Thursday, May 31, 2012

በጎ አድራጊ ምእመናን በራሳቸው ተነሳሽነት ለማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ተገለጸ

 ከማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል ድረ ገጽ ላይ የወሰድነው ዘገባ ነው::
•    የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በዮድ አቢሲንያ ተካሄዷል፡፡
•   “ቅዱስ ሲኖዶስ ከእናንተ ጋር ነው፡፡”ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ
•   “ይህን ቤት ለመሥራት የነበረው ውጣ ውረድ፣ የደረሰባቸሁ መከራ በዙ ነው፡፡ ብዙውን ፈተና አልፋችሁታል፡፡” ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኘውን የማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ሕንፃ ማስፈጸሚያ የሚውል በበጎ አድራጊ ምእመናን አነሣሽነትና አስተባባሪነት ሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም. ቦሌ በሚገኘው ዮድ አቢሲንያ የባሕል ምግብ ቤት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተካሄደ፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የአዲስ አበባና የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በመርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት በጸሎት ከፍተውታል፡፡

Monday, May 28, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ዓመታዊ ጉባኤ ተካሔደ

ዘገባውን የወሰድነው ከማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ድረ ገጽ ላይ ነው::
 20ኛ የምሥረታ በዓሉም ተከበረ
(ዴንቨር፣ ኮሎራዶ)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከሉ በየዓመቱ የሚያካሒደው ጠቅላላ ጉባዔ የዚህ ዓመት ስብሰባ ግንቦት 18-19/2004 ዓ.ም በኮሎራዶ ግዛት የዴንቨር ከተማ ተካሔደ። በመላው አሜሪካ ከሚገኙ 11 ንዑሳን ማዕከላት (ቀጣና ማዕከላት) እና 2 ግንኙነት ጣቢያዎች የመጡ አባላት በተሰበሰቡበት በዚህ ጉባኤ ላይ ከዋናው ማዕከል የተወከሉ ሦስት ልዑካን፣ የካሊፎርኒያና የምዕራብ ስቴቶች ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁ፣ አበው ካህናት እና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን በዓመታዊ አገልግሎት ሪፖርትና ዕቅድ እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሒዷል።

ለገዳማት የመብዐና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ

(ማኅበረ ቅዱሳን)፡-በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል በየወሩ እየተዘጋጀ የሚቀርበው የዜና ገዳማት መርሐ ግብር ግንቦት 7 ቀንYemeba Serchet to Monks 2004 ዓ.ም. ተካሔደ፡፡ በዋነኛነት ከየካቲት 24 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ በቆየው የመብዐ ሳምንት በሚል በችግር ላይ ለሚገኙ 400 አድባራትና ገዳማትን ለመርዳት ከምእመናን የተሰበሰበን መብዐ እና አልባሳት /ልብሰ ተክህኖ/ ስርጭት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ 800 ሺህ ብር ለመሰብሰብ የተቻለ ሲሆን እስከ 750 ምእመናን ተሳትፎ አድርገዋል በማለት የገለጹት የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ናቸው፡፡ በተገኘው ገቢ መሠረት ስርጭቱን በ4 ዙር ለማከናወን የታቀደ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር በትግራይ 7 ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ለሚገኙ 50 አድባራትና ገዳማት እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናት ለአንድ ዓመት የሚሆን የመብዐ ስጦታ ተሰጥቷል፡፡

ጳጳሳት ያልተገባ ጥቅም ያገኛሉ መባላችውን ተቃወሙ

(አዲስ አድማስ ጋዜጣ)፡- በጠቅላይ ቤተክህነት የሚታተመው “ዜና ቤተክርስቲያን” የተሰኘ ጋዜጣ፤ ጳጳሳት ያልተገባ ጥቅም ያገኛሉ በሚል ያወጣውን ዘገባ ተከትሎ ጳጳሳቱ ተቃውሞአቸውን ያሰሙ ሲሆን ሲኖዶስ ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ እንዲቋቋም በወሰነው መሰረት ኮሚቴው እንደተቋቋመ ምንጮች ጠቆሙ፡፡  ጋዜጣው በርዕሰ አንቀፁ “የአባቶች ገበና በሕገ ቤተክርስቲያን ሲጋለጥ” በሚል ርዕስ ያሰፈረው  ፅሁፍ፤ የቤተክርስትያኒቱን ሕግ ያልጠበቀና የሐይማኖቱን አንድነት ለመናድ ያለመ ነው ሲሉ  ጳጳሳቱ እንደተቃወሙት ምንጮች አመልክተዋል፡፡ ጉዳዩን እንዲያጣራ የተቋቋመውን ኮሚቴ የሰሜን ጐንደር ሃገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ ናትናኤልና ሌሎች ጳጳሳት እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረጡ ምሁራን እንደሚመሩት የጠቆሙት ምንጮች፤ ኮሚቴው የምርመራውን ውጤት በመጪው ጥቅምት ወር በሚካሄደው የሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ማቅረብ ይጠበቅበታል ብለዋል፡:

Friday, May 25, 2012

ቅዱስ ሲኖዶስ ‹በቦታው› የተገኘበት ስብሰባ እና መግለጫ

ማጠቃለያ ሪፖርታዥ (READ IN PDF)

·   የመግለጫው የመጀመሪያ ረቂቅ ምልአተ ጉባኤው ያልመከረባቸውን ዐበይት ጉዳዮች ያካተተ እንደነበር ተጠቁሟል፤ የዋልድባ እና የነ አባ ፋኑኤል የሐሰት ስኬት በሥርዋጽ ገብቶበት ነበር
·     አባ ጳውሎስ ምልአተ ጉባኤው ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ውሳኔ ባስተላለፈበት ቃለ ጉባኤ ላይ አልፈርምም ብለዋል፤ ስለማኅበሩ በመግለጫው ላይ የሰፈረውን አንቀጽም አላነብምየሚል አተካራ ውስጥ ገብተው ነበር
·     ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ከኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስነት አንሥቶ ወደ ጉጂና ቦረና ሊበን ዞኖች ሀ/ስብከት ለማዛወር በፓትርያ የቀረበው ሐሳብ ውድቅ ተደርጎ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ደርበው እንዲመሩ ተወስኗል
·      አገር ዓቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መሥራች ጉባኤ ከግንቦት 26 - 27 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

  ሙሉ ዘገባው ደጀ ሰላም ብሎግ ነው:: 

Thursday, May 24, 2012

ስለ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን የቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ ቃለ ምልልስ ከብሥራት ሬድዮ ጋር

የማኅበረ ቅዱሳን የዋልድባ ገዳም ሪፖርት ላይ የ "አንድ አድርገን" እይታ

 ከአንድ አድርገን ብሎግ የተወሰደ ነው::
ባሳለፍነው ሳምንት ማኅበረ ቅዱሳን በዋልድባ ገዳም ህልውናን ያናጋል የተባለው የስኳር ልማት ፕሮጀክት ላይ በላካቸው ልኡካን ቡድኖች አማካኝነት ያዩትንና የተመለከቱትን ፤ የእነርሱን እይታ ጨምረው የ9 ገጽ ሪፖርት ማቅረባቸው ይታወቃል ፤  በመጀመሪያ በዚህ ጊዜ ከቤተ ክርስትያኗ ጎን በመቆም የነበረውን ብዥታ ለማጥራት ጊዜ በመውሰድ በዋልድባ አካባቢ ያለውን እውነታ ለማቀመጥ ለደከሙ ወንድሞች አድናቆቴን ማቅረብ እወዳለሁ ፤ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ መናገርም ሆነ አለመናገር የሚያስጠይቅበት ወቅት ላይ አቅም በፈቀደ መጠን ሪፖርቱ የሚያመጣውን የወደፊት ተግዳሮት ግምት ውስጥ በማገባት ይህን ስራ መስራት መቻል ከኃላፊነትም በላይ መሆኑን ላስገነዝብ እወዳለሁ ፤ ቤተክህነቱ ምዕመኑን አንገት ያስደፋ ሪፖርት ስሙኝ በማለት የኢቲቪ ጋዜጠኞችን ጠርቶ ቢያቀርብም እንኳን አሁን ደግሞ ግልጽ ያለ ነገር ምዕመኑ ማወቅ ችሏል ፤ ይህን ሪፖርት ያስቀመጣቸውን ጥሬ ሀቆች ፤ አጠይሞ ያስቀመጠውን እና የጥናቱን ውስንነት ለመዳሰስ እንወዳለን፡፡

Wednesday, May 23, 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ የ2004 ዓ/ም የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ መግለጫ

አባቶቻችን በተሐድሶ መናፍቃን የወሰዱት የማያዳግም ውሳኔ አስደስቶናል::እንኳን ደስ አለን ተዋሕዶያውያን!!!

በዘንድሮው የግንቦት ወር የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ብፁዓን አባቶቻችን ሐዋርያዊት ለሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ እና ታሪካዊ  ውሳኔዎች በማስተላለፍ ጉባኤው ተጠናቋዋል:: ተመክረው አልመለስ ያሉት ውስጠ አርዮሳውያን እና ንስጥሮሳውያን የተሐድሶ መናፍቃን ተወግዘው እንዲለዩ ተወስኖዋል:: አምላከ ቅዱሳን የማይለያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ብዙ ፈተናዎች እንዳሳለፈች የቤተ ክርስቲያንናችን የታሪክ መዛግብት ያትታሉ:: ፈታኞቿ በመከራው ዘመን ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን ያሸነፉ ቢመስላቸውም የመከራው ዘመን ሲያልፍ ቤተ ክርስቲያን በድጋሚ እያበበች እና እየተሰፋፋች ኖራለች:: ትኖራለችም:: ዮዲት ጉዲት ጥንታውያን መጻሕፍ አቃጥላ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ አልባ ለማድረግ ሞክራ ነበረ:: ነገር ግን እነ  አባ ሰላማ መተርጉም ተነስተው ቅዱሳት መጽሐፍት በድጋሚ እንዲጻፍ አደረጉ:: እናም ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ተሸንፋ አታውቅም:: አትሸነፍምም::

ጽጌ ስጦታውና ሰባት ግለሰቦች ማዕርገ ክህነታቸው ተገፎ እንዲወገዙ ተወሰነ

የቅዱስ ሲኖዶስ ዐሥረኛ ቀን የቀትር በኋላ ውሎ(የደጀ ሰላም ዘገባ)

·         ቅዱስ ሲኖዶስ በውሳኔው መግለጫ ዝግጅት ላይ ጥንቃቄ አድርጓል፤ በመላው ዓለምየሚሠራጨውን መግለጫ በጽሑፍ የሚያዘጋጁት ከምልአተ ጉባኤው የተመረጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው።
·      አባ ሰረቀ በተጠየቁበት ጉዳይ እምነታቸውን በጽሑፍ ይገልጣሉ፤ ለ”እውነትና ንጋት” ሌላ ማስተባበያ መጽሐፍ እንዲጽፉ ተወስኗል።
·        ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ለፕሮቴስንታንት ቤተ እምነት የጻፉት ደብዳቤ የእርሳቸው ላለመኾኑ በጽሑፍ ያረጋግጣሉ።
·        በጋሻው ደሳለኝ ተጨማሪ ስሕተቶቹ ተመርምረውና ራሱም ተጠይቆ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብ ተወስኗል።

·         ሊቃውንት ጉባኤው በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚነሡ ማንኛውንም የሃይማኖት፣ የሥርዐትና የታሪክ ጥያቄዎች ለመመለስ በሚያስችል የሰው ኀይልና በልዩ በጀት እንዲጠናከር ተወስኗል።
 (ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 15/2004 ዓ.ም፤ May 23/ 2012)፦ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በትናንት፣ ግንቦት 15 ቀን 2004 ዓ.ም የቀትር በኋላ ውሎው በቅዱስ ሲኖዶስ የተሠየመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ኮሚቴ በሐሰተኛ ትምህርታቸው ሊወገዙና ሊለዩ ይገባቸዋል ባላቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ግለሰቦች ላይ ያቀረበውን ጥናታዊ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ አጸደቀ፡፡