Tuesday, June 28, 2011

ጥያቄ አለኝ?

ይህንን ጥያቄ መታሰቢያ ኃይለ ሚካኤል ከተባሉ ግለሰ ፌስ ቡክ(face book) ላይ የተገኘ ነው::  ሁል ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ ስናስባት ብዙኀኑ ምእመናን የሚያነሱት ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ ነው:: ጥያቄው ወደ እውነተኞቹ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ቢደርስ ተገቢውን ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት አለኝ::  እኔም አንዳንድ ነጥቦች ለማንሳት ተገድጃለሁ:: 
እንግዲህ  እኛ ባለንበት ዘመን በሰሜን አሜሪካ የምንኖር የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በአባ ጳውሎስ አስተዳደር ፍትሕ ጎደለ የሚሉ ወገኖች ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር በመነጠል “ራስችን ችለናል ወይም ገለልተኞች ነን (indenedent church)” በማለት ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር መዋቅር ከተገለሉ  ሁለት አስርት ዓመታትን አስቆጥረዋል። እንዲሁም በቅርቡ “የገለልተኞች ጳጳስ ይሾምልን” በማለት እጀ መንንሻ ይዘው መንበረ ፓትርያኩ ድረስ በመሄድ ደጅ በመጥናት ላይ ናቸው::


ይህ “የገለልተኝነት” አስተምህሮ በዚህ በሰሜን አሜሪካ አንቱ የተባሉ ሰባኪያን “ወንጌል እስከተሰበከ ድረስ ችግር የለውም” በማለት  የሚያስተምሩ አሉ::

በኦሬንታል የእንኛን ቤተ ክርስትያን ጨምሮ  አሐት አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ደግሞ በምስራቁ ኦርቶዶክሳዎያን ዘንድ ራስን የመቻል ወይም የገለልተኝነት አስተምህሮ እንደሌላቸው መዛግብት ይመሰክራሉ::  ታድያ አሁን እየተስፋፋ ያለው ገለልተኝነት አስተሳሰብ (indepedency) በቡድንም ሆነ በግል አስተምህሮው ከየት የመጣ ነው? አስተምህሮውስ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ እንዴት ይታያል? በእነዚህ ጥያቄዎች ዙርያ የተዋሕዶ ልጆች መወያየት ያለብን ይመስለኛል።
  
ጳጳስ እንዲሁም ሊቀ ጳጳስ የማይቀበል ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ያለ አይመስለኝም። በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ሰባቱንም ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን የመፈጸም ሥልጣን ያላቸው ጳጳሳት እና ሊቃነ ጳጳሳት ብቻ እንደሆኑ በፍትሐ ነገሥት ላይ ተጽፎዋል::
ሰለዚህ በዚህ በገለልተኞች አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት ሚስጥራተ ቤተ ክርስቲያን እና ቀኖና ቤተ ቤተ ክርስቲያን እየተፋለሱ ናቸው። አውቀውም ይሆን ሳናውቁ ከሚጥራተ ቤተ ክርስቲያን እና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ወጥተዋል ማለት ነው።
 
“የትኛው ሚስጥራተ ቤተ ክርስቲያን ተፋለሰ”? ቢባል። ሁላችንም እንደምናውቀው ከሰባቱ ሚጥራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ሚስጥረ ሜሮን ነው። ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ሜሮን ከቅብጥ ወይም ከግብጽ መንበረ ማርቆስ ከሆነችው ቤተ ክርስቲያን እያስመጣች ትጠቀም ነበረ። አሁን ግን በራሷ መንበር ማፍላት ጀምራለች።

ሜሮን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሊቃነ ጳጳሳት በአንድ ላይ ሆነው አፍልተው ለየ ሀገረ ስብከታቸው ይከፋፈላሉ። አዲስ ቤተ ክርስቲያን ሲታነጽ፣ ክህነት እና በቤተ ክርስቲያን ያሉት ንዋያተ ቅዱሳት የሚከብሩት በሜሮን ነው። በ40 እና በ80 ቀን ህፃናት ሲጠመቁ ማህተመ መንፈስ ቅዱስ የሚቀበሉት በሜሮን ነው።

ቅዱሳን ሐዋርያት በአንድሮተ እጅ ፀጋ መንፈስ ቅዱስ ያሳድሩ እንደነበረ ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል። ነገር ግን የአማኙ ቁጥር እየበዛ ሲመጣ በቅዱሳን ሐዋርያት እግር የተተኩ አባቶች ሚስጥረ ሜሮን እንደሰሩልን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል። ጳጳሳት ልክ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በአንብሮተ እጅ ማሳደር እንደሚችሉ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን ታስተምራለች። ሜሮን ቄስ ለአዲስ አማኝ በጥምቀት ጊዜ ሲቀባ ልክ ጳጳሱ በአንብሮተ እጅ እንዳደረገው እንደሚቆጠር ቤተ ክርስቲያናችን በሚስጥራተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቷ ታስተምራለች። ሜሮን አይደገምም በጥምቀ ክርስትና ጊዜ ብቻ ይፈፀማል።

በዚህ በሰሜን አሜሪካ በአባ ኤገሌ ወይም በአቶ ኤገሌ የሚተዳድሩ በየትኛውም መዋቅር ከሊ ቃነ ጳጳሳት ጋር አይገናኙም። መዋቅር እንኳ ባያገናኛቸው በግል ደረጃ ከጳጳሳት ጋር አይገናኙም። እንዲሁም “ገለልተኛ” ነን ከሚሉትም መካከል  ተአምር እንኳ ቢፈጠር የእነሱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጳጳሳት ሊገቡ እንደማይችሉ ተናግረዋል። ታዲያ እነዚህ አጥቢያዎች ከሰባቱ ሚስጥራተ ቤተ ክርስቲያን ሚስጥረ ሜሮን ለመፈጸም፤ ቅዱስ ሜሮን ከየት ይሆን የሚያገኙት? 

ከሚስጥራተ ቤተ ክርስቲያን መፋለስ በተጨማሪም ጠያቂው ግለሰብ እንዳነሱት የበቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር በተመለከተ “ገለልተኛ ነን” የሚሉ ወገኖች ከኦርቶዶክሳዊ አስተሳሰብ ውጪ ናቸው:: አንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ወይም አንድ ሰባኪ “ራሴን ችያልሁ፤ ከማንም ምንም አልፈልግም” ካለ አስተሳሰቡ የፕሮቲስታንት ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ራስን የመቻል(indepedency) አስተህምሮ የፕሮቴስታንት ነውና። ስለዚህ እምነት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተሳሰብ ደግሞ የፕሮቴስታንት ውሎ ሲያድር መጨረሻውስ ምን ይሆን?

የአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን የመጨረሻው የስልጣን አካል እንዴት ቦርድ ሊሆን ይችላል? የሃይማኖት እፀጽ ቢፈጠርስ አውጋዡ ማን ሊሆን ነው? ቦርዱ? ወይስ ማኅበረ ካህናቱ? መልሱን ለአንባቢው ትቼዋለሁ።

እግዚአብሔር ተዋሕዶ  ሃይማኖታችን ይጠብቅልን!!! አሜን

5 comments:

Anonymous said...

በከመ ይቤሉነ ሐዋርያት "ነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን" በማለት የሐዋርያዊት ቅድስት ቤተክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ አርቆ አስተዋይነት ይጠይቀናል።ስለ አስተዳደር በደል፤ ስለሥርዓተ ቤተክርስቲያን፤ ስለ ፓትርያርክ ተቀባይነትና ሕጋዊነት ምክንያት እየፈጠርን መሰደድና መገለል ለችግሩ መፍትሔ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም።ቤተክርስቲያንን እኮ የምናውቃት ናት ...ለምን እንግዳ እንሆናልን።ብዙ ፈተና ያለባት ናት።አድባራቱና ገዳማቱ ያለችግር ያለበደል ነው የሚተዳደሩት ለማለት አንችልም።እና ይገለሉ? ይሰደዱ? የራሱን አስተዳደር ይፍጠር?መፍትሔ ይመጣል? በአሜሪካው እንዳሉት ነጻነት ስለሌለ የሚል ተግዳሮት ልታመጡ ትችላላችሁ።እናንተ ነጻነታችሁን ተጠቅማችሁ መች ተወያያችሁና ተግባባችሁ? አንዱ ስደተኛ ሌላው ገለልተኛ ሲል ነው የምንሰማው። አይደለም ለመግባባት ለመነጋገርም የምንችለው በአንዲት ቤተክርስቲያን ጥላ ሥር ስንሆን ነው። የገለልተኞችም ገለልተኛ ላለመፈጠሩ ምን ዋስትና አለን? እንደው በእመብርሃን ይሁንባችሁ በቅድሚያ ስለቤተክርስቲያን ከዚያ ስለ ግለሰብ እንጨነቅ አቡነ በርናባስ እንደተናገሩ።የአስተዳደር በደሎችና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ለማስተካከል ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከምዕመን ፈተናውን ተቋቁመው የሚሰሩ አሉ።ይሔ ሲጨመርባቸው ሌላ የሚያሳምም ነገር ነው የሚሆነው።ለመለያየት ብዙ ምክንያት መደርደር ይቻላል።ለአንድነት ግን ፍቅርና ትሕትና። ለዚህም የአቡነ ሳሙኤልን አባባል እጠቅሳለሁ ”ለቤተክርስቲያኔ ሰላም ስል እናንተ አባቶቼ የምትሉኝን እቀበላለሁ‘ ልብ ላለው አንድምታው ብዙ ነው።ውይይቱን ወድጄዋለሁ።በስሜት አስቀይሜያችሁ ከሆነ ይቅርታችሁን እጠይቃለሁ።

Anonymous said...

መልካም ጥያቄ ወይም አሰተያየት ነው።ነገር ግን ምላሹ ገለልተኞች ጋር ሳይሆን ጳጳሳቱ ጋር ነው ያለው። እስቲ አህያውን ፈርታችሁ ዳውላውን አታሳዱ።በእውነት ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቁራችሁ ከሆነ? መጀመሪያ ጳጳሳቱ እራሱ ገለልተኛ አይደሉ እንዴ?እነርሱስ ቅብዐ ሜሮን ከየት አመጡ?ደግሞስ የግድ ጳጳስ ብቻ ነው እንዴ ቤተክርስቲያን የሚባርከው ቆሞስ አይችልም እንዴ?ገለልተኞቹን ደካሞቹን ከመንካት በሁለት ቢላ የሚበሉትን ጳጳሳት ወደ ቤተክርስቲያን ሕግ እንዲያዘነብሉ አትነግሯቸውም እንዴ?ሀገር ቤት የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አሜሪካ ገለልተኛ ያስቃል ማሰተካከል የሚጀመረው ከራስ አይደል እንዴ?አቡነ ፋኑኤል ዲሲ ሲገቡ አላስፈቀዱም የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ አላችሁ!ማነው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ? ለሲኖዶስ ስብሰባ የማይገቡ አባት የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ይባለል እንዴ? ስለዚህ ሁለቱም ገለልተኞች ስለሆኑ ፈቃድ መጠያየቅ እንደማያስፈልግ ይተዋወቃሉ?ስለዚህ ነው ከሀገረ ስብከቱ ምንም ያልሰማችሁት ገለልተኞቹ የተማሩት ከአባቶቻቸው ነው? ይህች አሰተያየት እንደማትወጣ አምናለሁ እኔ ግን ጻፍኩኝ እናንተ ለቤተ ክርስቲያን ካላችሁ አዉጡት። አምላከ ቅዱሳን መሳለቂያ ከመሆን ያድነን

Anonymous said...

@2nd Anonymous, can you please tell us where you got this idea from "ግሞስ የግድ ጳጳስ ብቻ ነው እንዴ ቤተክርስቲያን የሚባርከው ቆሞስ አይችልም እንዴ?" Fitha Negest tekisew biyaserdun. Instead of just stating your question, please have a reference.

Anonymous said...

አዎ ቆሞስ በተክርስቲያን አይባርክም ዲቁና አይሰጥም ያ የጳጳሳት ብቻ ስልጣን ነው።

Anonymous said...

፪ኛ/ ሁላችንም እንደምናውቀው በቤተክርስቲያናችን ታሪክ አንድ ጳጳስ በህይወት እያለ ምንም መታሰቢያ አይደረግለትም፣ በዚህ ምድር በነበረበት ጊዜ በሠራው ጥሩ ምግባር፣በጎ ሥራ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚወስነው መሠረት “ቅዱስ” ተብሎ ታቦት ተቀርፆለት፣ ገድል ተጽፎለት ሊታሰብ ሊወሳ ይችላል። አቡነ ፋኑኤል ግን ይህንን ቤተክርስቲያን የጣለችባቸውን ሃላፊነት ወደጎን በመግፋት “እኔም እንዳባቴ” በሚል ፈሊጥ ትልቁን ቢል ቦርድ የራሳቸውን ፎቶ አሰርተው በአዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ በቅዱስ ሚካኤል ዲሲ አሰቅለዋል። ይሄንን ፈሊጥ ያመጡት የክርስቶስ ጠላቶች ለመሆናቸው ማንም የሚክደው አይመስልኝም፣ የቤተክርስቲያን መሥራቿና እራሷ ከሆነው ከክርቶስ በላይ ከፍ ብለው ለመታየት ያላቸው ከንቱና የትም የማያደርሰው ምኞታቸው ነው፣ ታዲያ አቡነ ፋኑኤልን እንደ አንዳንድ የዋሃን ወይም የጥቅም አጋሮች ጥሩ አባት ናቸው ለማለት የሚያስደፍር አንደበት ሊኖረን አይገባም።

፫ኛ/ በቅድስት ቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ከሃዋርያት ጀምሮ የተለያዩ ቅዱሳን እንዲሁም ሰማዕታት ይህቺን ቤተክርስቲያን ለእኛ ያደረሱልን በብዙ ተጋድሎ እስክ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ነው፥ ታዲያ በኔና በናንተ ጊዜ በሕይወት መስዋዕት የሚሆን ቢጠፋ እንዴት ስለእውነት መመስከር ተሳነን፣ ሰማዕት ማለት እኮ ምስክር ማለት ነው። አዎ በአሁኑ ጊዜ የሕይወት መስዋዕትነት የሚጠይቅ ላይሆን ይችላል የተጠየቅነው፣ ነገር ግን ስለ እውነት እንድንመሰክር መዳኅኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር በተመላለሰ ጊዜ አስተምሮናል “በምድር ለሚመሰክርልኝ፥ እኔ በሰማዩ አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ” ብሎ አስተምሯል። ታዲያ ስለ አማናዊው ቃሉ እንዴት መመስከር ተሳነን፡ እንዴትስ በክርስቲያኖች ላይ ለዛውም እንዲጠብቋቸው፣ የበግ ለምድ ለብሶ ከሚመጣው ነጣቂ ተኩላ እንዲጠብቁ፣እንዲከላከሉ ለተሾሙባቸው ወገናቸው ላይ ያልሆነ የትዕቢት ቃል አንድ ጳጳስ ሊናገር ይችላል? መልሱን ለራሳቸው እንተወውና በሃዋሳና ጥንባሮ ዞኖች ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ የተናገሩትን ልንገራችሁ፣ ወቅቱ ክረምት ነበር እና የምዕመናን ተወካዮች ከሊቀ ጳጳሱ ጋር ስብሰባ ላይ ናቸው ታዲያ አሜሪካዊው መነኩሴ በጣም መመፃደቅ ያዘወትራሉ፣ በስብሰባው ላይ በተነሳ አለመግባባት አቡነ ፋኑኤል “ እያንዳንድሽ ነገ እዚህ ታኪያታለሽ፥ ነገ እኔ ተነስቼ ወደ አሜሪካኔ እሄዳለሁ” ብሎ መመፃደቅ በእውነት ሊጠብቋቸው፣ ሊያጽናኗቸው፣ ሊያበረቷቸው እንዲሁም የክርስቶስን ዘለአለማዊ መንግስት እንዲወርሱ ሊራዱ የተጠሩበትን ተልዕኮአቸውን ወደ ጎን ትተው እንዲያ መመፃደቅ ባልተገባ ነበር፣ ዳሩ የበግ ለምድ ለብሰው መንገዱን ሊያስቱ ከመጡት ሃሳዊያን አንዱ ላለመሆናቸውስ ምን መረጃ አለን።

የሆነ ሆኖ ከአንድ አባት የማይጠበቁ ብዙ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የሚያፋልሱ ብዙ ሥራዎች ባለፉት አምስት አመታት ሢሰሩ ታይተዋል ሥራቸውም ምስክር ነው፣ በእውነት ለሃዋሳ ክርስቲያኖች ይሄ ይገባቸው ነበር? በእውነት ለቤተክርስቲያን ያልተቆጩ አባት ለሃዋሳ ክርስቲያኖች ምን ሊገዳቸው። ከላይ የጠቀስኳቸው ጥቂቶቹን ነው ነገር ግን ብዙ ሥርዓቶችን አቡነ ፋኑኤልና ግብርአበሮቻቸው ብዙ ጥፋት እና ውድመት እያደረሱ ይገኛሉ፣ ታዲያ ለንዲህ አይነት አባት አጋር መሆን ይሻላል ወይስ ለቅድስት ቤተክርስቲያን አጋር መሆን ይሻላል? መልሱን ለአንባቢያን ትቼዋለሁ።
እግዚአብሔር አምላክ የቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ትንሣኤ ያቅርብልን፣
የዘመኑን አፅራረ ቤተክርስቲያን ያስታግስልን፡
እኛንም ሰውን ሳይሆን በመስቀል ላይ ሕይወቱን ሰጥቶ ወደ ብርሃን የወሰደንን ቅድስናው የባሕሪይ ገንዘቡ የሆነውን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማሪያም አንድያ ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናይ ይርዳን። አሜን