Friday, May 25, 2012

ቅዱስ ሲኖዶስ ‹በቦታው› የተገኘበት ስብሰባ እና መግለጫ

ማጠቃለያ ሪፖርታዥ (READ IN PDF)

·   የመግለጫው የመጀመሪያ ረቂቅ ምልአተ ጉባኤው ያልመከረባቸውን ዐበይት ጉዳዮች ያካተተ እንደነበር ተጠቁሟል፤ የዋልድባ እና የነ አባ ፋኑኤል የሐሰት ስኬት በሥርዋጽ ገብቶበት ነበር
·     አባ ጳውሎስ ምልአተ ጉባኤው ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ውሳኔ ባስተላለፈበት ቃለ ጉባኤ ላይ አልፈርምም ብለዋል፤ ስለማኅበሩ በመግለጫው ላይ የሰፈረውን አንቀጽም አላነብምየሚል አተካራ ውስጥ ገብተው ነበር
·     ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ከኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስነት አንሥቶ ወደ ጉጂና ቦረና ሊበን ዞኖች ሀ/ስብከት ለማዛወር በፓትርያ የቀረበው ሐሳብ ውድቅ ተደርጎ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ደርበው እንዲመሩ ተወስኗል
·      አገር ዓቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መሥራች ጉባኤ ከግንቦት 26 - 27 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

  ሙሉ ዘገባው ደጀ ሰላም ብሎግ ነው:: 
READ THIS ARTICLE IN PDF
 የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ 2004 . መደበኛ ስብሰባ ከትናንት በስቲያ፣ ግንቦት 15 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ባለዐሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡ ሚያዝያ 30 ቀን በመክፈቻ ጸሎት ተጀምሮ ለ16 ቀናት የዘለቀው ምልአተ ጉባኤው በመጨረሻው ቀን በአንድ በኩል የቅዱስ ሲኖዶሱ ወሳኝ የበላይነት የተመሰከረበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የቅዱስ ሲኖዶሱን ማእከላዊ አሠራርና ውሳኔ በልብ ይኹን በተግባር ለመቀበል ገና እየተቸገሩ መኾኑ የተጋለጠበት ኾኖ መዋሉ ተዘግቧል፡፡
የስብሰባው ምንጮች እንደሚያስረዱት በዕለቱ ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመጥራት ታቅዶ የነበረው ከረፋዱ 4፡00 ላይ የነበረ ቢኾንም በኋላ ወደ 10፡00 ይህም ቆይቶ ወደ 11፡30 እንዲሸጋሸግ ተደርጓል ስብሰባው ሲካሄድበት ወደከረመው የመንበረ ፓትርያርኩ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ቀድመው የደረሱ ጋዜጠኞችም ቢያንስ ከአንድ ሰዓት በላይ ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡ በመጨረሻ በቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ግብዣ ወደ አዳራሹ የዘለቁት ጋዜጠኞች የጠበቃቸው ትዕይንት ከጠዋት አንሥቶ በቤቱ የቆየውን ውጥረት የሚያሳብቅ ነበር፡፡
ጋዜጠኞቹ ወደ አዳራሹ ግር ብለው ገብተው የሥራ መሣሪያዎቻቸውን ቦታ ቦታ አስያዙ የመግለጫው አንድ ገጽ ወረቀት በእያንዳንዳቸው የምልአተ ጉባኤው አባላት ፊት ተዘርግቷል፡፡ ፓትርያርኩን ጨምሮ ሁሉም አባቶች የእጅ መስቀላቸውን በቀኝ እጃቸው እንደ ጨበጡ በጠረጴዛው ላይ አኑረው በተጠንቀቅ ተቀምጠዋል፡፡ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የፕሬስ ጉዳዮች ሓላፊ አቶ ስታሊን ገብረ ሥላሴ ከጋዜጣዊ መግለጫው ቀደም ብለው የወጡ ብፁዓን አባቶችን ስምና አህጉረ ስብከት የሚገልጹ ወረቀቶችን ከጉባኤው ጠረጴዛ ላይ አነሣሱ፡፡ ከዚህ በኋላ በአዳራሹ የሰፈነው ድባብ ጫታ (deafening silence) ሊባል የሚችል ነበር፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከአሁን አሁን መግለጫውን በንባብ ማሰማት ይጀምራሉ ተብሎ ሲጠበቅ እንዲያው ወረቀቱን አተኩረው እየተመለከቱ ጫ÷ እርጭ÷ ድምቡጭ አሉ፤ ገረገሩ፡፡
መቼም ግድ ነውና ከቆይታ በኋላ እንደምንም ማንበብ ጀመሩ፤ አሁን ሁሉም አባቶች በየአንፃራቸው የተቀመጠውን ወረቀት ይዘው የርእሰ መንበሩን ንባብ በጥታ÷ በርጋታ መከታተል ጀመሩ፤ በተለይ የብፁዕ ዋና ጸሐፊው ደግሞ ለየት ይላል፡፡ “ፓትርያርኩ መግለጫውን ለማንበብ ባይፈቅዱ ወይም አንዱንም አንቀጽ ከመነገር ቢያስቀሩ በቀጥታ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ጣልቃ ገብተው ማንበብ እንዲጀምሩ አቋም ተወስዶ ነበር” ይላሉ ከመግለጫው አስቀድሞ በአቡነ ጳውሎስና በብዙኀኑ አባላት መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ውዝግብ የሚያስረዱ የስብሰባው ምንጮች፡፡
በዕለቱ ጠዋት በነበረው የምልአተ ጉባኤው ውሎ በቀረቡ ጉዳዮች ሁሉ አቡነ ጳውሎስ የቅዱስ ሲኖዶሱን የበላይ አመራርነት እየተፈታተኑም ቢኾን ለመቀበል የተገደዱበት፣ በተወሰኑ ጉዳዮች ደግሞ አሻፈረኝ እንዳሉ የቀሩበት ነበር፡፡ ለአብነት ያህል በየስብሰባው መሀል እንደሚደረገው በአጀንዳ ተ.ቁ (15) በተመለከተው “ስለ ሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ እና ማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ” ከአንድ ቀን በፊት የተደረሰበትን ውሳኔ በሚገልጸው ቃለ ጉባኤ ላይ እንዲፈርሙበት ሲጠየቁ “አልፈርምም” ብለዋል፡፡ በዚህ የተነሣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በኹኔታው እስኪሰላቹ ድረስ ምልልስ የተደረገ ቢኾንም ፓትርያርኩ በእንቢታቸው በመጽናታቸው “ምልአተ ጉባኤው እስከ ወሰነ ድረስ እርስዎ ባለመፈረምዎ የሚመጣ ለውጥ የለም” በሚል ወደ ሌላ ጉዳይ ታልፏል፡፡
በሌላ በኩል አቡነ ጳውሎስ ዝውውር በሚል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከኮሚሽኑ ተነሥተው ወደ ጉጂና ቦረና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት እንዲዛወሩ፣ ለዚህም የሚፈልጉትን መኪና ይዘው እንዲሄዱ ይጠይቃሉ፡፡ ጥያቄውን ፓትርያርኩ ቀደም ሲል ከ‹ታማኞቻቸው› ጋራ መክረው በኋላ ለብፁዕ ዋና ጸሐፊውና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ያስታወቁትና ተቀባይነት ያጣ እንደ ነበር ነው የሚነገረው፡፡ በመጀመሪያ ወደ ጋምቤላ በኋላ ደግሞ ወደ ጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት የተቀየረውንና ከመደበኛ ስብሰባው ሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ ሲወራ የቆየውን የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ይነሡልኝ - ይዛወሩልኝ ጥያቄ ግን የምልአተ ጉባኤው አባላት ወዲያው ነበር የተቃወሙት፡፡
በርግጥ የጉጂ ቦረና እና ሊበን ዞኖች ሀ/ስብከት ከመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ ያለ ሥራ አስኪያጅ፣ ከጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ ያለ ሊቀ ጳጳስ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ምእመኑ የተቀበላቸው እና ከየዞኖቹ መንግሥታዊ አካላት ጋራ ተግባብተው በመሥራት የሚታወቁት ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ጥበባት ሲያምር ተክለ ማርያም መዋቅሩን ባልጠበቀ ውሳኔ ከብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ዮሴፍ ስምምነት ውጭ እንዲነሡ በመደረጋቸው፣ ከቀድሞው ሊቀ ጳጳስ ጋራ በተያያዘ ከሻኪሶ ቅድስት ማርያም ተወስዶ አለመመለሱ ከተነገረለት ብር 40,000 እና ለሀገረ ስብከቱ የካህናት ማሠልጠኛ ማሠርያ ከሀገረ ማርያም ወረዳ ምእመናን ተስብስቦ ርክክብ ሳይደረግበት ቀልጦ ከቀረው ብር 32,000 ጋራ በተገናኘ ሀገረ ስብከቱ ሰላሙ እንደታወከም የተዘገበ ነው፡፡
በዚህም በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በተዛወሩት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ምትክ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ከባሌ ሀገረ ስብከት ጋራ ደርበው እንዲመሩት ተወስኖ ነበር፡፡ ይኹንና መንበረ ጵጵስናው ባሌ በመኾኑ ከቦረና ወደ ባሌ ለመሄድ ቀናትን የሚፈጅ፣ አገልጋዩንና አብያተ ክርስቲያኒቱን ለወጪ የሚዳርግ፣ በሚያነሣው አስተዳደራዊ ጥያቄ ሳቢያ እስርና እንግልትን ጨምሮ በብዙ ችግሮች ተከቦ አባታዊ ቡራኬና ከፍተኛ ክትትል ለሚሻው የጠረፍ አገር ምእመንም አስቸጋሪ በመኾኑ ራሱን ችሎ ሊቀ ጳጳስ እንዲመደብለት÷ ይህም ካልኾነ ከመልክአ ምድራዊ አመቺነትና ከአስተዳደር አኳያ ከሲዳማ (ሐዋሳ) ሀገረ ስብከት ጋራ ተደርቦ በክፍሉ ሊቀ ጳጳስ እየተመራ እንዲቆይ ከሊበን፣ አዶላ፣ አዶ ሻኪሶ፣ ሀገረ ማርያም እና ያቤሎ ወረዳዎች የተውጣጡ የምእመኑ ተወካዮች ከሰኔ ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡
ከዚህ አኳያ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከኮሚሽኑ ተነሥተው ወደ ሀገረ ስብከቱ ተዛውረው እንዲሄዱ መጠየቃቸው በራሱ ችግር የሌለበት ቢኾንም መነሻው ግን ይህ አልነበረም፤ የይነሡልኝ - ይዛወሩልኝ ውስጠ ዘ ብቻ ከአዲስ አበባ ይራቁልኝ ዐይነት ነበር ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች፡፡ የዝውውሩን ጥያቄ የተቃወሙት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በበኩላቸው ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅነት ጋራ የቤቶች እና ሕንጻዎች አስተዳደር ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢነቱ ስለተደራረበባቸው ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የኮሚሽኑን ሊቀ ጵጵስና እንደያዙ እንዲያግዟቸው ጠይቀው ነበር፡፡
ከቤቱ የገጠማቸውን ተቃውሞ አጥብቀው የተከላከሉት አቡነ ጳውሎስ÷ በመጨረሻ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል አሁን ከያዙት የሲዳማ ሀገረ ስብከት ጋራ የጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖችን ሀገረ ስብከት ደርበው እንዲመሩ ምልአተ ጉባኤው የወሰነውን ለመቀበል ተገደዋል፡፡ በዚህም የፓትርያርኩ ጣልቃ ገብነት እስከሌለ ድረስ ከምእመኑ የተወከሉ የሀገር ሽማግሌዎች የጠየቁትን ያህል ባይሆንም እፎይታ እንደሚያገኙበት ተስፋ ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው÷ ቤቱ ብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከቱ ካለው አንጻራዊ ቅርበት አኳያ ደርበው እንዲመሩ ሲጠይቅ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን÷ “ቦረና ብዙ ችግር አለ፤ እርሳቸው ማኅበረ ቅዱሳን ናቸው” በሚል መክሰሳቸው ነው፡፡ ይገርማል፤ መፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች ማኅበረ ቅዱሳንን በችግር ፈጣሪነት በመክሰስ አንድ ዐይነት ሥዕል ለመፍጠር ከሚነዙት አሉባልታ ጋራ አንድና ያው የኾነው ንግግራቸው በተለይ በዚህ መደበኛ ስብሰባ የተደጋገመባቸውና የበቃቸው የሚመስሉት ብፁዕ አቡነ ገብርኤልም “አዎ! ማኅበረ ቅዱሳን ነኝ፤ አላፍርበትም” ሲሉ ቀጥተኛ ምላሽ እንደሰጧቸው ተሰምቷል፡፡
የኾነው ኾኖ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በነበሩበት የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ይቀጥላሉ፡፡ ይልቁንስ በዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው፣ መዋቅርን (ቃለ ዐዋዲን) አክብረው ለቤተ ክርስቲያን አሐቲነት ባለመሥራታቸው ብርቱ አቤቱታ የተነሣባቸው የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ነገር በምልአተ ጉባኤው ቀደምት ውሎዎች የተነካካ ቢኾንም አንዳች ውሳኔ ሳያርፍበት በቋሚ ሲኖዶሱ እና በመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል እንዲታይ ነው በይደር የተተወው፡፡ አቡነ ፋኑኤል የሀገረ ስብከቱን ጸሐፊ ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝን ክህነት አላግባብ በመያዝ የፈጸሙት ግዙፍ ስሕተትም በዚሁ መንገድ ‹እንደሚፈታ› (እልባት እንደሚያገኝ) ተስፋ ተደርጓል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የማኅበረ ቅዱሳንን መተዳደርያ ደንብ የማኅበሩ አገልግሎት ከደረሰበት ደረጃና ሊያሠራው በሚችልበት አግባብ ተጠንቶ እንዲሻሻል፣ ይኸው ርምጃም ከቃለ ዐዋዲው ማሻሻያ ጋራ ተጣጥሞ ለጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ ወስኗል፤ እስከዚያው ድረስ የማኅበሩ ተጠሪነት ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ኾኖ ከብፁዕነታቸው አመራር እየተቀበለ እንዲሠራ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይህ የመዋቅራዊ ተጠሪነት ለውጥ ከማኅበሩ አገልገሎት ማደግና መስፋፋት ጋራ ተያይዞ በአንዳንድ የማኅበሩ አመራር አባላት ሳይቀር ሲብላላ የነበረ ቢኾንም የቅርብ መነሻ የኾነው ግን ከመምሪያው ሓላፊዎች ጋራ በተለይም ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ተፈጥሮ የቆየው ውዝግብ ሊቋጭ ባለመቻሉ፤ ከውዝግቡና ሰንበት ት/ቤቶች ከደረሱበት ደረጃ ጋራ በተያያዘ የአመራር ብቃታቸው አጠራጣሪ ኾኖ የተገኙት የመምሪያው ምክትል ዋና ሓላፊና ጸሐፊ እንዲነሡ የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ቢጠይቁም ፓትርያርኩ ፈቃደኛ ኾነው ባለመገኘታቸው መኾኑ ተመልክቷል፡፡
ይህን ተከትሎ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የክስም የጥያቄም መንፈስ ባለው የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ትችታቸው ማኅበሩ ከማደራጃ መምሪያው ወጥቶ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተጠሪ እንዲኾን ያቀረቡትን ሐሳብ በመያዝ ምልአተ ጉባኤው በሙሉ ልብ የተቀበለውና ያስተላለፈው ውሳኔ በመምሪያው ሓላፊዎችና በማኅበሩ መካከል ተፈጥሮ የቆየው ውዝግብ ማሳረጊያ መስሎ ታይቷል፡፡ ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ምልአተ ጉባኤው ከአንድ ቀን በፊት ስለ ውዝግቡ ቀርበው እንዲያስረዱ የጠራቸውና በሕገ ወጥ መንገድ ዋና ሓላፊ የኾኑት መ/ር ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተ፣ የቀድሞው ዋና ሓላፊ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራውና የማኅበረ ቅዱሳን አመራሮች የመቅረባቸውን አስፈላጊነት አስቀርቶታል ተብሏል፡፡
ለራሱ ያህል የሚበቃ የአቋቋም ሞያ ያለው መ/ር ዕንቍ ባሕርይ በመምሪያው ዋና ሓላፊነት ይቆያል፡፡ መቼም መ/ር ዕንቍ ባሕርይ መምሪያው ለ20 ዓመት የቆየበት (የደከመበት?) ኾኖ ሳለ፣ መምሪያውም ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር ጋራ በመኾን ከ200 ወጣቶች በላይ ለሚገኙበት ታላቅ አገር ዓቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መሥራች ጉባኤ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት [ከግንቦት 26 - 27 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደው ይህ አገር ዓቀፍ መድረክ በይፋ ከሚታወቁት አጀንዳዎቹ ውጭ ለግል ጥላቻዎች ማስተጋቢያ እንዳይኾን ስጋቱ አለ] እንደ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ካሉ ዦቢራዎች ጋራ ባስፈጸመው የሽፍትነት መታዘዝ ያገኘው ሥልጣን ነውና እንደ ባህሉ ‹ሹመት ያዳብር› አንለውም፡፡
ለዚህ ዘገባ የቅዱስ ሲኖዶሱ የመጨረሻ ጉዳይ የሚኾነው በመግለጫው ዝግጅት ሂደት የታየው ‹ድራማ› ነው፡፡ የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት ጠዋት ላይ በውይይት መሀል ተዘጋጅቶ የቀረበው የጋዜጣዊ መግለጫው ይዘት በአንድ በኩል÷ በ16ቱ ቀናት ውስጥ ምልአተ ጉባኤው ያልመከረባቸውንና ውሳኔ ያላሳለፈባቸውን አንገብጋቢ አጀንዳዎች አቋም እንደተያዘባቸው አስመስሎ ያቀረበ፤ በሌላ በኩል ደግሞ÷ በምልአተ ጉባኤው ተመክሮባቸው ውሳኔ የተላለፈባቸውን አጀንዳዎች የውሳኔ ይዘት አሳስቶ የሚያቀርብ ነበር፡፡
ለአስረጅ ያህል፡- በወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ሳቢያ በዋልድባ ገዳም ህልውናና ክብር ላይ የተነሣውን ስጋት ምልአተ ጉባኤው በአጀንዳ ይዞ መነጋገር ሲገባው አልተነጋገረበትም፡፡ ይኹንና ጠዋት ተረቅቆ በቀረበው መግለጫ ላይ ፕሮጀክቱን የሚቃወሙት የፖቲካ ዓላማ ያላቸው ኀይሎች እንደኾኑና ቤተ ክርስቲያን ግን ልማቱን እንደምትደግፍ የሚናገር አንቀጽ እንደነበረው ተገልጧል፡፡ “የፖቲካ ዓላማ ያላቸው” የሚለው ክስ ይቆየንና መቼም ጥሩና ትክክለኛ ነገርን የሚጠላ ቢኖር ዲያብሎስ ነውና ቤተ ክርስቲያን ጥሩና ትክክለኛ ልማትን አትቃወምም፤ አይገባትምም፡፡ መንግሥትም አዘውትሮ እንደሚናገረው ትክክለኛ ልማት ፍትሐዊና ተደራሽ ነው፡፡ አዎ፣ ይህ የታመነ ነው እንላለን፤ ነገር ግን በተለይ ባለንበት ዘመን የልማት አስተሳሰብ፣ ዕቅድና ትግበራ ትክክለኛነት ተደራሽነቱና ፍትሐዊነቱ ብቻ አይደለም፤ አግባብነቱስ የሚል ጥያቄም በኾነ ደረጃም መነሣት ይኖርበታል፡፡
በአጀንዳ ተ.ቁ (5) ስለ ማኅበራት በተመለከተው ጉዳይ ምልአተ ጉባኤው የወሰነው÷ የቀረበው የመተዳደርያ ደንብ ዝግጅት ሰነድ ጥናት ወይም ትችት እንጂ የሕግ አቀራረብ እንደሌለውና በቀረበበት መልኩ ሊጸድቅ እንደማይችል፤ በውስጠ ዘ መልካም አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ማኅበራትን የማድቀቅና የማፈራረስ ተልእኮ እንዳለው፤ ይህም በመኾኑ ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ዐዋቂዎች በእውነትም ፈር ሊይዝ የሚገባውን የማኅበራቱን ብዛት የተገነዘበና ሊያሠራቸው የሚችል ሕግ አርቅቀው እንዲያቀርቡ ነበር፡፡ ይኹንና በጠዋቱ የመግለጫ ረቂቅ የቀረበው ግን ክፉኛ በተተቸው የዜና ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ እንደተገለጸው፣ ጥናት ተብዬውም እንደሚለው ቅዱስ ሲኖዶሱ “ማኅበራት አያስፈልጉም” ብሎ እንደ ወሰነ አስመስሎ ያቀረበ ነበር፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ አቡነ ፋኑኤል የስቴት (ወረዳ) ቤተ ክህነቶችን በዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ማቋቋማቸውን በውል አንሥቶ በመነጋገር በአንድነት ያሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ አልነበረም፡፡ በመኾኑም ይኸው ከምልአተ ጉባኤው አጀንዳዎችና ውሳኔዎች ውጭ አቋሞችን ይዞ የመጣው መግለጫ በቀላሉ ነበር ውድቅ የተደረገው ፡፡ ዋልድባን አስመልክቶ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ዓመታዊ ሪፖርት ተካትቶ የቀረበላቸው ነገር እንደሌለና እንዳልተነጋገሩበት ያስታወሱት የምልአተ ጉባኤው አባላት ባልተነጋገሩበት ጉዳይ መግለጫ ሊያወጡ እንደማይችሉ ነበር ያስቀመጡት፡፡ በማኅበራት ጉዳይ “ማኅበራት አያስፈልጉም” የሚል ውሳኔ እንዳልተላለፈና ሰነዱ ዳግመኛ ተጠንቶ እንዲቀርብ ማዘዛቸውን ተናግረዋል፡፡ ለድጋፍ ሸመታ የተሰነቀረው የአቡነ ፋኑኤል ‹የወሬ ፍሬ› “ኧረ እንዲያውስ ምን ተሠርቶ? ደብረ በጥብጥ ከመኾን በቀር” በሚል ተዘብቶበታል፡፡
በቀዳሚው ዜና ዘገባችን ላይ እንደገለጽነውና በርካታ ደጀ ሰላማውያንም እንዳመለከቱት ጋዜጣዊ መግለጫው የተሰጠበት ቀን ግንቦት 15 ኾኖ ሳለ በጽሑፍ በቀረበው መግለጫ መጨረሻ ላይ ግንቦት 10 የመባሉ ስሕተት መንሥኤ ይኸው ከምልአተ ጉባኤ አጀንዳዎችና ውሳኔዎች ውጭ ቀደም ብሎ ተዘጋጅቶ የቆየ ሐሰተኛ መግለጫ በፈጠረው ማምታት የተፈጠረ ሊኾን ይችላል፡፡
ስለኾነም በቤቱ ለውሳኔው የሚታመንለት ወዳጅ ያጣው ቅዱስ ሲኖዶሱ ደኀራዊውና ይፋዊውን መግለጫ አርቅቀው እንዲያቀርቡ ቀደም ሲል በመናፍቅነት ያወገዛቸውን ድርጅቶችና ግለሰቦች ውሳኔ በጽሑፍ እንዲያዘጋጁ ሠይሟቸው የነበሩትን አራት አባቶች ዳግመኛ ሠይሟል፡፡ እነርሱም “ከ20 ዓመት በኋላ ቅዱስ ሲኖዶሱን በቦታው ለመገኘት ያበቃ ነው” የተባለለትን ጋዜጣዊ መግለጫ አርቅቆ አቅርቧል፤ ቅዱስ ሲኖዶሱም ክራሞቱን የሚመስል ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲያነቡ ለፓትርያርኩ ይሰጣቸዋል፤ ቅዱስነታቸውም የመግለጫዋን አንዲት አንቀጽ ካልገደፍኹ ‹በመቃብሬ ላይ› ይላሉ፡፡
በየጉዳዩ ልምምጥ የበቃው ምልአተ ጉባኤውም በመነጋገርያ አጀንዳ ማጽደቅ ምልልስ ወቅት እንዳደረገው የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በውጭ በትንሹ ከአንድ ሰዓት በላይ የጠበቁት ጋዜጠኞችን እንዲያስገቡና ራሳቸው ብፁዕነታቸው እንዲያነቡ ይስማማሉ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ቍርጥ ውሳኔ ባደረገ ጊዜ ሁሉ ከአቋማቸው ሸተት የሚሉት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስም “እገድፋታለኹ እንጂ አላነባትም” ያሏትን ‹አንቀጸ ማኅበረ ቅዱሳን› ቀጸሏት፡፡ ንባቡ ግድፈተ አንቀጽ ቢኖርበት የመጣፍ መምሩ ብፁዕ አባ ሕዝቅኤል ከታጎለበት ለማቃናት ተዘጋጅተው ይጠባበቁ ነበር፡፡
ቅዱስነታቸውን እዚህ ውሳኔ ላይ ለማድረስ በተደረገው የተራዘመ ምልልስ የተዳከሙ፣ የተቆጡም አንዳንድ ብፁዓን አባቶች ከጋዜጣዊ መግለጫው በፊት ወጥተው ሲሄዱ ታይተዋል፤ ጋዜጣዊ መግለጫውም እንዳለቀ ለመቆየት የታገሡት በመጠን ነበሩ፡፡ ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ንባባቸውን እንደ ጨረሱ የፕሬስ ጉዳዮች ሓላፊያቸው አቶ ስታሊን ገብረ ሥላሴ ወደ መነጋገርያው ቀርበው መርሐ ግብሩ ማብቃቱን በመናገር ጋዜጠኞችን አሰናበተዋል፡፡
ምልአተ ጉባኤው በመጨረሻ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በሁለት ዙሮች ለቀጣይ ስድስት ወራት የቋሚ ሲኖዶስ አባላት የሚኾኑ አራት አራት ብፁዓን አባቶችን መርጧል፡፡ በዚህም መሠረት እስከ መጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ አቡነ ገሪማ፣ አቡነ ሉቃስ፣ አቡነ ሰላማ እና አቡነ ኤርሚያስ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት ኾነው የምልአተ ጉባኤውን ውሳኔዎች እንዲያስፈጽሙና ሌሎችም የቅዱስ ሲኖዶሱን ሥራዎች እንዲያከናውኑ መርጧቸዋል፡፡
የዘንድሮው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በታሪክ የሚታወሱ ክዋኔዎች የታዩበትና ደማቅ ውሳኔዎችም የተላለፉበት መኾኑ አያጠያይቅም፡፡ ከውሳኔዎቹ ውስጥ የሚበዙት ደጀ ሰላማውያን እግዚአብሔርን ያመሰገኑበት፣ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ያላቸውን አክብሮትና ድጋፍ የገለጹበት ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክቶ የተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡ መፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች ከዛሬ ነገ ይፈርሳል እያሉ ሲያሟርቱበት እና እንደ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ያሉት ምንደኞች በየመሸታ ቤቱ ሳይቀር እየተምነሸነሹ ጮቤ የረገጡበት ሟርት ግን አልሠራም፡፡ በምትኩ በፈረንጆቹ አባባል በመጨረሻ “በጠላቶቹ መቃብር ላይ የሣቀው” ማኅበሩ ነው፡፡
በብዙዎች ግንዛቤ የመዋቅራዊ ተጠሪነት ለውጥ ውሳኔው ማኅበሩ እንደ ተቋም ከነበረበት ቦታ አኳያ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ አካላት አንዱ የሚያደርገውና መዋቅራዊ ዕድገትን የሚያቀዳጀው ነው፤ መዋቅራዊ ዕድገቱ ቀና መነሻዎች ካሉት ከፍተኛ ሓላፊነትንም ጭምር ይዞ የሚመጣና ማኅበሩም ለዚያ የሚመጥን አቅም እንዲገነባ የሚያስገድደው ነውና፡፡ ውሳኔው ማኅበሩን ለዚህ ዐይነቱ በረከት የማብቃት መግፍኤ ያለው መኾኑን በሚጠራጠሩ ወገኖች ዘንድ ደግሞ የመዋቅራዊ ተጠሪነት ለውጥ ውሳኔው የማኅበሩን መሠረታዊ ዓላማዎች በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት አገልግሎቱንና ቀጣይ ግንኙነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፤ በአባላቱ መካከል የዘወትር አጀንዳ የኾነው በድርጅታዊ ቁመናው ተነጥሎ የመቅረት ስጋትን ያባብሳል፡፡ የመዋቅራዊ ተጠሪነት ለውጥ ውሳኔው ማኅበሩን ከእነ ዕንቍ ባሕርይ የሁልጊዜ ‹አበባዬ› አተካራ ለመገላገል ብቻ የተወሰደ አድርገው ያዩትም አልጠፉም፡፡
ብቻ አንድ ነገር ግልጽ ነው - የውሳኔውን የትመጣና ምንነት በውል ለሚረዱት የማኅበሩ ስትራቴጅስቶች ውሳኔው አሁን በቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን ደረጃ ግዘፍ ነስቶ ከመውጣቱ በፊት÷ በማኅበሩ የተከታታይ ስትራቴጅያዊ ዕቅድ ዝግጅቶች ሂደት ከማኅበሩ አገልግሎት ማደግና ከአገልግሎት አድማሱ መስፋፋት የተነሣ በተልእኮ መፈጸሚያ ሥልጣን ወይም ግዴታዎች ትንተና (Mandate analysis) ወቅት በተደጋጋሚ እንደሚነሣ ለሚወራው ክርክር አንድ ዐይነት ምላሽ ሊኾን እንደሚችል፡፡ የማኅበሩ ተምኔት በብርቱ ለሚያስጨንቃቸው ትጉህና ብዙኀን አባላቱ ግን ውሳኔው ገና የሐሳቦች ግብግብ መካሄድ የጀመረበትን የክርክር ምዕራፍ ያበሠረ ኾኗል፡፡
የሚመለከተው የማኅበሩ አመራር በቀጣይ አራትና አምስት የመተዳደርያ ደንቡ ማሻሻያ ወራት ከአባላቱም ይኹን ከአገልግሎት አጋሮቹ የሚመነጩ ወርቃማ ሐሳቦችን፣ ጥናታዊ መነሻዎችን የሚያቍትባቸውን ግልጽ መድረኮች በየደረጃው በቶሎ ቢያመቻች ፍጻሜው ለቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር መዋቅር መጠናከርና ለሐዋርያዊ አገልግሎቷ መስፋፋት የሚተርፍ፣ ለአገራችን ሰላምና ልማት የሚበጅ ድምር ውጤት ያለው ለውጥ እንደሚያመጣ ደጀ ሰላም በጽኑዕ ታምናለች፡፡
በሌላ በኩል ቅዱስ ሲኖዶስ በዘንድሮው የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው ለሃይማኖታዊ ጉዳይ ሰፊ ትኩረት መስጠቱ በቀጣይም በመሰል ወቅታዊ ጉዳዮች በዚህ ሊገፋ እንደሚችል አቅጣጫ የሰጠበት ነው፡፡ በዚህ መደበኛ ስብሰባ ፍጹም ውግዘት የተላለፈባቸው መናፍቃን ማኅበራትና ግለሰቦች ቀድሞውኑ በግልጽ የሚታወቁቱ በመኾናቸው የውሳኔው ትእምርታዊነት ያለው ዋጋ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይም የውሳኔው መሠረት የኾኑ ማስረጃዎችን በመሰብሰብና በማጠናቀር ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ለሠዉት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ለምእመኑ ግንዛቤ በመስጠት ለደከሙት ልዩ ልዩ ተቋማትና ግለሰቦች÷ በዚህም ሂደት ለክስና ለእስር የተዳረጉትን (የፍርድ ጊዜውን በጥብአት ለመጨረስ የወሰነውን ወንድማችን መ/ር ዘመድኩን በቀለን ያስታውሷል) ወገኖች ሁሉ ደጀ ሰላም በድጋሚ ልባዊ ምስጋና ታቀርባለች፡፡
የምልአተ ጉባኤው አባላት በአጀንዳው አቀራረጽ ሂደት ባሳዩት ርብርብ የቅዱስ ሲኖዶሱን አመራር የበላይነት ማስከበራቸው በእጅጉ ያስመሰግናቸዋል፡፡ በውይይቱ ሂደትና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የታየው ዐምባነንነትንና ሰርጎ ገብ አጀንዳዎችን ለመከላከል የተጀመረው ቁርጠኝነት፣ መግባባትና ጥንቃቄም ተጠናክሮ መቀጠል የሚኖርበት ነው፡፡ በመጨረሻም ምልአተ ጉባኤው “በዘመናችን የተከፈለች ቤተ ክርስቲያን ለትውልድ አናስረክም” በሚል ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጉባኤ አባላት በሰጠው ድጋፍ በቅዱስ ሲኖዶስና በሰሜን አሜሪካ በሚገኙት አባቶች መካከል የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስማማቱ በዘውዱ ላይ እንደ ምትጨመረዋ የመጨረሻ ዕንቍ ምልአተ ጉባኤው በድል የሚያንቆጠቍጠው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የበርካታ ደጀ ሰላማውያን ጥያቄ አንደኛ፡- አፈጻጸም፤ ሁለተኛ፡- አፈጻጸም፤ ሦስተኛ፡- አፈጻጸም የሚል ነው፡፡
ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ተግባራዊነት እንትጋ!!
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

1 comment:

Anonymous said...

I am always wondering about the pictures that are evrywhere in the country. the angel Mickael 9white) attacking the devil (black). why is that? look at the original Ethiopian Orthodox paintings in the most historical places. evn Jesus himself is not painted white. why forget the original church traditions? you like it or not people are asking? why angels white? why devils black (if not habesha)