Friday, March 23, 2012

ገዳመ ዋልድባን ለመታደግ የፖለቲካ እና የብሔር ልዩነቶቻችን ሊያግዱን አይገባም!!!

 READ IN PDF
እምነት የለሹ ትውልደ ኮሚኒስት  ቤተ ክርስቲያናችን ማሳደድ አሁንም አላበቃም:: አለመታደል ሆነና በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ የሚገኙ አባቶቻችን ሐዋርያዊ አደራቸውን ተቀብለው ቤተ ክርስቲያን ከመጠበቅ እና ከማስጠበቅ ይልቅ ትውልደ ኮሚኒስትን በመተባበር ቤተ ክርስቲንን እየተዋጓት ነው:: የሀገር ቤቶቹ አባቶች ከዘመነኛው መንግስት ጋር ተሰልፈው የቤተ ክርስቲያንን መብት ማስከበር አቅቶዋቸዋል:: በውጪ ሀገር የሚኖሩት አባቶች ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ህልውና ከመቆም ይልቅ ለፖለቲከኞች ህልውና በመቆም ቤተ ክርስቲያንን ለተሐድሶ መናፍቃን አሳልፈው ሰጥተዋል::  ከዚህ በፊት ኮሚኒስታዊው ኢትዮጵያዊ ትውልድ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሚል አንድ ጽሑፍ አቅርበን ነበረ:: ጽሑፉን ይህንን በመጫን ያንብቡ::

አሁን በገዳመ ዋልድባ እየተካሄደ ያለው የዚሁ የኮሚኒስቱ እምነት የለሹ ትውልድ ውጤት ነው:: እንግዲህ “የአባቶቼን ርስት አሳልፌ አልሰጥህም” በማለት የተነሳው ይሄኛው ወጣቱ ትውልድ የቤተ ክርስቲያን እሴቶች ጠብቆ ለማቆየት ከኮሚኒስቶቹ ጋር ትግል ገጥሞዋል:: በቀደሙት አባቶቻችን አምላክ ረዳትነት የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስጠበቅ የተሰለፈው ትውልድ ያሸንፋል ብለን እናምለን:: እውነት ሁሌም አሸናፊ ናትና::
 ገዳመ ዋልድባ ለመታደግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ለዘላቂው መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ እስከመጨረሻው ተስፋ ባለመቁረጥ የገዳማውያኑን አባቶቻችን ጮኸት ማስተጋባት አለብን የሚል አቋም አለን::

የመጨራሻው መፍትሄው እስከ ምን ድረስ መሆን አለበት?

መፍትሄው መሆን ያለበት የተጀመረው ግንባታ ለጊዜው መቆም አለበት ብለን እናምለን:: እስከ መቼ ድረስ ይቁም? ቢባል ጉዳዩን የሚያጣራ የሥነ ተፈጥሮ እና የቅርስ ጥበቃ የምሁራን ቡድን ተቋቁሞ ከገዳማውያኑ አባቶች ጋር እየተመካከረ የስኳር ፋብሪካው በገዳሙ ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ አያደርስም የሚል ትንታኔ እስኪሰጥበት ድረስ መቆም አለበት:: ይህ ደግሞ መንግስትን ተሸናፊ አደርገውም:: የሚቋቋመው የምሁራን ቡድን የቦታው ተፈጥሮአዊ ይዘት ተጠብቆ እንዲቆይ የሚገነባው ፋብሪካ “በስንት ኪሎ ሜትር እርቀት” መሆን አለበት የሚለውን ዝርዝር ጥናት እስኪያቀርብ ድረስ ግንባታው ለጊዜው መቆም አለበት:: ይህ እስኪሆን ድረስ የፖለቲካ እና የብሔር ልዩነቶቻችን ትተን የገዳማውያኑን አባቶችን ድምጽ ለሚመለከተው ሁሉ ማሰማት አለብን በማለት አሐቲ ተዋሕዶ አጥብቃ አደራ ትላለች::
   
                    እግዚአብሔር አሐቲ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን!!!


                                      +++
                           ኮሚኒስታዊው ኢትዮጵያዊ ትውልድ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን
“የራሱን ሀብትና ማንነት የማያከብር ሕዝብና ተቋም በቁሙ የሞተ ነው” በሚል በነመራ ዋቀዮ ቶላ የቀረበውን ጽሑፍ ሳነብ ልቤ እጅጉን ተነክቷል። ይህንኑ የደጀ ሰላም ጦማሪ ሀሳብ መነሻ በማድረግ እኔም መጦመር እንኳ ባልችልም ስሜቴን ግን ለመግለጽ ብዕሬን ለማንሳት ተገድጃለሁ። ባለፉት 40 ዓመታት ቤተ ክርስቲያናችን የአስኳላውን ትምህርት ተምሬያለሁ በሚለው በማርክሳዊና በሌኒናዊ ትውልድ እጅጉን ተፈትናለች። እንዲሁም አሁንም ‘በተረፈ’ ኮሚኒስቶች እየተፈተነችም ትገኛለች።

ማርክሳዊ እና ሌኒናዊ ፍልስፍና ምንም እንኳ በየክፍለ ዓለማት የሚገኙት የእምነት ተቋማት በሙሉ (ከእስልምና በስተቀር) ፈተና ቢሆንም፤ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን የተፈተነ ያለ አይመስለኝም። ሌኒን ተወልዶ ያደጉባት እንዲሁም ለዚሁ ፍልስፍና መሠረት የሆነችው ሀገር ሩሲያ ወይም ‘የሩሲያ ቤተ ክርቲያን’ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አልተፈተነችም ቢባል ማጋነን አይሆንም። እንግዲህ ትውልዱን ለመውቀስ አቅሙም ችሎታውም የለኝም፤ ነገር ግን ታሪክ በራሱ ጊዜ ይወቅሳቸው ይሆናል። የዚሁ ጽሑፌ ዋና ዓላማ ግን ‘ተረፈ’ ኮሚኒስቶች ከቤተ ክርስቲያናችን ላይ በትራቸውን እንዲያነሱ ለማስገንዘብ ነው። ቤተ ክርስቲያን ይህንን ትውልድ በማጣቷ ለሁላችንም የእግር እሳት ቢሆንብንም አሁንም በዚሁ ዘመንም ቤተ ክርስቲያኒቱን ማሳደድ አላማቆሙም እንዲሁም ደግሞ ሁለተኛ ትውልድ እንድናጣ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ግን የበለጠ ያበሳጨኛል።

ለመሆኑ ኮሚኒስቱ ትውልድ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰው ጥፋት ሳያንሰው አሁንስ ቢሆን ምን እያደረሰ ነው? እስቲ ከብዙ በጥቂቱ፦

1.     በማርክሳዊና ሌኒናዊ ፍልስፍና የተዋጠው ትውልድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፓትርያርክ ጨምሮ አያሌ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በግፍ ገድሏል፤ አስሯል፤ አሳዷል። በዚህም ብቻ አላበቃም። ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዘመናት ያፈራችውን ንብረትና ሀብት ወርሷል፤ በብዙ በገንዘብ የማይተኩ ንዋያተ ቅድሳት ዘርፏል።

2.  የቀድሞው የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበራቸው እንዲወርዱና እንዲሁም ከወረዱ በኋላም ከሀገር እንዲሰደዱ አድርጓል። የመጀመሪያው ኮሚኒስት የደርግ መንግሥት ፓትርያርኳን በግፍ ገደለ፤ሁለተኛውና ወይም አሁን ያለው ኮሚኒስቱ መንግሥት ደግሞ ፓትርያርኳን ከመንበራቸው እንዲወርዱ አደረገ። እንግዲህ ቅዱስ ፓትርያርኩ ከመንበራቸው ከወረዱ በኋላም ተቀማጭነቱ ሀገረ አሜሪካን ያደረገው ሌላኛው ኮሚኒስት ቡድን ደግሞ ቅድስት ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል። ከተሰደዱ በኋላም የራሳቸው ሲኖዶስ እንዲያቋቁሙና ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለት እንድትከፈል እዚሁ አሜሪካን ሀገር ያሉት ‘ተረፈ’ ኮሚኒስቶች በአማካሪነትና በዋና ተዋናይነት አስተዋፅዖ አድርገዋል።

3. አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ‘ተረፈ’ ኮሚኒስት ቡድን ቤተ ክርስቲያንን ማሳደድ አላቆመም። ባለሥልጣናቱ ቤተ ክርስቲያን የሌላትን ተቀጽላ ስም እየሰጡ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነፍጠኞች ዋሻ ናት” በማለት ሲያንቋሽሹ ሰምተናቸዋል። እንዲሁም ልጆቿዋ በተለያዩ አካባቢዎች በአክራሪው የእስልምና ቡድን በግፍ ሲታረዱባት ተገቢውን ፍርድ ሳያገኙ ቤተ ክርስቲያንን “ምንም አታደርገንም” ብለው በዝምታ አልፈውታል። እነዚህ ኮሚኒስት ባለሥልጣናት በዚህ ብቻ አላቆሙም። ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ያበረከተችውን በርካታ አስተዋጽዖ ወደ ኋላ በመተው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለኢትዮጵያ ድህነት ቤተ ክርስቲያንን ተጠያቂ ሲያደርጉ እንሰማቸዋለን።

4. ይኸው ኮሚኒስቱ ትውልድ በውጪው ዓለም በተለይም በአሜሪካን ሀገር ቤተ ክርስቲያን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ እንድትመራ አድርጓል። ቤተ ክርስቲያን ያስቀመጠችውን ከራሷ ቀኖና ወይም ‘ከሰበካ ጉባዓኤ አስተዳድር’ ውጪ ቦርድ የሚል ስያሜ በመስጠትና እንዲሁም ገለልተኛ አስተዳደር በሚል ተቀጽላ ቤተ ክርስቲያን እንዲቋቋም አድርጓል። ይህም ብቻ አይደለም ኮሚኒስቶቹ በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት የግላቸው ቤተክርስቲያንም አቋቁመዋል።

ከላይ እንደጠቀስኩት አሁንም በድጋሚ መጥቀስ የምፈልገው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ እነሱን ለመውቀስ አይደለም። ነገር ግን የዚሁ ፍልስፍና ተዋናዮች እያወቁም ሆነ ሳያውቁ እያደረጉት ያለውን ጥፋት እንዲያቆሙ ለመማፀን ነው። በስደት ላይ የሚገኙትም ‘ተረፈ-’ኮሚኒስቶች ጥንታዊቷንና ሐዋርያዊቷን ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን በይበልጥ እንድታስፋፋ እንቅፋት ከመሆን እንዲቆጠቡ እለምናችኋለሁ።

1 comment:

Habtegiorgis from hawassa said...

እባካችሁ ቤተክርስትያናችንን ከጥፋት ለመጠበቅ ሁላችንም በአንድ ልብ ሁነን ልንጸልይ ይገባል፡፡ የገዳማቱ መቃጠል፣የክርስቲያኖች በኢአማንያን መገደል፣የሚመለከታቸው የቤተክርስትያን አባቶች ሰምተው እዳልሰሙ አይተው እንዳላዩ ዝም ማለታቸው…….ወዘተ የወቅቱ ፈተናዎቻችን ናቸውና አባካችሁ ወደ አምላካችን እንጩህ፡፡ የቅዱሳን አምላክ ኢትዮጵያን ይጠብቅ፡፡ አሜን፡፡