Friday, July 22, 2011

የአቦይ ስብሐት “አስተያየት” እና አንድምታው

 ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና በደጀ ሰላም እንደተዘገበ:: መልካም ንባብ::
(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 22/2011/ TO READ IN PDF, CLICK HERE)፦ የኢሕአዴግ ፖለቲካ መሐንዲስ የሆኑት አቶ ስብሐት ነጋ ባለፈው ባስነነቡን ጽሑፋቸው ስለ ቤተ ክርስቲያን (እርሳቸው ቤተ ክህነት እያሉ አጠቃለውታል) ብዙ ቁምነገሮች አንሥተዋል። ደጀ ሰላም ለረዥም ጊዜ ስትዘግብበት፣ ርእሰ አንቀጾችን እና ሐተታዎችን ስታቀርባበቸው በነበሩ እና አሁንም በቀጠለችባቸው ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ብያኔዎችን በመስጠት ውይይቱን አንድ ርምጃ አራምደውታል። አቶ ስብሐት በዚህ በዓይነቱ ልዩ በሆነው ጽሑፋቸው የሚከተሉትን ነጥቦች አንሥተዋል። እነዚህም ነጥቦች፦ 1.   ለቤተ ክህነቱ አስተዳደራው ብልሹነት ተጠያቂው ቤተ ክህነት እንጂ መንግሥት አይደለም፤
 2.  ጳጳሳቱ “ለሃይማኖታቸው አይረቡም”፤
 3.  ቤተ ክህነት ከመንግሥት ሥር ወጥቶ አያውቅም፤ ምሳሌ፦ አጼ ኃ/ሥላሴ “ቅዱስ ተብለው ጽላት ተቀርጾላቸዋል”፤
 4. ለቤተ ክህነት በመንግሥት ሥር መውደቅ ተጠያቂዋ ራሷ ቤተ ክህነት ናት፤
 5. ቤተ ክህነቱ “ወደ ሞት አፋፍ እየሄደ ነው”፤
 6. ስለ ቤተ ክህነት እንደዚህ መሆን “አማኙ ሐቁን የመስማት መብት” አለው፤
 7. ሌሎች ሃይማኖቶች እንደ ቤተ ክህነት ለምን እንደዚህ አልሆኑም?
 8. ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ፦ የቤተ ክህነት ዕዳ ነው፤ የቤተ ክህነት አስተዳደራዊ ብልሽት ያውቃል ነገር ግን ዝም ይላል፣ ብልሽቱ እንዲስተካከል አይሠራም፣ የሚሠሩትን ያደናቅፋል፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ መድረክ ነው፤ …  የሚሉት ናቸው።
እነዚህን ነጥቦች በይዘት ደረጃ ለመመደብ ብንሞክር፦
 1. ቤተ ክህነት አስተዳደራዊ ብልሽት አለበት። ይህም አስተዳደራዊ ብልሽት ወደ ሞት አፋፍ አድርሶታል።
 2. የቤተ ክህነቱ ብልሹነት ይስተካከል ዘንድ ትልቁን ሚና መጫወት የነበረባቸው ጳጳሳት ምንም ርምጃ እየወሰዱ አይደለም፤ ጭራሹኑ ይፈራሉ። ፓትርያርኩ ደግሞ የአስተዳደራዊው ብልሹነት ዋነኛ አቀንቃኝ ናቸው።
 3. ቤተ ክህነቱ ለገባበት ቀውስ ተጠያቂ ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ የተለያዩ አካላት ቢኖሩም (ለምሳሌ መንግሥታት) በዋነኝነት ግን ሓላፊነቱን መውሰድ ያለበት ራሱ ቤተ ክህነቱ ነው። በተለይ ደግሞ ኢህአዴግ መንግሥት ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። እንዲያውም ምሉዕ ነጻነት ሰጥቶ “ሃይማኖት እና መንግሥት” እንዲለያዩ ያደረገው ኢሕአዴግ ነው። … የሚሉ ናቸው።
የአቶ ስብሐት ጽሑፍ ትልቁ ቁምነገሩ ቤተ ክህነቱ በከፍተኛ ዝቅጠት ውስጥ እንደሚገኝ ከአንድ ትልቅ የመንግሥት ባለሥልጣን (ወይም የቅርብ ጊዜ ባለሥልጣን) የተገኘ መሆኑ ነው። አስተዳደራዊ ብልሽቱ ስር የሰደደ መሆኑን ለረዥም ጊዜ የምናውቀው ቢሆንም መፍትሔ ለመስጠት ከብልሹው አስተዳደር ጎን ቆሟል ተብሎ ይፈራ የነበረው የኢሕአዴግ መንግሥት “ብልሽቱን ማወቁ” መፍትሔ ለሚፈልጉ አካላት ትልቅ እፎይታ ነው።
አቶ ስብሀት እንዳሉት “ቤተ ክህነቱ በሞት አፋፍ ላይ” ብቻ ሳይሆን በመሞትም ላይ ነው። ቤተ ክህነቱ በራሱ የሞተ ሳይሆን “ተገድሎ” ነው። ገዳዮቹ ደግሞ የመንግሥትን አለኝታነት እንደመከታ የሚጠቀሙ ከፓትርያርኩ እና ከቤተሰቦቻቸው እስከ ዓላማቸው አስፈጻሚዎቻቸው ያሉ ጥቅመኞች ናቸው። እነዚህ ጥቅመኞች ዓላማቸውን ለማስፈጸም የመንግሥትን ክንድ ይጠቀማሉ። የሚቃወማቸውን “በተቃዋሚ የፖለቲካ አራማጅነት” በመክሰስ እና ያስመታሉ። ለዚህም ምሳሌዎችን ለማንሳት እንወዳለን።
ባለፈው ዓመት በተደረጉ የተለያዩ የቅ/ሲኖዶስ ጉባዔዎች ብፁዓን አበው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ተንቀሳቅሰው ነበር። ነገር ግን እንቅስቃሴው ከግብ ሳይደርስ አፋኝ ማፊያዎች የቤተ ክህነቱን በር ጥሰው በመግባት ቤተ ክርስቲያን በማታውቀው ድፍረት ብፁዓን አባቶች ላይ እንግልት እና ማስፈራሪያ ደርሷል። አቶ ስብሐት “አይረቡም” ያሏቸው አባቶች ለእምነታቸው ለመናገር ባደረጉት ጥረት ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ይህንን ወንጀል ሊያጣራ የሚገባው መንግሥትም የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ማለትን መርጧል። አብዛኞቹ አባቶችም ይህንን የመንግሥት ዝምታ “እርሱም አለበት” ከሚል ተርጉመውታል።
የቤተ ክህነቱ አስተዳደራዊ ብልሹነት ፊት-አውራሪዎች ከመንግሥት ጋር ንክኪነት ያላቸው ሰዎች እንጂ ተራ ሰዎች አይደሉም። ከፓትርያርኩ ጀምሮ፣ ቤተሰባቸውን ይዞ እስከ ደብር ፀሐፊዎች ድረስ በአምቻ ጋብቻ፣ በአገር ልጅነት እንዲሁም በደፈናው በትግራይ ልጅነት እና በትግራዋይነት የሚያስፈራሩ ዘራፊዎች ቤተ ክህነቱን እና መዋቅሩ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ደሙን እየመጠጡት ነው። ፖሊስ የማይፈሩ፣ ፍርድ ቤት “ሃይ” የማይላቸው የሚመስሉ፣ መንግሥት ጓደኛቸው የሆነ የሚያስመስሉት እነዚህ ዘራፊዎች በእርግጥም ቤተ ክህነቱን “ወደ ሞት አፋፍ” አድርሰውታል።
መንግሥት የሙስናን ነገር በተመለከተ፣ በተለይም ስለ ቤተ ክህነት የሚገደው ከሆነ፣ በአገሪቱ ከሚፈጸሙ እና ከፍተኛ የሕዝብ ንብረት ከሚመዘበርባቸው ተቋማት መካከል ቅድሚያነቱን ሊይዝ ይገባ የነበረውን የቤተ ክህነትን ሙስና እንደ ቀላል ማየቱ  በአባ ጳውሎስ ላይ ብቻ ሳይሆን በራሱ በመንግሥትም ላይ ብዙዎች ፊታቸውን እንዲያዞሩ እና ውሎ አድሮ ደግሞ ጥርሳቸውን እንዲነክሱ የሚያደርግ ነው። ምንም እንኳን አቶ ስብሐት እንዳሉት ለብልሽቱ በዋነኝነት መጠየቅ ያለበት ቤተ ክህነት ቢሆንም መንግሥት እኔ የለኹበትም ብሎ እጁን ሊታጠብ የሚችልበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም። የአንድ መንግሥት ተግባር ሕዝቡን እና ንብረቱን መጠበቅ እንደመሆኑ ሕዝቡ በቀማኞች በጠራራ ፀሐይ እየተመዘበረ በሕዝብ ታክስ የሚተዳደረው ፖሊስ እና መንግሥት ምንም የማያደርግ ከሆነ ዞሮ ዞሮ ከተጠያቂነት የሚድን አይሆንም።
ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች ለመጥቀስ እንደተሞከረው “ሃይማኖት እና መንግሥት” የተለያዩ ናቸው ቢባልም ቤተ ክርስቲያናችን አሁንም በምሉዕነት ነጻነቷን አግኝታለች ብለን ለመናገር አንደፍርም። በአገር ውስጥ “ተራራውን ባንቀጠቀጠው ትውልድ” ከአገር ውጪ ደግሞ በ“ያ-ትውልድ” እና በመሰሎቹ ተጠፍንጋ ተይዛለች። በአንድ ወቅት መጣጥፋችን እንደጠየቅነው በተለያዩ የፖለቲካ ካምፖች የተደራጃችሁ ኢትዮጵያውያን “ልጆቿ፤ እባካችሁ ለእናታችሁ ለቤተ ክርስቲያን ነጻነቷን ስጧት” ብለን እስከመጠየቅ ደርሰናል።
ኢሕአዴግ በእርግጥም ለቤተ ክርስቲያን ነጻነቷን መልሶላት ከሆነ በኢሕአዴግ ፓርቲ አባልነታቸው እና በካድሬነታቸው እየተመኩ ንብረቷን የሚዘርፉትን “ሃይ” ሊልላት ይገባል። ምእመናንንም አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ፖሊስ እና ፍርድ ቤት መልስ ሊሰጡ ይገባል። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ አቤቱታቸውን ለማሰማት ወደ አዲስ አበባ ይመጡ የነበሩ የሐዋሳ ምእመናን ቃሊቲ ላይ በፖሊስ ታግተው እንግልት ደርሶባቸዋል። ወደ ቅ/ሲኖዶስ እንዳይደርሱም ተደርጓል። ይህንን ያስደረጉት ደግሞ የኦህዴድ/ ኢሕአዴግ አባል የሆኑት ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ መሆናቸውን ማወቃችን አቶ ስብሐት “መንግሥት ተጠያቂ አይደለም” የሚሉትን ድጋሚ እንዲመለከቱት እንድናስታውሳቸው ያደርገናል።
በመስከረም 2002 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተጠራ እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተገኙበት ስብሰባ እንዲካሄድ ያደረጉት እና አሁንም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ከፍተኛ የሃይማኖት ሙስና (ኑፋቄ) በማስፋፋት ላይ የሚገኙት አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል “የኢሕአዴግ አባል” መሆናቸውን በይፋ በመናገር እና በማስፋራራት ለመጠቀማቸውስ ምን ትርጉም ሊሰጠው ይሆን? 
ሌላው ቀርቶ ለኦርቶደክሳውያን የመወያያ እና ሐሳብ መለዋወጫ መድረክ የሆነችውን ይህቺን የጡመራ መድረክ ለአንባብያን እንዳትደርስ ያደረገው ማን ነው ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። በመንግሥት ቴክኖሎጂ ሐሳባችን እንዳይሰማ ሊያፍነን የሚሞክረው አካል ይህንን ወንጀል ሲፈጽም በእርግጥ መንግሥት አያውቅም ለማለት ይቻላል? ታዲያ የቤተ ክህነቱ ብልሹነት መፍትሔ እንዳያገኝ እየተዋጋን ያለው ማን ነው ማለት ነው?
አቶ ስብሐት ነጋ በጽሑፋቸው ያለምንም ርኅራኄ የሰላ ትችታቸውን ያወረዱባቸው ጳጳሳቱን ነው። በዚህ የሰላ ትችት ብዙ ሰዎች ላይስማሙ ይችላሉ። ይህንንም ከአንባብያን ያገኘናቸው መልሶች ምስክሮች ናቸው። ነገር ግን ተቃዋሚዎቹ የአቶ ስብሐትን ሐሳብ ያልደገፉት በመሠረታዊ ሐሳቡ የአቶ ስብሐትን አስተያየት “ሐሰት ነው” ወይም “አይ፤ ጳጳሳቱ እርሶ እንደገለጿቸው አይደሉም” ከሚል አመክንዮ ሳይሆን “አቶ ስብሐት ምን አገባቸው?” በሚል ነው።
በእኛ አስተያየት አቶ ስብሐት (“ፖለቲከኛም ቢሆኑ”) ቢያንስ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በመሆናቸው ስለ ሃይማኖታቸው ያገባቸዋል ብለን እናምናለን። ነገር ግን እንደማንኛችንም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች አንድ ድምጽና ሐሳብ ቢኖራቸው ችግር የለበትም። እርሳቸውም እንዳሉት ደግሞ ስለ ቤተ ክህነት እንደዚህ መሆን “አማኙ ሐቁን የመስማት መብት” አለው። እርሳቸውንም ጨምሮ።
በተለያዩ ጊዜያት እንደገለጽነው፣ ቤተ ክርስቲያናችን የገጠማትን ችግር በተመለከተ ምእመናን የማወቅ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ስላለባቸው እነዚህን ዜናዎች፣ ሐተታዎች እና ርዕሰ አንቀጾች ማቅረባችንን ቀጥለናል። ይሁን እንጂ አሁን በዓይናችን ፊት እየተደረገ ያለው ነገር ብዙ ሰዎችን በቀቢጸ ተስፋ ከእምነት ሊያናውጽ የሚችል ነገር ሊሆን እንደሚችልም ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ “ደካሞችን” በቃለ እግዚአብሔር እያጽናኑ የመጣብንን ችግር ግን በእውነት እና በመንፈሳዊ ወኔ ፊት ለፊት ልንገጥመው ይገባናል። ከዚህ ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ የለንም።
አቶ ስብሐት ያነሡት ሌላውና ትልቅ ቁምነገር ማኅበረ ቅዱሳን  ነው። ስለዚህ ማኅበር ማንሣታቸው መልካም ሆኖ ሳለ ከጽሑፋቸው ጋር ምንም ባልተገጣጠመ መልኩ ዱብ ያደረጉበት መንገድ ይገርማል። እርሳቸው መልስ የሰጡትም የፍትሕ ጋዜጣ ፀሐፊ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን  አላነሣም። ታዲያ እርሳቸው ለምን ለማንሣት ወደዱ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። የተናገሩት ሲጠቃለል ማኅበሩየቤተ ክህነት ዕዳ ነው፤ የቤተ ክህነት አስተዳደራዊ ብልሽት ያውቃል ነገር ግን ዝም ይላል፣ ብልሽቱ እንዲስተካከል አይሠራም፣ የሚሠሩትን ያደናቅፋል፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ መድረክ ነው”  የሚሉት ሐሳቦች ዋነኞቹ ናቸው።
በመጀመሪያ ደረጃ ማኅበረ ቅዱሳን በጠቅላላው ከተመለከትነው ለቤተ ክርስቲያኒቱ፣ በአስተዳደር ደረጃ ጠበብ አድርገን ካየነው ደግሞ ለቤተ ክህነቱ “ትልቅ ሀብት” (asset) እንጂ “ዕዳ” (liability) ሊሆን አይችልም።  በጭራሽ። ይህንን ደግሞ ከፓትርያርኩ ጀምሮ ብዙዎቹ የቤተ ክህነቱ ሰዎች አልተረዱትም፣ አቦይ ስብሐትም አልተረዱትም። እንዳለመታደል ሆኖ በታዳጊ አገር እና ባልሰለጠነ አእምሮ መካከል መገኘታችን ካልሆነ በስተቀር ለ19 ዓመታት መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎትን በቅንነት የሰጠ ተቋም “ዕዳ” ሊሆን ነው ሊባል አይገባውም ነበር። በሁሉም መስክ ብናነጻጽረው፣ በአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጪ ካሉ ኢትዮጵያዊ-መንግሥታዊ-ያልሆኑ ተቋማት እንደ ማኅበረ ቅዱሳን  ዓላማውን ዝንፍ ሳያደርግ እና የተከታዮቹን እምነት ሳያጎድል የዘለቀ የለም ማለት ይቻላል። ስንቱ ተደራጀ፣ ስንቱ ፈረሰ? ስንቱ ገንዘብ ሰበሰበ፣ ስንቱ ዘረፈ? ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ በኩል ንጽሕናውን እንደጠበቀ የዘለቀ ከመሆኑ አንጻር በቤተ ክህነቱ ብቻ ሳይሆን በቤተ መንግሥቱም ሊመሰገን ይገባው ነበር።
በእርግጥ “ዕዳ” ነው ከተባለ ዕዳነቱ በቤተ ክህነቱ ሙስና ለተጨማለቁ ሰዎች ነው። ይህ ደግሞ የዚህ ብልሹነት ፊት-አውራሪ ከሆኑት ፓትርያርክ ይጀምራል። የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕንጻዎች እንደ ግል ንብረታቸው የሚጫወቱበትን እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነን እና ተከታዮቻቸውን፣ በዚህ ውዥንብር መካከል በተሳሳተ ትምህርት የአማኙን ገንዘቡን ብቻ ሳይሆን ነፍሱንም ሊዘርፉት የተዘጋጁትን እነ አባ ሰረቀን፣ እነ በጋሻውን እና ጓደኞቻቸውን ያጠቃልላል።  
ማኅበረ ቅዱሳን  የቤተ ክህነቱን ብልሹነት ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ጽሑፎቹ፣ ተግባሮቹ እና አገልግሎቶቹ ይመሰክራሉ። ነገር ግን ችግር አፈታት ላይ ከብዙዎቹ የተለየ አካሔድ እንደነበረው የ19 ዓመት አገልግሎቱ ምስክር ነው። የቤተ ክህነቱ ችግር የሚፈታው “በአብዮት ሳይሆን በአዝጋሚ ለውጥ” (By Evolution, not by Revolution) የሚል ይመስላል። ይህም ቢሆን ግን “ፀረ ለውጥ፣ ፀረ መሻሻል” ሊያስብለው አይገባም ባይ ነን። ጭራሹኑ “መሻሻል የማይፈልግ” ተደርጎ የቀረበው ሐሳብ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን (ማኅበረ ቅዱሳን ን እንደዚህ ማለቱ) በእውነቱ “It is not fair”!!!!
“የተቃዋሚ ፖለቲካ መድረክ” የሚለውንም ለመቀበል ያስቸግራል። በዚህ የሚጠረጠር ብቻ ሳይሆን በእርግጥም ማስረጃ የሚገኝበት ቢሆን ኖሮ እስካሁን የቀን ፀሐይ ለማየት ይበቃ ነበር ብሎ ለመገመት አይቻልም። በዚህ በኩል ኢሕአዴግ የማያወላዳ መሆኑን እናውቃለን። ኢሕአዴግ፣ እንኳን በተቃዋሚ ዋሻነት እና መድረክነት የሚያገለግልን፣ ይሆናል ተብሎ ፍንጭ የተገኘበትን ከዋለበት የማያሳድር፣ ካደረበት የማያውል መሆኑን እናውቃለን።
መስፍን ነጋሽ የተባሉ ፀሐፊ እንዳሉት (Claim እንዳደረጉት) በ1997 ዓ.ም (2005) ምርጫ ማግስት የነበረው ግምገማ ማኅበረ ቅዱሳን ን በጠላትነት ያስፈረጀው ከነበረም ማስረጃዎቹ እስካሁን ሊሰወሩ አይችሉም ነበር። እውነቱ ግን ማኅበረ ቅዱሳን  የፖለቲካ ያለው ፍላጎት የሞተ መሆኑ ነው። ለዚህም ማስረጃው አንድ ግልጽ አመክንዮ እና ሎጂክ ነው።
የማኅበረ ቅዱሳን  አባላት ተረ ጀሌዎች (footsoldiers) ሳይሆኑ ማገናዘብ የሚችሉ ናቸው። አመራሩ የሚጭንባቸውን ብቻ በቀላሉ ተቀብለው የሚሔዱም አይደለም። በተለይም ከሃይማኖት ውጪ ባሉ ጉዳዮች ላይ የራሳቸው አመለካከት እና አስተሳሰብ ይኖራቸዋል። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ እንደየማንነታቸው የተለያየ ነው። ስለዚህ ማኅበሩን እና አባላቱን አንድ ያደረጋቸው የሃይማኖታቸው ጉዳይ እንጂ በዘር እና በቋንቋ፣ በፖለቲካ አስተሳሰብ እና አስተያየት ፍፁም የተለያዩ መሆናቸውን ለመገመት ምሁር መሆን አይጠይቅም። በፖለቲካ ጉዳይ አሐዳዊ አስተያየት እና አስተሳሰብ መጠበቅ ከባድ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን  የቃዋሚዎች መድረክ ለመሆን አደረጃጀቱ አይፈቅድለትም የምንለውን ያህል የኢሕአዴግም መድረክ ለመሆን አይመችም ማለታችን ነው።
በእርግጥ የማኅበረ ቅዱሳን  ዋና ፀሐፊ በቅርቡ ለ“ዕንቁ” መጽሔት በሰጠው እና እኛም በስፋት ባስነበብነውቃለ ምልልስ አባላቱ “በአብዛኛው የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው” ያለበት “Claim” እጅ እግር የሌለው ግምት የሚሆነውም በዚህ መነሻ ስንመለከተው ነው። ነገር ግን የኢሕአዴግ አባላት የሆኑ ሰዎች የማኅበረ ቅዱሳን  አባላት ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መሆኑ እርግጥ ነው። የፓርቲው አባላት ቢሆኑም የፓርቲያቸውን አጀንዳ እና ዕቅድ ወደ ማኅበሩ ይዘው ይመጣሉ ማለት አይደለም። ቢያመጡም የሚቀበላቸው አይኖርም። አባላቱ ጀሌዎች (foot-soldiers) አይደሉም ያልነውም ለዚህ ነው። አቶ ስብሐት ይህ አልጠፋቸውም።
ነገር ግን ማኅበሩ “በሕገ መንግሥት ጥሰት” የመከሰስ ትልቅ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል “ጠቆም” በማድረግ አባላቱ “ሰጥ ለጥ ብለው” እንዲኖሩ፣ አመራሩም “ነጻ መሆናችንን ኑና ማረጋገጫ ስጡን” እንዲል በር ለመክፈት የተደረገ በር ማንኳኳት ይመስላል። እንዳሉትም ተሳክቶላቸው ከሆነ አመራሩ አቦይ ስብሐትን ለማነጋገር ሄዷል ተብሏል። መሔዱ ብቻ ግን “ተንበርካኪ” አሰኝቶ ሊያስወግዘው የሚገባ አይመስለንም። ችግሩ “የተቃዋሚዎች መድረክ አለመሆኑን ለማሳየት የኢሕአዴግ መድረክ ለመሆን ከፈቀደ” ነው። በርግጥም አቦይ ስብሐት ማኅበረ ቅዱሳን ወደዚህ ዓይነቱ የተንበርካኪነት ደረጃ እንዲወርድ የሚያስገድዱት ከሆነ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል እየፈጸሙ ነው ለማለት እንደፍራለን። ለቤተ ክርስቲያኒቱም፣ ለአገሪቱም ሲሉ ያንን ከማድረግ ይቆጠባሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

No comments: