Monday, April 23, 2012

“እኛ «አክራሪ» የሚለውን ቃል በጥንቃቄ ነው የምንመረምረው” የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ

የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም በአጠቃላይ የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት አስመልክቶ ከዚህ በፊት ከስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አድረገው ነበረ:: በዚህ ቃለ ምልልሳቸው አክራሪነትን እና የማኅበሩ የፖለቲካ ተሳትፎ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ የማኅበሩን አቋም በመንተራስ ምላሽ ሰጥተው ነበረ:: ይህ አስቀድሞ ምላሽ የተሰጠበት አሁን ወቅታዊ ሆኖ ስላገኘነው ከቃለ ምልልሱ ቀንጨብ አድርገን በአክራሪነት እና የፓለቲካ ጉዳይ የሰጡት ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል:: ሙሉ ቃለ ምልልሱን የወሰድነው ከማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ላይ ነው::
 
ስምዐ ጽድቅ፡- ማኅበሩ አክራሪ ነው ስለሚባለውስ?
ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ፡- እኛ «አክራሪ» የሚለውን ቃል በጥንቃቄ ነው የምንመረምረው::  አክራሪ ማለት የሃይማኖቱን ሕግ አክብሮ የሚኖር ተግቶ የሚጾም፣ የሚጸልይ በሃይማኖቱ ላይ ለሚነሡ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ፣ ታሪኩን፣ ቤተክርስቲያኑን የሚወድ፣ ለሃይማኖቱ የሚቀና የማይዋሽ ወይም ወደ ከፍተኛ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ራሱንም የሃይማኖት ወገኑን ሁሉ ለማድረስ የሚተጋ ከሆነ የማኅበራችንን አባላት ሊገልጽ ይችላል፡፡ ሰዎች ምናልባት በልማድ በዚህ ብያኔ ለመጥራት ፈልገው ከሆነ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁኔታ የሚመላለሱትን ክርስቲያኖች «አክራሪ» ተብለው ከሚጠሩ አጥባቂ፣ ዐቃቤ ሃይማኖት ቢባሉ የተሻለ ነው፡፡


በሌላ በኩል ግን «አክራሪ» የሚለው የሚያሰቃይ፣ የሚገድል፣ የሚያስገድድ፣ የሚሳደብ፣ የሌላውን ሳይነኩ የራሳቸውን አምልኮ እየፈጸሙ ያሉትን የሚረብሸ፣.. ወዘተ ለማለት የተቀመጠ ብያኔ ከሆነ በወንጌል የሚያምኑ፤ አምነውም የሚያስተምሩ ክርስቲያኖች ሊያደርጉት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ከላዩ የተጠቀሱት ተግባራት ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ ጋር ተጣጥመው አይሔዱም፡፡ ማኅበራችንም ስብከተ ወጌልን በመላው ሀገሪቱ  እና ዓለማት የማስፋፋት ዓላማ ይዞ የሚሠራ በመሆኑ ለፍቅርና ለመከባበር ትልቅ ቦታ አለው፡፡

ምናልባት በማስጨነቅ ወይም በማስገደድ ሃይማኖታችንን ለማስጣል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ ቅሬታችንን መግለጻችንና በሃይማኖታችን ላይ በኅትመት ወይም በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ አማካኝነት የሚሰጡ አስተያየትና ጥያቄዎች ሲኖሩ መልስና የአጸፋ አስተያየቶችን መስጠታችን በዚህ ደረጃ አስ ፈርጆን ከሆነ ሚዛናዊ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እነዚህን የምናደርገው በሃይማኖታችን ላይ ጥያቄ ያነሣውን ወይም አስተያየት የሰጠውን አካል ለመተቸት ወይም ለመሳደብ ተፈልጐ ሳይሆን እነዚህ አካላት ካሠራጯቸው መልእክቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ሐሳብ እንዳይበረዝ፣ ሃይማኖታችን መልስና አስተያየት የሌለው መስሎ ለምእመናን እንዳይታሰብ ለመጠበቅ የሚደረጉና ለጠየቁን መልስ እንድንሰጥ በሃይማኖታችንም የታዘዘውን መንፈሳዊ ተግባር ለመፈጸም ነው፡፡

መከራ የደረሰባቸውና የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች ሲኖሩ ቅሬታችንን መግለጻችን ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ለሀገር ሰላምም የሚበጀው ችግሮች መኖራቸውን ጠቁሞ ሕዝብም መንግሥትም መፍትሔ እየሰጣቸው ሲሔዱ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ስሜታዊ በሆነ መልክና ከጀርባው ሌላ ዓላማ ያለው እንቅስቃሴን በክርስቲያኖች ስም ማካሔድን በጽኑ የምንቃወመው ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተክርስቲያን ያለውን ተቆርቋሪነት ከግምት አስገብቶ የተለያዩ አካላት በስሜት የሚያካሒዷቸው ግልጽና ሥውር እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳን ሳይሆን አይቀርም የሚሉ አካላት እንደሚኖሩ እናምናለን፡፡ ሌላው ቀርቶ በዓውደ ምሕረት ቆሞ ያለ ሕግና ሥርዓት የሚያስተ ምሩ መምህራንን ሁሉ የማኅበረ ቅዱሳን መምህራን ናቸው የሚሉም እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን በጭፍን የሚሰጡ እነዚህን የሚመስሉ አስተያየቶች ተገቢ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አካላት ማኅበሩ ያሰማራቸው መሆን አለመሆኑን ማጣራትም ወይም ሆኖም ከተገኘ ማኅበሩ ባለው አሠራር ርምጃ እንዲወስድ ማሳሰብ የተሻለ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓይነት አቋም ላይ ያለን ማኅበር አክራሪ የሚሉት አካላት ካሉ ያን ለማለት መነሻ ያደረጓቸውን ጭብጦች ማጤን ይኖርባቸዋል እላለሁ፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- የ­ፖለቲካ አቋምን በተመለከተስ?
ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ:- ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የእኛ ማኅበር ሃይማኖታዊ አገልግሎት ለመስጠት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር የተቋቋመ የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ እንደ ተቋም የሚሰጠውም አገልግሎት ሃይማኖታዊ ነው፡፡ ለየትኛውም የፖለቲካ ዓይነትና አደረጃጀት የሚያግዝ /የሚሠራ/ እንዲሆን መቼም ቢሆን ፍላጐቱ የለንም፡፡ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ አምስት እንደተቀመጠው «ማኅበሩ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አይኖረውም»  ይላል፡፡ የዚህን አንቀጽ ይዘት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል በማኅበሩ ያሉ የተወሰኑ አካላት በሓላፊነት ላይ እያሉ የማንኛውም የፖለቲካ አባል እንዳይሆኑ በ1998 ዓ.ም የሥራ አመራር ጉባኤያችን ወስኗል፡፡ በውሳኔውም መሠረት የሥራ አመራር ጉባኤ አባላት፣ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት፣ የማኅበሩ መደበኛ መምህራን፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ ጽ/ቤት አባላት፣ የኦዲትና ኤንስፔክሽን አገልግሎት ጽ/ቤት አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ የማዕከላት ሰብሳቢዎች በሓላፊነት ላይ ያሉ መደበኛ አገልጋዮች የማንኛውም የፖለቲካ ­ፓርቲ አባል አይሆኑም፡፡

ይህ ማለት ግን ­ለፖለቲከኞች በማኅበሩ የማገልገል ዕድል አይኖራቸውም ማለት አይደለም፡፡ ለፖለቲካ ዓላማቸው ማኅበሩን መጠቀም ግን አይችሉም፡፡ ስለዚህ የትኛውንም የማኅበሩን አባል በግሉ የ«ሀ» ወይም የ«ለ» ­ፓርቲ ደጋፊ፣ አባል ወይም አመራር እንዲሆን ወይም እዳይሆን ምንም ዓይነት ተቋማዊ ተጽዕኖ በማኅበሩ የሚፈጠርበት ዕድል የለም፡፡ ይህ ግን ሀገርን በመገንባት ረገድ ለአጠቃላዩ ማኅበረሰብ ትርጉም ያለው ልማታዊ ተግባራትን የማከናውን ዓላማና እንቅስቃሴ የለውም ማለት አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ያላት የሀገራዊ ልማት ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀጣይነት እንዲኖረው ክርስቲያን ምሁራንና ወጣቶች ባላቸው አቅም ሁሉ ይሳተፋሉ፡፡ የልማት ተሳትፎአቸው ለሀገርና ለትውልድ እንዲጠቅም፣ ቤተክርስቲያንም ያላትን ድርሻ እድትወጣ በማሰብ ነው፡፡ ብዙዎቹ ልማታዊ ተግባሮቻችን ደግሞ በቀጥታ የቤተክርስቲያናችንን ጥቅም የሚያስጠብቁ በመሆናቸው እንቅስቃሴያችን ለሌላ ትርጉም በሚጋለጥ መልኩ የሚደረግ ነው የሚል እምነት የለንም፡፡

በእርግጥ እንደተባለው በሀገር ውስጥም በውጪም በ­ፖለቲካ ወገንተኝነት ማኅበሩን ለማማት የሚፈለጉ ወገኖች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ በጣም የሚገርመው ግን የሚሰጡት አስተያየቶች የተዘበራረቁ መሆናቸው በራሳቸው መሠረት የሌላቸው አስተያየቶች መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ በሀገር ውስጥ ያለው ማኅበሩ የ«ሀ» ፖርቲ ደጋፊ ነው ሲል በውጪ ሀገር ያሉ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ የ«ለ» ፖርቲ ደጋፊ ነው እያሉ ተጨባጭነት የሌለውና ምናልባትም የማኅበራችን አባላት በሆኑ የአንዳንድ ግለሰቦች ተሳትፎን መነሻ አድርጐ የሚሰጥ ሚዛናዊ ያልሆነ ድምዳሜ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ማኅበራችን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ተመርኩዞ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ባለው የፖለቲካ ሥርዓት ከሚቋቋመው መንግሥት ጋር መሥራት ሃይማኖታዊም ሕገ መንግሥታዊም ግዴታው ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ማኅበሩ እንደተቋም የትኛውንም የፖለቲካ አስተሳሰብ /Ideology/ በመደገፍ ወይም በመቃውም ከፖርቲዎች ጋር ግንኙነት ስለሌለው /ስለማይኖረው/ ለማንም ስጋት ወይም ዕድል ልንሆን አንችልም፡፡ በዚህ ደረጃ ፈርጆን የሚነሣ አካል ካለ ግን ለመፈረጅ ያበቁትን የመረጃ ምንጮች እንዲመረምር በዚሁ አጋጣሚ ሳልጠቁም አላልፍም፡፡

6 comments:

Anonymous said...

Yetekeberu abate kesis doctor mulugeta syoum endehulgizew ejig yemiyakoru abat! Mahibere kidusan ewnetegna yebetechristian lij!!! bertulen!!!

Anonymous said...

Yetekeberu abate kesis doctor mulugeta syoum endehulgizew ejig yemiyakoru abat! Mahibere kidusan ewnetegna yebetechristian lij!!! bertulen!!!

Anonymous said...

ጠ/ሚ ማ/ቅ አክራሪ እንዳልሆነ አፋቸው ሳይሆን ልባቸው ጠንቅቆ ያውቀዋል። ጠ/ሚሩ "አክራሪ" የሚለውን ቃል "አንዳ አንድ የማ/ቅ አባላት" በሚለው ሃረጋቸው ከማ/ቅ ጋር ለማዘመድ የተጠቀሙበት በራሳቸው እሳቤ በቂ የሆኑ ፖለቲካዊና ጥቅማዊ ምክንያቶች ሰለአሏቸው ነው። ምክንያቶች በትንሹ አምስት ናቸው።
፩ በዋልድባ ጉዳይ የማ/ቅ አጣሪ ቡድን ዕውነትን ይዞ ብቅ እንዳይል ማስፈራራት፤
፪ ደጋፊዬ ናቸው የሚሏቸውን የእስላምና ክፍሎችና አብላት ለላማስከፋት - ከእነሱ እምነት ተከታዮች ብቻ አክራሪ እንዳልተባሉና በማ/ቅ ስም ክርስቲየኖችንም በማካተት በተነፃፃሪነት ማሳየት፤
፫ ማ/ቅ በሰፊው ምዕመን ዘንድ ያለውን ቀና እሳቤ ማዛባትና ጥላሸት በመቀባት ከኢሕአዲግ ውጭ ማንኛውም አካል የገዘፈ ስምና ዝና እንዳይኖረው፤
፬ ማ/ቅ ለቤ/ያን አስተምሮ ሳይሆን ለመንግስትና ለአባ ጳውሎስ ተገዢ እንዲሆን ያለዚያ በአክራሪነት ስም ያሻቸውን ለማድረግ መንገድ ሲያመቻቹና፤ ወያኔ/ኢሕአዲግ በቤ/ያን ላይ ያለውን ድብቅ ዓላማ በመፈፀም ላይ ማ/ቅ ይህን ድብቅ አላማ አውቆትም ሆነ ሳያውቀው ማህበሩ ከተመሠረተለት ዓላማ አንፃር የወያኔው ድብቅ ዓላማ ተፈፃሚነት ላይ በተጠናከረ መልኩ ማህበሩ አስጊ ሆኖ ከቀጠለ ማህበሩን ለማፈን ወይም ለማደከም ያለዚያም ማስወገድ እንዲቻል ከአሁኑ ምክንያት ለማበጀትና ለበኋላ ዜና ፍጆታ ስንቅ ለመሰነቅና
፭ በቤተ ክህነትና በመንግስት ውስጥ ያሉ ከኑፋቄ እስከ ንዋይ፣ ከዝና እስከ ስልጣን የመሳሰሉትን ዓለማዊ ፍላጎቶችን ያአነገቡ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ነገር ግን "አፍቃሬ ወያኔ/ኢሕአዲግ" በመምሰል ያን ፍላጉታቸው ለማሳካት ሌት ተቀን የሚባዝኑ "አፍቃሬዎቻቸውን" ፍላጉት ባለማጎደል እነዚህ ቡድኖችና ግለሰቦች በአፍቃሬ ወያኔ/ኢሕአዲግነታቸው እንዲበረቱና ሲጠሯቸው አቤት ሲልኳቸው ወዴት በሚለው ታዛዠነታቸው እንዲቀጥሉ ጉልበት ለመሰጠት ነው።

Anonymous said...

Weregna hulu tegnechacha enegedi eseki berasachehu siderese anegebegebachehu ayedele yale seme seme mesetete ayachehu enedi yaregale

Anonymous said...

April 27, 2012 1:11AM lay asteyayet yesetut Anonymous, at least yale simachin sim endesetun kemesekerulin yibekanal lelaw hulu tirf new. thank you!

Anonymous said...

እግዚአብሔር ለሀገራችንና ለቤተክርስቲያናች የሚበጀውን አባት ያምጣልን፡፡
ትልቆቹ የቤተክርስትያን ጠላቶች በፖለቲካውስጥ ያሉ ሰዎች መሆናቸው በሁሉም ምዕመን ዘንድ ይታወቃል ፡፡ ምክንያቱም ቤተክርስቲያንን የእድገት ማነቆ ብለው ስለሚያሰቧት ነው፡፡
አሁንም ለቤተክርስቲያን ይበልጥ ጠንክራችሁ ለመስራት እራሳችሁን አዘጋጁ በተለይ ደግሞ በዋልድባ ገዳም ላይ ያለው ነገር በገሃድ ምእመኑ ሁኑ ማወቅ አለበት