Friday, May 11, 2012

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ህልውና አጠያያቂ ኾኗል

·        ፓትርያርኩ በሰባት ወራት ውስጥ ከግማሽ ሚልዮን ብር በላይ ከኮሚሽኑ ጠይቀዋል

·        የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔና የኮሚሽኑን አሠራር በመጣስ የኮሚሽኑን ሊቀ ጳጳስ ከቼክ ፈራሚነት ሰርዘዋል፤ አካሄዱን የጠ/ቤ/ክ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የኮሚሽኑ ሠራተኞች ተቃውመዋል

·        የአመራር ብቃት ማነስ ያለባቸው ኮሚሽነሩ የአቡነ ጳውሎስን ፍላጎት ብቻ ለማስፈጸም ቅድሚያ በመስጠት ለጋሾችን አስመርረው ከኮሚሽኑ እንዲሸሹ አድርገዋል፤ የሠራተኛውን ሞራል በማጥፋት ተስፋ አስቆርጠዋል

·        ልማት ኮሚሽኑን አጥብቆ የጎዳው ታማኝ መስለው የሚሾሙ ኮሚሽነሮች መኾናቸውን የቀደሙት የኮሚሽኑ የሥራ ዘመናት ያስረዳሉ(የኮሚሽኑ ሠራተኞች)፤

ሙሉ ዘገባውን የወሰድነው ከደጀ ሰላም ብሎግ ነው::
 የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን ከመንፈሳዊ ተልእኮዋ ጎን ለጎን የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ የበኩሏን አስተዋፅኦ ለማድረግ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንን ታኅሣሥ 26 ቀን 1964 ዓ.ም አቋቁማለች፡፡ ኮሚሽኑ በዐዋጅ ቁጥር 621/2001 እና ደንብ ቁጥር 168/2001 በሚደነግገው መሠረት በዳግም ምዝገባ ሰርቲፊኬት ቁጥር 1560 የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት ኾኖ ተመዝግቧል፡፡ በበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ዐዋጅ ቁጥር 621/2009 መሠረት ማናቸውም የልማትና በጎ አድራጎት ማኅበር በቦርድ ብቻ የሚተዳደር ኾኖ አመራሩ በቦርድ ወይም በጠቅላላ ጉባኤ እንዲከናወን ስለሚያዝ ኮሚሽኑ 9 የቦርድ አባላት እና 20 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ባሉት ስብጥር እንዲዋቀርና እንዲደራጅ መደረጉን የኮሚሽኑ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

በፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር፣ በውኃ ሀብት ልማት እና በመሳሰሉት የማኅበረሰብ ልማቶች ዙሪያ የሚንቀሳቀሰው ይኸው የቤተ ክርስቲያናችን የልማት ክንፍ ከሰሞኑ በህልውና ፊት የተጋረጠ አደጋ እንደገጠመው የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስና ሠራተኞች እየተናገሩ ነው፡፡

ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በኮሚሽኑ ስም የተከፈቱትን የተንቀሳቃሽና ቁጠባ ሒሳቦች እንዳያንቀሳቅሱ ፊርማቸው እንዲሰረዝ ለአምስት ባንኮች የጻፉት ደብዳቤ በፓትርያርኩና በሊቀ ጳጳሱ መካከል የተዳፈነውን አለመግባባት ዳግመኛ ቀስቅሶታል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የፊርማ ስረዛውን ትእዛዝ የሰጡት በለጋሾች፣ በመንግሥት አካላት እና በኮሚሽኑ የጋራ ስምምነት ተፈርሞ በመጣው ገንዘብ ላይ ለበርካታ ጊዜ የሚያቀርቡትን አግባብ ያልኾነ ጥያቄ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በተደጋጋሚ በመቃወማቸውና በማገዳቸው መኾኑ ተገልጧል፡፡

አቡነ ሳሙኤል
ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ከቼክ ፈራሚነት ለማንሣት በስውር በጠሩት የቦርድ አባላት ስብሰባ ተላለፈ የተባለን ውሳኔ ሕጋዊ ልባስ በማድረግ ከኮሚሽኑ ደንብና መመሪያ ውጭ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስና ኮሚሽነሩ በጣምራ ቼክ እንዲፈርሙ ደብዳቤ ለኮሚሽኑ ልከዋል፡፡ ቼክ ከመፈረሙ በፊት ግን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ደብዳቤውን አግኝተው በማገድ ቅዱስ ሲኖዶስ በ2000 ዓ.ም ያወጣውን ሕገ ደንብ እንደሚፃረር በመጥቀስ ለኮሚሽነሩና ለማኔጅመንት አባላት ጽፈዋል፡፡ ይኹን እንጂ አሁንም በድጋሚ ፓትርያርኩ በቀጥታ የኮሚሽኑ የቁጠባና ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ለሚገኙባቸው ባንኮች በመጻፍ የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ፊርማ ተሰርዞ አሠራሩ እንዲለወጥ ማዘዛቸው ነው የተመለከተው፡፡

ፓትርያርኩ በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ምትክ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስ ከኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጋራ በጣምራ ፊርማ ቼኮቹን እንዲያንቀሳቅሱ ለኮሚሽኑ ያቀረቡት ጥያቄም በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተቃውሞ ሳቢያ ተቀባይነት እንዳላገኘ የኮሚሽኑ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የፓትርያርኩ ጥያቄ ጥቅምት 12 ቀን 2000 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወስኖ በሥራ ላይ በዋለው መመሪያ አንቀጽ 17 ቁጥር 2፡- “በኮሚሽኑ ስም የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦች ሁሉ በኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ፣ በኮሚሽነሩና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሦስቱ በሚገኙት በሁሉ ጣምራ ፊርማ ይንቀሳቀሳሉ” የሚለውን እንደሚፃረር በመጥቀስ በኮሚሽኑ በተከፈቱ ተንቀሳቃሽም ኾነ የቁጠባ ሒሳቦች ላይ እንደማይፈርሙ ሚያዝያ 22 ቀን 2004 ዓ.ም ለኮሚሽኑ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡

አቡነ ፊልጶስ
የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስ ተቃውሞ አላገዳቸውም የተባሉት አቡነ ጳውሎስ በቁጥር ል/ጽ/439/301/04 በቀን 29/8/2004 ዓ.ም በቀጥታ ለአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ቅርንጫፎች፣ ለወጋገን ባንክ አክስዮን ማኅበር አራዳ ቅርንጫፍ እና ለአቢሲኒያ ባንክ ፍልውኃ ቅርንጫፍ በጻፏቸው ደብዳቤዎች “ብፁዕ አባ ፊልጶስ ሌላ ጉዳይ ስላጋጠማቸው አልተመቻቸውም” በሚል የኮሚሽኑ የፋይናንስ መምሪያ ሓላፊ አቶ ከበደ በየነ ተተክተው ከኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጋራ ሒሳቦቹን በጣምራ ፊርማ እንዲያንቀሳቅሱ ባንኮቹ ትእዛዝ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው ተመልክቷል [በዚህ የአቡነ ጳውሎስ ጥያቄ ምክንያት ለልማት ኮሚሽኑ በመቆርቆሩ እና የፓትርያርኩን ጥያቄ ተፈጻሚ በማድረግ መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት የኮሚሽኑ ፋይናንስ መምሪያ ሓላፊ በልብ ሕመም ሳቢያ በአንድ ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ መኾኑ ተሰምቷል]፡፡

ፓትርያርኩ ጥያቄያቸው ተፈጻሚ እንዲኾን ትእዛዝ የሚያስተላልፉት በኮሚሽነሩ ኮሚሽነር ዶ/ር አግደው ረዴ በኩል ሲኾን የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳሙኤል በበኩላቸው የኮሚሽኑ ሥራ ሕግንና ደንብን ተከትሎ እንዲከናወን በማሳሰብ ኮሚሽነሩ ዶ/ር አግደው ረዴ “ለግለሰባዊ ፍላጎትና ሐሳብ ቅድሚያ ከመስጠትና ተባባሪ ከመኾን እንዲቆጠቡ፤ የኮሚሽኑን የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች ሥራ ማስፈታት እንደሌለባቸው” መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም እና ሚያዝያ 22 ቀን 2004 ዓ.ም በቃል እና በጽሑፍ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ምንጮቹ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ለኮሚሽነሩ ከጻፏቸው ደብዳቤዎች ለመረዳት እንደተቻለው የፓትርያርኩ ጥያቄ የሊቀ ጳጳሱ ስምምነት እና ዕውቅና የሌለበት፣ መመሪያን የሚፃረርና በማን አለብኝነት የሚፈጸም ነው፡፡ ይህም ኮሚሽኑ ከበጎ አድራጊዎች በልገሳ የሚያገኘውን ገንዘብ ከተያዘለት ዕቅድና ዓላማ ውጭ እንዲባክን የሚያደርግ በመኾኑ በጊዜው ካልታረመና ካልተስተካከለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሀገር ልማትና ዕድገት ላይ ያላትን የላቀ ድርሻና መልካም ስም ያደበዝዛል፤ የኮሚሽኑን ህልውናም አደጋ ላይ ይጥላል፡፡

የኮሚሽኑ ሠራተኞች በበኩላቸው እንዳስታወቁት “ለተቸገሩ ወገኖች የትንሣኤ በዓል መዋያ ርዳታ ለመስጠት” በሚል በፓትርያርኩ ትእዛዝና በአቡነ ገሪማ ፊርማ በተጻፈው ደብዳቤ የተጠየቀውን ብር 100,000፣ ፓትርያርኩ በየወሩ ችግረኞችን እረዳለኹ በሚል ሰበብ የሚሰጣቸውን ብር 10,000፣ ከመስከረም 2 - 7 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለተካሄደውና ቤተ ክርስቲያን ማረፊያ በመስጠት ከማስተናገድ በቀር የማቴሪያል ይኹን የገንዘብ ወጪ ላለወጣችበት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ብር 259,000፣ ጥያቄው በዚህ ሳያበቃ መጋቢት 10 ቀን 2004 ዓ.ም ኮሚሽኑ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዲከፍል የተጠየቀውን ብር 215,000፣ የኮሚሽኑን የማኔጅመንት አባላት (የሰው ኀይል)፣ የኮሚሽኑን ሹፌሮችና ተሽከርካሪዎች ጊዜ እና ንብረት ጨምሮ ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ በፓትርያርኩ በኩል ለኮሚሽኑ የቀረበው የገንዘብ ጥያቄ ከግማሽ ሚልዮን ብር በላይ ይደርሰዋል፡፡

ምንጮች አክለው እንደገለጹት “ኮሚሽነሩ ዶ/ር አግደው ረዴ እና ከቦርድ አባላቱም እንደ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ያሉት በግል ወዳጅነት የተሰበሰቡ ግለሰቦች ኮሚሽኑን ለዘመናት እየመጠመጡ ነው ተብሏል፡፡ የሥነ ልቡና ባለሞያ የኾኑት ኮሚሽነሩ ዶ/ር አግደው እርጅና የተጫጫናቸውና ስለ ልማትና በጎ አድራጎት ድርጅት ባሕርይ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው ሲሆን ኤጀንሲው ያወጣውን መምሪያና የኮሚሽኑን ሕገ ደንቦች አክብሮ ከመሥራት ይልቅ የፓትርያርኩን ፍላጎት ለማስፈጸም ቅድሚያ እንደሚሰጡ ተዘግቧል፡፡

ለጋሾች በኮሚሽነሩ የአመራር አቅም ማነስ ሳቢያ ምሬታቸውን እየገለጹ ከኮሚሽኑ በመሸሽ ላይ በመኾናቸው በአሁኑ ሰዓት ለሥራ ማስኬጃና ለደመወዝ የሚከፈል እየጠፋ ለፕሮጀክት ተብሎ ከሚላከው አነስተኛ ገንዘብ እየተወሰደ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም እየተጓተተ ይገኛል፡፡ ይህም ኾኖ ዶ/ር አግደው ሠራተኞችን ባለማዳመጥ፣ በመናቅና በመሳደብ ከእርሳቸው ጋራ ለመመካከርና ፍላጎቱ ያላቸውን ባለሞያዎች ተስፋ እያስቆረጡ፣ የሥራ ሞራላቸውን እያጠፉና ልባቸውን እያሸፈቱ እንደ ኾኑ በሠራተኛው አቤቱታ ቀርቦባቸዋል፡፡

ንት የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን ከመንፈሳዊ ተልእኮዋ ጎን ለጎን የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት የበኩሏን አስተዋፅኦ ለማበርከት ያቋቋመችው ኮሚሽን ከመዘጋቱ በፊት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ አጀንዳው ትላንት በተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በቋሚ ሲኖዶሱ ከተያዙት ሐሳቦች አንዱ መኾኑ በቀደመው ዘገባችን መግለጻችን ይታወሳል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

No comments: