Thursday, December 29, 2011

ለብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የተላከ መልዕክት


  • “እኛን ከጠላችሁ ለምን ቤተ ክርስቲያን ትመታላችሁ እዛው በየቤታችሁ መቅረት ትችላላችሁ”
  • “ብትፈነዱ እንደ እኛ ካህን ጳጳስ አትሆኑም”
  • “እኔ ተምሬ ዶክተር ፕሮፌሰር መሆን እችላለሁ እናንተ ግን ካህን ጳጳስ መሆን አትችሉም”
  • “ስትወለዱም ስትሞቱም ያለ እኛ አይሆንላችሁም የአህያ ሥጋ አደላችሁ አትጣሉም …”
  • “ማፈሪያ ማፈሪያዎች ናችሁ … ማፈሪያዎች”

እኛ በምንገለግልበት እና በምናገለገልበት የዋሽንገተን ዲሲ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በተደጋጋሚ አውደ ምሕረቱን የራስን ዲስኩር ፣ ዝና፣ ስድብ ፣ፓለቲካ መናገሪያ ሳይሆን ወንጌል መስበኪያ፣ ቃለ እግዚአብሔር መማሪያ ይሁን ብለን ብንጮህ የሚሰማን ስላጣን የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ሁሉ ችግራችን እንዲሰማን ለማሳሰብ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሰባኪም ይሁን ካህን ወይም ጳጳስ ለሕዝቡ ሊያስተላልፍ የፈለገው አስተዳደሪያዊ መልዕክት ካለ ወንገል የሚሰብክ አስመስሎ ሕዝቡን የሚያሳዝን ወቀሳ አይሉት ስድብ የመሰለ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ወንጌል ከሆነ በአውደ ምሕረት፣ የግል መልዕክት ወይም አስተዳደራዊ ጉዳይ ከሆነ ደግሞ ለይቶ በአዳራሽ ማድረግ ይገባል፡፡ ሁል ጊዜ ቦርዱና ካህናቱ የሚፈልጉትን ተናግረው ሕዝቡ እንዳይናገር ይገድባሉ:: ሕዝቡ ግን በአውደ ምሕረት ላለመናገር እግዚአብሔርን መፍራት ይዞት ዝም ይላል፡፡ ክርስቶስ ለዚህ ነው ቤተ የጸሎት ቤት ናት እንጂ የራስ ዲስር መደስኮሪያ፣ የግለሰብ ዝና ማውሪያ፣ የነጋዴዎች መነገጂያ አይደለችም ብሎ በጅራፍ እየገረፈ ከቤቱ ያስወጣቸው፡፡


በዲሲ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ቦርድ ለመምረጥ የሁለት ዓመት የፍርድ ቤት ውጣ ውረድ ከፈጀብን በኋላ በማን አለብኝነት በሕዝብ ተመርጠው የገቡት ተጨማሪ አስመራጮች ችግር አለ መፍትሔ ስጡን ብለው ከቦርዱ፣ ከካህናት እና ሰንበት ት/ቤቶች ጥምረት መፍትሔ እየተጠባበቅን፤ ቦርዱ መርጦ ያስቀመጣቸው ጥቂት አስመራጮች ስራውን አጠናቀናል ብለው እነሱ የማይፈልጉትን እጩ ሁሉ ከውድድሩ አስወጥተው ምርጫው ተጠናቀቀ አሉን፡፡ የሕዝቡን ድምጽ አፍነው በልተዋልና እግዚአብሔር ይፍረድባቸው ብለን ዝም ስንል፤ አቡነ ፋኑኤል (የቀድሞው አባ መላኩ) በአደባባይ ምን ታመጣላችሁ አይነት ስድባቸውን ወንጌል ላስተምር ብለው ባሳለፍነው እሁድ ሲሰድቡን አረፈዱ፡፡ ወገን እስከመቼ ነው የምንታገስ? … ማነው በቃችሁ የሚላቸው???

ለቦርዱ የተመረጡትን 8 ሰዎች (አብዛኛዎቹ ቦርዱ እና አጋሮቹ)፣ 4 የካህናት ተወካዮች ቃል ለማስገባት ብለው መድረኩን የያዙት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል “ድምሩ ዜሮ ለሚሆን ነገር ያለአግባብ ፍርድ ቤት ሄዳችሁ” ብለው ፍትሕ ለተጠማ ወገናቸው የሚያጽናና የእግዚአብሔር ቃል እንደማቀበል የስድብ እሩምታ መግበውታል፡፡
እኛ አባት አለን ብለን ነጻ ምርጫ ይኑር፣ በቤተ ክርስቲያኑ ተጠያቂነት ያለበት አሰራር ይፈጠር፣ በአዳራሽ እየሰበሰባችሁ አወያዩን ብለን ለጠየቅነው ጥያቄ “ቦርዱ መልስ ነፍጎናል እና እርሶ መፍትሔ ይስጡን” ብለን ብንጠይቆ “እኔ ቤተ ክርስቲያኑን አስረክቤያችሁ ሄጃለው እና አይመለከተኝም” ነበር ያሉት የዛሬ ዓመት ገዳማ፡፡ ይህ ጵጵስና ማዕረግ ከደረሰ አባት አይደለም በመካከላችን ካሉ ሽማግሌዎች የማይጠበቅ  መልስ ነው፡፡ በዚህም ሳይጸጸቱ አሁን ደግሞ ለምን ፍርድ ቤት ሄዳችሁ ብለው መሳደቦ ቅሌት ነው፡፡ ፍትህ ፍለጋ የሚሰማን ብናጣ ወዴት እንሂድ … እድለኛ ብንሆንማ እርሶ መፍትሔ ይሰጡን ነበር፡፡ ነገር ግን ቦርዱ እርሶ ባሉበት ቦታ ሆነው ያንቀሳቅሱት ስለነበር መልሱ አንድ አይነት ሆነ፡፡ ፍትህ ፍለጋ ሰብስቡንና አወያዩን፣ ሃሳባችንን እንግለጽ፣ በአውደ ምህረት ወንጌል ብቻ ይሰበክ፣ የአስተዳደር ጉዳይ በአዳራሽ እንወያይ ብንል እድል አልተሰጠንም:: አባት አለን ብለን ፍትህ እንዲሰጡን ብፁዕነቶን ብንጠየቅ… አይመለከተኝም ሲሉን ፍርድ ቤት ሄድን፡፡
አይመለከተኝም ባሉበት ቤተ ክርስቲያ ግን “የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ሆኜ መጥቻለውና ከሰራሁት ቤቴ ማንም አያስወጣኝም” ብለው ስለ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ማስተማር ሲገባዎ ስለራስዎ አስተመሩን፡፡ ቤቱስ የእግዚአብሔር እጂ የማናችንም እንዳልሆነ ልብ ይበሉ፡፡

ብፁዕነቶ ይህ ሁሉ ሳይበቃዎት “እኔን ከጠላችሁ ለምን ቤተ ክርስቲያን ትመጣላችሁ እዛው በየቤታችሁ መቅረት ትችላላችሁ” አሉን፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምንመጣው እኮ እግዚአብሔርን ፍለጋ ነው እንጂ እናንተን ለማየት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የሰጣችሁ ክህነት የምትፈልጉትን ልትጠሩበት ሌላውን ደግሞ ቤታችሁ ቅሩ ሊሉበት ነውን?፡፡ በጎቹን፣ ግልገሎቹን፣ ጠቦቶቹን ጠብቁ አለ እንጂ አባሩ ተብሎዋል እንዴ?፡፡ ብዙ የተጋደሉ ሐዋሪያቱ እንኳን እኛ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን አሉ እንጂ “ብትፈነዱ እንደ እኛ ካህን ጳጳስ አትሆኑም ” ብለው በሕዝብ ላይ አይደለም በአሕዛብ ላይ አልተዘባበቱም፡፡ … ምን አይነት ዘምን መጣ ወገን … በአውደ ምህረቱ “እኔ ተምሬ ዶክተር ፕሮፌሰር መሆን እችላለሁ እናንተ ግን ካህን ጳጳስ መሆን አትችሉም” ብለው በሕዝቡ ላይ ሲቀልዱ እና ሲያሽማጥጡ ምነው ወንጌሉ ጠፋዎ፡፡ ምን አልባት ካህን ጳጳስ ብቻ ሳይሆን እንደ ተክልዬ ቅዱስ ጻድቅ የሚሆኑ ሕጻናት እና ወጣቶች ልጆቻችን በመካከላችን እንዳሉ ዘንግተውት ነውን፡፡ ነገሩማ እንኳን 20 ዓመት እና ከዛም በላይ ጠንክሮ መማር የሚጠይቅ ዶክተር ፕሮፌሰር መሆን አይደለም ተራ ሞያተኛ ለመሆንም የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ዘነጉት፡፡
“ስትወለዱም ስትሞቱም ያለእኛ አይሆንላችሁም የአህያ ሥጋ አደላችሁ አትጣሉም …” ይህንን ቃላት ከአንድ መነኩሴ መንጋውን እንዲጠብቅ አደራ ከተሰጠው ጳጳስ ይቅር እና ከእኔ ቢጤ ወንበዴም አልጠብቅም ነበር:: ትዕቢት “የኃጢያት ሥር ናት” ብላችሁ ያስተማራችሁን እናንተ ናችሁ፡፡ ለነገሩ ምን አለብዎ ቢታበዩ ይህ ለመንፈሳዊ ሰው የሚገደው እንጂ አለማዊ ለሆነ አይደለም፡፡ መንፈሳዊ የሆኑት አባቶቻችን መነኮሳትማ ደሞዛቸው ለተቸገሩ እየረዱ ለታረዘ እያለበሱ ሕይወታቸውን ኖሩ እንጂ ሁለት ሶስት የተንጣለለ ፓላስ/ቤት ለራሳቸው ሰርተው አላከራዩም፡፡

እርሶ ብቻ ቤተ ክርስቲያኑን የሰሩ፣ እርሶ ብቻ ሞርጌጅ እንደከፈሉ ደጋግመው ሲናገሩት ያሳዝናል:: እግራችን እስኪንቀጠቀጥ ቆመን ሰርተን ያመጣነውን ገንዘብ ሳያሳዝነን ለቤተ ክርስቲያን የሰጠን እኛ ምዕመናን እኮ ነን፡፡ የሚያሳዝነው እኛን በአንድ ቤተ ክርስቲያን የምንገኝ አብረነዎት የሰራን ልጆች አንድ ማድረግ ሳይችሉ እንዴት  ሰሜን አሜሪካን ሊመሩ የመጡት?፡፡ “ማፈሪያ ማፈሪያዎች ናችሁ … ማፈሪያዎች” እያሉ ከዱርዬ እንኳን የማይጠበቅ ቃላት ሲደጋግሙት እኛ በንዴት አንድ ቃል እንድንናገር እና በፓሊስ ለማባረር እንደሆነ ይገባናል፡፡ “እዛው በየቤታችሁ ቅሩ” ያሉንም ለዚሁ ነው፡፡ እኛ ግን ከእግዚአብሔር ቤት ወዴትም አንሄድም ይልቁንም ጳጳስ ነዎት ብለን የሸፋፈነውን ጉድ ማውጣት ካስፈለገ አውጥተን በህግ ሁላችሁንም እንፋረዳለን፡፡ የተዘረፈው ገንዘብ፣ የደማው ልብ ሁሉ ይቅርታ ጠይቃችሁበት መፍትሔ እስካልሰጣችሁት ድረስ ሕግ እንዲገዛችሁ ያስፈልጋል፡፡
አሁንም የእግዚአብሔር ቤት የጸሎት እና የእምነት ቤት ናትና የራሳችሁን ዲስኩር በአውደ ምሕረቱ ከመስበክ ተቆጠቡ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ አስተምሩን፡፡

ከተቆርቋሪዎች ምእመናን

6 comments:

Anonymous said...

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።

የአባቶች ከሳሽና የወንድሞች ከሳሽ የሆነው የፈሪሳዊያን ማህበር \ማቅ\ ነው ይህችን ደብዳቤ ያቀነባበራት። መቼም ሰላም
የማይወድ ማቅ፤ካልከሰሰና ካልበጠበጠ በቀር ያገለገለ የእፉኝይት ልጅ፤ ብፁእ አባታችን እንደሆነ እውነቱን ከመናገር በቀር እንደ እናንተ አይነቱን ሽምቅ ሐይማኖተኛ መሳይ፡ እግዚአብሔር ነው የሚዋጋላቸው። ማቅ ግን በንፁሃን ምዕመናን ሥም ባትነግዱ መልካም ነው። በሰላም ክርስቲያኖች ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይሄዱና በረከት እንዳያገኙ አለቃችሁ ዲያቢሎስ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ነገር ግን የመውጊያውን
ብረት ብትቃወም ላንተ ይብስብሃል ነው የተባለው። ደግሞስ እናንተን የሚቀበል፤ እኔን ይቀበላል አይደል እንዴ ለአባቶች ጌታ በቃሉ የተናገረው ብቻ እናንተ መስሚያ ጆሮ የላችሁም፡ ምን ያደርጋል ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ ያሳዝናል። ደስ የሚለው ግን ምዕመናኑ አሁን እናንተ ማን እንደሆናችሁ በደንብ ከገባው ቆይቱአል። ከአሁን በሁላ ምንም አይነት የጠላት ወሬ ቢመጣ አንቀበልም። ለእናንተ ግን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማስተዋል ልቦና ይስጣችሁ።


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

desa said...

good job!!!

Anonymous said...

በእውነት የብፁዕ አቡነ አብርሃም አባታዊ ፍቅርና ትምህርት በሰማንበት ጆሮ የአቡነ ፋኑኤልን ንግግር በቅዱስ ሚካኤል በዓለ ንግስ ላይ በመስማታችን በጣም አሳዝኖናል በእውነት በዲሲና በአካባቢው ላለን ምዕመናን እውነተኛና ትክክለኛ የቤተክርስቲያንን ቅኖና የሚያስጠብቅ አባት ስለሚያስፈልገን እውነተኛውን እረኛ እግዚአብሄር እንዲልክልን ሁላችንም በፀሎት መትጋት ያስፈልገናል ለዚህም እግዚአብሄር ይርዳን ::

Anonymous said...

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን::
በእውነት የብፁዕ አቡነ አብርሃም አባታዊ ፍቅርና ትምህርት በሰማንበት ጆሮ የአቡነ ፋኑኤልን ንግግር በቅዱስ ሚካኤል በዓለ ንግስ ላይ በመስማታችን በጣም አሳዝኖናል በእውነት በዲሲና በአካባቢው ላለን ምዕመናን እውነተኛና ትክክለኛ የቤተክርስቲያንን ቅኖና የሚያስጠብቅ አባት ስለሚያስፈልገን እውነተኛውን እረኛ እግዚአብሄር እንዲልክልን ሁላችንም በፀሎት መትጋት ያስፈልገናል ለዚህም እግዚአብሄር ይርዳን ::

Anonymous said...

One day God may Give solution for such type of fathers because they are not depend on God rather they depend on their assets.

Anonymous said...

One day God may Give solution for such type of fathers because they are not depend on God rather they depend on their assets.