Thursday, May 10, 2012

“ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የሚያካሒዱት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ እንቅስቃሴ ይቁም”

መግለጫውን የወሰድነው ከማዕከሉ ድረ ገጽ ነው::
(በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ጽ/ቤት) (To read in PDF)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን  የሰሜን አሜሪካ ማዕከል ተዋቅሮ  አገልግሎቱን ሲፈጽም እነሆ 14 ዓመታትን አስቆጥሯል:: በነዚህም ዓመታት በቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው መመሪያ መሠረት:-
1.  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት እንዲስፋፋ፣
2.  የቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት  እንዲከበር፣
3. ከአጥቢያ  ቤተ ክርስቲያን እስከ አኅጉረ ስብከት ያለው የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር እንዲደራጅና እንዲጠናከር በማድረግ፣
4.  የሕዝበ ክርስቲያኑ አንድነት እንዲጠበቅና ማኅበራዊ ሕይወት እንዲጠናከር፣
5.  ወጣቱ በሰንበት ት/ቤትና በሰባካ ጉባኤ ገብቶ በንቃትና በባለቤትነት እንዲሳተፍ፣
6. አባቶች በአስተዳደር ምክንያት ቢለያዩም ይህን ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙርያ በመመካከር በእርቅ አንድነታቸውን እንዲቀጥሉና  እንዲያጠናክሩ በማድረግ ለእርቅ የተቻለውን ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ጥረት አድርጓል::
ማዕከሉ የሀገረ ስብከቱን መዋቅር በማጠናከር በኩል በተለይ ከአንድ ሀገረ ስብከት ወደ ሦስት አህጉረ ስብከት መዋቅሩ ተዘርግቶ  ተመድበው ከመጡት ብፁዓን አባቶች ጋር ሁሉ በአባትነትና ልጅነት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ በፍጹም መግባባት ሲሠራ ቆይቷል::


በዚሁ ዓመት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ከተመደቡት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ጋርም በተመሳሳይ መልኩ ለቤተ ክርስቲያን መጠናከር በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት መንፈሣዊ አገልግሎት መፈጸም ይቻል ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ እውቅና ከሰጠቻቸው የሰሜን አሜሪካ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ እና ከማኅበረ በዓለ ወልድ ሥራ አስፈጻሚ ጋር በመሆን በደብዳቤ ጥያቄ አቅርቧል:: ይሁን እንጂ ብፁዕነታቸው ደብዳቤውን ተቀብለው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ፈቃደኛ ሆነው ለማገልገል ካለመፈለጋቸውም ባሻገር የፈፀሟቸውና እየፈፀሟቸው ያሉት ተግባራት በሕዝበ  ክርስቲያኑ ላይ ችግርና እንቅፋት ሲፈጥሩ ተመልክተናል::

ለአብነትም ያህል፦
1.  ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ ብሔራዊትና ዓለም አቀፋዊት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነቷና ሥርዓቷ ተጠብቆ  ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ ቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ ያሉት አካላት እንዲዋቀሩበት የተዘረጋውን አስተዳደራዊ መዋቅር እና እንዲመሩበት የወጣውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን /ቃለ አዋዲ/ ከማስከበርና ከማስጠበቅ ይልቅ እንዲጣስ እያደረጉት ነው::
2.  ቀደም ሲል በተለያየ ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመድበው በሰሜን አሜሪካ የነበሩ ሊቃነ ጳጳሳት ያዋቀሩትንና አብረዋቸው ይሠሩ የነበሩትን ካህናትና አጥቢያ አብያተ  ክርስቲያናት አልተቀበሉም:: እውቅናንም አልሰጡም:: ይልቁንም የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር ባለመደገፍና በእምነትና ሥርዓት መጣስ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ በጉልህ ከሚታወቁ ቡድኖች  ጋር ጥብቅ ግንኙነት ፈጥረዋል::
3. ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በሰሜን አሜሪካ ያሉ አኅጉረ ስብከትን የኃላፊነት ድርሻ በመጋፋት የተቋቋመውና  ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲፈርስ ውሳኔ የሰጠበትን የውጭ ግንኙነት ጽ/ቤት ህልውናው እንዲቀጥል ከማድረጋቸውም በላይ የዚህ ሕገ ወጥ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆኖ ለተመደበው ለዲ/ን ኃይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን በተጨማሪ የሥራ አስኪያጅ ሹመት ደርበው ሰጥተዋል:: ይህም አካሄድ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ አክብሮ ማስከበር የሚገባቸው አባት ተቃራኒውን እየፈጸሙ ለመሆኑ ማስረጃ መሆኑን እናምናለን::
4.  ዲ/ን ኃይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ቀደም ሲል የማኅበረ ቅዱሳን አባል በነበረበት ጊዜ ማኅበሩ ሃይማኖትና ቤተ ክርስቲያን እናድሳለን ከሚሉት ጋር የነበረው ግንኙነት ስለተደረሰበት ከማኅበሩ እንዲገለል መደረጉን ሁሉም የሚያውቀው በመሆኑና አሁንም ፀረ ቤተ ክርስቲያን የጥፋት ሥራውን የቀጠለ ግለሰብ ከመሆኑ አንጻር በሀገረ ስብከትም ሆነ በየትኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ላይ ለመቀመጥ የማይገባው መሆኑ እየታወቀ ከአንድ ሊቀ ጳጳስ በማይጠበቅ መልኩ ተባባሪው እና አጋሩ መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል። ከርሱ ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ የሚጽፏቸውን ደብዳቤዎች ቅዱሳን በሚሰደቡባቸው፣ ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት በሚንቋሸሽባቸው ድረ ገጾች እና የጡመራ መድረኮች (ብሎጎች) ላይ ማስነበባቸው የሁሉንም ክርስቲያን አንገት አስደፍቷል።
5. የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር በማጠናከር ሕግና ሥርዓትን አክብረው ተረካቢውን ትውልድ በማስተማር በሰንበት ት/ቤትና በሰበካ ጉባኤ ጉልህ ተሳትፎ  እያበረከቱ ያሉና ቀደም ሲልም በቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው የሚያገለግሉትን መዋቅራት ማለትም የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤንና ማኅበረ በዓለ ወልድን እውቅናቸውን በመካድ በሰሜን አሜሪካ የተጀመረውን የወጣቶች ሰፊ አገልግሎት ለማደናቀፍ ከመሞከራቸውም በላይ የተጀመረው የአንድነት መንፈስ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል::
6. ከነዚህ ማኅበራት ጋር እና ከሌሎች የተጠናከረች ቤተ ክርስቲያን እንድትኖረን ከሚመኙ አብአተ ክርስቲያናት፣ አበው ካህናት፣ ዲያቆናት እና ከመላው ሕዝበ ክርስቲያን ጋር በገቡትም ቅራኔ ምክንያት የቅዱስ ሲኖዶስን ኃላፊነት ተልዕኮ መወጣት ቀርቶ በተገኙበት ሥፍራ ሁሉ በአዋሳ ተፈጥሮ የነበረው ችግር እንዲዛመትና በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ጥላቻው ሥር እንዲሰድ በማድረግ ላይ ይገኛሉ::
7.  በብፁዓን አባቶች መካከል የተፈጠረውን መለያየት ለመፍታት ለእርቅና ለሽምግልና ከአዲስ አበባ የተላከው ቡድን በውጭ ካሉት አባቶች ጋራ ከተደረሰው ስምምነት ውጭ በእርሳቸው አማካኝነት መግለጫ እንዲሰጥ መደረጉ የእርቅና ሰላም ሂደቱ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል:: በዚህም በውጪ ያሉ አባቶችንና ለዕርቅና ሰላሙ የሚሠሩትን ሁሉ እጅግ ያሳዘነ፣ የሰላም መልዕክተኞቹንም በጥርጣሬ እንዲታዩ የሚያደርግ ሁኔታ ተከስቷል።

ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ የተከሰቱንና ሌሎችም ያልተዘረሩ ችግሮችን በመመልከት በመታወክ ላይ ያለችውን የሰሜን አሜሪካ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና የሕዝቡንም ሆነ የአባቶችን አንድነት ለመፍጠር ይቻል ዘንድ፦

1. ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በአስቸኳይ ተነሥተው ለችግሩ መፍትሔ ሊሰጡ የሚችሉ አባት እንዲመደቡ እንዲደረግ፤
2.  የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን በመጣስ በሰሜን አሜሪካ ባለችዋ ቤተ ክርስቲያን ውስብስብ ችግር እንዲፈጠር በማድረግ በተለይ “ቤተ ክርስቲያንን እናድሳለን” ከሚሉ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጋር ሆነው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚገታ መፍትሔ እንዲሰጥበት፤
3. እጅግ የተጎዳውንና የቆሰለውን የክርስቲያኖችን ልብ የሚፈውስ፣ የተዘረጋውን መዋቅራዊ አደረጃጀት የሚያጠናክር፣ የተፈጠረውን ልዩነት አስወግዶ አንድነትን የሚያጠናክር የሰላም አባት እንዲተካ፤
4.  ቤተ ክርስቲያን በውጭው ዓለም የሚጠበቅባትን ኃላፊነት አውቆና ተረድቶ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆና አስጠብቆ መምራት የሚችል ይልቁንም ሃይማኖታችንን ለውጭ ሀገር ዜጎች ማስተማርና ማስፋፋት የሚቻልበትን መንገድ የሚያመቻች የሥራ ሰው እንዲመደብ፤
5. በተለይ በውጭው ዓለም በስደት ተወልደው ያደጉትን ትውልደ ኢትዮጵያውያን  እምነታቸውን፣ ሥርዓታቸውን፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን አውቀው ተረካቢውን ትውልድ እንዲፈጥሩ ማድረግ ብቸኛውና አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን የሚገነዘብና አባታዊ መመሪያ የሚሰጥ አባት ይላክ ዘንድ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን::

ልዑል እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!

በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ጽ/ቤት
አሜሪካ

ግልባጭ:-
•    ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣
•    ለመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣
•    ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
•    ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣
•    ለውጭ ግንኙነት መምሪያ፣
•    ለሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣
•    ለማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል ጽ/ቤት፣
•    ለሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት፣
•    ለሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ፣
•    ለማኅበረ በዓለወልድ፣

No comments: