Thursday, August 4, 2011

ማኅበረ ቅዱሳን በአባ ሰረቀ ብርሃን የክስ ሂደት ላይ መግለጫ ሰጠ

ማኅበሩ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል በስም ማጥፋት ወንጀል መክሰሱን ይታወሳል:: የክሱ ሂደት በፍርድ ቤት እየታየ ባለበት ሁኔታ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጻፉት ደብዳቤ መነሻነት የፍትሕህ ሚኒስቴር ክሱ እንዲቋረጥ አድርጓል:: ይህንን አስመልክቶ ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል::

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

በማኅበረ ቅዱሳን ማመልከቻ አቃቤ ሕግ በአባ ሠረቀ ብርሃን ወልደሳሙኤል ላይ አቅርቦ የነበረው የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የተቋረጠበት ሂደት አስመልክቶ ከማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ፦

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ባለፉት 19 አመታት በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ተዋቅሮ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በእነዚህ ዘመናትም ቀላል የማይባሉ መልካም አስተዋጽኦዎችን ለቤተ ክርስቲያን አበርክቷል። አሁንም እያበረከተ ይገኛል። ማኅበሩ በየሁለት ዓመቱ ዕቅዱን ለመምሪያው የሚያቀርብ ሲሆን ሪፖርቶችንም በየስድስት ወሩ ያቀርባል። ከመምሪያው ኃላፊዎች ጋርም በመልካም ስምምነት ሲሠራ ቆይቷል።


ይህ መልካም ግንኙነት ላለፉት ስድስት ዓመታት በአባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ምክንያት ችግር ላይ ወድቆ የቆየ ሲሆን፥ ማኅበሩ የገጠመውን ችግር በየጊዜው ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሲያቀርብ ቆይቷል። በተለይም በዚህ ዓመት በግንቦት ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ ሦስት ሊቃነ-ጳጳሳትና አራት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የተሰየሙበት አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

ይህ አጣሪ ኮሚቴ በተቋቋመ በሦስተኛው ቀን ሚያዝያ 23 ቀን 2003 ዓ.ም አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃንን ጠርተው የማኅበሩን ስም በይፋ አጠፉ። ይህ ድርጊት ከመፈጸሙ በፊት ማኅበሩ መረጃው የደረሰው በመሆኑ ግለሰቡ ከዚህ አድራጎታቸው እንዲቆጠቡ እንዲደረግ ለሚመለከታቸው አካላት አመልክቷል። ጥፋት አለ የሚሉ ከሆነ ለተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ እንዲያቀርቡ ጠይቋል። ሆኖም ግን ማንም ምላሽ አልሰጠም። እርሳቸውም በድርጊታቸው ገፉበት።

በዚህም ምክንያት ማኅበሩ በቤቱ ያጣውን ፍትሕ ፍለጋ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዞት ሄደ። ወንጀል መፈጸሙን በማመን አቃቤ ሕግ ክሱን አቀረበ። አባ ሠረቀ ብርሃንም ጠበቃቸውን ይዘው ለሦስት ጊዜያት ፍ/ቤት ቀረቡ፤ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችና የሰው ምስክሮች ተሰምተው የጥፋተኝነት ብይን ተሰጠና እንዲከላከሉ ታዘዙ።

ሆኖም ግን ለመከላከል በተያዘው ቀጠሮ በቅዱስ ፓትርያርኩ ጠያቂነት በፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ትእዛዝ ክሱ ተቋርጦ ፋይሉ ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዲላክ ተወሰነ። ይህ ማለት በማደራጃ መምሪያው መካነ ድር ላይ እንደተዘገበው ክሱ ተዘግቷል ሳይሆን ተገቢው ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል።

ማኅበሩም አቤቱታውን ለፍትሕ ሚኒስቴር አቅርቧል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ እንደሚያገኝ ተስፋ ያደርጋል።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አገራችንን ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን አሜን።

                                                                     ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments: