Thursday, July 7, 2011

"የጥንተ አብሶ" አስተምህሮን በተመለከተ ሊቃውንቱ ምን ይላሉ?

እዚህ ሀገረ አሜሪካ በወላዲተ አምላክ ቅድስ ድንግል ማርያም ላይ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ነገረ ማርያም አተምህሮ ውጪ የተዛባ አስተምህሮ በይፋ አቋማቸውን በፊርማ ካረጋገጡት መካከል ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ፤ አባ መዓዛ በየነ እና አባ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ናቸው:: ቀሲስ አስተርአየ እና አባ መዓዛ በየነ የግላቸው ቤተ ክርስቲያን በእነሱ አጠራር “church” አላቸው:: እነኚህ ሁለቱ ግለሰዎች በየትኛውም መዋቅር ከሊቃነ ጳጳሳት ጋር ግኑኝነት የላቸውም:: ከሰባቱ ሚስጥራተ ቤተ ክርስቲያን ሚስጥረ ሜሮን ከተፋለሰባቸው አጥቢያዎች መካከል የሚመደቡም ናቸው::

 አባ ሠረቀ ብርሃን ወደ ኢትዮጵያ ከመግባታቸው በፊት “በገለልተኛ አስተዳደር ሥር” በቨርጂኒያ ግዛት ፍኖተ ጽድቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ የራሳቸው ቤተ ክርስቲያን ነበራቸው:: አሁንም ቢሆን ይህ ቤተ ክርስቲያ በባለቤትነት የእርሳቸው መሆኑን የደብሩ አባላት ይናገራሉ:: አባ ሠረቀ ብርሃን የዛሬ ስድስ ዓመት በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ “በገለልተኛ አስተዳደር ሥር” ያሉት በወቅቱ ማኅበረ ካህናት ተብሎ ይጠራ የነበረው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “የውርስ ኃጥያት አለባት ወይም ጥንተ አብሶ” አለባት ብለው ከተፈራረሙ ካህናት መካከል አንዱ ናቸው:: ከዚህ  በፊት ነጭ እንቁ በአዳም ገላ የሰኘ  የተፈራረሙበት ሙሉ መረጃ አካቶ ኢትዮጵያ ውስጥ በገበያ ላይ መዋሉን መዘገባችን ይታወሳል (ዘገባውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ)::


ከተፈራራሚዎቹ መካከል ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ኃይሌ እና ሊቀ ማእምራን ዶ/ር አማረ ካሣዬ ዘንድሮ በጥር ወር አካባቢ በዋሽንግተን ዲሲ ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን  የደብሩ ካህናት “በነገረ ማርያም አስተምህሮ ያለን አቋም መታወቅ አለበት” በሚል ሊቀ መዘምራን ሞገስ ባነሱት ጥያቄ መሠረት ሁሉንም ካህናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የውርስ ኃጥያት የለባትም በማለት በፊርማቸው አረጋግጠዋል::  አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል አቋማቸውን አሁንስ ቀይረው ይሆን?

የሚከተለውን ጽሑፍ  ጥንተ አብሶ ለሚያስተምሩ የተዛባ አስተሳሰባቸው እዲያቆሙ ምላሽ የተሰጠበት ነው::

  •  «ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሸ ውብ ነው ነውርም የለብሽም» በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን ከመዝሙራት ሁሉ በሚበልጥ መዝሙሩ የዘመረላትን እመቤታችንን «ጥንተ አብሶ» /የቀደመ በደል/ ደርሶባታል ለሚለው ትምህርት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት /ውሳኔ/ ምንድን ነው ?


(ከመንግሥት አብ አራንሺ) :- «እመቤታችን አዳም በጥንተ ተፈጥሮው ሳለ /ከመበደሉ በፊት/ የተቀዳች ዘር ናት፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ...» እንዲል፡፡ ጌታችንም ይህን ንጹሕ ሥጋ ነው የተዋሐደው፡፡ የተአምረ ማርያም መቅድም «እመቤታችን አስቀድማ በአምላክ ሕሊና ትታሰብ ነበረ» ማለቱም ምክንያተ ድኂን ያደረጋት ንጹሕ ዘር መሆኗን ነው የሚገልጠው፡፡
 አነጻት፣ ቀደሳት የሚሉት ቃላት የሚገልጡት አሳብ አንድ ነው፡፡ አስቀድሞ ያዘጋጃት የመረጣት እናት መሆኗን ብቻ፡፡ ቅዱስ ያሬድ «ማርያምሰ ተሃቱ እምትካት ውስተ ከርሡ ለአዳም ከመባሕርይ ፀዐዳ፤ ማርያም አስቀድሞ በአዳም አካል /ባሕርይ/ ውስጥ እንደ ዕንቁ ታበራለች፡፡» እንዲል፡፡ አዳምና ሔዋን በጥንተ ተፈጥሮ ሳሉ ካልበደለ ዘር የተቀዳች ንጹሕ መሆኗን በነጭ እንቁ መስሎ ተናግሮላታል፡፡

ሊቁ ቅዱስ ሳዊሮስ ደግሞ በሃይማኖተ አበው «መንፈስ ቅዱስ አቀባ እም ከርሠ እማ፤ መንፈስ ቅዱስ በእናቷ ማኅፀን ጠበቃት» ነው የሚለው፡፡ ሊቃውንቱ አንድ ትምህርት ያላቸው ናቸው፡፡ ቅዱስ ያሬድ «አንጺሖ ሥጋሃ ሃደረ ላእሌሃ» ያለውን ትርጉም ለመስጠት የቅዱሳን አባቶችን ትምህርትና እምነት መረዳት ያሻል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከላይ በዕንቁ መስሎ በአዳም ባሕርይ ውስጥ ታበራለች ያላትን እናት ደርሶ ሌላ ይላታል ማለት አይቻልም፡፡ ብዙዎቹን ወደ ስህተት የከተተው የቋንቋ ችግር ነው፡፡ ቋንቋ ንባብ እንጂ ምስጢር አይደለም፡፡ ፊደል ይገድላልና፣ ትርጓሜ /ምስጢር/ ግን ሕይወትን ይሰጣል፡፡ «አንጺሖ ሥጋሃ ሀደረ ላእሌሃ» መረጠ፣ አከበረ፣ ቀደሰ፣ ለየ እና አደረባት የሚል ነው፡፡ ሊቁ ስለ ሰንበተ ክርስቲያን ክብር የተናገረው ለዚህ አስረጅ ይሆናል፡፡ «ቀደሳ ወአክበራ ወዐልዓላ እምኩሎን መዋእል» ምን ማለት ነው፡፡ ሰንበተ ክርስቲያንን ለያት፣ አከበራት ማለት ነው፡፡ «ንጹሕ አነ እምደሙ ለዝ ብእሲ፤ እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ» ስንልስ ልዩ ነኝ አይመለከተኝም ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህ ሊቁ «አንጺሖ ሥጋሐ» ያለው «ሥጋዋን ከአዳም ለይቶ አነጻ ቀደሰ ለየ» ማለት እንደሆነ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ ያብራራሉ፡፡

በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀው መጽሐፍ የእመቤታችንን ንጽሕናና ቅድስና አስመልክቶ ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን አስተምህሮና አቋም እንዲህ ያስረዳል፡፡ «አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢአት /ጥንተ አብሶ/ ያላገኛት፤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት፤ ገና ከመውለዷ አስቀድሞ በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር የነበረች፤ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ አሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች፤ ከተለዩ የተለየች ንጽሕት ቅድስተ ቅዱሳን ናት ይላል፡፡ /መሐል. 4፥7/፡፡» /የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዓተ አምልኮና የውጪ ግንኙነት፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት፣ 1988 ዓ. ም./፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሊቃውንት ጉባኤ አባል እና ጸሐፊ በመሆን ያገለግሉ የነበሩት መምህር ሀብተ ማርያም ተድላ፤ የወላዲተ አምላክን ቅድስና እና ንጽሕና የበርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ጠቅሰው ባስረዱበት መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል፡ «አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኀጢአት /ጥንተ አብሶ/ ያላገኛት ለመሆኗ በቅዱሳት መጻሕፍት የተረጋገጠ ነው፡፡ «መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ ደስ ይበልሽ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው፣ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት...» /ሉቃ. 1፥28-38/ ይህ አባባል፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እርሷ ከመላኩ በፊት ጸጋን የተሞላችና የተባረከች መሆኗን በማያጠራጥር ሁኔታ ነው የሚገልጸው፣ ምክንያቱም መልአኩ ሰላምታውን በኃላፊ እንጂ በትንቢታዊ ግሥ አላቀረበምና፤ ወደፊት ጸጋ ይመላብሻል ከሴቶችም ሁሉ የተባረክሽ ትሆኛለሽ አላላትም፡፡ እንደገና መልአኩ በሰላምታ መደንገጧን አይቶ... «ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋን /ባለሟልነትን/ አግኝተሻልና አትፍሪ...» አላት፡፡ አሁንም የመልአኩ ማረጋጊያ ዐረፍተ ነገር እንደ ኃላፊ እንደ ትንቢት አይደለም፤አግኝተሻል አላት እንጂ ወደ ፊት ታገኛለሽ አላላትም፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው እመቤታችን ከመፀነሷ በፊት ወይም ወደዚህ ዓለም ከመምጣቷ በፊት ጀምሮ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ያልነበረባት መሆኑን ነው፡፡» /ነጭ ዕንቁ በአዳም ገላ፤ በመምህር ሀብተ ማርያም ተድላ፤ አዲስ አበባ 2002 ዓ.ም፤ ገጽ. 43/፡፡

ልበ ብርሃኑ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ /ሊቀ ጠበብት/ «ምልጃ እርቅና ሰላም» በተሰኘው መጽሐፋቸው፤ «ለእናትነት የመረጣትን ማደሪያውን ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ከኀጢአት ከርኩሰት ከእድፈት ሁሉ ጠብቋታል፡፡ የሰው ልጆች በተያዙበት በአዳም በደል ወይም በራሳቸው በደል ምክንያት የረከሱበት የኀጢአት ቅሪት መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የለባትም፣ አላገኛትም፤ ምክንያቱም እርሱ ራሱ ማደሪያ አድርጎ ስለመረጣት» በማለት አብራርተዋል፡፡ /ምልጃ እርቅና ሰላም፤ አለቃ አያሌው ታምሩ፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ 49/፡፡

ወላዲተ አምላክ የውርስ ኃጢአት አለባት ማለት ጽርፈት ሆኖ ሳለ፤ ጥንተ አብሶ /መርገመ ሥጋ ወነፍስ/ በመልአክ ብሥራት ራቀላት ማለትም ከፍተኛ የሆነ የነገረ ሃይማኖት ስሕተት ውስጥ የሚጨምር ነው፡፡ የመልአክ ብሥራት የቀደመ በደልን /ጥንተ አብሶን/ የሚያርቅ ከሆነ በብሥራተ መልአክ የፀነሱ እመው /እናቶች/ የሶምሶን እናት፣ የዮሐንስ እናት ኤልሳቤጥ... ምነው ከጥንተ አብሶ ያልነጹ ? በዚያውስ ላይ የወልደ እግዚአብሔርን ሞት ከንቱ አያደረገውምን ? የኑፋቄ ትምህርቶች መሠረታዊ ችግር አንዱን ጥቅስ ብቻ መዞ መነሣት ብቻ አይደልም፡፡ አንዱ ስሕተት ማለቂያ ወደ ሌለው ክህደት የሚጨምር መሆኑ ነውና፤ ምእመናን ራሳቸውን በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጠብቀው ሊያቆዩ ይገባል፡፡

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል የሆኑት መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን የወላዲተ አምላክን ንጽሕና በመሰከሩበት ቃል፡- «... ከዚህ ዓለም ቅዱሳንና ቅዱሳት መካከል እንደ እመቤታችን ያለ፤ በእርሷ መጠን ጸጋን የተመላ፤ በንጽሕናና በቅድስና የተዋበ፤ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነና በልዑል ኃይልም የተጠበቀ ሰውነት ያለው /ሉቃ. 1፥28-36/ የለም፡፡ ይኸውም እመቤታችን ለአምላክ እናትነት የተመረጠች ድንግል በመሆንዋና እንዲሁም የአምላክ እናት እንደ መሆንዋ መጠን በሐልዮ፤ በነቢብና በገቢር ሁሉ ንጽሐ ጠባይዕ ያላደፈባት ቅድስትና ቡርክት በመሆንዋ ነው፡፡ ስለዚህ ራስዋ አስቀድማ በወንጌል ቃል እንደተናገረችው፤ ትውልድ ሁሉ «ቅድስት ወብፅዕት» እያለ ሲያመሰግናት ይኖራል፡፡ ሉቃ. 1፥48፡፡»/ ሰአሊ ለነ ቅድስት የነገረ ማርያም ትምህርት፤ ክፍል አንድና ሁለት፤ የማእዶት መጽሔት ልዩ እትም፤ 1993 ዓ. ም. 2ኛ እትም፤ ገጽ 48/

No comments: