሶቅራጥስ ምን ታውቃለህ ተብሎ ቢጠየቅ “አለማወቄን አውቃለሁ” ብሎ መለሰ ይባላል። የኛ ምሁር የድርሳነ ዘለፋ ጨንቋሪ ግን እግዚአብሔር ለዓለም ያበረከተህ ብቸኛ ሊቅ አድርገህ ራስህን የምትመለከት የከንቱ ከንቱ ነህና ይብላኝልህ።

“አሌ ሎሙ ለእለ ይሬስዩ ርእሶሙ ባሕቲቶ ጠቢባነ / ራሳቸውን ብቻ አዋቂዎች ለሚያደርጉ ሰዎች ወዮላቸው” (ሃ.አ. ገጽ 363) የሚለውን አስተውል።

10/ በዚህ ቁጥር የጠቀስካቸው ሰዎች በሙሉ በሕይወት ያሉ ስለሆኑና ቢሻቸው መልስ ሊሰጡ ስለሚችሉ አንዲት አስተያየት ብቻ ሰጥቼ አልፈዋለሁ።

በዚህ ክፍል ግለሰቦችንም ያስተዳደር አካላትንም ወቅሰሃል፣ አስፈራርተሃል። በተለይ ደግሞ ደራሲውን ከደብረ ሰላም ያስወጡልኛል፣ መጽሐፉም እንዳይሸጥ ያደርጋሉ የምትላቸውን "ሊቃውንት" ጠቅሰሃል። አንተ የምትፈልገውን ሳያደርጉልህ ቀርተው እስክትዘረጥጣቸው ድረስ "ሊቃውንት" ብትላቸው የሚቃወም የለም። በቅርብ የሚያውቋቸው አገልጋዮችና ተገልጋዮች ግን ነገሩ "በጸዊረ ስም ደብረ ዘይት ኢኮነ ደብረ ታቦር" እንደተባለው ያለ መሆኑን በሚገባ ያውቃሉ።

ለመሆኑ አንተ 1/ እመቤታችን ኃጢኣት አለባት እያልክ 2/ በሊቀ ጳጳስ ተወግዘህ 3/ የዘላን ኑሮ የምትኖር ስትሆን 4/ ከሃይማኖትና ከምግባር የተራቈትህና በየቦታው እየዞርክ ጸብና ክርክር የምትዘራ የጸላኤ ሠናያት ደቀ መዝሙር ሆነህ፣ አንተ ቅዳሴ ማርያምን በነፃነት ስትቀድስ ደራሲው ከእናንተ ጋር እንዳይቀድስ ከልክሉት እያልክ ሊቃውንት የምትላቸውን ሰዎች ያዘዝከው ለምን ይሆን? የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብር የሚናገርና የቤተ ክርስቲያንን ቅዱሳን አባቶች ትምህርት በእውነት የሚያንፀባርቅ መጽሐፍ ስለጻፈ ነውን?

11/ ደራሲው በዝሙት ተከሰሰ ይህም በማስረጃ ተረጋግጦበታል ስትል ልትጠነቀቅ ይገባሃል።

እንዲህ ያለ ስም ማጥፋት በሕግ ስለሚያስቀጣ አፍህ እንዳመጣ መናገርህን ብታቆም ይሻልሃል። ደብረ ሰላም ያለው የትሮይ ፈረስህ ያቀበለህን ሁሉ እውነት ነው ብለህ ተቀብለህ ካናፈስክ ጉርጓድ ትገባለህ። ያን ጊዜ አፍህም ሆነ ፈረስህ አያድኑህም።

የቦሩ ሜዳን ታሪክ መጥቀስህ መልካም ነው። ሆኖም ይህን " እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት" የሚል ክሕደትህን እንደ ጀብዱ ያወራኸው ያን ጊዜ ቢሆን ኖሮ እንደ ሁለቱ እንግዳዎች ከፍ ብሎ መላስህን፣ ዝቅ ብሎ እግርህን ትቈረጥ ነበር። አሁን ግን በዚህ አገር፣ በአሁኑ ዘመን እንደ አህያ ብታናፋ ማን ይነካሃል? ስለዚህ ሃይማኖተ አበው አለቀብህና “ሥጋዬ ላንቺ ነው፣ ነፍሴም ለፈጣሪ” እያልክ መዝፈን ጀመርክ። (ለመሆኑ ማን ናት?) ሥጋህ የት እንደሚወድቅ አላውቅም፣ ነፍስህ ግን ንስሓ ካልገባህ ክፋትን እንደ ጋቢ ተከናንበሃት እያለህ ወደ ፈጣሪ እንደማትሄድ የታወቀ ነው። በሃይማኖትና በመልካም ምግባር የሚያሾፍ፤ ከአፉ ዘለፋ እንጂ ደግ ነገር የማይወጣ እንደ አንተ ያለ ዕቡይ የሰይጣን ምርኮኛ የሲኦል ጥገኛ መሆን ዕጣ ፈንታው መሆኑ የታወቀ ነው። እግዚአብሔር ይቅር እንዲልህ ጸልይ።

12/ ስለ ደራሲው የእውቀት ደራጃ በእልኽ የምትደጋግመው ነቀፋ አልበቃ ብሎህ የአቡነ ማቴዎስን ሬሳቸውን ለመውጋት ተነሣህ።

እግረ ተማሪ ሆይ! የስድብ አረንቋህን በደራሲው ላይ ስትወረውር ጉዳዩ በማይመለከታቸው ብዙ ሰዎች ላይ ተፈናጥቆአል። ከእነዚህ አንዱ ታላቁ አባት ብጹእ አቡነ ማቴዎስ ሊቀ ጳጳስ ዘኢየሩሳሌም ናቸው። እኒህ አባት እንደ አንተ ባለ አንጎለ ጮርቃ፣ አፈ ጭቃ እግረ ተማሪ ሊነሡና ሊሰደቡ የሚገባቸው ሰው አልነበሩም። ባለጌ ስለሆንክ የማትዘረጥጠው ሰው የለም። ዱሮ ቢሆን እንዳንተ ያለ አሳዳጊ የበደለው ባለጌ ጀርባው እስኪመለጥ ይገረፍ ነበር።

ለመሆኑ “ዘጠኝ መለኮት” እያልክ የምትቀባጥረው ምን ዓይነት ተረት ነው? ይህንስ የባልቴት ተረት ከየት አገኘኸው? ብጹእ አቡነ ማቴዎስ በእውቀታቸው፣ በስነ ምግባራቸው፣ በአስተዳደር ችሎታቸው የተመሰገኑ ብርቅዬ አባት ነበሩ። አንተ ይህን ልቅ አፍህን ከፍተህ የምትዘልፋቸው ብጹእ አቡነ ማቴዎስ በተሾሙበት ቦታ ሁሉ ብዙ ቋሚ ሥራ የሠሩ፣ ብዙ ትሩፋት ያላቸው፣ እጅግ የተከበሩና መተኪያ የሌላቸው አባት ነበሩ። በእሳቸው ደረጃ የነበረ ማንም የቤተ ክህነት ባለሥልጣን ያላደረገውን በማድረግ ማለትም ለሕይወታቸው ሳይፈሩ ደርግን በይፋ በመቃወም ብቸኛ የሆኑ እኒህን ታላቅ አባት የምትለው ብታጣ “ዘጠኝ መለኮት” ብለዋል ማለትህ ተው የሚልህ ሽማግሌ፣ የሚፋረድህ ዳኛ ባይኖር መሆኑ አይጠረጠርም።

ማወቅ ለሚፈልግ ግን ታሪኩ እንዲህ ነው። አንድ የነገረ መለኮት መጽሐፍ የአራተ ማርያም አስተዳዳሪ በነበሩት በአለቃ መኮንን ሰሎሞን እጅ ነበረ። ይህ መጽሐፍ ከሃይማኖተ አበውና ከሌሎችም መጻሕፍት ተወስዶ የተቀነባበረ ሲሆን የጻፉት የአሰቦትን ገዳም ያቀኑትና የመንግሥት ባለሥልጣኖችን ለማስታረቅ እስከመመረጥ ድረስ የተከበሩ ማደሪያቸውም በቤተ መንግሥት የነበረ አለቃ ገብረ መድኅን ናቸው ይባላል። ይህን መጽሐፍ መምሕር ፍሥሓ የተባሉት የደብረ ሊባኖስ የመጽሐፍ መምሕር ላንብበው ብለው ከአለቃ መኮንን በውሰት ይወስዱታል። ብጹእ አቡነ ማቴዎስ በዚያ ጊዜ ጸባቴ ኃይለ መስቀል ገብረ መድኅን ተብለው የደብረ ሊባኖስ ገዳም አስተዳዳሪ ነበሩ። ጸባቴ ኃይለ መስቀል መጽሐፉ ወደ ገዳሙ መግባቱን ባወቁ ጊዜ እንዲገለበጥላቸውና እንዲያነቡት ለአንድ ቁም ጸሐፊ ትእዛዝ አስተላለፉ። ራሳቸው የኔታ አፈ ወርቅ መንገሻ በምስክር ፊት እንደገለጹት፣ ያ ቁም ጸሐፊ ማድቤት ይገባና ዳቤ የሚጋገርበት ፍልጥ ሲንጣጣ (ሦስት የተባለውን አባዝቶ) “ኧረ በዘጠኙ” እያለ ሲያሾፍ ይሰማ ነበር። ወዲያው “ዘጠኝ መለኮት” የሚል ክሕደት ያለበት መጽሐፍ ወደ ገዳማችን ገባ የሚል ጉምጉምታ በገዳሙ ውስጥ ይሰማ ጀመር። ወሬው በቤተ ክህነት በተሰማ ጊዜ ጉባኤ ሊቃውንት ተሰብስቦ መጽሐፉ ይመርመርና ስሕተትም ካለበት ታርሞ ይታተም የሚል ውሳኔ አስተላለፈ።

በሌላ በኩል እኒሁ አባ አፈ ወርቅ መንገሻ የተባሉት የቅኔ መምህር መጽሐፉን ከቁም ጸሐፊው በዘዴ ተቀብለው ወደ ምርፋቅ በመውሰድ የክሕደት መጽሐፉ በኔ እጅ ስለሚገኝ እንዲቃጠል ትፈቅዳላችሁን ብለው በጠየቁ ጊዜ ማኅበሩ ይቃጠል ሲሉ ተስማሙ። በዚህ ጊዜ መምሕር አፈ ወርቅ መጽሐፉን ገልጠው እንኳን ሳያዩ ወስደው እሳት ውስጥ ጨመሩት። ይህም ራሳቸው መምህር አፈ ወርቅ ኢየሩሳሌም ሳሉ በአንደበታቸው ያረጋገጡት ሐቅ ነው። የሊቃውንት ጉባኤ መጽሐፉ እንዲላክለት ቢጠይቅ መምህር ፍሥሓ ተቃጥሎአል፣ የለም የሚል መልስ ሰጡ።

ጸባቴ ኃይለ መስቀል መጽሐፉ መቃጠሉን በሰሙ ጊዜ የቀለም ሰው ሆነህ እንዴት ገልጠህ እንኳን ሳታይ መጽሐፍ ታቃጥላለህ? ብለው መምህር አፈ ወርቅን አሰሯቸው።

አለቃ መኮንን በበኩላቸው መጽሐፌ ይመለስልኝ በማለት መምሕር ፍሥሓን በፍርድ ቤት ከሰው ሲከራከሩ ቆይተው ጉዳዩ በእንጥልጥል እንዳለ አለቃ መኮንን ሞቱ። ታሪኩ ይህ ነው፣ መጽሐፉን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ያስገቡት አንተ ጤሜዎስ አስተምረውኛል የምትላቸው መምሕር ፍሥሓ ስለሆኑ ወቀሳ ካስፈለገ የመናፍቅ ልጅ መናፍቅ መባል የሚገባህ አንተ እግረ ተማሪው ነህ እንጂ ደራሲው አይደለም።

አንተ እግረ ተማሪ፣ በብልግናህ መምሕሩን ታሰድባለህ። ከሕፃንነት እስከ ሽምግልና፣ ከዲቁና እስከ ጵጵስና ቤተ ክርስቲያናቸውንና አገራቸውን በቅንነትና በችሎታ አገልግለው ያለፉትን ታላቁን አባት ብጹእ አቡነ ማቴዎስን “እኩይ ሰማዕት” ብለህ ተሳድበህ የምትቀር አይምሰልህ። ቅዱስ ዳዊት “እስመ ይትፍጸም አፍ ዘይነብብ ዓመፃ/ ሐሰትን የሚናገር አንደበት ይዘጋል” እንዳለው፣ ብጹእ አቡነ ማቴዎስ በሕይወተ ሥጋ ሳሉ የጸለዩት ጸሎት፣ የሠሩት ትሩፋት ብዙ ነውና ለጻድቃኑ የሚበቀል አምላክ ሳይበቀልህ እንደማይቀር እርግጠኛ ነኝ። የብጽእነታቸው ልጆችና ወዳጆች የሆናችሁም ይህን ባለጌ በዝምታ ልታልፉት አይገባም፣ አምላካቸው ያያችኋል፣ አጥንታቸውም ይወቅሳችኋል።

መደምደሚያ
አንተ አስቸጋሪ የሆንክ ጤሜዎስ! እንደ ዕርጎ ዝንብ እዚያም እዚያም ጥልቅ ማለት፣ ሁሉንም መነካካት አይሰለችህም። እኔ ግን ስለሰለቸኝ ቅዱስ ሚካኤል ሰይጣንን እግዚአብሔር ይገሥፅህ እንዳለው፣ በእውነት እግዚአብሔር ይገሥፅህ በማለት እዚህ ላይ ማቆም እፈልጋለሁ። ሆኖም አንድ ምክር ልለግሥህ! በደራሲው የሳይኮሎጂ ትምህርት ላይ የሰነዘርከውን መሠረተ-ቢስ ትችት ሳነብ አንድ ትዝ ያለኝ ርእስ አለ፣ “ፕሮጀክሺን” ይባላል። ይህም ማለት የራስን ሐሳብ፣ ስሜት፣ አመለካከት ወዘተ፣ በተለይ የራስን ድክመት፣ ስሕተትና ተወቃሽነት ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ማለት ነው። እንዲህ የሚያደርግ ሰው እርዳታ የሚያስፈልገው ሕሙም ነው፣ የራሱን ድክመት ወደ ሌላ የሚያስተላልፈው አብዛኛውን ጊዜ አውቆ ሳይሆን ከሰውና ከሕሊና ወቀሳ የተነሣ ሊደርስበት ከሚችለው ጭንቀት ለመዳን ነው። በአንተ በጤሜዎስ ላይ የማየው ይህን የመሰለ ችግር ስለሆነ የሳይካያትሪ እርዳታ እንድትፈልግ እመክርሃለሁ።

እንግዲህ ለአንባቢ ጥያቄ አቀርብና በደብተራው ዝማሬ ጽሑፌን እደመድማለሁ።

አንባቢ ሆይ ስለ እግረ ተማሪው/ ጤሜዎስ ይህን ያውቃሉን?

1. እመቤታችን ኃጢኣት አለባት ብሎ ያምናል፣ ይሰብካል።

2. በዚህ ኑፋቄው የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሆኑት በብጹእ አቡነ ማትያስ ተወግዞአል።

3. ሥልጣነ ክህነቱ ስለተያዘ ቀሲስ ተብሎ መጠራት፤ ቀድሶ ማቁረብ፣ መስቀል ይዞ መባረክ፣ “እግዚአብሔር ይፍታ” ብሎ መናዘዝ፣ ማጥመቅ፣ ማጋባት፣ሜሮን መቀባት፣ በጠቅላላው ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም አይችልም።

4. እግረ ተማሪው ጤሜዎስ በክሕደቱ እንደ አርዮስ፣ እንደ መቅዶንዮስና ይልቁንም እመቤታችንን በመሳደቡ እንደ ንስጥሮስ የሚቈጠር ከሐዲ ነው።

5. የግብጽ ቤተ ክርስቲያንን የምንቃወመው በኢየሩሳሌም ጉዳይ ብቻ ነው በማለት ግብጾች ኢትዮጵያን ለ1600 ዓመታት ሲያታልሉ የኖሩበት የሐሰት ሕገ ቀኖና እንዲረሳ ይጥራል።

6. የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አሁንም ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ተገዢ እንድትሆን ለማድረግ ባለው ሕልም አባቶቻችን ደክመው ያመጡትን ነፃነት ውድቅ ለማድረግ ይሞክራል።

7. በኢትዮጵያውያን መካከል ለተነሣው ክርክር የኢትዮጵያዊውን ጳጳስ ውሳኔ አሻፈረኝ፣ አልቀበልም በማለት ግብጾችን ለዳኝነት ጋብዞአል።

8. ከተወገዘ በኋላ አሁንም በዞረበት ቦታ ሁሉ ካህን ነኝ እያለ በማታለል ላይ ይገኛል።

9. ከአቡነ ጳውሎስ ጋር በምሥጢር እየተጻጻፈ ዞር ብሎ ደግሞ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር አብሮ የሚያቀነቅን አስመሳይ፣ በሁለት ቢላዎ የሚበላ አደገኛ ቀሳጢ ነው።

10. በየጊዜው እየጫጫረ ኢንተርኔት ላይ በሚለጥፈው መጣጥፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን ይሰድባል፣ የተከበረ ስሟን ያጎድፋል።

11. የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጠንቋይ ቤት ነው፣ በዝማሬና በቅኔ እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ደብተራዎችም ጠልሳሚዎች/ጠንቋዮች ናቸው ብሎአል።

12. በአገራችን ያለው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ “ለገንዘብና ለጥቅም የተገዛ፣ ሕዝቡን በጫጫታ ለማደናቈር ሆን ብሎ የተዋቀረ ነው” ብሎ ተሳድቦአል።

13. አቡነ ጳውሎስ ሕጋዊ አይደሉም በማለት የሾሟቸውን ታላቁን አባት ሁለተኛውን የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ስሕተተኛ አድርጎአል።

14. ስድሳው ባለሥልጣኖች ያለፍርድ በግፍ በተረሸኑ ጊዜ ደርግን ያለፍርሃት በድፍረት በጽሑፍ በመቃወም ብቸኛ የሆኑትን ታላቅና ጅግና አባት ብጹእ አቡነ ማቴዎስ ሊቀ ጳጳስ ዘኢየሩሳሌም “ዘጠኝ መለኮት” የሚሉ ከሐዲ እንዲሁም “እኩይ ሰማዕት” ናቸው ብሎ የተከበረውን ዝክረ ስማቸውን አጉድፎአል።

15. ሰማያዊውን የቅዱስ ያሬድ ዜማ የጠንቋዮች ጠልሰም በማለት አንቋሿል።

16. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በነገረ መለኮት ተሳስታለች፣ እኔ ትክክለኛ ነኝ እያለ ይታበያል።

17. የኢትዮጵያ ሊቃውንት ሁሉ አልቀው እኔ ብቻ በአሜሪካ ቀርቻለሁ ብሎአል።

18. የርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ መቅደስ (ዋሺንግተን ዲሲ) የሰይጣን መፈከሪያ ነው ብሏል።
----------------======------------

በመጨረሻም ደብተራው የሚከተለውን መልክአ ጤሜዎስ ያመረግዳል፡
ሰላም ለሰብእናከ አምሳለ ሜልኮል ወኮቲባ፣

እንተ ፍጥረቱ ክርዳድ ወግዕዘ ነገሩ ገለባ፣

ሕፃነ አእምሮ ጤሜዎስ ኅዙለ ክሕደት አንቀልባ፣

ይዜምሩ ለከ እንዘ ይብሉ ለሀገረ ካንሳስ ሕዝባ፣

እግረ ተማሪ ዘስሙ ደጎባ።

ይቀጥላል!

5 comments:

Anonymous said...

ቄስ ደጀኔም ሆነ አብርሃም ምንም አይነት ስር ያለው የበሰለ የቤተክርስቲያን ትምህርት የሌላቸው ፡የትምህርት ደረጃቸው የሰንበት ትምህርት ቤት የሆነ ነው። እነሱ ይህን አሉ ያን አሉ ደረጃቸው ከሊቃውንት በታች ስለሆን ብዙም አትደነቅ

Anonymous said...

ጥሩ መልስ ለዚህ መናፍቅ፥፥ ጌታ ይባርክህ፥፥

Anonymous said...

ሰላም ለሰብእናከ አምሳለ ሜልኮል ወኮቲባ፣

እንተ ፍጥረቱ ክርዳድ ወግዕዘ ነገሩ ገለባ፣

ሕፃነ አእምሮ ጤሜዎስ ኅዙለ ክሕደት አንቀልባ፣

ይዜምሩ ለከ እንዘ ይብሉ ለሀገረ ካንሳስ ሕዝባ፣

እግረ ተማሪ ዘስሙ ደጎባ።

ግሩም ነው፡፡ግሩም ነው፡፡

Anonymous said...

wow Mr Abraham,
I just read your defense paper. but, make me even more to lean on kesis Asterayo teaching. I coundn't find yours convicing. what I remember when I was sunday school student at dc st mary church, you were teaching about tinte tehabiso back 15 or 16 years ago.and some of the students did against you. what made you change of heart. I feel sorry for you. I pray for you.

Anonymous said...

guys I don't think so this is a spiritual person response. Yeseferen Duriywoch astawesen, please be polite for every one. “ለቀጣፊ ይደልዎ ጥፊ፣ ለቀልቃላ ይደልዎ ዱላ፣ ለመናጢ ይደልዎ ቡጢ”