Wednesday, May 9, 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ጸሎት ተካሄደ

ዘገባው የደጀ ሰላም ነው::

Photo: Courtesy of  Anke Wagner 
 
  •  “የቅዱስ ሲኖዶስ ሥራ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና መጠበቅ ነው፤ ስለ ሃይማኖት መጠበቅና ስለ ምእመናን ሕይወት መጽናት የማይነጋገር ሲኖዶስ ከተራ የመንደር ስብሰባ ተለይቶ አይታይም” /ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/ 
  • ፓትርያሪኩ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱና በልማት ኮሚሽኑ ስም በተንቀሳቃሽ እና በቁጠባ ሒሳብ የተመዘገቡ የባንክ ሒሳብ አንቀሳቃሾችን በተመለከተ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ያስተላለፉት ጥያቄ ከጉባኤው አነጋጋሪ አጀንዳዎች አንዱ እንደሚኾን ይጠበቃል

·         የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ቅዱስ ሲኖዶስ ለኮሚሽኑ በሰጠው መምሪያ መሠረት የፓትርያሪኩን ጥያቄ ያገዱ ሲኾን ፓትርያሪኩ በበኩላቸው ብፁዕነታቸው “የቀደመው ዐይነት [የ2001ዱ] ሁከት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሱ ነው” የሚል ክስ ለመንግሥት መጻፋቸው ተሰምቷል
·         ቅዱስ ሲኖዶስ በገዳማት ይዞታና በመነኰሳት መብት መከበር ላይ ቤተ ክርስቲያን ያላትን አቋም እንዲገልጽ ተጠይቋል
·         የዋሽግንተን ዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት ልኡካን “ቃለ ዐዋዲው ይከበር፤ የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ይጠበቅ” በሚል አቡነ ፋኑኤልን የተመለከቱ አቤቱታዎችን ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል
·         ማኅበረ ቅዱሳን በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መ ዋና ሓላፊ ላይ የተወሰደውን ሕገ ወጥ ርምጃ ቅዱስ ሲኖዶስ ተመልክቶ እንዲወስንበት ጠይቋል፤ ማኅበሩ በሕገ ወጥ መንገድ ከተሾመው ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተ ጋራ ለመሥራት እንደሚቸገር ገልጧል
 (ደጀ ሰላም፤ ሚያዚያ 30/2004 ዓ.ም፤ May 8/2012)፦ ፍትሕ መንፈሳዊ በአምስተኛው አንቀጽ ቁጥር 164 በሚያዝዘው መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ መደበኛ ስብሰባ ያካሂዳል፡፡ የመጀመሪያው ጉባኤ በየዓመቱ ጥቅምት 12 ቀን ሲኾን የሁለተኛው ጉባኤ ደግሞ ትንሣኤ በዋለ በ25ው ቀን /በርክበ ካህናት/ የሚካሄደው ነው፡፡ የዘንድሮው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመክፈቻ ጸሎት ዛሬ፣ ሚያዝያ 30 ቀን 2004 ዓ.ም ተሲዓት በኋላ በመንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተካሂዷል፡፡
የመክፈቻ ጸሎት መርሐ ግብሩን አስመልክቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስን ጨምሮ 26 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት የጸሎት ሥነ ሥርዐቱ ተከናውኗል፡፡
መርሐ ግብሩ የጸሎቱን ሥነ ሥርዐት በሚከተለው ቅደም ተከተል መሠረት ይገልጸዋል፡-
ሀ. ዳዊት
ለ. ውዳሴ ማርያም ይደገማል፤
ሐ. አድኅነነ ሕዝበከ ይባላል፤
መ. መልክአ ማርያም ደርሶ እግዝእትነ በዜማ ይሰማል፤
ሠ. መልክአ ኢየሱስ ተደግሞ ኢትግድፈነ የሚለው በዜማ ይደርሳል፤
ረ. መስተብቍዕና ሊጦን ዘሠርክ አምላክነ ዘዲበ ኪሩቤል ትነብር የሚለው ይዜማል፤
ሰ. ዘበእንቲአሃ ለቤተ ክርስቲያን ተጸፋዕከ በውስተ ዐውድ የሚለው ደርሶ መሐረነ አብ ተብሎ አጭር እግዚኦታ ይደርሳል፤
ሸ. ምስባክና የወንጌል ምንባብ ከተሰማ በኋላ በአራራይ ዜማ ቅዱስ ተብሎ የሠርክ ኪዳን ይደርሳል፡፡
የመክፈቻ ጸሎቱ በተጠቀሰው ቅደም ተከተል ከተከናወነ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ቃለ ምዕዳን አሰምተው ቡራኬ እንደሚሰጡ የተገለጸ ቢኾንም ትምህርቱ የተሰጠው በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ - ሰላሌ እና የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበር፡፡ 
ብፁዕነታቸው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 18 ቁ. 18 ላይ በተመሠረተውና ለዕለቱ መርሐ ግብር ተስማሚ አድርገው ባቀረቡት ትምህርታቸው “ልዑል እግዚአብሔር በማይወሰን ቸርነቱ ለዚህ ዕለትና ሰዓት ካደረሰን ዘንድ የምናስተላልፈው መልእክት÷ አባቶቻችን ሐዋርያት፣ ሠለስቱ ምእት፣ ሊቃውንትና መምህራን እንዳስተማሩን የምንከተለው የቀናውን የሃይማኖት መንገድ ነው” የሚል እንደ ኾነ አመልክተዋል፡፡ ከዚህም ጋራ በማያያዝ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ጥምቀትን፣ ምሥጢረ ቍርባንንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ለሁሉ በሚረዳው ፍሰትና ትይይዝ እያብራሩ አቅርበዋል፡፡ በተለይም የምሥጢራት ሁሉ ጉልላት በኾነው የምሥጢረ ሥጋዌው ክፍል “ወልደ እግዚአብሔር፣ ቃለ እግዚአብሔር በተለየ አካሉ በተወላዲነት ግብሩ ንጽሐ ጠባይዕ ካላደፈባት ንጽሕት ድንግል እመቤታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተወልዶ ሰው ኾነ፤ በዚህም የሥጋ ገንዘብ ለቃል፣ የቃል ገንዘብ ለሥጋ ኾነ” በሚል አጽንዖት የሰጡባቸው ኀይለ ቃላት ወቅታዊም መልእክት እንዳላቸው ብዙዎች የተግባቡባቸው ናቸው፡፡
ብፁዕነታቸው ዕለቱን አስመልክቶ ሲያስረዱ “ሲኖዶስ ማለት የኤጲስ ቆጶሳት፣ የጳጳሳት ጉባኤ ነው፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ሥራ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና መጠበቅ” እንደ ኾነ ገልጸዋል፡፡ የዘላለም ሕይወት፣ ድኅነት የሚገኝባትን የቀናችውን ሃይማኖት የመጠበቅ ሓላፊነት ከእግዚአብሔር የተሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስ ከሌላው ተለይቶ ቅዱስ የሚባለው ከእግዚአብሔር በተቀበለው አደራ ሃይማኖት የሚጸናበትን፣ የሰው ልጆች ሕይወት ወደ እግዚአብሔር የሚቀናበትን፣ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያት የሚሰፋበትን ሥራ በጥንቃቄ መፈጸም ስለሚገባው መኾኑን አስረድተዋል፡፡ በተፃራሪው ስለ ሃይማኖት መጠበቅና ስለ ምእመናን ሕይወት መጽናት የማይነጋገር ሲኖዶስ ከተራ የመንደር ስብሰባ ተለይቶ እንደማይታይ ብፁዕነታቸው አሳስበዋል - “ቅዱስ ሲኖዶስ በተሰበሰበ ቁጥር አጀንዳ ቀርጾ፣ ርእስ አድርጎ የሚነጋገረው የሃይማኖት ነገር፣ የምእመናን ሕይወት ያለበት ጉዳይ በመኾኑ ያስጨንቀዋል፡፡ ይህን ችላ ካለ ግን ቅዱስ አይደለም፡፡”
ብፁዕነታቸው በመጨረሻም ዛሬ አባቶችም ምእመናንም ተሰብስበን “ስምአነ አምላክነ ወመድኃኒነ” ያልነው ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን አደራ ለመፈጸም በጸሎት መጠየቅ አስፈላጊ መኾኑን በማስታወስ “ጉባኤውን ፍጻሜውን ያሳምርልን፤ ሥራችንን የተቃና እንያደርግልን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን” በማለት ትምህርታቸውን አጠቃለዋል፡፡
በነገው ዕለት የምልአተ ጉባኤውን የመወያያ አጀንዳዎች አርቅቀው የሚያቀርቡ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ኮሚቴ በመሠየም ሥራውን የሚጀምረው የቅዱስ ሲኖዶሱ መደበኛ ስብሰባ ከጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎች አፈጻጸም ይቀርቡበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከእኒህም መካከል የቃለ ዐዋዲው ማሻሻያ ሐሳቦች፣ የቤተ ክህነቱ መዋቅር ጥናት፣ በአባ ሰረቀ እምነት ሕጸጽ፣ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅነት መረጃ የቀረበባቸው ግለሰቦች እና ማኅበራትን አስመልክቶ የተቋቋሙት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አጣሪ ኮሚቴ እና የሊቃውንት ጉባኤ ሪፖርቶችና የውሳኔ ሐሳቦች ይገኙባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል የቤተ ክህነቱ ምንጮች በምልአተ ጉባኤው አነጋጋሪ ኾነው ሊነሡ ይችላሉ ያሏቸውን ሌሎች አጀንዳዎች ጠቁመዋል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

No comments: