Tuesday, October 11, 2011

“በቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ዝም አንልም” (መግለጫ)

በዓለ ወልድ ማኅበር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ባሉ የቅዱስ ሲኖዶስ ተወካዮች ሊቃነ ጳጳሳት ባጸደቁት ሕግና ደንብ የሚመራራ ማኅበር ነው::  በወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ እንደማንኛውም የተዋሕዶ ልጆች እለት ከእለት የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ግድ ይለናል፣ ያስለቅሰናል፣ ያሳዝነናል ስለሆነም ዛሬ የማኅበሩ አመራር ተነጋግሮ ይህንን የአቋም መግለጫ አውጥተናል:: መግለጫውም በመላው ዓለም ለሚገኝ የተዋሕዶ ልጆች በሙሉ እንዲሁም
በተለያዩ አሕጉረ ስብከት ለሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት በየሀገረ ስብከታቸው ለመንበረ ፓትሪያሪክ፣ ለተለያዩ ማኅበራት፣ በአጠቃላይ ለመላው የተዋሕዶ ልጆች በሙሉ እንዲያውቁት የእናንተንም ትብብራችሁን እንጠይቃለን።    መስከረም ፳፱ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ማኀበረ በዓለ ወልድ
ወቅታዊ የቤተክርስቲያንን ችግር መነሻ በማድረግ የተሰጠ መግለጫ

“ በቤተክርስቲያናችን ጉዳይ ዝም ማለት አንችልም ”


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊት እንደመሆኗ መጠን የሰው ልጆች ዘላለማዊ ሕይወት የሚያገኙበትን ቅዱስ ወንጌል በማስተማር ሁለት ሺህ ዓመታትን አሳልፋለች ። በእነዚህ ዓመታት ታማኝ አገልጋዮቿ በከፈሉት መስዋዕትነት እምነቷ ሥርዓቷ እና ትውፊቷ ተጠብቆ  ለእኛ መድረስ ችሏል ። ለእኛ የደረሰውን ይህንን የሃይማኖት አደራ  ከሁሉም በላይ አስበልጠንና ከሁሉም በፊት አስቀድመን  ጠብቀንና አስጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ  ማስረከብ  የሁላችንም  መንፈሳዊ ግዴታ ነው ። ይህንን አደራ ለመወጣት የሚያስፈልገው ፈቃደኝነት ፤ የጸና አቋምና ቁርጠኝነት ነው።  በዘመናችን ቤተክርስቲያን የገጠማትን ፈተናና ችግር ከተመለከትን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ተብሎ የሚጠራ ሁሉ ፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ፤  የተረከበውን ታሪክ በሚገባ የተረዳ እና  በተለይም ቤተክርስቲያንን በንቀት አይን የሚመለከቱ  ሰዎች የሚፈጽሙትን ተግባር ያስተዋለ ሁሉ ዝም ብሎ ለመቀመጥ የሚያስችለው ህሊና ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም።

ሁላችንም እንደምንመለከተው  ቤተክርስቲያናችን ከተለያየ አቅጣጫ  እየደረሰባት ያለውን ችግርና ፈተና እየተመለከቱ  ዝም ይላሉ  ብለው ለገመቱን፤ ለቤተክርስቲያናችን ግድ የለሽ አድርገው ለሚያስቡን ፤በቁማችን የሞትን አድርገው ለሚቆጥሩን ሁሉ የእናታችን የቤተክርስቲያን ጉዳይ እንደሚያሳስበን ፤ እንደሚያስቆጨን  በመግለጽ  ለእናታችን ለቤተክርስቲያን ታማኝ ልጆች መሆናችንን  ማረጋገጥ ጊዜው የሚጠይቀን እውነት ነው ።

አንድ ሰው በሃይማኖት ሲኖር ሁለት ነገሮች ያስፈልጉታል እነዚህም እምነትና ምስክርነት ናቸው። በቅድስት ቤተክርስቲያን ዶግማ ሥርዓትና ቀኖና  አምነን  የምንገኝ ከሆነ  መገኘታችንም ፤ መመስከራችንም ለክብር የሚያበቃን ጉዳይ እና የምንድንበት መንገድ ስለሆነ በቤተክርስቲያን ስም የጥፋት ተግባር ሲፈጸም  ዝም ማለት እንደማንችል በቃልና በተግባር መግለጹ ተገቢ ነው ። “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።” ሮሜ ፲ ፥ ፱ - ፲ ።  በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው እውነትን ይዞ መመስከር የክርስቲያን ሁሉ ግዴታ መሆኑን ለማሳወቅ ነው ።

ቤተክርስቲያናችን በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተወሳሰበ  ችግር ውስጥ ትገኛለች። በውስጥና በዉጭ የከበባት ችግር  ዘርፈ ብዙ ቢሆንም  በተለይም የተወሳሰበው የውስጥ አስተዳደራዊ ችግር ለአጽራረ ቤተክርስቲያን ጭምር መልካም አጋጣሚን በመፍጠሩ የፈለጉትን የጥፋት ተግባር ያለ ተቆጣጣሪ እንዲያከናዉኑ እድል ሰጥቷል። የቤተክርስቲያን ሕግ እንደሚያዘው ቅዱስ ሲኖዶስ የመጨረሻ የቤተክርስቲያኒቱ  ባለ ስልጣን ቢሆንም በተለያየ ጊዜ የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዳይደረጉ  በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ያሉ ኃላፊዎች በሚያደርጉት ጥረት በወረቀት ላይ ከመስፈር ያለፈ ውጤት ሊያመጣ አልቻለም ።
እንደ ምሳሌም ብናነሳ  የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከሚኖረው የገቢ መጠንና የተለያዩ ጉዳዮች በመነሳት ከቅዱስ ሲኖዶስ በተመረጡ የሊቃነ ጳጳሳት ኮሚቴ እንዲመራ ተብሎ በሕገ ቤተክርስቲያን ቢወሰንም ይህ መመሪያ ተጥሶ  የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ከመዋቅር ውጪ ለፓትርያርኩ  ተጠሪ በማድረግ የሚመደቡትንም ጳጳሳት ረዳት ጳጳስ  በማለት ከመመሪያው  ውጪ በተግባር ሲፈጸም  ይታያል ። ይህ በመሆኑና በአዲስ አበባ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከብዙ አቅጣጫ የሚያዛቸው እንዲኖርና ሥር የሰደደ የገንዘብና ንብረት ዘረፋ እንዲጋለጡ አድርጓል። ከዚህም የተነሳ ከገንዘብ ጉድለት ጋር የተገናኙ ክሶች እና ዜናዎች የምእመናን ጆሮ በየእለቱ የሚሰማው ተግባር ሆኗል።  በአዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን የተተከለው የፓትርያርኩ ሐውልት ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ውጪ በመሆኑ እንዲፈርስ ቅዱስ ሲኖዶስ ቢወስንም እስካሁን ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል።   በሕገ ወጥ ሰባኪያነ ወንጌል እና በመሰሎቻቸው የሚፈጸመው ተግባር እንዲቆም  ቅዱስ ሲኖዶስ ቢወሰንም አሁንም ግን የጥፋት ተግባራቸውን ከማከናወን ቤተክርስቲያንን እንደ ግል ንብረታቸው እየተመለከቱ የፈለጉትን ከማድረግ አልተመለሱም ። የቋሚ ሲኖዶስ በሚል ሰበብ የቅዱስ ሲኖዶስን ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ማዳከም ፤ ያለተፈቀደውንም ገንዘብ መጠቀም ፤ የሚፈልጉትን በመሾምና በመሻር የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ እና የቤተክርስቲያንን አሰተዳደር ተማምኖ የሚኖር  እውነተኛ የቤተክርስቲያን አገልጋይ  እንዳይኖር ተደርጓል ። በአጠቃላይ ቅዱስ ሲኖዶስን የመናቅ ፤ ጥቅምንና ዝርፊያን በማን አለብኝነት የመፈጸም ተግባር ሲከናወን  እያየን ነው ። ይህም ቤተክርስቲያን ለተወሰኑ ሰዎች የግል ቤት ናት ወይስ የክርስቲያኖች ሁሉ ናት  የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገደደናል ። 

በቤተክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን በደል  የተመለከቱ እና እውነትን እንመሰክራለን ብለው የሚነሱ ሊቃነ ጳጳሳትም  በስድብና በንቀት ሲንገላቱ ማየቱ የተለመደ ተግባር ሆኗል። ከዚህም የተነሳ ደሃ ሲበደል ፍርድ ሲጓደል  የሚሰማ አካል እየጠፋ  ነው ።  ቅርብ ዓመታት ወዲህ እንኳን የተፈጸመውን ብንመለከት በቤተክርስቲያን  ወስጥ የሰፈነውን ቤተሰባዊ አስተዳደር  እናስተካክላለን ብለው  ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የተነሱ ሊቃነ ጳጳሳት ሆን ተብሎ  በተቀነባበረ ተንኮል መኖሪያ ቤታቸው እስከ መሰበርና እስከ መደብደብ መድረሳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ። ይህ ሁሉ ተግባር ለቅዱስ ሲኖዶስ እነዚህ አካላት ያላቸውን ንቀት ከማመላከት ውጪ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም ። በአጠቃላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በጥቂት ግለሰቦች ተግባራዊ እንዳይሆን የሚደረግበት ፤ በቤተክርስቲያን ስም የደሃው ምእመን ገንዘብ የሚዘረፍበት ፤ብዙ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የሚፈጸመውን ተግባር አይተው ያዘኑበት ፤ ለመንፈሳዊ ዓላማ እንዳይነሱ ተስፋ የሚያስቁርጥ ምላሽ የሚያገኙበት ፤ ዘረኝነትና ቤተሰባዊ አስተዳደር የተስፋፋበት በአጠቃላይ ለጥቅም ሲባል የቤተክርስቲያንን ሥርዓት ለማፈራረስና አሳልፎ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ለመስጠት ዝግጅቱ የተጠናከረበት ጊዜ ላይ መድረሳችንን እንገነዘባለን ።  ይህንን ዝም ብሎ መመልከት ከማንኛወም ክርስቲያን ስለማይጠበቅ  የተደበቀው ተገልጦ  ግልጽነት ያለው እውነተኛ አሰራር በቤተክርስቲያን እስከሚሰፍን ድረስ በምንችለው ሁሉ ጥረት ማድረግ እንዳለብን ተገንዝበናል ።

በአሁኑ ሰዓት ቤተክርስቲያናችን ሦስት ዋና ዋና ችግር ውሰጥ እንደምትገኝ ተገንዝበናል። እነዚህም አስተዳደራዊ መዋቅርን እና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ጠብቆ የመስራት  ችግር ፤ የሃይማኖት ችግር እና ከጥቅም ጋር የተገኛኘ ችግር ናቸው።

፩ኛ. አስተዳደራዊ መዋቅርን እና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ጠብቆ የመስራት  ችግር ፦
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው መመሪያ መሰረት  ሐዋርያትም በቀኖና ቤተክርስቲያን ደንግገው ባስቀመጡት መሰረት ቤተክርስቲያን የምትመራበት አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ መዋቅር አላት። ይህ  የቤተክርስቲያን መዋቅር ካህናትና ምእመናን ተባብረው የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የሚያደርግ ነው ። የቀደሙት አባቶቻችን ለቤተክርስቲያን መዋቅር በመገዛት እና በማክበር ታላቅ መንፈሳዊ ተግባር አከናውነዋል ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ይህንን አባቶቻችንን ያስቀመጡትን ድንበር የሚያናጋ ተግባር በኃላፊነት በተቀመጡ አባቶች ሲፈጸም እያየን እንገኛለን ። ይህ አስተዳደራዊ መዋቅር ደሃ ሲበደል ፍርድ ሲጓደል ማስተካከል የሚችል ሁኖ እያለ በየደረጃው በተቀመጡ ሙያና ብቃት ሳይኖራቸው ወይም ለግል ጥቅም ለስጋዊ ጠባይና ለምድራዊ አመለካከት የተሸነፉ ሰዎች በመያዛቸው  ብዙ ችግር እተፈጠረ ይገኛል ።

አንዳንድ ብጹዓን አባቶች እንደሚናገሩት በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወስኑት ተግባራዊ ሳይሆን እየቀረና በተቃራኒው የጥፋት ተግባር ሲፈጸም እያዩ አሁን ምን እናድርግ ብለው ግራ እስከ መጋባት ደርሰዋል ።በዚህም የተነሳ የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ አቅሟ እንዲዳከምና የላይኛው አካልና የታችኛው ክፍል በሀሳብና በዓላማ ተለያይተው ለመሄድ ተገደዋል ። በአሁኑ ወቅት የቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር እና ሥርዓት ይጠበቅ ለማለት የሚነሱ ካህናትና ብጹዓን አባቶች ከፍተኛ ጫና የሚደረግባቸው ሲሆን ተስፋ እንዲቆርጡም የሚደርስባቸው መንገላታት ከባድ ነው ።  መዋቅርን በመጣስ የፈለጉትን ለማድረግ የሚንቀሳቀሱትን ግን  በተለያየ መልኩ ለጥፋት ተግባራቸው ቤተክርስቲያንን የመምራት ኃላፊነት የተሰጠው አካል በተለይም ልዩ ጽ/ቤት በመባል የሚጠራው ድጋፍ በመተማመን በአደባባይ አስነዋሪ ተግባር ለመፈጸም ሲነሱ ይታያሉ ። ለምሳሌም ብናነሳ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ሆነው የተቀመጡት በዘር ወይም በግብር አንድነት ካላችው የቤተክርስቲያኒቱ ሀላፊዎች ጋር በመሆን ከጥፋት በቀር ምንም አይነት የልማት ተግባር ባለፉት አስር ዓመታት መፈጸም ያልቻሉ፥  በዚህ በአሜሪካም /ሎስ አንጀለስ ጀምሮ/ ብዙ አሳዛኝ ተግባር በመፈጸም የሚታወቁ  የቤተክርስቲያንን መዋቅር ባልጠበቀ መልኩ ብዙ ደብዳቤዎችንና መመሪያዎችን ሲያስተላልፉ ፤ ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ ከተሰለፉ ጋር አብረው ደፋ ቀና ሲሉ፤በርካታ የሰንበት ት/ቤት አባላት ይህንን የክፋት ስራቸውን በመቃዎም አቤቱታ ቢያቀርቡም እስካሁን በመመሪያው ኃላፊነት እንዲቀጥሉ መደረጋቸው ቤተክርስቲያንን ለማዳከምና ለማፍረስ የተሰለፉ አካላት የቱን ያህል ስር የሰደደ ችግር እየፈጠሩ እንደሆነ አመላካች ነው ። በሰሜን አሜሪካም ደረጃ ስንመለከት በኃላፊነት የተቀመጡት ብጹዓን አባቶች  የሚያደርጉት ተግባር በአግባቡ መገምገም ሲገባው ፤ ከተለያየ አቅጣጫ የሚደረግባቸው ተጽእኖ ላስተዋለው ይህንን አስተዳደራዊ መዋቅር ለማዳከም  የሚደርግ ተግባር መሆኑ ግልጽ  ነው ።

የሚደንቀው  አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ አሜሪካ  በግል ጉዳይ እንደመጡ በአንድ በኩል እየተናገሩ በሌላ በኩል ደግሞ  ከሚመለከታቸው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሳይነጋገሩ በአንዳንድ ከመዋቅር ውጪ በሆኑ አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት ሥልጣነ ክህነትና አመራር በመስጠት የቤተክርስቲያንን ቀኖና ሲተላለፉ ይታያል ።  ከዚህ ደግሞ በባሰ መልኩ አህጉረ ስብከቱን የበለጠ ለማዳከም በማሰብ የውጪ አገልግሎት መምሪያ ጋር የተገናኘ ነው በሚል ሰበብ በዋሽንግተን ዲሲ ተከፈተ የተባለው ጽ/ቤት ቃል በቃል አይነገር እንጂ ሊቃነ ጳጳሳቱን እና አብያተ ክርስቲያናቱን ለዚሁ ጽ/ቤት ተጠሪ የሚያደርግ አሰራር በመፍጠር የበለጠ ቤተክርስቲያንን አስተዳደራዊ እና የቁጥጥር መዋቅሯ እንዲላላ ለመደረግ የታሰበ መሆኑ ግልጽ ነው ። ይህንን ለምሳሌ  ያህል አነሳን እንጂ እየተከሰተ ያለው ችግር በርካታ ነው ። በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ በመካከል የሚፈጠረው የመለያየት አደጋ አሳሳቢ ነው ።

፪ኛ. የሃይማኖት ችግር:-  በአሁኑ ሰዓት የፕሮቱስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ በቤተክርስቲያናችን ሥር እየሰደደ የመጣ ሲሆን ይህንን ቤተክርስቲያንን ለማፈራረስና ወደ ፕሮቴስታንት ለመቀየር በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ በቤተክርስቲያን ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ከመንበረ ፓትሪያርክ እስከ አጥቢያ ባሉ አባቶች ስልታዊ ሽፋን በመስጠት ላይ በመሆናቸው ችግሩን ውስብስብ እና አሳሳቢ አድርጎታል። የቤተክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት ይህንን ዓላማ በሚያራምዱ ሰዎች ተንቋል ፤ ቁጥጥር እና ክትትል እንዲላላ ተደርጓል ፤ የአብነት ት/ቤቶች  ክብራችንን በሚነካ መልኩ ተደፍረዋል ። ይህንን ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ በአግባቡ ተመልክቶ ውሳኔ እንዳይሰጥ ከእነዚህ የተሐድሶ አካላት ጋር ግንኙነት የፈጠሩት ሊቃነ ጳጳሳት የሚያስተጋቡትን የማደናገሪያ ሀሳብ በቀላል የሚታይ አይደለም ።  ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እየተፋለሰ ፤ለአጽራረ ቤተክርስቲያን በር እየተከፈተ ባለበት ወቅት ለዚሁ ተግባር የተሰለፉትን ያለሙያቸው እና ችሎታቸው በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ተቀምጠው  የበግለ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ኃላፊነት ለመስጠትና በኃላፊነት ለማቆየት የሚደረገው ጥረት ቤተክርስቲያንን ለማፈራረስ የተጠነሰሰውን ተንኮል እንደሆነ አመላካች ነው ። ይህንን ችግር የቤተክርስቲያን ኃላፊዎች ዝም የሚሉ ከሆነ ግን ሕዝበ ክርስቲያኑ ዝም ማለት የሚችልበት ትዕግስት እንደሌለው አስቀድመን ልንገነዘበው የሚገባ እውነታ ሊሆን ይገባል ። አባቶችም ቢሆን እንዲከበሩ ያበቃቸውን ምክንያት ካላወቁ በሰዉም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ መዋረድ እንዳለ መረዳት አለባቸው ።

፫ኛ. ከጥቅም ጋር የተገኛኘ ችግር: - በአሁኑ ሰዓት የብዙዎችን አይን ያሳወረ የበለጠ እየተገለጸ የመጣው ችግር ደግሞ ከጥቅም ጋር የተገናኘ ነው ። እንደ  ቤተክርስቲያን ልጅነታችን ህሊናችንን የሚያቆስል  ከዚህ ጋራ  የተገኛኙ በርካታ ችግሮችን እንሰማለን ። የካህናት ምደባ  እና ዝውውር ጋር ለደጅ ጥናት የሚቀርበው የገንዘብ መጠን ተመን ወጥቶለት በአደባባይ እስከመነገር ደርሷል።  የሃይማኖት እውቀቱና ብቃቱ ሳይኖራቸው  የጵጵስና ሹመት ፍለጋ ገንዘብ እጅ መንሻ በማቅረብ ደጅ የሚጠኑ መበራከታቸውም አደባባይ ምሥጢር ሆኗል። ቤተክርስቲያኒቱ ባላት የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ጋር በተገናኘ  ፤ ቤተሰባዊ ዝምድናን በመጠቀም ስር የሰደደ የግል ጥቅም ማሰባሰቢያ ሰንሰለት መዘርጋቱ ፤ ሆን ተብሎ የምድዋይ ምጽዋትና የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ዝርፊያ መበራከቱ የማይደበቅ ሆኗል። በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር በሚገኙ አጥቢያዎች እንኳን  በቅርቡ በተደረገው ለውጥ  ምእመናን በገንዘብ ቁጥጥሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ መለስተኛ የቁጥጥር መንገድ በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ አመራር መሰጠቱ የታየው የገቢ ለውጥ  ምን ያህል ገንዘብ ይባክን እንደነበረ አመላክቷል። የእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ ከየት መጡ ሳይባሉ እንደዚህ ስማቸው በክፋት የገነነው እዚህ የጥቅም መረብ ውስጥ በመግባታቸው ነው ። ጥቅም አይንን ያሳውራልና ከደሃ ምእመናን የተሰበሰበውን  ገንዘብ ለግል ጥቅም በማዋል የሰውን ደም በመምጠጥ ተግባር ላይ ዛሬም በርካቶች ተሰማርተዋል። ቤተክርስቲያኒቱ ከዚህ በለጠ ውርደት በእኛ ዘመን ሊገጥማት አይችልም ። ለምሳሌ ያህል አነሳን እንጂ እየደረሰ ያለው ችግር ከባድና መጠነ ሰፊ እና አሳሳቢ ነው ።

ቤተክርስቲያናችን ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ በመረዳት በሰሜን አሜሪካ የሚገኘውና በሦስቱም አህጉረ ስብከት እውቅና የተሰጠው  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ማኀበረ በዓለ ወልድ ይህንን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት መንፈሳዊ ግዴታውን  ለመወጣት ወስኗል። ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅና አደራችንን ለመወጣት በምናደርገው እንቅስቃሴ መመሪያችን የሚሆነው እውነት ብቻ ነው ። ይህንን በመረዳት ቤተክርስቲያን ያለችበትን ወቅታዊ ችግር በመረጃ በተደገፈ መልኩ በመላው ዓለም የሚገኙ ምእመናን እንዲያውቁ ማድረግ እንዳለብን ተረድተናል። ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ  ክርስቲያኖች ሁሉ ይህ የተከሰተው  ተስተካክሎ እስከሚታይ ድረስ መንፈሳዊነት ባልተለየው መልኩ እና አግባብ ባለው መንገድ የልጅነታችንን ግዴታ በጋራ እንድንወጣ  ጥሪያችንን እያስተላለፍን የሚከተለውን የአቋም   መግለጫ አውጥተናል።

፩ኛ/  የቤተክርስቲያናችን የበላይ አመራር አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ሁሉ በተግባር ላይ እንዲዉሉ ፤ ይህንንም ለማጠናከር  የድረሻችንን መወጣት እንድንችል ግልጽ መመሪያ ከቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሰጠን እንጠይቃለን ። የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይደረግ እንቅፋት የሆኑ አባቶችን እና ምእመናንን ሁሉ ይህንን የክፋት ተግባራቸውን እንዲያቆሙ እናሳስባለን።

፪ኛ/ አባ ሰረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል  በቤተክርስቲያን  የኃላፊነት ቦታ ላይ እንዲቀመጡ የሚያደርጋቸው ብቃት ስለሌላቸውና ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ከለላ በመስጠት የሚፈጽሙትን ተግባር  ከባድ በመሆኑ ጊዜ ሳይሰጠው በአስቸካይ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ እንጠይቃለን::

፫ኛ. ከዚህ ቀደም ወቅታዊ የቤተክርስቲያኑቱን ችግር መነሻ በማድረግ የሰሜን አሜሪካ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ያወጡትን መግለጫ የምንደግፍ ከመሆኑም በመተጨማሪ ከእነዚህ መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ጋር በመሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ መወሰናችንን እናረጋግጣለን ።

፬ኛ. በሰሜን አሜሪካ የሚመደቡ ብጹዓን አባቶች  የሚደረግባቸው  ተጽእኖ ተነስቶ የሚያከናውኑት ተግባር በቅንነት እንዲገመገም እንጠይቃለን ።

፭ኛ. ከቅዱስ ሲኖዶስና ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ውጪ ወደ ሰሜን አሜሪካ በመምጣት ያለ ሀገረ ስብከቱ እውቅና ስልጣነ ክህነት እና መመሪያ የሚሰጡ አባቶች ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡና የቤተክርስቲያንን ስርዓት እንዲያከብሩ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እና ውሳኔ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን።

፮ኛ. በዋሽንግተን ዲሲ ተከፈተ የተባለው ጽ/ቤት ቅዱስ ሲኖዶስ የማያውቀው እና የቤተክርስቲያኒቱንም መዋቅር ለማዳከም የታሰበ በመሆኑ መሉ በሙሉ እንቃወማለን ፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የማያዳግም ውሳኔ እንዲሰጥበት  እንጠይቃለን ።

፯ኛ. በቤተክርስቲያን ውስጥ ሳይገባቸው የኃላፊነት ቦታ የተሰጣቸው ፤ የቤተክርስቲያንን ሀብትና ንብረት በመዝረፍ የተቀመጡ ኃላፊዎች እና ተባባሪዎቻቸው ጉዳዩ ሕጋዊ  እና ሙያዊ በሆነ ግምገማ ታይቶ ተገቢው ውሳኔ እንዲሰጣቸው  እንጠይቃለን።

፰ኛ. በቤተክርስቲያናችን ውስጥ የተከሰተውን ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ለማጥፋት ለሚደረገው እንቅስቃሴ  የበኩላችንን ለማድረግ መንፈሳዊ ዝግጁነታችንን እንገልጻለን ። ቅዱስ ሲኖዶስም ጥብቅ ሃይማኖታዊ መመሪያና ውሳኔ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር::

እግዚአብሔር አምላክ ሀገራችንን ኢትዮጵያን፣ ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን አሜን::

ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር


መስከረም ፳፻፬ ዓ. ም
ግልባጭ
፩/ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
፪/ ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ  ልዩ ጽ/ቤት
፫/ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
፬/ ለዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
፭/ ለኒዮርክ እና የመከለኛው አሜሪካ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
፮/ ለካሊፎርኒያ እና ለምእራብ እስቴቶች ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
፯/ ለብጹዓን አባቶች በየአህጉረ ስብከቶቻቸው
፰/ ለአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት
፱/ ለሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኀበረ ቅዱሳን
፲/ ለሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ

የማኅበረ በዓለወልድ ሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት

ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር

No comments: