Tuesday, April 24, 2012

አቡነ ፋኑኤል አዲስ አበባ ናቸው

  • በጉጉት የሚጠብቁትን ደብዳቤ ከፓትርያርኩ አግኝተዋል፤ 
  • ብፁዓን አባቶች በቅ/ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ በጥብዓት ሐሳባቸውን ከሰጡ የአሜሪካ ምእመናን ከገቡበት የሐዋሳ ዓይነት ፈተና እና መከራ ይታደጓቸዋል ተብሎዋል
  ሙሉውን ዘገባ የወሰድነው ከደጀ ሰላም ነው:: 
አወዛጋቢው የአሜሪካ ሁለት አህገሩ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቅዳሜ አዲስ አበባ ገብተዋል፤ በመላው አሜሪካ የተነሣባቸውን ተቃውሞ ለማድበስበስ እና ከአሜሪካ እንዳይነሡ ለማድረግ እንደተዘጋጁ የደጀ ሰላም ምንጮች አስታወቁ። በአሜሪካ የተቀሰቀሰባቸውን ተቃውሞ የሚያበርድ ደብዳቤ ከፓትርያርኩ አግኝተዋል።


አርብ ተነሥተው ቅዳሜ ሚያዚያ 13 አዲስ አበባ የገቡት ብፁዕነታቸው ከሳምንት አስቀድመው የተልዕኮዋቸው የቀኝ እጅ እና “አባ ሰላማ” ከተባለው የተሐድሶ ድረ ገጽ እና የተሐድሶ ክንፍ ጋር ድልድይ ሆኖ የሚያገናኛቸው እንዲሁም በአሜሪካ የጀመሩትን “አዲስ ሀገረ ስብከት እና ከእውነተኛ ኦርቶዶክሳውያን የጸዳ ቡድን” የማቋቋም ዘመቻ መሐንዲስ ነው የሚባለውን ዲ/ን ኃ/ጊዮርጊስ ጥላሁንን ወደ አዲስ አበባ ልከዋል። ዲያቆኑ የቅዱስ ፓትርያርኩ ጥብቅ ወዳጅ እና ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተቋቋመውና እንዲፈርስ ቢታዘዝም በፓትርያርኩ እና በአቡነ ፋኑኤል እምቢተኝት በመንቀሳቀስ ላይ ያለው  “የውጪ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት ባለሙሉ ሥልጣን ኃላፊ” ነው። የግለሰቡ ተልዕኮ አቡነ ፋኑኤል በአሜሪካ የገጠማቸውን ተቃውሞ ለማለዘብ ከቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ አስቀድሞ ብፁዓን አባቶችን ማግባባትና ሎቢ ማድረግ ነው ተብሏል።

በፓትርያርኩ ብቸኛ መሪነት ልዩ ተልዕኮ ሰጥቷቸው አሜሪካንን ልክ እንደ ሐዋሳው በማመስ ላይ የሚገኙት አቡነ ፋኑኤል መንግሥት እና ፓትርያርኩ ሊደሰቱባቸው ይችላሉ፣ በዚህም የሹመቴን ዕድሜ ያራዝማሉ ያሏቸውን ንግግሮች ሲናገሩ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ሲያስቀዱ ሰንብተዋል ተብሏል። በዋልድባ ጉዳይ ተቃውሞ የሚያሰሙት “ፖለቲከኞች ናቸው”፤ ፓትርያርኩ አኩሱም ላይ የጀመሩት የሙዚየም ግንባታ የቤተ ክርስቲያኒቱ ትልቅና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ስለሆነ ገንዘብ አዋጡ እያሉ በቀጥታ ለቪዲዮ ካሜራዎች የሚናገሩባቸው ንግግሮች ተቀድተው የተዘጋጁ ሲሆን ለፓትርያርኩ እጅ መንሻ ሆነው እንደሚቀርቡ ምንጮች ለደጀ ሰላም አብራርተዋል።

በዕድሜ ለጋ፣ በሥራ ልምድ አናሳ ከሆኑትና በዘመነ አቡነ ጳውሎስ ልማድ ተደርጎ የተወሰደው የወጣት ጳጳሳት ሹመት ውጤት የሆኑት አቡነ ፋኑኤል ይህንን ጉድለታቸውን ለማሟላት በጥበብ ከመጓዝ ይልቅ ከሐዋሳ ጀምሮ አሜሪካ እስከ ሔዱበት ጊዜ ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕድሜ ጠገብ ተቋማት በማፍረስ  ሥራ ላይ ተጠምደው ቆይተዋል። ይህ ጉዳይ ሲያስደምመን ቆይቶ ከተደመምንበት ድማሜ፣ ከገባንበት መደነቅ ሳንወጣ፣ ጭራሽ በይፋ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሚያዋርዱ እና ክብረ ቅዱሳንን ከሚያቃልሉ ግለሰቦች እና ድረ ገጾች ጋር እጅና ጓንት ሆነው በይፋ መሥራት ጀምረዋል። የሚጽፏቸውን ደብዳቤዎችም የራሳቸው ድረ ገጽ አዘጋጅተው ማውጣት ሲችሉ ወይም ሌላ መንገድ መፈለግ ሲገባቸው በተሐድሶ ድረ ገጾች በመጠቀም በቤተ ክርስቲያናችን ብፁዓን አበው ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ አሳፋሪ ተግባር መፈጸም ጀምረዋል።

ማንም ሰው የራሱን ስም እና አገልግሎት የሚያሰናክል ተግባር ለመሥራት የማይፈልገውን ያህል አቡነ ፋኑኤል ለራሳቸው ስምና ክብር መቃብር ለመቆፈር መታተራቸውን የሚያዩ አባቶች “ከጀርባቸው አይዞህ እያለ ወደ ጥፋት የሚመራቸው ሰው አለ” ሲሉ የቆዩ ሲሆን ብዙዎቹ ደግሞ “ፓትርያርኩ ናቸው” በሚለው ይስማማሉ። ፓትርያርኩ አቡነ ፋኑኤልን ያቀረቡ በመምሰል ከዚህ በፊት ፓትርያርኩን ለመቃወም ባደረጉት ሙከራ እየተበቀሏቸው ነው ሲሉ ያትታሉ። ይህንን አመክንዮ በሚያስረዳ መልኩ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለአቡነ ፋኑኤል እና “ሾምኳቸው” ላሏቸው ሰዎች እውቅና በመስጠት ደብዳቤ የጻፉ ሲሆን የተሐድሶዎቹ ድረ ገጾችም የፓትርያርኩን የግል ደብዳቤ “ከቅዱስ ሲኖዶስ የመጣ” በማስመሰል ለመጻፍ ሞክረዋል። እውነቱ ግን ይህ እንዳልሆነ ይታወቃል። ለማንኛውም የሊቀ ጳጳሱን እና የፓትርያርኩን ደብዳቤዎች ከዚህ በታች አስቀምጠናቸዋል። ለታሪክ። (ደብዳቤዎቹን ለማንበብ ይህንን ይጫኑ)

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቡነ ፋኑኤል ሊቀበሉት ፈቃደኛ ያልሆኑበት የዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት በሥሩ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት እንደያዘ አቤቱታውን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት በማሰማት ላይ ሲሆን ይኸው አቤቱታ እንዳይሰማ የፓትርያርኩ ጠንካራ አስተዳደር እጅ ሳይጫነው እንዳልቀረ ምንጮች ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ግንቦት ላይ በሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ በአጀንዳነት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ እንዳይሆን ደግሞ አቡነ ፋኑኤል “ያላቸውን ኃይል ሁሉ አጠራቅመው” ሄደዋል ተብሏል። የተጠራቀመው ኃይል ምን እንደሆነ ሁላችን ይገባናል። ቤተ ክርስቲያን በዚህ ከአሜሪካ ተጭኖ በሚሄደው “ኃይል” እስከመቼ እንደምትዘወር ትልቅ ጥያቄ ነው። ብፁዓን አባቶች በቅ/ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ በጥብዓት ሐሳባቸውን ከሰጡ የአሜሪካ ምእመናን ከገቡበት የሐዋሳ ዓይነት ፈተና እና መከራ ይታደጓቸዋል።
ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን 
 እግዚአብሔር አሐቲ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን!!!

2 comments:

Anonymous said...

እግዚኣብሔር እንደ ቅዱስ ኣትናቲዎስ ኣይነት ኣባት ይስጠን

Anonymous said...

Abune Fanueil Addis Abeba Nachew malet min malet new ? yihim yasiweksal end ahunis beza yibka min yitsekmal bezih fanta melkam neger mezigibulin Aba Selama Yetebalew yemenafikan blogg yemyasitelalfewn kihidet lemin mels atisetsum Abune Fanueil Bezih wetsu Bezih weredu malet mann lemastemar new bertu