Sunday, September 11, 2011

አድናቂ እንጂ መካሪ ለሌላቸው የወንጌል መምህራን የተላከ መልዕክት

የሚከተለውን ጽሑፍ የዚህ ጡመራ መድረክ ተከታታይ ከሆኑ ግለሰብ የደረሰን ነው::  መልዕክቱም አድናቂ እንጂ መካሪ ለሌላቸው አንዳድ አስበውበትም ይሁን ሳያስቡበት በፖለቲካው ለተዘፈቁት የወንጌን መምህራንን ይመለከታል:: መልካም ንባብ::
+++
ለእኛ የማናውቀውን ንገሩን ለእናንተም የሚያምርባችሁን ልበሱ!
በላፈው ዓመት ከእናንተ ብዙ ተምረናል። በሃይማኖት እና ማሕበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ ቁም ነገሮችን ቀስመናል። ቃለ ሕይወት ያሰማልን። ታዲያ ውጤቱን ሁላችንም በሕይወታችን የምናየው ቢሆንም፤ ዓመት መጨረሻ ላይ ስለትምህርት አሰጣጡ ሁኔታ ተማሪዎች በተራቸው አስተማሪዎቻቸውን የሚገመግሙበት አሰራር ደግሞ አለ። ይህ አሰራር ሀገራችን ውስጥ በመጠኑ ቢሰራበትም፤ በሰለጠነው ዓለም ግን በስፋት ይጠቀሙበታል። ዓላማውም ስህተቶችን አርሞ መጪውን የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤታማ ለማድረግ ብቻ ነው። በዚሁ መሠረት እኔም ከተማሪዎቹ አንዱ ስለነበርኩ ፤ ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀልኝ ፎርም ባይኖርም ራሴ ባመቸኝ መልኩ መስተካከል አለበት የምለውን  እነሆ!

እናንተ አስተማሪ የምትባሉት ተማሪዎቻችሁ የማያውቁትን ስለምትናገሩ እንጂ የሚያውቁትን ስለምትደጋግሙ አይደለም። አስተማሪነታችሁም በሁሉም ዘርፍ ሳይሆን እኛ በምናውቀው እና አስተማሪዎቻችን አድርገን በተቀበልናችሁ ትምህርተ ሃይማኖትን በተመለከተ ብቻ ነው። ይህ ሲሆን እኛም በተማሪነታችን እናንተም በአስተማሪነታችሁ ቦታ ቦታችንን እንደያዝን የመማር ማስተማሩ ሂደት ይቀጥላል። አስተማሪ ሆናችሁ የምትቀጥሉት እኛ አስተማሪዎች ብለን ስለተቀበልናችሁ ብቻ እንጂ ለአስተማሪነት የሚያበቃ ዲፕሎማ ወይም ዲግሪ ስላላችሁ አለመሆኑን አስተውሉ…..በአዲሱ ዓመት!


በእርግጥ ድፍረቱ ካላችሁ ስለፖለቲካውም ያለውን እውነታ በጨዋ አነጋገር ሊያንጸን በሚችል እና መፍትሔ ሊጠቁም በሚችል መልኩ ብታወሱልን ይበል የሚያሳያን ነው።  ይሁንና በፖለቲካው ዘርፍ እናንተ ከምታውቁት በተሻለ ለሚያውቁት ተማሪዎቻችሁ የምትናገሩትን በጥንቃቄ ልታስቡበት ይገባል። ከፖለቲካው ጋር ያሉትን እውነታዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎቻችሁ ያውቁታል። ዕውቀታቸው የመነጨው ደግሞ ከማንበብ ወይም የተለየ ስልጠና በማግኘት አይደለም፤ በኑሮአቸው እንጂ።

ተማሪዎቻችሁ ፖለቲካውን ያወቁት በግፍ አገዛዝ ቤተሰባቸውን በሞት በማጣት፣ በመቁሰል፣ የደከሙበትን ንብረታቸውን በመነጠቅ፣ ካላ በደላቸው በጨለማ እስር ቤት በመወርወር፣ በዘረኝነት መብታቸውን በመገፈፍ፣ በሀገራቸው እንደዜጋ ባለመቆጠር፣ በባህር በየብስ እየተሰደዱ፣ የአውሬ ሲሳይ በመሆን፣የአረብ ሀገር ጨካኞችን ግፍ ለመሸከም በመገደድ ነው። እንግዲህ ፖለቲካን በቲዎሪ ሳይሆን ህሊናን እና አካልን በሚያሰቃይ ተግባር ለተማሩት ተማሪዎቻችሁ ቢያንስ እውነታውን በማንጸባረቅ ብትናገሩ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ( voice for the voiceless) በመሆን በጎ ሚና መጫወት ትችላላችሁ። ከዚህ ወጣ ሲል ግን በቁስላቸው ላይ ጨው መነስነስ ይሆናል። እውነትን እንማር ብለው አስተማሪዎቻቸውን አክብረው የተሰበሰቡ ተማሪዎችን ማሳዘንም አይገባም……በአዲሱ ዓመት!

እኛ የግድ ስላለው መንግስት ግፈኝነት ተናገሩልን ወይም ስለ ተቃዋሚዎች ቅድስና አውሩልን አላልንም። እንናገር ካላችሁ ግን እናንተ በቃላት ከምታውቁት እኛ በኑሮ የምናውቀው ስለሚሻል እውነታውን ያለማደብዘዝ ስለማንጸባረቃችህ እርግጠኛ ሁኑ። እኛ  በትምህርት ትበልጡናላችሁ አልን እንጂ መች በፖለቲካው አልን? ታዲያ እኛ ከእናንተ ምን የምንማረው ነገር ይኖራል? መማር ማለት እኮ እውነትን መረዳት እንጂ ሀሰትን መስማት አይደለም። እውነታውም ቢሆን ሚዛኑን እና ቅደም ተከተሉን የጠበቀ መሆን አለበት፤ የገደለውን ትቶ የሟችን ቤተሰቦች አለቃቀስ ላይ ትችት መሰንዘር፣ ልብስ የዘረፈውን ትቶ ልብስ ያሰጣውን መገምገም፣ አሳዳጁን ትቶ ስደተኛውን ለምን ሮጥክ ብሎ መኮነን፣ ዝሆኑን ትቶ ሳሩን ለምን ተበታተንክ ብሎ መውቀስ፣ ትምህርት ቤቱን ያፈርሳል እንጂ ገንቢ ውጤት የለውም። የፈረሰውን ትምህርት ቤት መልሶ መሥራት ደግሞ የበለጠ አዳጋች ነው።

ድፍረቱ ካላችሁ የትምህርተ ሃይማኖት አስተማሪነታችሁ ሳይናጋ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ፣እነደ አቡነ ሚካኤል እውነታውን ተጋፈጡት። ይህ ሳይሆን ፍርሃት ካደረባችሁ ደግሞ እንደ ሐዋርያት በመንፍስ ተሞልታችሁ ፍርሃታችሁን እስክታስወግዱ ድረስ  ከፖለቲካው ሸሸት ብላችሁ የሚያምርብችሁን፤ የሃይማኖት መምህርነታችሁን ካባ ብቻ ልበሱ። ፖለቲካ ውስጥ ሳትገቡ (politically neutral) በመሆን አንድ ስለሚያደርጉን ነገሮች ብታሳስቡን፣ በጎነትን ብታስተምሩን፣ መተዛዘንን ብትሰብኩልን፣  ወደፊት ይከሰታሉ ብለን የምንፈራቸው ነገሮች እንዳይከሰቱ በማድረግ ወይም ቢከሰቱም ጉዳታቸው ከመጠን ያለፈ እንዳይሆን አዎንታዊ ተጽዕኖ ማሳደር ትችላላችሁ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ለእኛ የማናውቀውን እውንታ ብቻ ስትነግሩን፤ ለእናንተም የሚያምርባችሁን ብቻ ስትለብሱ ነው። ያን ጊዜ ትምህርት ቤታችን ንጹህ የዕውቀት ምንጭ ይሆናል።
መልካም አዲስ ዓመት

2 comments:

ሕሊና said...

ጆሮ ያለዉ ይስማ! ሰባኪዎቹ ቀን የሚያዩዋት ፀሐይ አመሻሹ ላይ የማትጠልቅ መስሏቸዋል

Matewos said...

Lante, kalhiwoten yasemalen mengist semayaten yawerslen Lensu, Weladite amlak libona testelen! Amen