Friday, March 23, 2012

"በደኖቹ መቃጠል ማን ብዙ ይጎዳል”? ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

 READ IN PDF
“የገዳማቱ የተፈጥሮ  ደን  መጠበቅ ተጠቃሚው ማን ነው”? በሚል በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ የቀረበ ጦማር አግኝተናል:: ይህ ጽሑፍ ዲ/ን ብርሃኑ  በፌስ ቡካቸው  ላይ አስቀምጠውታል::  እኛም እንደሚከተለው አቅርበነዋል:: መልካም ንባብ!!!
+++
በዚህ በሰሞኑ የገዳማቱ ደኖች መቃጠል አንድ ያስገረመኝ ነገር ቢኖር ኦርቶዶክሳዊ ከሆኑት ዉጭ ከሌሎቹም ብዙም ጉዳዩን ጉዳይ የማድረግ ነገር አለማየቴ ነዉ፡፡ ሁኔታዉን ደጋሜ ሳስብበት ቢያንስ ሁለት ችግሮች እንዳሉብን ገመትኩኝ፡፡ አንደኛዉ እንደ ዜጋና ሀገር የደኖችን ጠቀሜታ በዉል አለማወቃችን ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛዉም ራሳችን ተቆርቋሪዎች ነን የምንለዉም ብንሆን ቦታዉ የእኛ መሆኑ የጣለብን ሓላፊነት አድርገን ስለቆጠርነዉ እንጂ ከዚህ ያለፈ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያመጣ ማስረዳት የቻልን አልመሰለኝም፡፡ ይህንን ማድረግ አለብን ወይም ነበረብን የምለዉ ዛሬዉን ማለቴ አይደለም፤ ቀደም ብለን፡፡ እንማን? እኛ፡፡ በቃ እኛ የሚለዉ የሚበቃ መሰለኝ፡፡ ምን አልባትም በየገዳማቱ ዙሪያ ያሉ ነዋሪዎች እሳቱን ለማጥፋት ሲረዱ የማይታዩት እንዲያዉም እሳቱን የሚያስሰነሱት ከሰል በማክሰል ለመጠቀም ሲሉ ነዉ ተብለዉ የሚነሱት በርግጥም አድርገዉት ከሆነ የሚወቀሱት ይህን እንዲረዱ ባለማድረጋችን ይመስለኛል፡፡ በአካባቢዉ ያለዉ ሰዉ ስለደኑ ጥቅም በደንብ የሚረዳዉ ነገር ከሌለ ለምን ይጠብቀዋል? በርግጥም በማቃጠሉ በቀላሉ ከሰሉን ስለሚያገኝና ስለሚሸጥ ራሱኝ የተሻለ ተጠቃሚ አድርጎ ሊያስብ ይችላል፡፡ ለመሆኑ ደኖቹ በመቃጠላቸዉ ከፍተኛ ተጎጂዎች አነማን ናቸዉ? እስኪ ከዛፉ በፊት ከእያንዳንዱ ፍጥረት መጠበቅ ምን ያህል ልንጠቀም እንደምንችል የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ላቅርብና ወደ ደናችን ልምለስ፡፡


እዉነቱን ለመናገር እኔን ጨምሮ ዐይጥን ብዙ ሰዉ ይጠላታል፡፡በቀጥታ እርሷን ለምግብም ሆነ ለሌላ ነገር ባንጠቀምባትም በምድር ላይ ለምንኖርበት ሕይዎት በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ፍጥረታት አንዷ ግን እርሰዋ ናት፡፡ ለዚህ ማስረጃ ይሆነን ዘንድ አንድ ድርጊቷን ብቻ ልጥቀስ፡፡ ለሰዉ ልጅና ለሌሎቹም ፍጥረታት በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ዛፎች መካከል እንደ ዋንዛና ዝግባ የመሳሰሉት ፍሬያቸዉ በቅሎ የሚበዙት የፍሬያቸዉን የላይኛዉን ክፍል አይጥ ከበላችዉ በኋላ ነዉ፡፡ በዚህ መንገድ እርሷ ካልበላችዉ ፍሬዉ ወይም የዉስጠኛዉ ሊበቅል ስለማይችል እነዚህን የመሰሉ ታላላቅ ጠቀሜታ ያላቸዉ ዛፎችን ዐለማችን ላታገኛቸዉ ትችል ነበር ማለት ነዉ፡፡ ተመልክቱ፤ አስተዋዮች ከሆንን ልክ እንደዚህ የእያንዳንዱን ፍጥረት ግንኙነት የሥነ ሕይዎትና የሥነ ምሕዳር ባለሞያዎች ባይነግሩን አንኳ እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረቱን አንዱን የአንዱ ምግብ እያደረገና ሌላዉን በሌላዉ እያሸጋገረ እንዴት ምድራችንን ጠቃሚ እንደሚያደርግልን ከዚህ በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡ በዚህም ያለ ዐይጥ ዐለማችን ምን ያህል ልትቸገር እንደምትችል መረዳት እንችላለን፡፡

ልክ እንዲሁ ስለደኖች ብዙዎቻችን ከምናወቀዉ ወጣ ያለ ነገር ግን ደግሞ እጂግ መሠረታዊ ጠቀሜታ አንዱን ብቻ ላቅርብ፡፡ በቅርብ ጊዜ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተፈጠረ ክስተት ልነሣ፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚኖሩ ገበሬዎች በብዛት እየገጠማቸዉ ያለዉ አንዱ ችግር የባቄላ፣ አተር፣ አደንጓሬ፣ ጓያና የመሳሰሉት የጥራጥሬ ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆል ነበር፡፡ በቅርባቸዉ ከሚገኙት የልማት ወኪሎች(DA) ጋር ተመካክረዉ ማዳበሪያ አጠቃቀሙንና ሌላዉንም ቢያስተካክሉ እንዲያዉም ጭራሽ አላፈራ አለ፡፡ ገበሬዉ ሲጠይቅ መልሱ አንድ ብቻ ነበረ፤ መሬቱ እንቢ አለ፤ በቃ ሌላ የሚያዉቀዉ ነገር አልነበረም፡፡ በኋላ አንዳንድ ዐይናቸዉ የበራላቸዉ የሥነ ምሕዳር (Ecologists) ባለሞያዎች ሲያጠኑት ግን ችግሩ ከመሬቱም፣ ከዘሩም፣ ከማዳበሪያዉና ከሌላዉ ግባትም አልነበረም፡፡ ችግሩ እነዚህ ጥራጥሬዎች የሚያፈሩት ብዙዎቻችን በታች ክፍል የሥነ ሕይዎት (Biology) ትምህርት እንደተማርነዉ ከወንዴ ቡቃያዎቹ ወደ ሴቴ ቡቃያዎች ለፍሬ የሚሆነዉን ዘር የሚወስዱት እንደ ንብና ቢራቢሮ የመሳሰሉት ትንንሽ ፍጥረታት(Polinators) አለመኖር ነበር፡፡ እነርሱ ደግሞ የጠፉት ሊጠጉበት የሚችሉበት ምንም ዐይነት ደን በእርሻዉ አካባቢ ባለመኖሩ ምክንያት ነበር፡፡ ስለዚህ ደኖች በቀጥታ በረሃማነትን ከመከላከልና የከርሰ ምድር ወኃን ወደ ላይኛዉ የመሬት ክፍል በመጎተትና ምንጭ በማዉጣት(ይህ ባሕር ዛፍን አይጨምርም እንዲያዉም ምንጩን ሁሉ ያደረቀዉ እርሱ ነዉ) ከሚሰጡት ጥቅም ባሻገር ለእኛ ሕልዉና በተዘዋዋሪ የሚጠቅሙንን ትንንሹንም ትልልቁንም አዉሬዉን፣ ትላትሉን፣ ተዉሳኩን፣…. በማስጠጋትና ተፈጥሮ ሥርዓቷን ጠብቃ እንድትጓዝ እኛም ተረድተንም ሆነ ሳንረዳ በዚህ የተፈጥሮ ሚዛን መጠበቅ ከሚገኘዉ የተመጣጠነና ጤናማ ተፈጥሮ እንድንጠቀም የሚያደርጉ ተተኪ የሌላቸዉ ስጦታዎች ናቸዉ፡፡

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በምድር ወገብ ለሚኖሩ ሀገራት የደኖች ነገር በዚህ እኔ በሞነጨርኳት የስሚ ስሚ (እግዚአብሔር ይስጠዉና እኔንም በዚህ የሞረደኝ ዶክተር አለማየሁ ዋሴ ነዉ)ጠቀሜታ ብቻ እንደማይወሰን የታወቀ ነዉ፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ከዳሉል እስከ ራስ ዳሽን ከፍታ በሚገኝ የመሬት ከፍታችን ልዩነት(ultitude difference) ዉስጥ የነበረዉን ከፍተኛ የስብጥር(Diversity) ሀብት አሁን ተሟጦ አልቆ ምልክቱን ወይም ደግሞ ተረፈ ተፈጥሮ ሀብቱን የምናገኘዉ ረጂም ዘመናትን ታፍረዉና ተከብረዉ በኖሩት በአብያተ ክርስቲያናትና በገዳማት ዙሪያ ነዉ፡፡ተረት የሚመስለዉን የ‹‹ለምለሚቷ ኢትዮጵያ›› መፈክር የዛሬዉ ትዉልድ በዐይኑ ማየት ባይችልም ዕምቅ ሀብቱ(the Potential) ግን አሁንም አለ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ኢትጵያን በዓለም በጣት ከሚቆጠሩት የጀነቲክ ባለሀብቶች አንዷ ያደርጓትም እነዚህ ሀብቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እብድ የያዘዉ መልክ አይበርክትም የተባለዉ ደርሶባት ሀብቷም መልኳም በአንድነት ረገፈ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና ተጠያቂዎቹ ይሄ ዲግሪ የሚሉት የምስክር ወረቀት ይዘን ትምህርት ቤት ለመክረማችን እንጂ ለመማራችን ማስረጃ የሌለን (Educated but never or may not be learned)አካላት ከፍተኛዉን ድርሻ የምንይዝ ይመስለኛል፡፡ በምዕራባዉያን ዘንድ በሃይማኖትና በሌላዉ ቢለያዩም የምንኖርበት ዐለም ደኅንነት እንዴት እንደሚጠበቅ ስለገባቸዉ የአሕያ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ የቀበሮ፣ የአካባቢ፣ …. እያሉ ፍጥረትን ሁሉ እንዲጠበቅ የሚሟገቱት ትምህርት ቤት ከመክረም በላይ የተማሩም ስለሆኑ ጭምር ነዉ፡፡ ለንደን ከተማ ዉስጥ መኝታ ቤት ዉስጥ ገብተዉ የተኛ ሕፃን እስከመብላት የደረሱት ቀበሮዎች እጂግ እየበዙ ያሉት በዚህ አስተሳሰብ ባመጣ የተማረ ሰዉ ጥበቃ ነዉ፡፡የሥነ ትምሕርት(Education) ባለሞያዎች እንደሚሉት መማር(learning) በአእምሮ ዉስጥ የሚቀመጥ የዕዉቀት ክምችት ብቻ ሳይሆን ተከታታይ የሆነ የአመለካከት፣የአስተሳሰብና የአኗኗር ለዉጥ ያለበት ነገር ነዉና፡፡ ስለዚህ በደኖቹ መቃጠል ገዳማቱ ወይም አብያተ ክርስቲያናቱ ብቻ ሳይሆኑ መጀመሪያ የአካባቢዉ ነዋሪዎች በተለይም ገበሬዎቹ ሁለተኛም ሁላችን ኢትዮጵያዉያን ከዚያም ስብጥሩንና በእኛ ሀገር ብቻ ያለዉን (endemic)በማጣት ዐለም ራሷ ትጎዳለች፡፡ ስለዚህ አባካችሁ ጉዳቱ ያለ ልዩነት የሁላችን ነዉና በጋራ እንጠብቃቸዉ፡፡

በፌስ ቡክ አንድ ወዳጄ "የተማረ ይግደለኝ ይላል የሀገሬ ሰዉ፣
ይሄዉ ተምሬለት መጣሁ ልጨርሰዉ፡፡ ሲል እንደ ጉባኤ ቃና ቅኔ በሁለት ስንኝ ቋጥሮ የሰጠንን ከመጽሐፍ በላይ የሚናገር ድንቅ እይታ ተረድተን ችግራችንን ለመፍታት በመጣር ሥጋቱን ሐሰት እናደርግለት ዘንድ እማጸናለሁ፡፡

No comments: