Wednesday, November 9, 2011

የፓትርያርክ ጳውሎስ ቁማርና የቤተክርስቲያን ተስፋ

 ከቀሲስ ወንድምስሻ አየለ ፌስ ቡክ የተወሰደ:: READ IN PDF
ቁማር ከመዝናናት ሌላ ጥቅም ለማግኘት ሲባል የሚጫወቱት ሕጋዊና ሕገወጥ ጫወታ መሆኑና ማንኛውንም ጫወታ በቁማርነትም ሆነ በመዝናኛነት ለይቶ የመጫወቱ ድርሻ የተጫዋቹ መሆኑ ግልጥ ነው፤ ካርታን ለመዝናኛነትም፣ ሲያስፈልግ ደግሞ በሕገወጡ ቁማርነትም መጫወት እንደሚቻል። ይህም መንፈሳዊውን ሥልጣን በያዘው ሰው ዘንድ መነገሩ እጅግ የሚያሳስብና የሚያሳዝን ነው። «አባት»ን ቁማርተኛ ብሎ ለሚናገረውም ሁለት ጊዜ ብቻ ሳይሆን አሥር ጊዜ አስቦ ዓላማንም ለይቶ የሚጸናውን ከያዙ ላያሳፍር ብሎም ሊጠቅም ይችላል። ተሳድቦና ዘልፎ ለመርካት ወይም ብስጭትን ለመወጣት ሊረዳ ቢችልም ከኅሊና ዕዳ ነፃ ለመሆን ግን እውነተኛ መረጃ ይፈልጋል፤ እንደነ በጋሻውም በአደባባይ ለመገላበጥ አይገደድም። እኛምይህን ታሳቢ አድርገን እንቀጥል።

ከረጅሙ ታሪካቸው ባጭሩ

አባ ጳውሎስ አሁን በሕይወት ከሌሉ አንድ ዘመዴ ጋር የሃይስኩል ተማሪ ሆነው በቅድስት ሥላሴ ት/ቤት ሲማሩ የነበሩበትንና ከያኔው ግርማ /አሁን አቡነ ገሪማ/ ጋር ሆነው ሁለቱ ጓደኞቻቸው በጥቁር ራስነት እሳቸው ግን ያኔም በምንኩስና ሲኖሩ ድብቅነት ይታይባቸው ነበረ። ጵጵስና ከተሾሙ በኋላ ሳይቀር ቆባቸውንና ቀሚሳቸውን አውልቀው በሱሪና ኮት እንደተራ ሰው ከተማ የሚዞሩበት አጋጣሚም ነበረ፤ ምክንያቱን ራሳቸው ይወቁት። ከሃይስኩል በኋላ ባገኙት ዕድል የቲዎሎጂ ዲግሪ ይዘው ቅዳሴ ተምረው ጵጵስና ለመቀበል እንዴት እንደቻሉ መጠናት አለበት፤ ምክንያቱ ደግሞ ዕድሜያቸው ለጵጵስና ያልደረሰ፣ ቅስና እንኳ ለመቀበል የቤ/ክ/ ጥልቅ ሙያ በሚጠየቅበት ተጠይቆም ሲገኙ /በዘመኑ ሞልተዋል/ አልሾምም እያሉ በሚሸሹበት ዘመን በወጣትነታቸው ለኤጲስ ቆጶስነት መታጨታቸው፣ በከባዱ የፖለቲካ ውጥረት መሐል የፓትርያርኩን ልብ ከፍተው የገቡትና ለዛሬው ጥፋት መሪ ተዋናይ የሆኑበት ሁኔታ ቀድሞ የተጠና ይመስላል። ያኔ ግን ታላላቁ ብፁዐን አባቶች በዕውቀታቸውና በመንፈሳዊ ሞገሳቸው በሕዝቡ ዘንድ እጅግ የተከበሩ ነበሩ።ሌሎች አባቶች በመንግሥት ጭምር እየተፈሩና እየተፈለጉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሚናቸውን እንዲጫወቱ በአስፈሪው ደርግ ሲጋበዙ ለተራበ ለምነው እርዳታ በማስመጣት፣ ቤተክርስቲያን የሄደውን ምእመን አስተባብረው ልማትንና ወንጌልን በሙሉ ኃይላቸው በማስፋፋት በገቢረ ተአምር ጭምር ሲመላለሱ ነው የሚታወቁት። አቡነ ጳውሎስና ሌሎች ሁለት ግን ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ጋር በፖለቲካ ጉዳይ ተከሰው ታሠሩ።

ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ እንዲገደሉ ሤራ ሲሸረብ እነርሱ ሰባት ዓመት ታሥረው ተፈቱ፤ አሜሪካም ሄደው በብዙ በሚያስወቅሳቸው ተግባር ተጠመዱ፤ ፓትርያርክ ከሆኑ በኋላ አሜሪካ ሲሄዱ የበሰበሰ ቲማቲምና የገማ እንቁላል የተወረወረባቸው ከዚሁ ቆይታቸው መታወቅ ጋር በተያያዘ ነበረ። ዛሬ እንደምሳሌ የሚያነሧቸውና የእርሳቸውን ሥራ እንደቀጠሉ የሚያስወሩት ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ጠንካራ አቋም ይዘው ከንጽሕናና ቅድስና ጋር ርስቷን ላጣችው ቤተክርስቲያን መተዳደሪያ ዕቅድ ያወጡላት፣ ዛሬ እንደፈለጉ የሚዘርፉትን የሰበካ ጉባኤ አስተዳደርና ፐርሰንት አሰባሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ዐውጀው የተገበሩት፣ በየሀገረስብከቱም እየታደመባቸውና እየተዘለፉ ያደራጁት እርሳቸው ናቸው። አስተዳደራዊና ቀኖናዊ ነገሮችን በመቀላቀል ከመንግሥት ጋር ሲያጣሏቸው አድርባይ ባለመሆናቸውና ሀሳባቸውን ባለመለወጣቸው በሞቅታ ውሳኔ ፓትርያርኩ ሲገደሉ ብዙ ይሠራሉ ተብሎ ሲጠበቁ የነበሩትና ባለብሩህ አእምሮው ቴዎፍሎስ ንጽሕናቸውን ይዘው በክብር ዐረፉ። እዚህ ጋር ተሐድሶዎች እንደ ደቂቀ እስጢፋ ታሪክ ለሀሳባቸው ማስኬጃ ሊጠቀሙባቸው እንደሚፈልጉ ያስታውሷል። አቡነ ቴዎፍሎስም ሆኑ ደቂቀ እስጢፋ ያላቸው ሀሳብ ከዛሬዎቹ ፕሮቴስታንታዊዎቹ ተሐድሶዎች ጋር ምንም ተዘምዶ የላቸውም /ታሪካቸውን በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመሥርተን መናገር ያለብን ወቅት ላይ ሳንደርስ አንቀርም።/

 የዛሬው ፓትርያርክ ጳውሎስ በየትኛው ሥራቸው እንደተከተሏቸው ታሪክና ፈጣሪ ይግለጠው እንጂ ለእኔ ከሽፋን በቀር የተረዳሁት ነጥብ የለም። ባይሆን አሁን የሃይማኖት ድብቅ አጀንዳ ይዘው በሚታዩ የአስተዳደር ችግሮች ላይ ድምፃቸውን እያጮኹ «ቤተክርስቲያን ትታደስ» የሚሉትን ተሐድሶዎች ለመተባበር የማያዛልቅ መደገፊያ ሊሆኗቸው ይችላሉ። ቴዎፍሎስ ግን እንደተገለጡት ተሐድሶዎች /ለምሳሌ ጽጌ ስጦታው/ ኢየሱስ ክርስቶስን ይለምንልናል አማላጅ ነው፣ ቅዱሳንን ከእመቤታችን ጀምሮ እነ አቡነ ተክለሃይማኖት «ጣዖቶችና ሰይጣን» እያሉ አንድም ቀን ተናግረውም ሆነ ሲነገር ዝም ብለው አያውቁም ነበረ። ቆይቶ በዩኒቨርሳሊዝም አስተሳሰብ የተጠለፈውን የወጣቶች ማኅበር «ሃይማኖተ አበው» በወቅቱ ቤተክርስቲያንን ከማጠናከርና ዘመኑን ከመዋጀት አንጻር ተፈላጊ በመሆኑ ይደግፉት ነበረ፤ በእርሳቸው ዘመን ግን «የማያድን ሃይማኖት የለም፤ ሁሉም በማዳን አይበላለጡም እኩል ናቸው» ብሎ ከፕሮቴስታንቶች ጋር ያለውን የልዩነት ድንበር ይህ ማኅበር ሲያፈርስ አያውቁም፤ አልተገለጠም ነበረ። የሃይማኖተ አበው በዩኒቨርሳሊዝም አስተሳሰብ መጠለፍ የተገለጠው በባሕታዊው ፓትርያርክ ተክለሃይማኖት ዘመን ነው፤ ወዲያውም ተወግዟል። ፓትርያርክ ጳውሎስ እነጽጌ ስጦታው በግልጥ ኑፋቂያቸውን እያስፋፉ አባቶችን ሲዘልፉ ሊያወግዟቸው አላሰቡም፤ እንዲያውም እንዳይወገዙ ሽፋን በመስጠትና ሊቃውንቱን በማሳደድ ሥራ ተጠምደው እስከዛሬ ቆዩ።

ከአሜሪካ የተመለሱትና ለአንድ ዓመት ያህል በልዩ ልዩ ኃላፊነት የቆዩት አዲስ አበባ ነው። ከምንኩስናቸው ጊዜ ጀምሮ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስን በማንቆለጳጰስ ለጵጵስና ሲጎመጁ ሰነበቱ እንጂ አንድ ሀገረስብከት ወይም ደብር በክህነት ወይም በመምህርነት በወጉ ያገለገሉበት ጊዜ አልተጠቀሰም። የፓትርያርክ መርቆሬዎስ ስደት ሲሸረብ /እጃቸው ይኖርበት እንደሁ እንጃ፤/ ዋናው አጀንዳ ፖለቲካ በመሆኑ ለኢሕአዴግ ደግሞ በደርግ ተበዳይነትም ሆነ በትጥቅ ትግል የበላዩ ሕወኃት ወገንነት በመኩራራት ተገቢ ሰው ሆነው፤ ለዕውቀትም ሆነ ለመንፈሳዊነት እንደሚጠቅም ባልተገለጠው ፒኤችዲ ተከልለው /በእውነቱ እንደተማሩ የሚያሳይ ምሁራዊ ተግባር የላቸውምና እኔ መማራቸውን እጠራጠራለሁ/ «አማራጭ የሌለው አማራጭ» ሆነው ፓትርያርክነት ሐምሌ ፬ ቀን ፲፱፻፹፬ ዓም ተሾሙ። ይህንም በወቅቱ የነበሩት ሊቃውንት ከሰብሳቢያቸው ሊ/ሊ/ አያሌው ታምሩ ጭምር ተቃወሙት፣ የግብፅ ሲኖዶስም አወገዘ። በዚያው ወቅት እንደወረራ የተከሠቱት ባሕታያንም ከፊሎቹ በኃይል ሌሎቹም በየጉባኤያቸው ተቃወሟቸው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ትልቁ ሽፋን «ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደእሳቸው ማን አጻፈ፣ የቤ/ክ/ ርስቶችና ቤቶችን ማን አስመለሰ» እያሉ በቅኔና በዜማ ማሰበክ ነው። ተደርጎ የማይታወቀው መሣሪያ ታጥቆ መቅደስ መግባት፣ ከመጠን በላይ በተረፈ ወጪና ዘመናዊነት መምነሽነሽ፣ ጳጳሳት በዐዋጅ ሀብት እንዲያፈሩና ለፈለጉት ሰው እንዲያወርሱ የተፈቀደው፣ የአዲስ አበባ አድባራት ለሌሎች አኅጉረስብከት መዳከምና ለጥቅም እሽቅድምድም አደባባይነት የተዳረጉት፣ የትም ያለው ካህንና መምህር ከጠቅላይ ቤተክህነት በጀት የሚያገኘው በእሳቸውና በረጅሙ ሥራአስኪያጅነት ሥልጣን ዘመናቸው አብሮ አደጉ አቡነ ገሪማ ዘመን ነው። ነገሩ መመርመርና መፈተን የጀመረው፣ ለዘላቂ መፍትሔነትም ቃለዐዋዲውም ሆነ ሕገቤተክርስቲያኑ የተከለሰው በ፲፱፻፺፩ ነበረ። ይህ ባይሆን ኑሮ፣ በፓትርያርክ ሥልጣን ያለው ገደብ ባይተነተን ኑሮ ደግሞ ከዚህ የባሰ ጥፋት ይመጣ ነበረ። /አሁንም ቃለዐዋዲው ብቻ ተስተካክሎ የሚፈጸም ላይሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ሳይሻ አይቀርም/ በአጠቃላይ ካልታወቀባቸው አሠራሩን እየጣሱ፣ ተቃዋሚ ከገጠማቸው ደግሞ ሥልጣናቸውን አላግባብ እየተጠቀሙ ያሻቸውን ሲያደርጉ የቆዩት ፓትርያርክ ዛሬ እንዴት እናሸንፋቸውና ቤ/ክ/ ሰላም ታግኝ? ጥያቄያችን ነው።

ሊቀካህናት ሃና /«ሃ» ላልቶ ይነበብ/

«ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል። ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ።» እንዳለው የሾማቸው እግዚአብሔር ፊታቸውን ጸፍቶ አፋቸውን ከፍቶ «ዓለሙ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ቢጠፋ ይሻላል» እንዲሉ አድርጓቸዋል። ይህ አባባል ከአዳም ጀምሮ ያለው ትውልድ ከሚጠፋ አንድ ክርስቶስ ሞት ተፈርዶበት ዓለሙን በሞቱ ቢያድን ይሻላል በሚለው ትርጓሜ ይኸው ዛሬም በበጎነት ጭምር ይጠቀሳል፤ የትምህርት ርእስም ይሆናል። ይህ ማለት ግን የሃና ሀሳብ ከበጎ ኅሊና የመነጨና ለቤተመቅደስ ጥቅም የተነገረ ነው ማለት አይደለም። ግን ሃና ባለበት መቅደስ ጌታችን ሥራውን ፈጽሟል። ጌታችን ቤተመቅደሱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሐዲስ ሥርዓተ ክህነትና ሥርዓተ መሥዋዕት እያደሰ፣ ምሥጢረ ሥላሴን እየገለጠ፣ ሐዋርያትን እያከበረ፣ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን እንዲመለሱ እየገሰጸ፣ ካልተመለሱም ከነቢያቱ ትንቢት እንደተለዩ እያስረገጠ በመናገሩ ከኦሪት ሊቃውንት እንደነ ገማልያል ያሉ መምህራን የተመለሱበት ሐዋርያትም የዘላለም መንግሥት ካህናት ሆነው በ፲፪ቱ ዙፋን /ነገደ እስራኤል ዘነፍስ/ ላይ የተሾሙበት ፍጻሜ ተገኝቷል።

ዛሬ እንደሃና በየተሾምንበት ሥልጣን አፋችንን ከፍቶ ፊታችነን ጸፍቶ ሳንወደውና ሳንረዳው ደገኛውን ነገር ልንናገር እንችል ይሆናል። ሳንረዳውና ሳንወደው መናገራችን የሚታወቀው ደግሞ በሌላ አጋጣሚ /ያንኑ ሀሳብ ሳንጨርስ ሊሆን ይችላል/ የተናገርነውን የሚቃወም ሀሳብና ተግባር ስንከውን በመገኘታችን ነው። እኔ ፓትርያርክ ጳውሎስን የማያቸው እንደ ሊቀካህናት ሃና ነው። ሀሳባቸውን መርጠን የምንታዘዛቸው በሥራቸው ግን የማንተባበራቸው ኑፋቄን የሚያራምዱ ስመ ካህን፣ እምነታችን በእግዚአብሔር ላይ ስለተመሠረተ የማንናወጽ ሆነን እንጂ ዕቅዳቸው የሁላችንን ድምፅ አሰባስበው ቤ/ክ/ንን ስቀሏት፣ አርጅታለች አድሷት፣ እንድንልላቸው የሚፈልጉ የፍርድ ሰው ሆነው ይታዩኛል።

መምህር ዘመድኩን በቀለ «አርማጌዶን» ቁጥር አንድ ትምህርቱን ባሰራጨ ማግሥት ለተሰበሰቡ ሰባክያነ ወንጌል «ቤተክርስቲያንን እናድሳታለን አትበሉ» እንዳላሉ፤ ነገሩ ፈጥጦ ሊሸነፍባቸው ሲል ደግሞ «ማንንም ተሐድሶ ማለት…አይቻልም። ማንኛውም እንቅስቃሴ ቀኖናን የጣሰ በመሆኑ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል» ብለው ስለተሐድሶ ግንዛቤ እንዳይሰጥ በደብዳቤ ያግዳሉ። ሌላም ሌላም። ስለዚህ ስለተሾሙ የሚናገሩ፣ ስላልወደዱት የሚያደናግሩ በመሆናቸው እንደ ሃና ብቻ ልናከብራቸውና ልንሰማቸው ይገባ ይሆናል። በተረፈ ግን በተገለጠው ኢ-ሲኖዶሳዊ ተግባራቸው ጥቡዕ እንደ አንበሳ፣ ትሑት እንደ መሬት፣ እንደዮሐንስ አፈወርቅ ጠበቃዋ፣ እንደናቡቴ ሰማዕቷ ሆነን፣ የኪልቂያ ልጅነትን ለመብት፣ ዕብራዊነትን ለማሳፈሪያ ትምክህት፣ መስቀሉን መሸከምን ለመጨረሻው ቁርጥ ፈቃድ ማድረግ ይጠበቅብናል። ምሳሌው ለመንግሥተ ሰማያት ልጆች የተገለጠ ቢሆንም ጥቂት ነጥቦችን ለማብራሪያነትና መፍትሔነት ልግለጥ።

አእማደ ኅሊናት

ስለዛሬዋ ቤተክርስቲያን ስናስብ መዘንጋት የሌለብን የምላቸው ምሰሶዎች አሉኝ፤ አእማደ ኅሊናት።

ምሰሶ ፩፡ የቤተክርስቲያን አንድነት፡- ፓትርያርክ ጳውሎስ ከእርሳቸው በፊት ጭምር የነበሩትን ክፍተቶች በማስፋትና አዳዲስ በመጨመር የሚያከናውኑት ግልጥ ነገር ባገኙት አጋጣሚ ቤተክርስቲያኗን መቅበር፣ ኅልውናዋን ማስረሳት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፤ ይህን ዛሬ በግልጥ ብናወሳው ጥሩ ነው። ለቤተክርስቲያን ኅልውና ወሳኙ ምዕራፏ ደግሞ ከሌሎች የእምነት ተቋማት የተለየ የውስጥ አንድነቷ ነው። ከዚህ አንጻር አባቶች ጳጳሳትንና ሊቃውንትን ሲቀጥልም ምእመናንም በተረዱትና ባልተረዱት ምክንያት እንዲከፋፈሉና የካቶሊክና ፕሮቴስታንቶች አድናቂና ከሳሽ፣ የዘመናዊነት ለምድ ናፋቂና ተቃዋሚ /በእርሳቸው አባባል ዘመናዊና ኋላ ቀር/፣ የተፈላጊ ለውጥ አቀንቃኝና የተቃውሞ ሙሾ አውጪ፣ ወዘተ በማድረግ መከፋፈል ነበረ ሀሳባቸው። ከዚህም የተነሣ ለተወሰኑ ጊዜያት ጥቂት ዘመን ቀመስ የተባሉትን ደጋፊያቸው ለማድረግና ከሌሎች አባቶች ለማለያየት እየተሳካላቸው ነበረ፤ ጥቂት የሰመረላቸው የሚመስለው በአቡነ ፋኑኤል ያልበሰለ መንገድና፣ የእነ አቡነ ጎርጎሪዮስ ላይናገሩ መሸበባቸው ነው። በጸሎትና ትሕርምት ምክንያት እጅግ የዋሕ የሆኑትን አባቶች ሲያደናግሩና ያለተቃውሞ እንዲቆዩላቸው ያስቻለ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን እንደነ አቡነ በርናባስ በመጨረሻ ሰዓትም ቢሆን እውነቱን እንዲመሰክሩ አድርጓል። በአማራ ክልል «ማኅበረቅዱሳን የሰላም ጸር ነው» በሚል በመንግሥት አቋም ተወስዶ የነበረው በአቡነ በርናባስ የዋሕነት በባሕርዳሮቹ ተሐድሶዎች አቀናባሪነት ቢሆንም ፓትርያርክ ጳውሎስን ግን ረድቷል፤ የዋሑ አባት ነገሩ ሲገባቸው ግን «ለአንድ ሰው ነው የምንታዘዘው ወይስ ለእግዚአብሔር? እስከመቼ» ብለው አፈረጡት፤ ወዲያውም ዐረፉ።??

ስለዚህም ዛሬም የሚከስቷቸውን አጋጣሚዎች በየዋሕነት ወይም በደመ ሞቃትነት ሳይሆን አንድነታችንን ለማፍረስ የተሸረበ ይሆን ወይ ብለን መጠርጠር ተገቢ ነው። ቤተክህነቱን ያለሥራ ድርሻቸው ማበጣበጥ የያዙትም እንጥፍጣፊ ድጋፍ የሚሰጧቸው ሰዎች የቀሩላቸውና ከውሳኔ ያለፈ ፍሬ ያለው ነገር ሊከውኑበት የሚችሉበት ቦታ ስለሆነ ነው። አንድ «አባ» ሰረቀ እንኳ ይኸው ስንቱን ከወነላቸው አይደል።

አቡነ ፋኑኤልም ለዚህ የታሰቡና አሜሪካዊ ተልዕኮ ጭምር የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል፤ እርሳቸው ያን ያህል ባይረዱትም። ባይሆን በተጠሪ ጽ/ቤቱ በኩል እንደፈለጉ ሊያሽከረክሯቸው ሲሞክሩ ጥቂቱን እየተግባቡ ሌላውን እየተጨቃጨቁ ሊከውኑት ይችሉ ይሆናል። አሜሪካዊው አሠራር ደግሞ «ሰውን ማመን ቀብሮ ነው» በሚለው የሲ አይ ኤ አማራጭ ጉዳያቸውን ከፈጸሙላቸው በኋላ ወይም ሲከሽፍባቸው ምናልባት ደግሞ ሳይግባቡ ሲቀሩ ሊያስወግዷቸው ይችላሉ። የዚህ አማራጭ ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለመገመት ደግሞ ቀላሉ ምስክር በአሁኑ ሲኖዶስ በሥውር የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለሲኖዶስ ሲያጋልጡ «ፓትርያርኩ ልከውኝ ነው አሜሪካ የሄድኩት» ሲሉ ያላስተዋሏቸው ብዙ ነገሮች መኖራቸውን ይጠቁማልና ነው። አቡነ ፋኑኤልን ከማዳን አንጻርም ሆነ /ማንስ ቢሆን ለምን ይጎዳ?/ የአሜሪካ ምእመናንን አንድነት ከማስጠበቅ አንጻር በተቃውሞ ከመቀበል ይልቅ በዐዋጁ ሥራቸው /ሐዋርያዊ ልዑክነታቸውን መተባበር ብንችል፣ የተለየ ተግባር ሊከውኑ ሲጀምሩም በአብዮት ሳይሆን በድርሻችን ሥልጣን ብንቃወማቸው በቂ ሊሆን ይችላል። ሰበካውን፣ ሰ/ት/ቤቱን/፣ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን በምእመናኑ በቂ ተሳትፎና በቃለ ዐዋዲው መሠረት እንዲመሩና እንዳያፈርሷቸው ማስገደድ፤ ከዚህ መንገድ ሲያፈነግጡ ደግሞ ባለን ሥልጣን በጥብዓት መከላከል ውጤቱ የተሻለ ሊሆን ይችላል። በአንጻሩም በጥበብ ከተጠቀምንበት የሚሄዱባቸውን «ገለልተኛ» አጥቢያ ምእመናን ወደ ሀገረስብከቱ አስተዳደር እንዲያስገቧቸው «መርዳት» ይቻል ይሆናል። ይህን የመሰለውን ትቶ አሜሪካ እንደገቡ አብዮታዊ እርምጃ ከሞከርን ግን ውጤቱ ማንም የማይፈልገውና የከፋ አንድነት ማጣት፣ ሌላ ትልቅ የቤት ሥራም ሊሆን ይችላል። ሐዋሳ በነበሩበት ወቅት እየታዘዝናቸው ለመፈጸም ከሞከርናቸው ጉዳይ አንጻር ሳስበው ደግሞ ባለማወቅ የሚያጠፉ፣ ለማሸነፍ የማይበቁ፣ ከክፉዎቹ ቀድመውና በልጠው «ከቀረቧቸው» ሌላውን ወገን ትተው ለቤ/ክ/ ሊሠሩ የሚችሉ ዓይነት ሰው ናቸው እንደ እኔ፤ ያም ሆነ ይህ ግን የገንዘብ ነገር ካልተዉት የማይችሉት ጠላት ሊሆንባቸው ይችላል። በቂ መረጃ ካላችሁ አልቃወምም፤ እንዲከፋፍሉን ዕድል ላለመስጠት እናተኩር ነው ነጥቤ። ሌሎች አማራጮችንም በዚህ ምሳሌነት ስለቤተክርስቲያን አንድነት እየታሰበ ቢታይ እላለሁ።

ምሰሶ ፪፡ ያሉና የነበሩት  ዛሬ ያልተጀመሩ ችግሮች አስቀድሞም የነበሩ ጥቂት አይደሉም። ልዩነቱ አሁን በመሪ ደረጃ ችግሮቹ ተፈላጊ መሆናቸውና ለጥፋት ዓላማ ለመጠቀም የሚፈልግ ፓትርያርክ መሾሙ ነው። በአንጻሩ ደግሞ በየዋሕነትም ሆነ ባለመረዳት አባቶች ጳጳሳት፣ ሊቃውንትና ምእመናን ለፓትርያርኩ አሳልፈን የሰጠናቸው ሥልጣኖቻችን አሉ። ለቤተክርስቲያን አንድነትና ጥንካሬም ወሳኝ ፍቱን የሆኑ ቀኖናዎችም በሲኖዶስ ባይሻሩም በተግባር ተዘንግተዋል። ጥቂቱን ለመጥቀስ ያህል የተክሊል ጋብቻ እንኳ በሕዝብ ፊት በሰንበት ወይም በበዓል አስቀድሞ እንዲገመገምና ሕዝቡ «ተክሊል አይገባቸውም» ብሎ እንዲበይን መብት የተሰጠበት ቀኖና ተዘንግቶ ጳጳሳትና ፓትርያርክን ሳይቀር በጓዳ መምረጥና የሚሾሙበትን ሀገረስብከት በውል የማያውቁ መልእክተኞች መሆናቸው፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት የሚሾሙበት ቅድመ ሁኔታ /ከራሴ ጭምር/፣ በጳጳሳት መሾም የሚገባቸውና የተዘነጉት መሪጌቶች /በቅዳሴ የሚዘከሩት መዘምራን/፣ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ /የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጨመር አለበት/ ንዋያተ ቅድሳት፣ መባዎችና መሥዋዕቶች የሚያዘጋጃቸውና የሚያሰራጫቸው ሰው፣ የሚመረቱበት ቦታ ሃይማኖታዊ ይዘት፣ ቀኖናን የሚጥሱ ትእዛዛትን የሚያፈርሱ ካህናትና ምእመናን ላይ የሚበየንበት አማራጭ መጥፋት፣ የሃይማኖት ትምህርት ወይም ቀኖና ልዩነት ያለው ሰው ሀሳቡን አቅርቦ ለመከራከርና ለማመን ወይም ለማሳመን መድረክና ዳኛ አለመኖር ብሎም ችግሩ ቢታወቅ እንኳ ተመሳስሎ ለመኖርና የራስን መርዝ ባላቸው ዕድል ለመርጨት አለመቸገር ወዘተ።

ከዚህ አንጻር ስናይ ፓትርያርክ ጳውሎስ ያስፋፉትና የጀመሩት የጥፋት መንገድ ብዙ ቢሆንም የተወሰኑት ከግራኝ አሕመድ ሌሎች ጥቂቶቹም ከንጉሠ ነገሥት ምኒሊክ ዘመን በኋላ የተከሠቱ ናቸው። ስለዚህ የራሳችን ሲኖዶስ ባገኘንበት ዘመን አሁን ሁሉንም ማስተካከል ስለምንችል የሲኖዶሱን አንድነትና አቅም የሚያውኩ ጉዳዮችን እየተጠነቀቅን በመሥራት ለተናጠል ክስተቶች /events/ ስንቸኩል ሊፈጠሩ የሚችሉ ጉዳቶችን መቀነስ አለብን።

አማራጭ መፍትሔ

እኔ ፓትርያርክን ማውረድ ወይም ሥልጣናቸውን ለመነካካት /እንደ ሥራአስፈጻሚው/ ቀኖና ወይም ዶግማ ማጣቀስ ከወቅቱ አለመመቸት አንጻር ጥቅሙ ብዙ አይመስለኝም። ከጊዜያዊ ድል አያልፍም ባይ ነኝ፤ በተለይ የሰሞኑ አካሄዳቸው «ያውግዙኝና እኔም አውግዤያቸው የራሴን ድርሻ እካፈላለሁ» ለማለት የፈለጉ ነው የመሰለኝ። ከዚህ አንጻር መፍትሔዎች በሚገባ መጠናት አለባቸው እላለሁ። በአማራጭነት ከሚቀጥሉት ሁለት መፍትሔዎች አንዱ ወይም ሁለቱ በጋራ ቢወሰዱ የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ። የውሳኔ ተግባራዊነት ላይ ተስፋችን ከጸና ሐውልቱን ለማፍረስ ማን ከለከለን? የሲኖዶስን ውሳኔ ተከትሎ ሃይማኖትን መጠበቅና ማስጠበቅ የሁላችን ሥራ አይደል? አታፍርሱ ብሎ ሊቃወመን የሚችል ሕጋዊ አካል አለ? ያው ስለፈራን ወይም ዘላቂ ስለማይሆን እንጂ።

መፍትሔ ፩ ሥራቸውን በየደቂቃው መከታተልና መቆጣጠር

ይኼ አማራጭ እጅግ አድካሚና ለቤተክርስቲያን መልካም ስም ሲባል ብቻ የሚደረግ እንጂ ቅድሚያ አይወስድም። በአንጻሩ ግን ግልጽ ሕግጋትና ቀኖና ላላት ቤተክርስቲያን ልበ ሰፊና ጥበበኛ የእሳቸውንም ተንኮል ቀድሞ የሚረዳ ሰው አብሮ ከሠራ የእሳቸውን ቁማር የሚበልጥ ጥበብ መጠቀም /በእሳቸው ላይ ቁማር መጫወት/ ሊባል የሚችል ነው። ይህም በዋናነት በቋሚ ሲኖዶስ፣ በሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ፣ በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በየሀገረ ስብከቱና የጠቅላይ ቤተክህነት አመራሮች ሊፈጸም የሚችል ሲሆን የሚራመዱበት እግራቸው የሚሰዱት እጃቸው ከሚገባው አልፎ በሥልጣናቸው ሥር ባሉ ጉዳዮች እንዳይደርሱ ለማድረግ ሳይሰለቹ መታገል ነው። እርግጡ ነገር ይኼ በመንፈሳዊው ዐውድ ብዙ የሚያስደስት ተግባር አይደለም፤ ተማምኖና አምኖ ለበረከት መሽቀዳደም ሲገባ አንዱ አጥፊ ሌላው ጠበቃ ሆኖ መሳደድ ያበሳጫል። በምን ዓይነት መድኃኒት በምን ያህል ወጪ የየዕለት ሕይወታቸውን እንደሚቀጥሉና እስከመቼ እንደሚያዛልቃቸው ባይገባኝም ቀናቸውን በሚያሳጥር ጋንግሪንና የጭንቅላት ዕጢ ከሌሎች ተደራራቢ በሽታዎች ጋር ለሚሰቃዩ ጳውሎስ እያንዳንዷን ደቂቃን በሰጠናቸው ቁጥር ለእኛ ባንረዳውም በፈጣሪም በሰውም የሚፈለግ ንስሐ ገብተው ወደልባቸው ተመልሰው ቢሞቱ ስለሚሻል ለአንድ ሰው ሲባል የሚከፈል ከባድ መሥዋዕትነት ነው። ያም ሆኖ ከታች በዘረዘርኳቸው ምክንያቶች ከሌላ ወገን የተላኩ የትሮይ ፈረስ ስለሚመስሉ ንስሐ ቢገቡ እንኳ የላካቸው አካል ደቂቃም ሕይወት አይሰጣቸውምና ይህ አማራጭ ጥቅሙ እምብዛም ሊሆን ይችላል።

መፍትሔ ፪ የፓትርያርኩን ጥፋቶች ለዳኝነት ማቅረብ

በ፲፱፻፺፯ ምርጫ ወቅት ይመስለኛል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ታይቶ ነበረ። በተደጋጋሚ በፕሮቴስታንትነት የተከሰሰው አሰግድ ሣህሉም ለግል ጥቅሙ ብፁዕ አቡነ ጢሞቲዎስን ፍርድ ቤት አቁሟቸዋል። ወንጀሎች በያይነቱ በሚጠቀሱባቸውና ከበቂ በላይ መረጃዎች በየአደባባዩ ሊቀርብባቸው በሚቻልባቸው ፓትርያርክ ላይ ለቤተክርስቲያን ሰላምና ጥቅም ሲባል ብቻ ክስ መመሥረትና በፍርድ ቤት እንዲታይ ማድረግ ለምን አይሞከርም? አዋጭ ይመስለኛል፤ አፈጻጸሙ ምንም ይሁን ምን። ይልቁንም ዝም በመባላቸው የተዘፈቁበትን ተራና ዘርፈ ብዙ የውንብድና ሥራ ቢያንስ ለማስቆም ከተሳካም ለቤተክርስቲያን ጥቅም የሚሆን ውጤት ሊያመጣ ይችላል። ምእመናኑን በየጊዜው የሚያስበረግገውና ጥርሱን ነክሶባቸው ከቤ/ክ ያራቀው አልጠግብ ባይ ዝርፊያቸው በምሁራንም ሆነ በሊቃውንት በግልጥ የታወቀ ነው። ተሿሚዎቻቸውም የሚያስፈጽሙት ይህንኑ አጠናክረው መሆኑን የአዲስ አበባና የታላላቅ አድባራትና ገዳማት ምእመናን የሚያውቁት የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህንም ወንጀል ማንኛውም ግለሰብና ቡድን ለሕግ ሊያቀርበው፣ መረጃውም ከየጓዳው ሊገኝ፣ የክስ ሂደቱም በፌደራል ፍርድ ቤቶች በቀጥታ ሊታይ የሚችል ምንም ቅድመሁኔታ የማይፈልግ ነው። ውሳኔውን ለዳኞቹ እንተወውና ፓትርያርኩ በሥልጣን ዘመናቸው ከሚከሰሱባቸው ጉዳዮች ጥቂቶቹን ለማንሳት እንሞክር።

ከባድ ሙስናዎች፣ ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ ከባድ የእምነት ማጉደል፣ በኃላፊነት ቸልተኛነት ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ። በዝምድናና አላግባብ ከሚሰጡ ቅጥር፣ ዝውውር፣ ዕድገት፣ ሹመትና ጥቅማ ጥቅሞች ጀምሮ ከመሥሪያ ቤቱ ዕቅድና ዓላማ ውጪ ለግላቸው ጥቅም የሚባክነው ግዙፍ መጠን ያለው የገንዘብ ዝርፊያ፣ ተያይዞም እሳቸው አላግባብ በሾሟቸው ሰዎች የሚፈጸሙ ሙስናዎች እሳቸውን ከሚያስጠይቁ ሙስናዎች ጥቂቶቹ ናቸው። ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም የመሥሪያ ቤቱን ጥቅም ከመጉዳት ጀምሮ በፓትርያርክነት ስም የበላያቸውንና የበታቻቸውን የሲኖዶሱንና የወከላቸውን መሪዎች ሥልጣን በመጋፋት የተሠሩ ሥራዎች ብዙ ናቸው። በፓትርያርክነት ሥልጣናቸው ሊያስጠብቁት የሚገባውን የቤተክርስቲያን /የመሥሪያ ቤታቸውን/ ጥቅምና ዝና የቤተክርስቲያን ወገን ወይም ወዳጅ ያልሆኑ ሲጠቀሙበት ዝም ማለትና ይህም በብዙ ምክረ ሀሳብ ሲቀርብላቸው እንዲዘነጋ ማድረግ አንዳንዴም መተባበር ለታመኑበትና ለተሾሙበት ሥልጣን ያልታመኑ እምነት አጉዳይ የሚያደርጋቸው ይመስለኛል። አሜን ብለው በተቀበሉት ኃላፊነት ላይ ተቀምጠው የማይገባውን ከመሥራት ባሻገር ሊሠሩት የሚገባውን ባለመሥራትም ምክንያት የተፈጠረ ጉዳት ካለ በቸልተኝነትና ኃላፊነትን ባለመወጣት መጠየቃቸው እውነታውን ሊያስገኝ የሚችል ዕድል አለው። ሌሎቹን እንርሳቸውና የሚከብዱትን የቸልተኝነት ጉዳቶች እንመልከት። ቤተክርስቲያንን በግልጥ ቋንቋ ሲዘልፉ የሚታዩ ግለሰቦችና መንግሥታት በዝምታ መታለፍ አልነበረባቸውም። አቶ ተፈራ ዋልዋ እንዳሉት ቤተክርስቲያን «የአማራና የጉራጌ ትምክህተኞች ዋሻ» ነች? የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ቤተክርስቲያን የዓለም /የአሜሪካ ስጋትና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ እኩልነት አደናቃፊ ልትባል ይችላል? ፒኤችዲያቸው ለዚህ መልስ አጣ? ብፁዐን አባቶች ያረፉበት የማያሳምን አሟሟት ሲደጋገም የሀገሪቱ ሕግ ምን ነበረ የሚለው? ለምሳሌ በአደባባይ እየታየ መኪና ገጭቶ የገደለውን ሰው እንኳ የሞተበትን ምክንያት በሕክምና ተቋም እንዲረጋገጥ ማድረግ በሚቻልበት ዘመን የአባቶች አሟሟት አለመመርመሩ አሳሳቢ ነው። ታመው በማያውቁት የጉበት በሽታ ለወሬ በማይመች ምክንያት ጉበታቸው አልቋል ተብለው ሳይመረመሩ የተቀበሩት አቡነ መልከጸዴቅ፣ ቅዳሴ እንዲገቡ ለመጋበዝና ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ውጪ ሀገር ለመጓዝ ብቁ የነበሩት ከሰዓት ከቅዳሴ ወጥተው ለሠርክ ጸሎት ሳይደርሱ ሞት ያጣደፋቸው አቡነ ይስሐቅ ፣ በሀኪሞች አስተያየት ቀላል የሚባለውና በተሳካ ሁኔታ የተከናወነው የሀሞት ጠጠር ቀዶ ጥገና አብቅቶ ከኦፕሬሽን ክፍል ከወጡ በኋላ ከሰመመን ሳይነቁ ያሸለቡት አቡነ ሚካኤል፣ በጤንነትና በሰላም መጽሐፍ ቅዱስ ለመተርጎም ከጉባኤ ቤታቸው መጥተው ባልታወቀ ምክንያት የቀሩት እነ ሊቀ ሊቃውንት መንክር፣ ማታ 11፡00 ሰዓት ድረስ ጤናማና ሰላም የነበሩት አዲሱ የቤተክህነት አደረጃጀት የአስተዳደር መምሪያው ተሿሚ ጠዋት እንዲቀብሯቸው ለቤተክህነቱ መርዶ ሲነገር በድምፅ አልባ ለቅሶ የተሸኙት አቶ ነገደ ስዩም ፣ ያው ፍንጩ ወደራሳቸው ጠቁሟል ተባለ እንጂ የ፳፻፩ዱ የአባቶች ቤት ሰበራና የአባቶች መደብደብ ቤተክርስቲያንን ወክለው ያሉ መሪዎች እንደመሆናቸው አሟሟታቸው ሳይጣራ መቅረቱ ከፍተኛ ቸልተኝነት ነው። ይህም ሁሉ ሲሆን ፓትርያርኩ የአንዳቸውን ሬሳ እንኳ ወደ ምኒሊክ ቢያስልኩ ምናልባት የቤተክርስቲያን ሥራ ሲሠሩ የጠላቸው አጥቅቷቸው ከሆነ ይታወቅና ለሌሎችም አባቶች ለራሳቸውም ጭምር ደህንነት የሚያግዝ መረጃ ይገኝ ነበረ። አሳማኝ ምክንያት ሊቀርብ የማይችልበት የ፲፮ ጳጳሳት በመኪና አደጋ ማለቅ፣ የቤተክርስቲያን መሪዋና ቸር ጠባቂዋ ለሆነ ፓትርያርክ ዝም ብሎ ለጥቂቶቹ ሐውልት በመመረቅና ሂዶ በመቅበር መታለፉ ከቸልተኝነትም በላይ ነው ብዬ አምናለሁ። እነዚህ ሁሉ ሲደማመሩ ለቤተክርስቲያንና መሪዎቿ በቂ ጠበቃ ባለመሆን ኃላፊነታቸውን ላለመወጣት ቸልተኛ ነበሩ ብሎ በሕግ ፊት እንዲዳኝ ማድረግ ቀጣይ ጥፋትን ይታደግ ይሆናል። ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠም ከቀኖናና ዘዴ ምርምር የቀለለ መፍትሔና ሥልጣናቸውን ወዲያው /by default/ ሊያሳጣ የሚችል ይሆናል።

ሲጠቃለል፡

እንግዲህ አንዱም አማራጭ በአንዴ የሚጠናቀቅ ስላልሆነ ሁለቱንም አማራጭ እያስኬዱ የቤተክርስቲያንን ጉዳት መቀነስና የበለጠ የችግሮቹ ዓይነት ግልጥ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል። በሂደትም የራሳቸውን መጨረሻ ሳያውቁ የሚላላኳቸውንና የሚራዷቸውን ሰዎችም መቀነስና ለቤተክርስቲያን የሚያግዙ ማድረግ ይቻል ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ሁላችንም የምንስማማው ግን ፓትርያርክ ጳውሎስ በቤተክርስቲያን ውስጥ የዘሩት እሾኽና አሜከላ በአጭር ጊዜ ተነቅሎ የማይጠናቀቅ፣ ነገር ግን እሾኽነቱን ከመኮነን ጀምሮ ለመንቀስና ለማረም ሰፊና አሠራር/ሀሳብ ላይ ያተኮረ /idea & system/ ሥራ መጠናከር እንዳለበት ነው። የየዕለት ጉዳዮችን /events/ ትኩረት ስንሰጥላቸውም ደስታቸው ወደር የለውም፤ ዓላማቸውን ከበጣም መጥፎ በመጥፎው እያጽናኑና ያልተተኮረበትን እያስፋፉ ዓላማቸውን /የትሮይ ፈረስነቱን ወይም የኑፋቄውን ካልሆነም የተራና ሌጣ ውንብድናውን/ ተግባር በበለጠ ዐቅም ሊሠሩት ስለሚችሉ። ምነው ኮራ ብለን የቤተክርስቲያንን በዳይ ለመፋረድ ሕጋዊ አማራጭን ብንጠቀም፤ ጥላቻችንን ወይም ቁጣችንን ለመግለጥ ድንጋይና የገማ ዕንቁላል መወርወር ወይም ይሁዳ ብሎ ብቻ መሳደብ የፈሪ ዱላ እንጂ እውነተኛ ፍርድ ፈላጊ አያደርገንም ብዬ አምናለሁ። ይቆየን።

8 comments:

Anonymous said...

ድንቅ ጽሁፍ! በእውነት በጣም ጥሩ እይታ ነው። የተነሱትን ሃሳቦች በደንብ ነው የምደግፋቸው ሆኖም ግን ወደ ተግባር ለመግባት በተለይ የአዲስ አባባ እንዲሁም መላዉ የኢትዮጵያ ምእመን በደንብ ሊወያይበትና የጋራ ግንዛቤ ሊይዝ ይገባል ባይ ነኝ። የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሄር ሁላችንንም በሃይማኖት ጸንተን ቤተክርስቲያንን እንድንጠብቅ ይርዳን።
መ.ዘ ከሽሮሜዳ

Anonymous said...

hasabu tiru new, tiyakew gin bikesesu feraju man naw? sewuyewunis man new amitito yaskeetachew? America's endelelechibet erigtegna nen woy? manen yizew yemigoriru yimeslachihual? yemilew new. wana meftihe kesiru menkel neber. Hulum ER gizew siders yihonal. Ersiwom tenagire yiwutalign sayhon ayikerm enji, tinish tezenagito yersiwonm mot endansema ER yirdan!!!

Anonymous said...

selam mk lemehonu enanete man nachehu aba sereke weyem abune fanueal belachehu metekesut ayee ahunema tenekabachehu ahun zim belachehu melekam sera seru yesew sim kematefat yibekachehu aba selama teru blog new endenanete sew mewenjel alebet malet new? yiker yebelachehu

Anonymous said...

It is good idea.Bertu

Anonymous said...

አኖኒመስ 3፡ አንተስ ማን ስለሆንክ ነው የተዘረዘሩትን ወንጀሎች እንዳይነገሩና ለሕግ እንዳይቀርቡ የምትቃወመው? የቤ/ክ ጠበቃ መሆንህ ነው?
ሕግ ዐዋቂዎችን ጠይቅ፡ ማንም ሰው ወንጀል ሲፈጸም አይቶ ማለፍ በራሱ የወንጀል ተባባሪነት ነው፤ ያስጠይቃል።

Anonymous said...

ግሩምና ትክክለኛ ጽሑፍ ነው ፀሐፊውን በጣም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ እንደተባለው ይህችን ቤተክርስቲያን ለማጥፋት ከወዲህ ወዲያ ለሚባዝኑት አጥፊዎች እግዚአብሔር አስተዋይ ልቦና ይስጣቸውና ወደራሳቸው ተመልሰው ምን እየሠራን ነው ብለው ራሳቸውን ለመጠየቅ ያብቃቸው፡፡ የዚህ ጥያቄ መልስ እውነትም ጤነኛ አእምሮ ላላቸው የሕሊና ቁስል ሆኖባቸው ወደንስሐ እንዲመለሱ የሚጋብዛቸው ነው፡፡ ወደ እርምጃ አወሳሰዱ በምንመጣበት ጊዜ ከጅምሩ ፓትርያርክ ሳይሞት ፓትርያርክ አይሾመም እውነተኛ ሰው ቢሆኑ ኖሮ አልሾምም ባሉ ነበር ነገር ግን ይህች ሁሉ በዕቅድ የተያዘች ስለነበረች ይህችን ጥፋት አድርሰው ወደማያልፈው ዓለም ለመሄድ በመጣደፋቸው ራሳቸውን ጐድተዋል፡፡ አጋፊሪዎቻቸውም አልጠቀሙአቸውም ገንዘብ እንደሆነ የትም አያደርስም ለጊዜው ሁሉን ነገር ሊያደርግልን ይችላል ብለን ብንገምትም ውጤት አልባ ነው በገንዘቡ ደስተኞች የሆንን ስንቶቻችን ነን ያውም መበለቲቱ ድሃዋ ከመቀነትዋ ፈትታ ለአምላክዋ መብዓ ያገባችውን እንዲህ ቅጥ ባጣ መልኩ ሲወድም እግዚአብሔር ዝም ያለ ቢመስል መልሱን እኮ በብዙ መልኩ እየሰጠ ነው እስኪ ጤናችንን፣ ሰላማችንን ፍቅራችንን እንየው የተሟላ ነው እንዴ? አይደለም አይዋሽም፣ ከሁሉም የሚከብደው ስንሞት የነፍሳችን አወጣጥ ጣር እንኳን ይለያል ሌሎች ቅዱሳን አባቶቻችን ተለይተውን ቢያልፉም እንኳን አሟሟታቸው ቅጽበታዊ ቢመስለንም አምላካቸውን ሳያማርሩ ጻራቸው ሳይበዛ ሄደዋል እግዚአብሔር በቀኙ ያቁማቸው፡፡ የአጥፊዎች አባቶችን ሞት ለማየት ያብቃን ከአምላካቸው አንዴ ተጣልተዋል እንደገና ደግሞ ሞታቸውን በመናፈቅ አልጋ ላይ ሆነው ዳግም ይጣሉታል ስለዚህ ይሄንን በማሰብ ከወዲሁ ራሳቸውን አርመው እግዚአብሔርን ይቅርታ ጠይቀው ቤተክርስቲያናቸውን ጠብቀው አስጠብቀው ፍቅረ ንዋይን አስወግደው የሕዝብን ፍቅር ታድለው ቢኖሩ ለራሳቸው ስለሚበጃቸው አጋፊሪዎቻቸውን በቅድሚያ አስወግደው ቀስ እያሉ ነገሮችን ወደ ትክክለኛው ቦታዎቻቸው በመመለስ፣ ለንስሐ ራሳቸውን በማብቃት ብልጥ መሆን አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ ፍርድ ቤት ለቤተክርስቴያን መፍትሔ አይደለም፡፡ እንደተባለው ማን ማን ላይ ይበይናል፡፡ ሁሉ በእጃቸው ሆኖ እኮ ነው ይኸው ሁሉ ጥጋብ ቶሎ ወደ ፌዴራል መደወል ነው እኮ መፍትሔ ብለው የያዙት የተማመኑትን ተማምነው ይህ ደግሞ ከዓለም ነው ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር ናት ፍርዷም ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ቤተክርስቲያንና ገንዘብ እኮ አይተዋወቁም ነበር፣ ካህኑ ፍቅረ እግዚአብሔር ኖሮት ነበር በነፃ ለዘመናት ሲያገለግል የነበረው ለደሞዝ ሳይሆን ለእውነተኛ አገልግሎት፣ ጳጳሳትና ገንዘብም እኮ አይተዋወቁም ምን ሊሠራላቸው እነሱ እኮ ዓለምን ንቀዋት ሁሉን ትተው ያሉ ሰዎች ናቸው ተሳስተው አሳሳትዋቸዋልና ሲሞቱም ወራሽ አለን ብለው ብቅ ይባልም ሊጀመር ጭራሽ አይገባም እኮ ኧረ እስኪ ቀና ብለን ወደ ላይ እናንጋጥጥ እነሱ እኮ የእግዚአብሔር ሆነው ነው መኖርም ያለባቸው ገንዘባቸውም ወደገጠሪቷ ቤተክርስቲያን ሄዶ ይሰራበት እንጂ አቤቱ አምላኬ ለሁሉም ልቦናን ስጥልን ቤተክርስቲያችንን ጠብቅልን፣ ፍርድህን አታጓድልብን ቶሎ ተመልከተን፡፡

ፍቅረ ተዋህዶ፣ ከቂርቆስ

Anonymous said...

አሳማኝ ምክንያት ሊቀርብ የማይችልበት የ፲፮ ጳጳሳት በመኪና አደጋ ማለቅ፣ የቤተክርስቲያን መሪዋና ቸር ጠባቂዋ ለሆነ ፓትርያርክ ዝም ብሎ ለጥቂቶቹ ሐውልት በመመረቅና ሂዶ በመቅበር መታለፉ ከቸልተኝነትም በላይ ነው ብዬ አምናለሁ።

Habib le ethiopiyam said...

የቤተክርስቲያናችን ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍተናው የከፋ መሆኑ ለሁሉም የቤተክርስቲኒቱ ልጆች ግልጽ ነው። የከፋ የሚያድርገው ወልዳ አሳድጋ ለዚህ ሰማያዊ ወምድራዊ ክብር የአበቃቺው መሪዋ ለእምነቷ፣ እድገቷና አንድነቷ ሳይሆን ይህንን አፍራሽና አጥፊዎቿ ለሆኑ እኩይ ስዎችና ማኅበራት የቆመ መሆኑ ነው። ታዲያ መፍትሔው ምን ይሁን? የተለያዪ አስተያያቾች ተሰንዝረዋል። በኔ በኩል በተናጥል ከምናድርገው ሩጭና ቁጭት የልቅ በአንድነት የምናድርገው ውጤት ሊያመጣ ስለሚችል ማድረግ አለብን ብዬ የማስባቸውን እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ።
1. በቤተክርስቲያንችን ላይ በተጋረጠው ፋተና ያለንን ስጋትና አቋማችን (የመፍትሄ ሃሳቦችን ጭምር) ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለሁሉም አህጉረ ስብክቶች፣እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ለገዳማት፣ ለአጥቢያ ቤ/ያን ሰበካ ጉባኤና ሰ/ት ቤቶች ድረስ ማድረስ።
2. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን በሚመለከት በተጨማሪ ፕሬዜዳንት ለሆኑባቸው የአለም አብያተክርስቲያናት ጽ/ቤት በቤተክርስቲያናችን እየሰሩ ያለውን እኩይ ተግባር በመግለጽ ለቦታው የማይመጥኑ መሆኑን እንዲታወቅ መግለጽ። ይህንንም በተራ ቁጥር 1 ለተገለጹ አካላትም ጭምር ማሳወቅ፣
3. በሀገር ወስጥ ሆነ በውጭ ያሉ ምዕመናንና የሰ/ት/ቤት ወጣቾች በሰላማዊ ሰልፍ በአቡነ ጳውሎስ ሃይማኖታዊና አስተዳዳራዊ አመራር ላይ ያለንን ስጋት መግለጽ፣
4. እንደያ ሃቅማችን ያምንችል ሁሉ ሱባኤ ከማያዝ በተጨማሪ በጋዳማት የሚኖሩ አባቶቻችን ቤተክርስቲያናችንን በሚመለከት የተለየ ሱባኤ እንዲይዙ መላክ፤ ለዚህም መባዕ ማዘጋጀትና መላክ፣
5. በዚህ ተግባር ውስጥ ጥያቄያችን ቤተክርስቲያናችንን ብቻ የሚሚለከት እንጂ ምንም ፖለቲካዊ ይዘት የሌለው መሆኑን በተራ ቁጥር 1 ላይ ከምንገልጸው ይዘት ጋር ለመንግስት አካላት በመገለጽ የልቁንም መንግስት የችግሩን ምፍትሔ በማፈላለግ ሂደት ላይ ተባባሪ እንዲሆን መጠየቅ፣
6. ይህንን የሚያስተባብር ኮሚቴ በሀገር ቤት፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በሌሎችም ክፍላታ አሃጉራት ማቋቋም። ይህም ኮሚቴ ይህንን መነሻ በመያዝ ሌሎች ስልቶችን በመቀየስ ለቤተክርስቲያን አንድነትና ሰላም ማድርግ ያልብንን እየቀየሰ ቢያሳውቀን አፋጻጻሙንም ቢከታተል፣
በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ የምፈልገው የቤተክርስቲያናችን ችግር የአንድ ግለሰብ ወይንም ማኅበር ሳይሆን እያንዳዳችንን የሚመለከት የሁላችንም ጉዳይ መሆኑን ሁላችንም በማጤን ሁላችንም ይመለከተኛል በማለት ተሳታፊ እንድንሆን በቤተክርስቲያናችን አምልክ ስም በዚች ከሁሉ በምታንስ አንደበቴ አደራ እላለሁ።
የሚጨመር፣ የሚስተካክልና መቅረት አለበት የሚባል ሃሳብ ካለ እና አሁን እንዲት እንጀምረው የሚለውን እንድንወያይ ክፍት አድርጌዋለሁ። ለዚሁ ውይይት ደግሞ ደጀ ሰላም፣ ገብረ ሄር፣ አሃቲና ሌሎቹም ለቤተክርስቲያናችን ተቆርቋሪ ብሎጎች ተባባሪ እንዲሆኑ በምንወዳትና ሌት ተቀን በምታሳስበን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ስም እጠይቃለሁ።
የቤተክርስቲያናችን አምላክ መነሳሳቱን እንዲሰጠንና ፍጽሜያችንን እንዲያሳምርልን የቅዱሳኑ ሁሉ ልመናና ምልጃ አይለየን። አሜን።