Monday, August 15, 2011

"ይቅርታ" ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት

በማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አመራር ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በገባው ቃል መሠረት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “ዕንቁ” ለተሰኘው መጽሔት በጻፈው መልዕክት “እንግዲህ በአብራከ ሕሊናዬ ተንበርክኬ ይቅርታ እጠይቃለሁ” በማለት ይቅርታ ጠይቋዋል:: ዕንቁ መጽሔት ላይ የቀረበው የይቅርታ መልዕክት የሚከተለውን ፒዲፍ በመጫን ያንብቡ:: READ IN PDF

ይኅንን ይቅርታ አስመልክቶ ቀሲስ ወንድምስሻ አየለ በፌስ ቡክ ላይ ያስቀመጡትን የግል አስተያየታቸው እንደሚከተለው ቀርቦዋል::
+++
መንግሥተ ሰማያት ገብቼ ተመለስኩ!
ዕለቱ እሑድ ነሐሴ ፰ ከጠዋቱ ፭ ሰዓት ነው። የቤተክርስቲያን የፍልሰታው የመጨረሻ ሰንበት የአምልኮ ሥርዓት ተፈጽሞ ብዙው ወደ ቤቱ ገብቷል፤ በቤተክርስቲያን ግቢ መዘግየት ደስ የሚላቸው ወዳጆቿ ደግሞ የፍልሰታን በረከት እያጣጣሙ ገና እየተመለሱ ነው፤ ይህ በራሱ ደስ ያሰኛል። ቋንቋው አይገባንም የማይሉት ሰዓታትና በየዓመቱ የሚናፈቀው ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ተደምጦ አይጠገብም፤ ከሥጋ ድካም ጋር እየታገሉ ብቻ ለዘመናት የሚበቃውን ስንቅ ማከማቸት ነው። እኔ ደግሞ ቅዳሜ የታተመችውን ዕንቁ መጽሔት በማየቴ ለመግዛትና ይዘቷን ለማየት ጓግቻለሁ፤ ሰሞኑን የኤሌክትሮኒኩና ፕሪንት ሚዲያውን ሳስስ የቆየሁበትን አጀንዳ ይዛ ተገኝታለችና። ምን ላድርግ የራሷ ሚዲያ የሌላት ግን «ታላቅ» የሚያስብሏት ታሪክ፣ ሕዝብ፣ ሀብት፣ ቅርስ፣ ጥበባት፣ ወዘተ ያላትን የቤታችንን ጉዳይ ለራሳቸው ሴኩላር ዓላማ ከተቋቋሙ ምንጮች ነውና የምናገኘው፤ ቢያምርም፣ ቢመርም ለጊዜው ግድ ነው።

በአጭርና ግልጽ አነጋገር «ይቅርታ» ይላል ትልቅ ርእስ ከሥሩ ደግሞ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስሙና ፎቶው ተቀምጧል። በነገራችን ላይ ስምና ፎቶ ስለወጣ ሁሌ ትክክል ተዘግቧል ማለት አይደለም። ከሁለት እትም በፊት የነበረው ቅጽ ላይ መምህር ሙሉጌታ ኃ/ ማርያም የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ አላግባብ የተቆነጻጸሉና በድፍን ስሕተት ቃል የተጻፉ እንደነበረ የዲያቆን ዳንኤልን ጉዳይ ስንመረምር አጣርተናል። ስለ ሕገ መንግሥት፣ ስለ ሰ/ት/ቤትና ስለ ዲያቆን ዳንኤል የገለጠው ሀሳብ በቂ ግልጥነት ባለው ሁኔታ እና ከተጻፈው ፍጹም በተለየ ሁኔታ እንደነበረና መጽሔቱ ይቅርታ ካልጠየቀበት ራሱን እንደሚያስጠይቀው ተረድተናል።

በሰው ፊት የተከበረና የታወቀ መምህርና ወንድም የልብም ሰው ያልነው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እርሱ ወደፊት በሚያብራራው ምክንያት /ላያስፈልግ ይችላል/ በወጣበት ሁኔታና ጊዜ ሳይጠይቅና ሳይልክ ደጀሰላም ብሎግ ላይ የወጣው የምክክር ጥያቄ፣ ሀሳቡን ላልታሰበ ዓላማ ያዋሉበት ሁኔታ ምክንያት ሆኖ ሐምሌ ፴ በተደረገው ውይይት በማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ ፊት ተንበርክኮ፣  በሆነው ነገር፣ በውጤቱም የሚወዳቸውና የሚወዱት፣ የከተማና የሩቁ የገጠር ወንድምና እኅቶቹ ሀሳባቸው ልቡን ወግቶት እያለቀሰ፣ ይ ቅርታ አድርጉልኝ እባካችሁ አለ። ለብዙዎቻችን ባለ ክፉ ልቦች - ቀድሞ ይህን ማሰብ አቃተው? ለምን አይጠነቀቅም ነበረ? አሁንስ ማን ያምነዋል? ብለን የየራሳችንን መላምት ፈጥረን ነበረ። ግና ነገሩ እውነት ነው። ስላዘኑ ላለቀሱት ወዳጆቹ፣ እያለቀሱ ዕርቅን ለተማጸኑት ክቡሮቹ የተከበረ ነውና በቃሉ አከበራቸው፤ በአደባባይም በዕንቁ መጽሔት ደገመው። ለምን ተሳሳተ ማለት በራሱ ስሕተትና ተፈጥሮን መዘንጋት ሲሆን በአደባባይ ተሳስቻለሁ ብሎ የሚዲያን አቅምና መረጃነት ጠንቅቆ መተግበር ደግሞ ዐዋቂነትን ለእውነትና ለሚበልጥ ጥቅም አለመሰሰት ነው። «...ለዚህ መቶ በመቶ ተጠያቂ ነኝና በአብራከ ኅሊናዬ ተንበርክኬ ይቅርታ እጠይቃለሁ።»  ድንቅ አባባል። አንብቤ እስክጨርስ ድረስ በየዐረፍተነገሩ ያለባብሰው ይሆን? እያልኩ እየፈራሁ ሳነብ በግልጥ ቋንቋ የልቡን ተንፍሶ አሳረፈን/ አሳፈረን።

የቀጠርኩት ሰው መዘግየቱን ያወቅሁት ደስታዬ ገደብ ጥሶ በቆምኩበት መንገድ ዳር እንባ ሲተናነቀኝ ያየኝን ለማየት ስገላመጥ ነው። በወንጌሉ «መንግሥተ ሰማያት በመካከላችሁ ነች»  የተባለው እንደዚህ ባለ የፍቅር ሕይወት መመላለስን ይሆን? የፍቅርን/ዕርቅን ጣዕሙንም በመጠኑ የቀመስኩት መስሎኝ ጣዕሙ ከልቤ አልጠፋ ስላለኝ ሌላ መንግሥተ ሰማያት ባትኖር እንኳ ለእኔ ይህ ፍቅርና ትሕትና በቃኝ፤ የምናፍቃት መንግሥተ ሰማያት ለሰዓታትም ቢሆን ገብቻለሁና፤ የምትበልጠዋ ገና አለች እንጂ። ቃለ ሕይወት ያሰማልን ዳኒ። አምላከ ቅዱሳን በሕይወትህ ሁሉ ይጠብቅህ። አዛኝቷ እናትህ በአማላጅነቷ አትለይህ። ይህን የመንግሥተ ሰማያት ደጅ ያዘጋጃችሁ፣ የተራዳችሁ ፈጣሪ ዋጋችሁን ይክፈላችሁ፤ በጎውን ሁሉ ያድርግላችሁ።

ዋይ! ተሐድሶ!  ዕርቁስ ምን ተብሎ ይተረጎም ይሆን? ተመለሱ! ኑና መንግሥተ ሰማያት ግቡ።
 

5 comments:

Anonymous said...

Thanks Dani!

Anonymous said...

Thanks for sharing. It is a great lesson.

Anonymous said...

እንዲህ ነው ክርስትና። የተግባር ሰው ሆኖ መገኘት። እግዚአብሕር አብዝቶ በረከቱን ያትረፍርፍላችሁ። ቅድስተ ቅዱሳን አትለችሁ

T... said...

እግዚአህሄር ይስጥልን:: ድንግል ማርያም ትጠብቅልን:: ወንድማችን ዳንኤል አሁን በጣም ደስ ብሎናል።

Anonymous said...

ማሀበረ ቅዱሳኖች በአባቶች መካከል እየገባችሁ መከፋፈልና አባቶቻችሁን ሰድባችሁ ለሰዳቢ በመስጠት እንደ ካም በአባቶቻችሁ እርቃን ስትሳለቁ ውድ የብዙ አባቶችንና የምእመናንን ልብ ስትሰብሩ ቆይታችሗል ።
የሃጢአታችሁና የእብሪታችሁ ብዛትም ከጣሪያ በላይ ስለሆነ የብዙ አበቶችን ዕንባ ስላፈሰሳችሁ በመካከላችሁ ሃይለኛ መከፋፈል ተፈጥሮ ድንብራችሁ ወጣ ። አሁንም ካልታገሳችሁና በዚሁ ክፋታችሁና ትእቢታችሁ ከቀጠላችሁ ፡ እግዚአብሔር ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ እንደሚሰጣችሁና የተወሰነ ቁጥር ባላችሁ እበሪተኞች ሃጢትና ዓመጻ ፡ የብዙ የዋሃንን ሕይወት የታደገ ማሀበር ጭራሹኑ ሊጠፋ ሁሉ ይችላል ፡
በብር ብዛትና በአለማዊ የፍልስፍና ትምሕርት በመመካት ብቻ ብትደገፉ እግዚአብሔር ሃይሉን ከእናንተ ስለሚያርቅ እርስ በርስ ተባልታችሁ ታልቃላችሁ ።
ስለዚህ ባለፉት ሳምንታት በመካከላችሁ የተነሳው የፈተና እሳት ትምሕርት ሊሰጣችሁና ወደ ውስጣችሁ ተመልክታችሁ ንስሐ ልትገቡበት ይገባችሗል ።
ይህች ፈተና የመጨረሻዋ የደወላችሁ ጥሪ ናት ፡ ከተጠቀማችሁባት ትጠቅማችሗለች ፡ ካመለጠቻችሁ ግን ትጠፉባታላችሁ ።