Monday, April 30, 2012

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተማላጅ እንጂ አማላጅ አይደለም::

የተሐድሶ መናፍቃኑ አንደበት ደጀ ብርሃን ድረ ገጽ “ክርስቶስ አማላጅ ነው” በማለት በዛሬው ዕለት የእምነት አቋሙን የገለጹበት ጽሑፍ አውጥቶዋል:: ደጀ ብርሃን፣ አባ ሰላም እና ሌሎችም በስም እኛን መስለው የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች በጎቹን ከበረት ለማስወጣት እጀ ለእጅ በመያያዝ የምንፍቅና ትምህርታቸው በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ:: በጣም በሚያዛዝን ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኒቷን ደሞዝ እየበሉ በጠቅላይ ቤተ ክህነት እነ አባ ሠረቀ ወልደ ሳሙኤል እና ዲ/ን ኃይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ለእነዚህ የመናፍቃን ብሎጎች መረጃ በማቀበል ተባባሪ እንደሆኑ በቂ መረጃዎች አሉን::
          የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ወልደ አምላክ ብላ ታምናለች፤ ታስተምራለችም:: ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ተማላጅ እንጂ አማላጅ እንዳልሆነ ቅዱሳን መጻሕፍ ይናገራሉ:: በዚህ በተሐድሶ መናፍቃን ደጀ ብርሃን ድረ ገጽ ለወጣው የምንፍቅና ትምህርት ምላሽ ይሆን ዘንድ የሚከተለውን የቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የሚገልጽ ጽሑፍ አቅርበንላችኋል:: ጽሑፉን የወሰድነው ከቤተ ደጀኔ ብሎግ ነው:: 
+++

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱን ማንነት ገልጦ ያስተማረበት ትምህርት ነው። በዚህም ትምህርቱ፥ እርሱ የበጎች እረኛ እንደሆነ፥ የበረቱም በር እርሱ መሆኑን ተናግሯል። እውነት የባህርይ ገንዘቡ ስለሆነም፥ ትምህርቱን «እውነት እውነት እላችኋለሁ፤» በማለት ጀምሯል። በዚህም አማናዊ በሆነ ትምህርቱ «ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኲል የሚገባ ሌባ፣ ወንበዴም ነው፤» ብሏል። ይኽንንም ስለ ሦስት ነገር ተናግሮታል።

፩ኛ፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ብላቴና በምራቁ ጭቃ አድርጐ፥ በሰሊሆም ጠበልም እንዲጠመቅ በማድረግ ፈጽሞ ስለፈወሰው፥ አይሁድ ብላቴናውንም ወላጆቹንም አስቸግረዋቸው ነበር። ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፦ «ይህ ሰው (ኢየሱስ) ከእግዚአብሔር አይደለም፥ ሰንበትንም አይከብርምና፤» እያሉ ብላቴናውን ተከራክረውታል። እርሱ ግን፦ «ኃጢአተኛ ሰው እንዲህ ያለ ተአምራት ማድረግ (በደረቅ ግንባር ላይ ዓይን መፍጠር) እንዴት ይችላል? . . . እርሱ ነቢይ ነው፤» አላቸው። ይኸውም፦ የነቢያት አለቃ ሙሴ፥ ከእግዚአብሔር አግኝቶ፥ «እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ መካከል (ከእናንተ ወገን) እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋልና እርሱን ስሙት፤» በማለት ለእስራኤል ዘሥጋ የነገራቸው ቃለ ትንቢት ነው። የሐዋ ፯፥፴፯። ምክንያቱም በብዙ መንገድ ሙሴ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነውና። የነቢያት አምላካቸው ኢየሱስ ክርስቶስ «ነቢይ» መባሉም ነቢያት በአንድም ሆነ በሌላ ምሳሌዎቹ በመሆናቸው ነው።
    የብላቴናው ወላጆች ደግሞ አይሁድ ወጥረው በጠየቋቸው ጊዜ፥ «ይህ ልጃችን እንደሆነ፥ እውር ሆኖም እንደተወለደ እናውቃለን። አሁን ግን እንዴት እንደሚያይ፥ ዓይኖቹንም ማን እንደ አበራለት እናውቅም፥ እርሱን ጠይቁት፥ አዋቂ ነውና፥ ስለራሱም መናገር ይችላልና፤» አሉ። እንዲህም ማለታቸው «እርሱ ክርስቶስ ነው፥ ብሎ በእርሱ የሚያምን ቢኖር ከምኲራብ ይውጣ፤» የሚለውን የአይሁድን ዓዋጅ ፈርተው ነው። ብላቴናው ግን ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ «አትሰሙኝም እንጂ ነገርኋችሁ፥ እንግዲህ ምን ልትሰሙ ትሻላችሁ? እናንተም ደቀመዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁን?» ብሎ ሳይፈራ ተከራከራቸው። በዚህን ጊዜ «ራስህ በኃጢአት የተወለድህ አንተ እኛን ታስተምራለህን?» ብለው ከምኲራብ አወጡት። በዚህም ንግግራቸው በጌታ ቃል፦ «የእግዚአብሔር ሥራ ሊገለጥበት ነው እንጂ እርሱ አልበደለም፥ ወላጆቹም አልበደሉም፤» የተባለውን ሰው በልበ ደንዳናነት ኰነኑት። ከቤተ መቅደስም አስወጡት። ዮሐ ፱፥፫። ጌታችንም አግኝቶት «አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?» አለው። ብላቴናውም፦ «አቤቱ፥ አምንበት ዘንድ እርሱ ማነው?» ብሎ መለሰለት። ጌታችን ኢየሱስም «የምታየው፥ ከአንተ ጋርም የሚነጋገረው እርሱ ነው፤» አለው። ይኸውም «ነቢይ ነው፤» እንዳለ በምሳሌው እንዳይቀር «አምላክ ወልደ አምላክ» ብሎ እንዲያምን ነው። እርሱም «አቤቱ ፥ አምናለሁ፤» ብሎ ሰገደለት። ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እኔ የማያዩት እንዲያዩ (አላዋቆች ነን የሚሉ ሐዋርያት አዋቆች ይሆኑ ዘንድ) የሚያዩትም እንዲታወሩ (አዋቆች ነን የሚሉ ፈሪሳውያን አለዋቆች ይሆኑ ዘንድ) ለፍርድ መጥቻለሁ። (ላመነብኝ ልፈርድለት ላላመነብኝ ልፈርድበት፥ ለሰው መፈራረጃ ለመሆን ከሰማይ ወርጃለሁ)። አለው። በዚህን ጊዜ ይኽንን የሰሙ ፈሪሳውያን፦ «እኛ ደግሞ ዕውሮች ነን?» አሉት። ጌታችን ኢየሱስም ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ (ነውረ ሥጋ ከመንግሥተ ሰማይ አያወጣምና)፤ አሁን ግን እናያለን (እናውቃለን) ትላላችሁ፥ አታዩምም፤ (አታውቁምም)፤ ስለዚህም ኃጢአታችሁ ጸንቶ ይኖራል፤ (ንስሐ ስለማትገቡ ኃጢአታችሁ አይሰረይላችሁም)፤ አላቸው። ዮሐ ፱፥፩፥፵፩። እንግዲህ በዚህ ምክንያት «ለሰው መፈራረጃ እሆን ዘንድ መጥቻለሁ።» በማለቱ፥ ለምሕረትም እንደመጣ ለማጠየቅ በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ አሥር ያለውን አስተምሯል።
    ፪ኛ፦ ይህ ዕውር ሆኖ ተወልዶ ጌታ የፈወሰው ብላቴና፥ ፈሪሳውያን፦ እንዴት እንዳየ ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ፥ ደጋግሞ እውነቱን ነግሯቸዋል። በተጨማሪም፦ «እናንተም ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁን?» ብሎም ጠይቋቸዋል። እነርሱ ግን፥ «አንተ የእርሱ ደቀመዝሙር ሁን፥ እኛስ የሙሴ ደቀመዛሙርት ነን። እግዚአብሔር ሙሴን እንደተነጋገረው እናውቃለን፥ ይህን ግን ከወዴት እንደሆነ አናውቅም፤» አሉት። በዚህን ጊዜ «. . . ከወዴት እንደሆነ፥ አታውቁምና እጅግ ድንቅ ነው፤ ነገር ግን ዓይኖቼን አበራልኝ። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ምንም ማድረግ ባለቻለም ነበር፤» ብሎአቸዋል። እንግዲህ፦ «ከወዴት እንደሆነ አናውቅም፤» ብለውት ስለነበረ ከወዴት እንደሆነ ለማጠየቅ አንቀጸ አባግዕን አስተምሯል።
    ፫ኛ፦ «ቸር እረኛ አይደለህም፤» ብለውት ስለነበር፥ ቸር እረኛ መሆኑን ለማጠየቅ ነው። ይኽንንም፦ «ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፥ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን፥ ተኲላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሻላል፤ ተኲላም መጥቶ በጎቹን ይነጥቃቸዋል፥ ይበትናቸዋልም። ምንደኛስ ይሸሻል፥ ስለ በጎቹም አያዝንም፥ ምንደኛ ነውና።» በማለት ነግሯቸዋል።
    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በጎች ያላቸው ምእመናንን ነው። የዕለተ ምጽአት ፍርድ እንዴት እንደሆነ ለደቀመዛሙርቱ በነገራቸውም ጊዜ፥ ጻድቃንን በበጎች መስሎ፥ «በጎቹን በቀኝ ያቆማቸዋል፤» ብሏል። ማቴ ፳፭፥፴፫። ቅዱስ ጴጥሮስንም፦ «በጎቼን ጠብቅ፤» ብሎታል። ዮሐ ፳፩፥፲፭። ተኲላ ያለው ደግሞ ሰይጣንን እና መልክተኞቹን ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ በልዑል ረድኤት የሚያድር፥ በሰማይ አምላክ ጥላ ውስጥ የሚቀመጥ፥ እግዚአብሔርን፦ «አንተ መጠጊያዬና አምባዬ፥ አምላኬና ረዳቴ ነህ፥ በአንተ እታመንብሃለሁ፤» የሚል ሰው፥ የሚያገኘውን ጸጋ ሲናገር፥ «ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፥ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኲላና በእባብ ላይ ትጫናለህ፥ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ፤» ብሏል። መዝ ፺፥፩-፲፫። ካልተጠነቀቁ በስተቀር ተኲላት (መናፍቃን) አደገኞች ናቸው። ይኽንንም ጌታችን «የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ከሐሰተኞች ነቢያት (ከመናፍቃን) ተጠንቀቁ፥ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኲላዎች ናቸው።» በማለት ነግሮናል። ማቴ ፯፥፲፭። ከዚህም ሌላ «እነሆ እኔ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ . . . ከክፉዎች ሰዎች ተጠበቁ፤» ብሎናል።
    ተኲላ ተንኰለኛ አውሬ ነው፥ ተመሳስሎ ከበጎች ጋር መደባለቅ ያውቅበታል፥ ሥጋ በል ሲሆን ሣር እንደሚነጭ እንስሳ አንገቱን ቀብሮ ይውላል፥ ቢርበውም ምቹ ጊዜ እስኪያገኝ ይታገሣል። በጎች በራሳቸው አቅም ይኽንን መከላከል አይችሉም፥ ምክንያቱም የዋሃን ናቸውና። በመሆኑም ተግቶ የሚጠብቅ እረኛ ያስፈልጋቸዋል። እረኛ ከሌላቸው ግን ይጠፋሉ። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከምእመናን ሕይወት ጋር በማገናዘብ፦ «እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁንም ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመለሱ፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፭። በጎች የምእመናን ብቻ ሳይሆን የክርስቶስም ምሳሌዎች ናቸው። መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ፦ «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፳፱። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «እርሱ ግን በመከራው ጊዜ አፉን አልከፈተም፥ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም።» በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። ኢሳ ፶፫፥፯።
፩፥፩፦ በበሩ የሚገባና የማይገባ፤
    በበሩ የሚገባ ማለት፦ ትንቢት ተነግሮለት፥ እግዚአብሔር አብ መስክሮለት፥ ምእመናን ወደ አሉበት ወደ ኢየሩሳሌም በመምሕርነት የሚመጣ ማለት ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ትንቢት ተነግሮለት፥ ሱባዔ ተቆጥሮለት ነው። ኢሳ ፯፥፲፬፤ ፱፥፪-፮፤ ፲፩፥፩። የባህርይ አባቱም በዮርዳኖስ፦ «በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤» በማለት መስክሮለታል። ማቴ ፫፥፲፯። ከዚያም በፊት የልደቱን ብሥራት ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የነገረ፥ ቅዱስ ገብርኤል፥ «ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ። እርሱም ታላቅ ነው፥ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤» ብሏል። ሉቃ ፩፥፴-፴፪። በተወለደ ጊዜም ቅዱሳን መላእክት፥ ለእረኞች ተገልጠው፥ «እነሆ፥ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፥ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው።» በማለት መስክረውላቸዋል። ሉቃ ፪፥፲፥፲፩። መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስም፦ «ጫማውን እሸከም ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፥እርሱ በእሳትም በመንፈስ ቅዱስም ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውን በጎተራ ይከታል፥ ገለባውን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።» ማቴ ፫፥፲፩። «ተጐንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።» ማር ፩፥፯፣ ሉቃ ፫፥፲፭። «ዳሩ ግን እናንተ 
የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው። . . . አንድ ሰው ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ነገር ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ መጣሁ።» ዮሐ ፩፥፳፮። «ከሰማይ ካልተሰጠው ሰው አንዳች ሊቀበል አይቻለውም። እናንተ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፥ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ። ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፥ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምፅ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባል።» ብሏል። ዮሐ ፫፥፳፯።
    ከእግዚአብሔር አብ፥ ከነቢያት ትንቢት፥ ከቅዱሳን መላእክት ብሥራትና የምሥራች፥ እንዲሁም ከመጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ ምስክርነት እንደተማርነው፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በበሩ የገባ ቸር እረኛ ነው። በመሆኑም «ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፥ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፥ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፥ አውጥቶም ያሰማራቸዋል።» ብሎአል። በረኛ የተባለ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ሕዋሳቱን በሰበሰበ፥ ዐሠርቱ ቃላትን በያዘ፥ በሰቂለ ኅሊና፥ በነቂሐ ልቡና በሚኖር ሰው የሚያድር እርሱ ስለሆነ የሰውን አእምሮ ለበጎ ይከፍተዋል። አንድም በረኛ የተባለ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ምክንያቱም፥ ለጊዜው አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን የተዘጋች ገነትን በቤዛነቱ የሚከፍት፥ ለፍጻሜውም በዕለተ ምጽአት መንግሥተ ሰማያትን የሚከፍት እርሱ ነውና። «በጎቹ ቃሉን ይሰሙታል፥» እንዳለ፥ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፥ ሰባ ሁለቱ አርድእት፥ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ትምህርቱን ተቀብለውታል። በየስማቸውም ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥ ስምዖን፥ ታዴዎስ፥ ዲዲሞስ፥ ቶማስ እያለ ጠርቶአቸዋል። «አውጥቶም ያሰማራቸዋል፤» የተባለው ደግሞ፦ «በጠባቢቱ በር ግቡ፤ . . . እኔን ሊከተል የሚወድ ራሱን ይካድ፥ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ፤» እያለ ያስተምራቸዋል ማለት ነው። መሰማሪያ የተባለው ትምህርተ ወንጌል ነው፥ አንድም መከራ ነው፥ አንድም በመጨረሻ የሚወርሱት ክብረ መንግሥተ ሰማያት ነው።
    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ካስተማራቸው በኋላ  ይሰቀልላቸዋል (ነፍሱን አሳልፎ ይሰጥላቸዋል)። «በጎቹም ይከተሉታል»፤ እርሱን አብነት አድርገው ወንጌልን ያስተምራሉ፥ መከራን ይቀበላሉ፥ በመከራ ይመስሉታል። «ቃሉን ያውቃሉና።» ትምህርቱን ተቀብለውታልና። «ሌላውን ግን ይሸሹታል እንጂ አይከተሉትም፥ የሌላውን ቃሉን አያውቁምና።» ትንቢት ሳይነገርለት፥ መጻሕፍት ሳይመሰክሩለት የመጣውን ግን ሌባ ወንበዴም በመሆኑ አብነት አያደርጉትም፥ አይመስሉትም፤ ይነቅፉታል፥ ያወግዙታል እንጂ ትምህርቱን አይቀበሉም። ጌታችን ይኽንን ምሳሌ ቢነግራቸውም እረኛ የተባለ እርሱ፥ አባግዕ የተባሉ ደግሞ እነርሱ እንደሆኑ አልገባቸውም።
    ዳግመኛም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የበጎች በር እኔ ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፥ ነገር ግን በጎች አልሰሙአቸውም። እውነተኛው የበጎች በር እኔ ነኝ፥ በእኔ በኲልም የሚገባ ይድናል፤» (ወደ ሃይማኖት ወደ ወንጌል ይገባል)፤ «ይወጣልም፤» (ከፈቃደ ሥጋ ይወጣል፤ አንድም በጎ ሥራ ለመሥራት ለማስተማር ይወጣል)፤ መሰማሪያም ያገኛል። (መከራን ማለትም እስራቱን፣ ግርፋቱን፣ እሳቱን፣ ስለቱን፣ ያገኛል)። አንድም በጉባኤ ምእመናንን ያገኛል፤ አንድም ክብረ ሥጋን ክብረ ነፍስን ያገኛል)። ሌባ ግን ሊሰርቅና ሊያርድ፥ ሊያጠፋም ካልሆነ በቀር አይመጣም። (ሌባው ወንበዴው ግን በነፍስም በሥጋም ሊጐዳ ሊያጠፋ ነው እንጂ ሊያለማ ሊጠቅም አይመጣም)። እኔ ግን የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኙ፥ እጅግም እንዲበዛላቸው መጣሁ።» አላቸው።
    በበሩ የማይገባ ማለት ደግሞ፦ ትንቢት ሳይነገርለት፥ ሱባዔ ሳይቆጠርለት፥ እግዚአብሔር አብ ሳይመሰክርለት፥ ቅዱሳን መላእክትም ብሥራቱንም የምሥራቹንም ሳይናገሩለት የመጣ ማለት ነው። ይኸውም እንደ ይሁዳ ዘገሊላ አንድም እንደ ቴዎዳስ ዘግብፅ ነው። የአይሁድ ሸንጎ በቅዱሳን ሐዋርያት ተቆጥተው ሊገድሉአቸው በወደዱ ጊዜ፥ በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የከበረ ስሙ ገማልያል የሚባል የኦሪት መምህር ነበረ። እርሱም ቅዱሳን ሐዋርያትን ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው ካዘዘ በኋላ፥ «እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በእነዚህ ሰዎች በምታደርጉት ነገር ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ቀድሞም ከዚህ ዘመን በፊት ቴዎዳስ ተነሥቶ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ (እኔ አምላክ ነኝ አለ)፤ አራት መቶ ሰዎችም ተከተሉት፥ ነገር ግን እርሱም ጠፋ፥ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ፥ እንደ ኢምንትም ሆኑ። ከእርሱም በኋላ ሰዎች ለግብር በተቈጠሩበት ወራት ገሊላዊ ይሁዳ ተነሣ፥ ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፥ እርሱም ሞተ፥ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ፥ ከእነዚህ ሰዎች (ከቅዱሳን ሐዋርያት) ራቁ፥ ተዉአቸውም፥ ይህ ምክራቸው ይህም ሥራቸው ከሰው የተገኘ ከሆነ ያልፋል፥ ይጠፋልም። ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን ልታፈርሱት አትችሉም፥ ከእግዚአብሔርም ጋር እንደሚጣላ አትሁኑ።» ብሎአል። የሐዋ ፭፥፴፬፥፴፱።
፩፥፪፦ ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤
    ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር እረኛ ጠባቂ መሆኑን ሲናገር፦ «እግዚአብሔር ይጠብቀኛል፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፥ በዕረፍት ውኃ ዘንድ አሳደገኝ፤» ብሎአል። መዝ ፳፪፥፩። ቸር እረኛ የጠፋውን በግ እስኪያገኘው ድረስ ይፈልገዋል። ይኽንንም፦ «የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና። ምን ትላላችሁ? መቶ በጎች ያለው ሰው ቢኖር፥ ከመካከላቸውም አንዱ ቢጠፋው፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ሊፈልግ ይሄድ የለምን? እውነት እላችኋለሁ፥ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ ስለተገኘው ፈጽሞ ደስ ይለዋል፤» በማለት ነግሮናል። ማቴ ፲፰፥፲፩-፲፫። እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን የፈጠራቸው በነገድ መቶ አድርጎ ነበር። አንደኛው ነገድ (የሳጥናኤል ነገድ) በክህደት በመጉደሉ ምክንያት አዳም መቶኛ ሆኖ ተቈጥሯል። በመሆኑም የጠፋው በግ የተባለው አዳም ነው። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «እነሆ እግዚአብሔር በኃይሉ ይመጣል፥ በክንዱም (በሥልጣኑ፥ በባህርይ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ) ይገዛል፥ እነሆ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ ነው። መንጋውን እንደ እረኛ ይመራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።» በማለት እርሱ አምላካችን የሕይወታችን እረኛ እንደሆነ ተናግሯል። ኢሳ ፵፥፲፩። ነቢዩ ሕዝቅኤል ደግሞ፦ «ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ፥ እጎበኛቸዋለሁ። ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ፥ ከሀገሮችም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ ሀገራቸውም አመጣቸዋለሁ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ፥ በፈሳሾችም አጠገብ፥ በምድርም ላይ ሰዎች በሚኖሩባት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ። በመልካም ማሰማርያ አሰማራቸዋለሁ፥ ጉሮኖአቸውም በረዥሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፥ በዚያ በመልካም ጉረኖ ውስት ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ መሰማሪያ ይሰማራሉ። እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ፥ አስመስጋቸውማለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጠፋውንም እፈልጋለሁ፥ የባዘነውንም እመልሳለሁ፥ የተሰበረውንም እጠግናለሁ፥ የደከመውንም አጸናለሁ፥ የወፈረውንና የበረታውንም እጠብቃለሁ፥ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ።» ብሏል። ሕዝ ፴፬፥፲፩-፲፮።
    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጎቹን ፍለጋ የመጣ ቸር እረኛ በመሆኑ፥ «ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፥ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን ተኲላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፥ ተኲላም መጥቶ በጎቹን ይነጥቃቸዋል፥ ይበትናቸዋልም። ምንደኛስ ይሸሻል፥ ስለ በጎቹም አያዝንም፥ (የምእመናን ጥፋት አያሳዝነውም)፥ ምንደኛ ነውና። (ሥጋዊ፥ ዓለማዊ በመሆኑ መናፍቅ ጳጳስ፥ አላዊ ንጉሥ በተነሣ ጊዜ ይክዳል፤ ምዕመናንን አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ ሐሰተኛ ነውና)። ቸር ጠባቂ (እውነተኛ መምህር) እኔ ነኝ፥ የእኔ የሆኑትን መንጋዎቼን (ወልድ ዋሕድ ብለው ያመኑብኝን) አውቃለሁ፥ የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል፤ (በእኔ ያመኑብኝ እኔን አብነት አድርገው መከራን ይቀበላሉ)፤ ብሏል።
፩፥፫፦ አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን አውቀዋለሁ፤
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው። አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፥ ወልድም በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፥ መንፈስ ቅዱስም በአብ በወልድ ህልው ነው። «እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤» ብሏል። ዮሐ ፲፩፥፲፩። በስም በአካል በግብር ሦስት የሆኑ ሥላሴ በህልውና አንድ እንደሆኑ ሁሉ በመለኰት፥ በሥልጣን፥ በባህርይ፥ በፈቃድ አንድ ናቸው። «እኔና አብ አንድ ነን፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፲፥፴። እንግዲህ፥ አይሁድ በክፋታቸው «ይህ ከወዴት እንደመጣ፥ ማን እንደሆነ አናውቅም፤» ብለውት ስለነበረ፥ እናንተ ባታውቁኝ የባህርይ አባቴ አብ ያውቀኛል፥ እንደማለት፥ «አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን አውቀዋለሁ፤» ብሎባቸዋል። ይኸውም፦ «እኔ ልሰቀል ልሞት መምጣቴን አብ እንደሚያውቅ ሁሉ እኔም የመጣሁበትን ዓላማ አውቃለሁ፤» ሲል ነው። ለዚህ ነው ከዚያው አያይዞ፥ «ለበጎችም ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ፤»ያለው። በማቴዎስ ወንጌልም፦ «ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቀው የለም፤ (ያለ አብ ወልድን በባሕርዩ የሚያውቀው የለም፥ በባሕርይ አንድ ናቸውና)፤ አብንም ከወልድ በቀር፥ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ ማንም የለም። (ያለ ወልድ አብን በባሕርዩ የሚያውቀው የለም)፤» የሚል አለ። ማቴ ፲፩፥፳፯።
ትንቢት ተነግሮለት፥ ሱባዔ ተቆጥሮለት፥ ወደዚህ ዓለም የመጣ ቸር እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ «ከዚህ ቦታ ያይደሉ ሌሎች በጎችም አሉኝ፤ (በኢየሩሳሌም የሌሉ በአራቱ ማዕዘን ያሉ ሌሎች አሉኝ)፤ ቃሌንም ይሰሙኛል፤ (ትምህርቴን ይቀበሉኛል)፤ ለአንድ እረኛ አንድ መንጋም ይሆናሉ። (ለአንድ ለክርስቶስ አካሉ ይሆናሉ፤ አንድም ለአንድ ሊቀ ጳጳስ አንድ ማኅበር፥ አንድ ቤተሰብእ ይሆናሉ)፤ ብሎአል። ይህም ወደዚህ ዓለም መምጣቱ ለቤተ አይሁድ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም መሆኑን ያስተምረናል።
፩፥፬፦ ሥልጣን አለኝ፤
ነፍስንም ሥጋንም ከእመቤታችን ነስቶ (ወስዶ) በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ዓለምን ለማዳን መከራ የተቀበለው፥ የሞተውም በፈቃዱ ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ፦ «ስለዚህም አብ ይወድደኛል፤» ካለ በኋላ «እንደ ገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እአጣለሁና። ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ነገር ግን እኔ በፈቃዴ እሰጣታለሁ፥ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ (ነፍሴን በገነት፥ ሥጋዬን በመቃብር ላኖራቸው ሥልጣን አለኝ)፤ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝ። (ነፍሴን ከሥጋዬ አዋሕጄ በማስነሣት፥ በዕርገት፥ በየማነ አብ፥ በዘባነ ኪሩብ አስቀምጣት ዘንድ ሥልጣን አለኝ)፤ ብሏል። መከራውን፥ ትንሣኤውን እና ዕርገቱን በተመለከተም ነቢያት አስቀድመው ተናግረውታል።
-       «እርሱ ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፥ ስለበደላችንም ታመመ፤ የሰላማችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቊስል እኛ ተፈወስን። . . . እግዚአብሔርም ስለ ኃጢአታችን ለሞት አሳልፎ ሰጠው።» ኢሳ ፶፫፥፭-፮።
-       «እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤» መዝ ፸፯፥፷፭።
-       «እግዚአብሔር በእልልታ፥ ጌታችንም በመለከት ድምፅ አረገ።» መዝ ፵፮፥፭።
በመጨረሻ የምንመለከተው፥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እውነተኛ የበጎች በር እኔ ነኝ፤»ያለበትን ዋና ምክንያት ነው። ይኸውም በር የተከፈተለት እንደሚገባ፥ የተዘጋበት ደግሞ በአፍአ እንደሚቀር ሁሉ፥ በጌታችን ያመነ የመንግሥተ ሰማያት በር ይከፈትለታል፥ ያላመነበት ደግሞ በሩ ተዘግቶበት በአፍአ እንደሚቀር ነው። በመሆኑም በር የተባለው በእርሱ ላይ ያለን እምነት እንደሆነ ከትርጓሜው እንረዳለን። የበሩንንም ቊልፍ ለቅዱሳን አስረክቧል። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ቅዱስ ጴጥሮስን «አንተ ብፁዕ ነህ፥ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች ዐለት ላይም ቤተክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥ የሲኦል በሮችም (ደጅ ጠባቂ አጋንንት) አይበረቱባትም። የመንግሥተ ሰማያትም መክፈቻ እሰጥሃለሁ፥ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል።» ብሎታል። ማቴ ፲፮፥፲፯-፲፱። ሌሎችን ግን፦ «መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተም አትገቡም፥ የሚገቡትንም ከመግባት ትከለክላላችሁ።» ብሏቸዋል። ማቴ ፳፫፥፲፬። ስለዚህ በር በተባለ በኢየሱስ ክርስቶስ ፈጽመን ልናምን ይገባል። እናምናለን ማለት ብቻም ሳይሆን የምናምነውስ ማን እና ምን ብለን ነው ማለትም ያስፈልጋል። ምክንያቱም ስሙን እየጠሩ፥ እንምንበታለን እያሉ፥ ስለ እርሱ የሚያስተምሩት ትምህርት ፈጽሞ መስመር የለቀቀባቸው ብዙዎች ናቸውና። የእኛ ግን መስመሩን የጠበቀው ፍጹም እምነታችን እንደሚከተለው ነው።
፩ኛ፦ ፈጣሪ ነው፥ ብለን እናምንበታለን። «ሁሉም በእርሱ ሆነ፥ (በእርሱ ተፈጠረ)፥ ከሆነውም (ከተፈጠረውም) ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። ዮሐ ፩፥፫።
፪ኛ፦ የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ የባሕርይ አምላክ ነው። «የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፤ እውነተኛም የሆነውን እግዚአብሔርን እናውቅ አንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛውም በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንኖራለን፤ እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው።» ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳።
፫ኛ፦ ፈጣሪ፥ የባሕርይ አምላክ በመሆኑም እግዚአብሔር ነው። «በመጀመሪያ ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ (በፈጣሪነት ከአብ ተካክሎ) ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ (በፈጣሪነት ከመንፈስ ቅዱስም ተካከልሎ) ነበረ። . . . ያም ቃል ሥጋ ሆነ፥ በእኛም አደረ፤ (ነፍስንና ሥጋን ነስቶ በተዋሕዶ ሰው ሆነ)።» ዮሐ ፩፥፩፣ ፩። «አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቁ አንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤» የሐዋ ፳፥፳፰።
፬ኛ፦ ወልድ በተለየ አካሉ ከሰማይ ወርዶ፥ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለዱ በሥልጣን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አላነሰም። «እኔና አብ አንድ ነን፤» ዮሐ ፲፥፴። በሕልውናም አንድ ነው። «እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤» ዮሐ ፩፥፲፩። «እኔን የሚጠላ አቤን ይጠላል። . . . አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተዋል፥ ጠልተውማል።» ዮሐ ፲፭፥፳፫።
፭ኛ፦ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ የተወለደ እርሱ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ነው። «እነሆም፥ በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው።» ማቴ ፫፥፩።
፮ኛ፦ ሰው የሆነው በተዋሕዶ ነው፥ በመሆኑም ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት የለም፥ ይህ የሥጋ ነው፥ ይህ ደግሞ የመለኰት ነው ተብሎ መከፈል የለበትም። አብ «ልጄ ነው፤» ያለው በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ወደ ሠርግ ቤት የተጠራውም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ የለወጠውም ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት የሌለበት አንድ እርሱ ነው። ዮሐ ፪፥፩-፲። ሥጋን እንደተዋሐደ ለማጠየቅ «አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?» ያለም ከሞት ያስነሣም አንድ እርሱ ነው። ዮሐ ፲፩፥፴፬፣፵፫። ከዚህም ሌላ መቃብሩ ሳይከፈት ከመቃብር የወጣው (ሞትን ድል አድርጐ የተነሣው) አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማቴ ፳፯፥፷፮፣፳፰፥፩። በተዘጋ ቤትም በሩ ሳይከፈት ከአንዴም ሁለት ጊዜ የገባው አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ዮሐ ፳፥፲፱፣፳፮።
፯፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅ ዳኛ ነው። «አሁንም በእግዚአብሔር ፊትና በመንግሥቱ በሚመጣበት ጊዜ፥ በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ባለው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እመክርሃለሁ። . . . እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል።» ፪ኛ ጢሞ ፬፥፩፣፰።
፰፦ እኛ የምንለምነውን በቅዱሳንም ጸሎት የምናስለምነውን ሁሉ እርሱ ያደርገዋል። «እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብ በወልድ ይከብር (ይገለጥ) ዘንድ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ። በስሜ የምትለምኑት ነገር ቢኖር ያን አደርግላችኋለሁ።» ዮሐ ፲፬፥፲፪-፲፫። እንግዲህ ሥጋን መዋሐዱን ለማጠየቅ የተናገረውን ቃል፥ አብነት ለመሆንም የሠራውን የትህትና ሥራ ሁሉ በትርጓሜ እያስታረቅን በትክክለኛው እምነት ጸንተን ልንቆም ይገባናል። በአምልኮታችን ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስን፥ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ፥ ከአብ ተካክሎ ልናየው ይገባል እንጂ ዝቅ ልናደርገው አይገባም። «እነሆ ሰማይ ተከፍቶ፥ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ፤» ይላል። ጸሎታችንም፦ ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል፤ . . . አቤቱ ይህን ኃጢአት አትቊጠርባቸው፤» የሚል መሆን አለበት። የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማለጅነት አይለየን። አሜን።  

1 comment:

Betty Jesus said...

1)besmiea yemitilemnuten ale enji .. bemelaekt weyem beqedusan sim mechea ale ????
2) "liferd balew" kale ahun yiferdal mech hone beziyan qen ...mechea? be ferd qen ....not now !!