Thursday, April 5, 2012

የሰሜን አሜሪካ እና የካናዳ ምእመናን ለሦስተኛ ጊዜ በዋልድባ ገዳም ጉዳይ በተመለከተ ስብሰባ አካሄዱ

  •    “ከእንግዲህ ወዲህ በቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ላይ አባቶችን አንጠብቅም” ተሳታፊ
  •   ቤተ ክህነት ለቤተ ክህነት ሰዎች፤ ቤተ መንግስቱም ለፖለቲከኞች መንግስት በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ አይግባ፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከፖለቲካ ወገንተኝነት ይጽዱ” የስብሰባው ተሳታፊዎች
ዛሬ መጋቢት 26 ፣2004 ዓ/ም ለሦስተኛ ጊዜ በዋልባ ገዳም ጉዳይ እና በቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመወያየት በካናዳ እና በአሜሪካን እስቴቶች የሚኖሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች በኮንፈረንስ ስልክ ተሰባስበዋል:: በዋሽንግተን ዲሲ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 9pm በዊስስት ኮስስት አቆጣጠር  ደግሞ 6pm ላይ ከአራት መቶ ሃምሳ(450) በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ስብሰባው ተካሄዶዋል:: የስብስባው አስተባባሪ በጸሎት ካስጀመሩ በኋላ አክራሪው የእስልምና ቡድን በቤተ ክርስቲያናችን እያደረሰ ያለውን ጥፋት በተመለከት ከተለያዩ የአክራሪዎቹ ሚድያ የተቀረጹ ከአክራሪዎቹ አንደበት በድምጽ ተሰምቶዋል:: በተለይ በዚህ በሃያ ዓመታት ጊዜ ውስጥ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ያደረሱት ጥፋቶች እንደ መግቢያ በስብሰባው አስተባባሪ ለተሳታፊዎች ቀርቦዋል:: የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ቸልተኝነት ለደረሰው ጥፋት እና ለጥፋቱ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳበረከተ ተገልጾዋል::

የመወያያ አጀንዳው ዓለም ዓቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ በተመለከተ ነበረ:: በአወያዩ የቀረበው የመወያያ አጀንዳ የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የዓለማቀፍ ሚድያ ሽፋን እንዲያገኝ በሰሜን አሜሪካ በኢስት ኮስት በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ አንድ ቦታ ላይ ይካሄድ፤ ወይስ በዌስት ኮስት በካሊፎርንያ ሎሳንጀለስ ከተማ ጭምር በሁለት ቦታ ይካሄድ የሚል ሃሳብ ቀርቦ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተውበታል:: ብዙኃን ተሳታፊዎች ሁላችንም አንድ ላይ መታየታችን በዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃን(ሚድያ) ሽፋን ለማግኘት ጠቀሜታ ስላለው አንድ ቦታ በዋሽንግተን ዲሲ ላይ እንዲካሄድ የሚለው ሃሳብ ጎልቶ ታይቶ ነበረ:: “ለእግር ኳስ እንኳን ከእስቴ እስቴ እንዘዋወራለን ቤተ ክርስቲያናችን በገጠማት ፈተና ድምጻችን ለማሰማት ከያለንበት እስቴት በአንድነት ወደ  ዋሽንግተን ዲሲ መሄድ አለብን” በሚል ብዙ ተሳታፊዎች በቁጭት ተናግረዋል::

አንድ አስተያየት ሰጪ “የዛሬ ስብሰባችን ቤተ ክርስቲያን እናድናት የሚል ሲሆን ስለዚህ ዘር ወይም ቀለም ሳይለየን በአንድነት እንቁም፣  ፖለቲካውን ወደ ጎን በመተው ቤተ ክርስቲያን የገጠማት ፈተና እንታደጋት” የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል:: ሌላው አስተያየት ሰጪ “ዋልድባ ገዳም በትግራይ ክልል ስለሚገኝ የዋልድባ ጉዳይ የሚለከታቸው የትግራይ ተወላጆች ብቻ አይደለም፤ ዋልድባ የኢትዮጵያ ገዳም ነው፣ ዋልድባ ዓለም ዓቀፍ ቅርሳችን ነው፤ ሥለዚህ “ዋልድባ በትግራይ ክልል ውስጥ ስለሚገኝ እናንተ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አያገባችሁም” ያሉት የመንግስት ባለ ሥላጣን የትግራይ ተወላጆች ለቤተ ክርስቲያን ህልውና ስትሉ ፖለቲካውን ወደ ኋላ በማለት ይህ የተናገረው ባለ ሥልጣን ተሳስተሃል በሉት” በማለት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል::

“አባቶቻችን በተለየያ ምክንያት ተከፋፍለው እኛንም ከፋፍለውን ነበረ:: ከዚህ በኋላ በእኛ መካከል ክፍፍል መኖር የለበትም:: የዋልድባ ጉዳይ አንድ አድርጎናል:: ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው:: እግዚአብሔር በምክንያት አሰባስቦናል ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አንድነታችን የሚጠናከርበት ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለብን:: ከዚህ በኋላ በቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ አባቶችን አንጠብቅም:: በእኛ በደካሞች እግዚአብሔር ሥራ ሊሰራ ፈልጎዋል እኛም ወደ ኋላ ማለት የለብንም:: ይህ አሁን እያካሄድን ያለው ጅምር ሥራ ነው:: በዘለቄታው ዓለም ዓቀፍ ኮሚቶዎችን አዋቅረን ሥራ መቀጠል አለብን:: አንድ ቋንቋ እየተነጋገርን አንድ እግዚአብሔር እያመለክን እስከ ዛሬ ድረስ መግባባት አልቻልንም ነበረ:: ዛሬ ግን መግባባት እና መነጋገር ችለናል ሥለዚህ ከየተኛውም የፖለቲካ ወገተኝነት ነጻ ሆነን ቤተ ክርስቲያናችን በገጠማት ፈተና ላይ በአንድነት ለመሰለፍ ለራሳችን ቃል እንግባ” የሚሉ አስተያየቶች ከተለያዩ ተሳታፊዎች ተሰጥቶዋል::

“ቤተ ክህነት ለቤተ ክህነት ሰዎች፤ ቤተ መንግስት ለፖለቲከኞች መሆን አለበት:: ቤተ ክርስቲያኒቷ የሚመሩ ሰዎች  ከፖለቲካ መጽዳት አለባቸው:: የቤተ መንግስት ሰዎች በቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት መቆም አለበት:: የሀገራችን ሕገ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ላይ መንግስት ጣልቃ አይገባም ይላል:: ሥለዚህ መንግስት በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ አይግባ:: መንግስት የቤተ ክርስቲያን መብት ያክብር” የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥቶዋል::

በመጨረሻም ዓለም ዓቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያስተባብሩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው በኢስት ኮስት በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ እና በዌስት ኮስት በሎሳንጀለስ በተመሳሳይ ቀን እንዲካሄድ ተወስኖዋል:: እንዲሁም ከካናዳ በኮንፈረስ ስልክ የተገኙ ወንድሞች እና እህቶች ባነሱት ጥያቄ መሰረት በተመሳሰይ ቀን ሰላማዊ ሰልፍ በቶሮንቶ ካናዳ ለማካሄድ እንዲያስተባብሩ ሓላፊነት ወስደዋል:: የሚቀጥለው የስልክ ኮንፈረንስ April 18, 2012 በተመሳሳይ ሰዓት እንዲሆን ተወስኖዋል:: የኮንፈረንስ ስልክ ቁጥር 559-726-1200 pass code 157715# መሆኑን ከአስተባባሪዎች ተገልጾዋል::
      እግዚአብሔር አሐቲ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን!!!

No comments: