Tuesday, May 8, 2012

በዋልድባ ጉዳይ ደብዳቤዎች ለቅ/ሲኖዶስ እና ለጠ/ሚኒስትሩ ተላኩ

ከደጀ ሰላም የተወሰደ ነው::
 “ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ ጊዚያዊ ኮሚቴ” የተሰኘ ስብስብ “ታሪካዊ የዋልድባ ገዳማችን ይዞታና የመነኮሳት ሰብዓዊ መብት” ይከበር ሲል ጥያቄውን ለቅ/ሲኖዶስ እና ለጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አቅርቧል። መቀመጫውን በዋሺንግተን ዲሲ ያደረገው እና ከዚህ በፊት ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ያዘጋጀ ኮሚቴ ሲሆን የላካቸውን ሁለት ደብዳቤዎች ከዚህ በታች ያንብቡ። ፒ.ዲ.ኤፍ ማንበብ ለሚፈልጉ በስተመጨረሻ ማግኘት ይቻላል።
ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን

ደብዳቤ አንድ፦ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከ (PDF)
ለአቶ መለስ ዜናዊ
ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ
ጉዳዩ  ፦  ታሪካዊ  የዋልድባ ገዳማችን ይዞታና  የመነኮሳት ሰብዓዊ መብት  እንዲከበርልን  ስለመጠየቅ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ታሪክ ማኅበራዊና ሥነ- ጥበብ እድገት ያበረከተችው  አስተዋጽዖ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም የሚታወቅ አውነታ ነው ። ቤተ ክርስቲያናችን ባላት  ታሪክና መንፈሳዊ  ሀብት ለበርካታ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ትልቁን ድርሻ የምትይዝ ሲሆን  በዚህም መንግሥትንና የተለያዩ ተቋማትን ተጠቃሚ እያደረገች ስትገኝ ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶችም በዋነኛነት የቤተ ክርስቲያናችንን  ጥንታዊያን ገዳማት አድባራት እና እንደ ጥምቀት መስቀል/ደመራ/ እና ልደት የመሳሰሉ ታላላቅ በዓላት መንፈሳዊ  አከባበርን ለመመልከት እንደሚመጡ   ዘወትር የሚመሰክሩት ነው ።  በአጠቃላይ  ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ  ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ጥበብ እድገት ያበረከተችውን አስተዋጽዖ በየትኛውም ዘመን የነበረ እና ወደፊትም የሚኖር  በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ይዘነጋዋል ብለን አንጠብቅም። በተለይም አሁን አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው መንግሥት  የባህልና ቱሪዝም ኮሚሽንን የበለጠ አጠናክሬ እሰራለሁ ብሎ በተነሳበት ፤ በዚህ ሰዓት  የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሆነባትን ቤተ ክርስቲያን ገዳማቷ እና  አድባራቷ እንዲጠበቁ ማድረግ  መንግሥታዊ  የአስተዳደር ኃላፊነቱ ነው ።
ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ጥቃት በኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት እንዲሁም ሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ መድረሱ ፤ በወቅቱም መፍትሔ ሳይገኝላቸው እየተባባሱ መምጣታቸው የእምነቱን ተከታዮች የበለጠ እያሳሰበን መጥቷል።  በእነዚህ ገዳማት እና አድባራት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እንዳይከሰት ማድረግ ፤ ጥፋቱን ያከናወኑ ሰዎችም በወቅቱ ፍርድ እንዲያገኙ  አለመደረጉ ፤ መንግሥትም የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ እና መብት በመጠበቅ ለሌሎች ጭምር ምሳሌ መሆን ሲገባው አገርን ለማስተዳደር ከወሰደው ኃላፊነት  አንጻር የተከሰቱትን ችግሮች ስንመለከት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ  መንገድ መንግሥትን ተጠያቂ እንደሚያደርገው አምነንበታል ። አንድን መንግሥት ትክክለኛ መንግሥት  የሚያሰኘው ከሚያስተዳድራቸው ሕዝቦችና የሃይማኖት ተቋማት የሚቀርቡትን  አቤቱታ  ሰምቶ በወቅቱ ትክክለኛ ፍርድ እና አስተዳደራዊ ውሳኔ በመስጠት እንጂ የሚመራው ሕዝብና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሰቀቁ  የሚያደርግ ምላሽና እርምጃ በመውሰድ አይደለም ።  የሕዝብን ድምጽ አለመስማት ፤ የቤተ ክርስቲያንንም አቤቱታ አለመቀበል  ትዕግሥትን የሚፈታተን ፤ መፍትሔ ካልተሰጠውም ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ነገሮች እንዲሔዱ  የሚያደርግ፡ አገርን የሚጎዳ፡ ታሪክንም የሚያበላሸ ክስተትን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ። እኛም ይህንን ደብዳቤ የምንጽፈው መንግሥት አገርን  የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብና በኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም ለመጠየቅና የተሰማንን ሐዘን በምሬት  ለመግለጽ ነው ።
ይህ ችግር ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ እና በተለያዩ ዓለማት የምንገኝ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች በየሳምንቱ በስልክ እንዲሁም በአካል በመገናኘት ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በመነጋገር ላይ  እንገኛለን። ይህንን ጉዳይ ለማሳሰብ በአሜሪካና ካናዳ የተለያዩ ግዛቶች በርካታ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በተገኙበት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ዓለማቀፋዊ ተቋማት ቢሮዎች ሰላማዊ ሰልፍ አድርገናል። አሁንም ጉዳዮን  ለኢትዮጵያ መንግሥትና  ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለማሳሰብና የዋልድባ ገዳም የቦታ ይዞታ  እና የመነኮሳትም ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ግንቦት 27 ቀን 2004 ዓ. ም በአሜሪካና በካናዳ የተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ተላልፏል ።
የዋልድባ ገዳም መነኮሳት እያቀረቡ ያለውን አቤቱታ  ትኩረት ሳይሰጠው የተከበረው የቅድስና ቦታ ለልማት በሚል ሰበብ መንፈሳዊ ስሜትን በሚጎዳና ለቤተ ክርስቲያን  እየተሰጠ ያለውን ንቀት በሚያመላክት ደረጃ በመንግሥት ጭምር አሳዛኝ ምላሽ መሰጠቱ  ከፍተኛ ቁጣ  ፈጥሮብናል ። ስለዚህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት ስናቀርብ  ለጥያቄዎቻችን ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሰጠን ተስፋ በማድረግ ነው ፦
  1.    የዋልድባ ገዳም የኢትዮጵያውያን ሁሉ መንፈሳዊ ሀብትና የተቀደሰ ቦታ በመሆኑ የገዳሙ መነኮሳት ባቀረቡት አቤቲታ መሠረት  የገዳሙ ክልል በማንኛውም ወገን እንዳይደፈርና ለልማታዊ ተግባር በሚል ሰበብ  የተጀመረው የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት እንቅስቃሴ አሁን ባለበት ቦታ በከፍተኛ ሁኔታ ሃይማኖታዊ ህልውናችንን ስለሚዳፈር በአስቸኳይ እንዲቆምልን እና ከገዳሙ ክልል ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወር እንጠይቃለን ፤
  2.    የኢትዮጵያ ገዳማት እና አድባራት ለኢትዮጵያውያን ሁሉ መንፈሳዊ ሀብትና የቅድስና ቦታዎች ስለሆኑ የቦታ ይዞታቸው በማንም እንዳይደፈር ማረጋገጫ  በመንግሥት  እንዲሰጥ፤
  3.    በኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት እና ክርስቲያኖች  ላይ የሚደርሰው ጉዳት በግልጽ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አንዲዘገብ ፤
  4.    የቤተ ክርስቲያንን መልካም ስም በሚያጎድፍ መልኩ ጥላቻቸውን የሚያንጸባርቁ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከዚህ ተግባራቸው ተቆጥበው  ሕዝቡን  በትክክለኛ አስተዳደር እንዲመሩ  እንዲደረግልን ፤
  5.     የቤተ ክርሰቲያንን መብት ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀሱ አባቶች እና ክርስቲያኖቸ ላይ ዛቻና አንግልት እንዲቆም እንጠይቃለን ።
  6.    በመንግሥት ባለስልጣናት ገዳማውያኑ ላይ የተለየ የፖለቲካ ተልዕኮ ያላችሁ ናችሁ በሚል ሰበበ የሚደርስባቸው እንግልት በአስቸኳይ እንዲቆም።
  7.    በአሁን ሰዓት በገዳሙ ዙሪያ የሚደርሰውን ዝርፊያና ምዝበራ መንግስት ለገዳማውያኑም ሆነ ለቅርሶቹ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግ እንጠይቃለን።
                           እግዚአብሔር አገራችንን  እና ገዳማችንን ይጠብቅልን
ግልባጭ
·         ለአፊዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
·         ለአፊዲሪ ፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
·         ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
·         ለትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
·         ለኢትዮጵያ ኤምባሲ  ዋሽንግተን ዲሲ
·         ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ኦታዋ
·         ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
·         ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት
·         ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
·         ለብፁዓን አባቶች በያሉበት

ደብዳቤ ሁለት፦ ለቅ/ሲኖዶስ ተላከ (PDF)
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ
ጉዳዩ  ፦  የታሪካዊ  የዋልድባ ገዳማችን ይዞታና  የመነኮሳት ሰብዓዊ መብት  እንዲከበርልን  ስለመጠየቅ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ያደረጉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑን በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ ነው። የቤተ ክርስቲያንን እና የክርስቲያኖችን መብት የማስጠበቅ ፤ እውነትን የመመስከር እና ምእመናንን በትክክለኛው መንገድ የመምራት ኃላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ እንደሆነ ይታወቃል፣  ቅዱስ ሲኖዶስ የገዳማት የቦታ ይዞታ እና የመነኮሳት መብት በሚጣስበት በአሁኑ ወቅት ትክክለኛ አመራር ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን  መስጠት ይጠበቅበታል ። 
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በታላቁና በታሪካዊ የዋልድባ ገዳም ላይ መንግሥት የስኳር ፋብሪካ ልማት በሚል ሰበብ የገዳሙን እና ገዳማውያኑን መብት በሚጥስ መልኩ እና እንግልት እያደረሰ ለመሆኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙኅን ሰምተናል።  ይህ ችግር ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ እና በተለያዩ የዓለማት የምንገኝ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች በተለያዩ የአሜሪካን፣ የካናዳ ከተሞች እና በተለየዩ የዓለማችን ክፍሎች በየሳምንቱ በስልክ እንዲሁም በአካል በመገናኘት ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በመነጋገር ላይ  እንገኛለን። ይህንን ጉዳይ ለማሳሰብ በአሜሪካ ፣ በካናዳ የተለያዩ ከተሞች እንዲሁም በተለለያዩ ዓለማት በርካታ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በተገኙበት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገናል። አሁንም ጉዳዮን  ለኢትዮጵያ መንግሥትና  ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለማሳሰብና የዋልድባ ገዳም የቦታ ይዞታ  እና የመነኮሳትም ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ግንቦት ፳፯ ቀን ፳፻፬ ዓ. ም በዋና ዋና የአሜሪካ ከተሞችና በካናዳ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ተላልፏል ። ከዚህ በፊት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተወክለው የሄዱትና ሪፖርት ያቀረቡት ዓለም ያወቀውን ጸሐይ የሞቀውን ጉዳይ ለቤተ ክርስቲያን ወገንተኝነት በሌለው መልኩ ያቀረቡት የማደናገሪያ ሪፖርት ሁላችንንም አሳዝኖናል ። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተሰጣችሁ መንፈሳዊ ኃላፊነት የተነሳ እውነቱን መናገርና የገዳማትን መብት የማስከበር ከፍተኛ ገድል ስለሚጠበቅባችሁ ይህንን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን አቋም በትክክል ለመንግሥታና ለዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲገለጽ እየጠየቅን በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት  ተከታዮች በሙሉ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር ለእውነት የምንቆም መሆናችንን ማረጋገጥ እንወዳለን ። ተመሳሳይ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መንግሥት  የተላከ መሆኑን እንገልጻለን::
እግዚአብሔር ገዳማችንን ይጠብቅልን
ግልባጭ
  •          ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት
  •          ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
  •      ለብፁዓን አባቶች በያሉበት

3 comments:

getachew said...

egziabher yibarikachihu

Anonymous said...

“የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች” አሉ፡፡ እናንተ ሀገሬ የምትሏትን ኢትዮጵያ ጠልታችሁ፣ ክዳችሁ አይደለም እንዴ በሰው አገር (ተመችቷችሁም ባይሆን ) እየኖራችሁ ያላችሁት? እባካችሁ አትበጥብጡን የኛውን በኛው እንፈታዋለን፡፡ ደግሞስ ይሁን ያለው ሊሆን አይሁን ያለው ላይሆን ይችላልና የእግዚአብሔርን ብቻ ብንጠባበቅ ይሻለናል፡፡ እባካችሁ ጃንክ ፈዳችሁን እየበላችሁ እዛው በፀበላችሁ ኑሩ ፤፤፤

Anonymous said...

አወ እየተሠራ ያለዉ ነገር በውነቱ በጥዓም ያሣዝናል

ዕባካችሑ ጽዐወች እዉነትን ተሸከሙ