Wednesday, March 21, 2012

“ጥያቄው ከስኳር እና ከዋልድባ መምረጥ አይደለም” አቶ መስፍን ነጋሽ

 READ IN PDF
መንግስት በዋልድባ ገዳም አካባቢ የስኳር ፋብሪካ እያቋቋመ መሆኑን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተገልጾዋል:: በዚህ ልማት እና የቅርስ ጥበቃ አስመልክቶ አቶ መስፍን ነጋሽ የሚከተለውን ጽሑፍ በአዲስ ነገር ኦንላይ(addis neger online) ላይ አውጥተዋል:: እኛም ጽሑፉን ለውይይት እንዲሆነን እንደሚከተለው አቅርበነዋል:: መልካም ንባብ!!!
+++
ሰሞኑን በዋልድባ ገዳም አካባቢ ከተጀመረው የስኳር ፋብሪካ ልማት ጋራ ተያይዞ የተነሣው ውዝግብ በመሠረቱ መሬት ከማረስ ወይም የአንዱን ይዞታው ሌላው ከመንካቱ ጋራ የተያያዘ ብቻ አድርጌ አልተመለከትኩትም። ጥያቄው “ለልማት” (በጠባቡ በአቶ መለስ ትርጉም) እና ከቁሳዊ ዋጋቸው ይልቅ ረቂቅ/መንፈሳዊ ዋጋቸው እንደሚበልጥ ለሚታሰቡ እሴቶች ከሚሰጠው ዋጋ ጋራ የተያያዘ ነው። እንዳለመታደል ሆኖ አገራችን እንዲህ ያሉ አገራዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ላቅ ያሉ ጉዳዮችን አደባባይ አውጥቶ ለመከራከር የሚቻልባት አገር አልሆነችም፤ በብዙ ምክንያቶች። አለበለዚያ በጉዳዩ ላይ ሕዝባዊና ምሁራዊ ክርክሮች በኖሩን፣ ሚዲያውም ዜና ከማተም አልፎ ጉዳዩን በጥልቀት ለመመርመር በሞከረ ነበር።

ጥያቄው “ልማት ያስፈልጋል አያስፈልግም?” የሚል አይደለም፤ “መንፈሳዊ/ታሪካዊ/ማኅበራዊ እሴቶች መጠበቅና መዳበር አለባቸው የለባቸውም?” የሚልም አይደለም። ለዚህ ነው “ጸረ ልማት ሃይሎች የስኳር ፋብሪካውን ተቃወሙ” (አይነት) የሚለው የኢቲቪ ቀፋፊ ዜና የሚያስጠላውን ያህል “ጸረ መንፈሳዊ/ማኅበራዊ እሴት የሆነው የአቶ መለስ መንግስት ሆን ብሎ ገዳሙን…..ስኳር ፋብሪካ…አደረገ” የሚለው አይነቱ ክርክርም ትርጉም የሚያጣው።


ጉዳዩ “የበለጠ ጉልበት ያለው የፈለገውን ያደርጋል” በሚል መንፈስ መያዝም መፈታትም የለበትም። የዛሬውን የኢቲቪ ዜና ስመለከት ግን መንግሥት የተለየ አቀራረብ እንደሌለው አረጋግጫለሁ።

ቁሳዊ ልማትና የማፋጠን እና ታሪካዊ/መንፈሳዊ እሴቶችን የመጠበቅ ጉዳይ ሁልጊዜም አብረውና ተስማምተው ላይሄዱ ይችላሉ። አንዱን ለማሳደግ ሌላውን ዋጋ ማስከፈል የሚያስፈልግበት አጋጣሚ የመስተጋብሩ ቋሚ መገለጫ ይመስላል። ጥያቄውን በአንድ ነጠላ የልማት ፕሮጀክት አንጻር መመልከት ይቻላል። “ፕሮጀክቱ እገሌ የተባለውን ታሪካዊና መንፈሳዊ እሴት ያለው ቦታ/ሕንጻ… ይነካዋል አይነካውም? ከነካው ምን ያህል? ወዘተ” በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ መነጋገርም መደራደርም ተገቢ ነው። ከዚህ መሰሉ ዝርዝር ንግግር በፊት ግን በመጀመሪያ ስለ “ልማቱ” እና ሰለ “እሴቶቻችን” ምንነትና ፋይዳ ዘርዘር አድርጎ መነጋገር ይገባን ነበር። ይህ በተለያዩ ወገኖች የሚሰጠው የተለያየ ሚዛን ቢያንስ ለሚቀጥሉት 100 ዓመታት በሚካሔዱ የልማት ክንውኖች መላልሶ እንደሚገጥመን አልጠራጠርም። ለዚህም ነው በቅድሚያ በሐልዮት ደረጃ ጉዳዩን ማብላላት አስፈላጊ ነው የምለው። የቁሳዊ ልማታችን እና የባህል ልማታችን ምንና ምን ናቸው?

“ ቁሳዊ ልማት” ስለሚያስከፍለን ዋጋ፣ እንደ ኅብረተሰብ ለልማት ስንል ልንከፍለው ስለምንችለውና ስለማንችለው ዋጋ ወዘተ መነጋገር በጣም አስፈላጊ ነው። በመተማመመን እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ልውውጥ ይጠይቃል። ዞሮ ዞረ ቁሳዊም ሆነ ባህላዊ ልማቱ ለእኛው እስከሆነ ድረስ፣ መነጋገሩ ሁለቱንም ፍላጎቶች በጋራ የሚጠቅም ተደርጎ ካልታየ በመጨረሻ እንደማኅበረሰብ መጎዳታችን አይቀርም። ፋብሪካ በመሠራቱ የተጠቀምን ሲመስለን፣ ለፋብሪካው ሲባል በፈረሰ ታሪካዊ ቦታ የተነሳ የምናዝን ከሆነ በድምሩ አትርፈናል ማለት አይቻልም። በተቃራኒውም ታሪካዊ ቦታውን ብዙ ሳይጎዱ (ሌላ ምንም አማራጭ የለም ከሚል ሐሳባዊ መነሻ) ፋብሪካውን መሥራት እየተቻለ ይህ ባይደረግ የልማቱ ተጠቃሚ ያልሆነው ሕዝብ ሕይወት የኀዘናችን ምንጭ መሆኑ አይቀርም።

የዚያኑ ያህልም ታሪካዊ/መንፈሳዊ ዋጋ አላቸው የምንላቸው እሴቶችም እንዲሁ በዝርዝር መታየት ይኖርባቸዋል። በኢትዮጵያ አንድ ቦታ ወይም ቁስ በሕግ “አገራዊ/አካባቢያዊ ፋይዳ ያለው” (ይህ ከቅርስ የተለየ ነው) የሚባለው ምን ሲያሟላ እንደሆነ በዝርዝር አላውቅም። ይህን የሚደነግግ ቢያንስ የሚያብራራ አገራዊ መመዘኛ አለን? ቅርሳ ቅርስን የሚመለከተው ሕግ የአሁኑን ጥያቄያችንን ሙሉ በሙሉ የሚመልስ አይመስለኝም። ይህ ሕግ ካለን ለየትኛው እሴት ምን አይነት ጥበቃ እንደሚደረግለት መነጋገርና መግባባት ይቻላል። ይህ ቢሆን ኖሮ እኮ የዋልድባ ገዳም ተወካዮች ሁሉን ማድረግ ወደሚችሉት ወደ አቶ መለስ ቢሮ ሳይሆን ወደ ፍርድ ቤት ሔደው “በሕግ የተሰጠን ጥበቃ እና ጥቅም ተጣሰ” ብለው መብታቸውን በጠየቁ ነበር። ለምሳሌ፣ አንድ በርካታ ተረፈ ምርቶችን እና ጭስ የሚያወጣ ፋብሪካ ወይም ትልቅ የመኪና መንገድ ከአንድ ታሪካዊ ቦታ በምን ያህል ርቀት መሠራት አለበት? እርግጥ ሁሉንም ሁኔታዎች በሕግ ማስቀመጥ አይቻልም፤ ከሐልዮታዊ መነሻዎች ጀምሮ ይህን መሰል ዋና ዋና ጉዳዮችን አስቀድሞ ማስቀመጥ ግን ይቻላል።

በገዳሙ ምሳሌ አንድ ተጨማሪ ነጥብ እናንሳ። ገዳማውያኑ አንድ የራሳቸው የህይወት ዘይቤ አላቸው። ይህን የሕይወት ዘይቤያቸውን የመጠበቅ መብትም አላቸው፤ ልክ ብሔረሰቦች ባህላቸውንና የኑሮ ዘይቤያቸውን የመጠበቅ መብት እንዳላቸው ሁሉ። ታዲያ ከልማት ጋራ ተያይዘው የሚመጡ የኑሮ ዘይቤ ልዩነቶችንና ለውጦችን የምናያቸው እንዴት ነው? ለዚህ መሰል የሕይወት ዘይቤ የሚሰጠው ጥበቃስ እምን ድረስ መሔድ ይችላል? ይህን ያነሳሁት ሰሞኑን ከሰማኋቸው ክርክሮች አንዱ የስኳር ፋብሪካው በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚቀጥርና የሚያሰባስብ እንደመሆኑ መጀመሪያውንም በገዳሙ አካባቢ መታሰብ አልነበረበትም ማለቱን ስለታዘብኩ ነው። ነገሩ ከስኳርና ከዋልድባ የመምረጥ ተራ ጥያቄ አይደለም የምለው እንዲህ ያሉ ክርክሮችንም ስለሚጋብዝ ነው።

በመጨረሻ ለአፈና ካልሆነ በቀር ከስሕተቱ መማር የማይችለው መንግሥት፣ ከዋልድባው ውዝግብ ትምህርት ወስዶ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋራ ግልጽ አገራዊ ውይይትና ክርክር እንዲያደርግ እመኛለሁ። መቼም በክርስትናውም በእስልምናውም, ሕይወት ያለው ተቋም ስለሌለለ “በጉዳዩ ላይ ምሑራዊና ስነመለኮታዊ ትርጉማቸው ላቅ ያለ ውይይቶች አድርጉ፣ ከመንግሥት ጋራ አስቀድመን ብንነጋገር ይሻላል በሉ” ለማለትም የተመቸ አይደለም። ይህን ጉዳይ በቁምነገር ወስዶ ውይይት የሚያዘጋጅ፣ ክርክር የሚጋብዝ ከመንግሥት ውጭ ያለ ተቋም ከኖረ ደስታችን ነበር፤ ግን አንድዬ አልፈቀዱምና እንዲህ ያለ ድርጅት መኖሩን እጠራጠራለሁ። እነዛው የፈረደባቸው የአንድ እጅ ጣት የማይሞሉ የአደባባይ ምሁራን (እነ ዶ/ር ዳኛቸው) ከዚህ ቀደም ያሉት ቢሆንም በድጋሚ በጉዳዩ ላይ ሐሳብ ያካፍሉን እንደሆነ ማየት ነው።

No comments: