Tuesday, March 20, 2012

(ሰበር ዜና) በዝቋላ ገዳም ፖሊስ አንድ ተማሪ አቆሰለ

·         ትኩረታችን ወደ መከላከሉ - መዘናጋት አይገባም!!
READ THE ARTICLE
ዘገባው የደጀ ሰላም ነው::
በዝቋላ ገዳም ቃጠሎውን ለማጥፋት በተሰበሰቡ ወጣቶች እና በኦሮሚያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ መካከል በተቀሰቀሰው አለመግባባት ከአዳማ ዩኒቨርስቲ ከተጓዙት መካከል አንድ ተማሪ ከፖሊስ በተተኰሰ ጥይት እግሩ ላይ ቆስሎ ወደ ሕክምና በመወሰድ ላይ መሆኑ ተሰማ፡፡
የአለመግባባቱ መንሥኤ ወጣቶቹ ቃጠሎውን አስመልክቶ በቀጥታ ስርጭት ዘገባ ማስተላለፍ ሥራ ላይ የነበረውን ጋዜጠኛ መቃወማቸው ነው ተብሏል፡፡ የዐይን እማኞች እንደተናገሩት ጋዜጠኛው እሳቱ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ የሚገልጽ ዘገባ በማስተላለፍ ላይ ነበር፡፡

በተማሪው ላይ ከደረሰው የመቍሰል አደጋ ውጭ ከትላንትናው ዕለት ጀምሮ ቃጠሎውን ለመከላከል በየሸጣሸጡ፣ በየገደሉ ሲጥሩ ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች በመውደቅ፣ በመሰበር እና በመላላጥ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተዘግቧል፡፡ ይሁንና አሁን በተማሪው ላይ ያጋጠመው የመቁሰል አደጋ ትኩረታችንን ሳይቀለብሰው ኀይላችን ሁሉ የቃጠሎውን አደጋ በመከላከል ላይ እንዲወሰን መልእክት ተላልፏል፡፡
በሌላ በኩል ወደ ዝቋላ ገዳም ከተለያዩ ከተሞች የሚሄዱ መኪኖች ድሬ በተባለችው መዳረሻ ከተማ ላይ በፖሊስ መታገዳቸው ተሰምቷል፡፡ የተሰጠው ምክንያትም የሰዉ አለመጠን መብዛትና ‹‹አንዳንዶች በዚህ ተጠቅመው የሚያደርሱትን ጉዳት ለመከላከል ነው፤›› ተብሏል፡፡ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኀይለ ግብር የሆኑና በስፍራው የሚገኙ ባለሞያዎች እሳቱ እንዳይዛመት አሁን ባለው የመከላከል አቅም ግንድ እየተቆረጠ መሠራት ለሚገባው አርፍተ እሳት(fire break) ከፍተኛ የሰው ጉልበት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡
 አየር ኀይል በሄሊኮፕተር እገዛ እንዲያደርግ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል እንዲያመለክት ለመጠየቅ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የተገኙትን ወጣቶች ያነጋገሩት በቅጽረ ግቢው ጥበቃ እያደረገ የሚገኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኀይል ሓላፊ ናቸው፡፡
ትላንት ከዋልድባ ገዳም የተመለሱት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ እና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያው ሓላፊ አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ጥያቄውን ለማቅረብ በደብረ ዘይት አየር ኀይል እንደሚገኙ የተነገራቸው ወጣቶቹ፣ የቃጠሎ መከላከሉን ጥረት የሚከታተል ስድስት አባላት ያሉት ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡ ወጣቶቹ ትላንት በሁለት የሕዝብ ማመላሻ እና በአራት ሚኒባሶች ወደ ዝቋላ አምርተው የነበረ ሲሆን ምሽት ላይና በውድቅት የተቀሰቀሰውን እሳት እስከ ንጋት ድረስ ግንድ እየቆረጡ የቃጠሎውን መዛመት የሚያግድ እሳተ ከላ ሲሠሩ አድረዋል፡፡
የቃጠሎውን መዛመት ለመግታት እየተቆረጠ የሚሠራው ማገጃ (አረፍተ እሳተ) ለጊዜውም ቢሆን ከቃጠሎ ተርፎ ለሚታየው የደኑ ክፍል መራቆት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ‹‹ይህ ሁሉ በአየር መከላከል ቢታገዝ የግማሽ ሰዓት ሥራ ይሆን ነበር፤›› ያለው አንድ ወጣት እንደገለጸው መነኰሳቱ አረፍተ እሳቱን ለመሥራት ዛፉን የሚቆርጡት እያነቡ ጭምር ነው - ገዳማችንን አራቆትነው እያሉ!!
ዓርብ ረቡዕ፣ አጣብቂኝ እና በጋራው ሥር በርትቶ የሚታየው ቃጠሎው ሰዓት የገዳሙ ከብቶች በሚገኙበት ማደሪያ በኩል እንደ አዲስ ተቀስቅሷል፡፡ ሌሊት ሌሊት የሚነሣው ከባድ ነፋስ፣ እርጥበት አጠር የሆነው የቀኑ ዋዕይ እና ቀን ቀን ተዳፍኖ ሌሊት በነፋሱ የሚቀጣጠለው ክምችት የሠራው ፍሕም (በአብዛኛው የጥድ ነው) ለቃጠሎው ማየል አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ የገዳሙ አበምኔት አባ ዮሐንስ አሁን ማምሻውን ለሸገር ኤፍ፣ኤም 102.1 ሬዲዮ እንደተናገሩት ቅዳሜ ከሰባት ሰዓት ጀምሮ የተነሣው እሳት ምንም ዐይነት መገታት አይታይበትም፤ ሕዝቡ ውኃ ወደ ገዳሙ እያመጣ ያለው በሃይላንድ ጠርሙስ ጭምር ነው፡፡ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ አዛዥ ጫላ ሆርዶፋም ይህንኑ በማጠናከር እሳቱ በአንድ ቦታ ጠፋ ሲባል በሌላ ስለሚቀሰቀስ የማጥፋቱን ሥራ አስቸጋሪ አደርጎታል፡፡ ሸገር የጠየቃቸው ምእመናንም በጣም ተመራጭ የሆነው መንገድ የአየር መከላከል (ሄሊኮፕተር መጠቀም) መሆኑን እንደተናገሩ ዘግቧል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን

አሜን

No comments: