Friday, May 18, 2012

"የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ሰባተኛ ቀን ውሎ ሪፖርታዥ" የደጀ ሰላም ዘገባ·         አባ ጳውሎስ በእመቤታችን ንጽሕና ላይ እምነታቸውን እንዲገልጡ ቢጠየቁ አንደበታቸው ተሳሰረ፤ ለጥያቄው መነሻ የኾነው ፓትርያርኩ በአባ ሰረቀ ‹መጽሐፍ› ላይ ስለተጠቀሰው የዶክትሬት ጽሑፋቸው ዝምታን በመምረጣቸውና ኮሚቴውም የእርሳቸውን ምላሽ ወይም አቋም አለመመርመሩ ነው - “አባ ሰረቀ ጽሑፍዎን ጠቅሰው መጽሐፍ ከጻፉ በኋላ ለምን ዝም አሏቸው? ኮሚቴውስ ለምን አልጠየቀም? ይሉኝታ ነው ወይስ ተመሳስሎ ለመኖር ነው?” /ብፁዕ አቡነ አብርሃም - ነደ ‹ተሐድሶ›/
·         አባ ጳውሎስ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች ላይ ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ “አልቀበልም፤ ኮሚቴው በትክክልና በጥራት አልሠራም” በሚል ያመጡትን ተለዋጭ ሐሳብ ቅዱስ ሲኖዶሱ ውድቅ በማድረግ ሪፖርቱ ተባዝቶ እንዲደርሰው አዝዟል፤ ከዛሬ ጀምሮ በእያንዳንዱ የውሳኔ ሐሳብ ላይ በጥንቃቄ እየተወያየ እንደሚያጸድቀው ይጠበቃል

·         አባ ጳውሎስ የቅዱስ ያሬድን በዓል ለማክበር በሚል ሰበብ የቅዱስ ሲኖዶሱን ስብሰባ አቋርጠው ዛሬ ወደ አኵስም ለማምራት ያሰቡትን ጉዞ ምልአተ ጉባኤው ተቃውሟል - “በሐዋርያት ቃል፣ በሐዋርያት ቃል÷ ይህ የሃይማኖት ጉዳይ ነው፤ ይህ አጀንዳ ሳምንትም ቢፈጅብን እርስ በርሳችን ሳንፈታተሽ አንድ ሰው እንዳይሄድ!” /ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ እንዳስጠነቀቁት/
·         በማኅበራት መተዳደሪያ ደንብ ዝግጅት ላይ በ”ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ባለሞያዎች የተጠና ነው” የተባለው ሰነድ በምልአተ ጉባኤው አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፤ ጥናቱ በልዩ ኹኔታ ማኅበረ ቅዱሳንን እንደሚመለከት አባ ጳውሎስ ግልጽ ቢያደርጉም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ “ለማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ አርቅቀንና አጽድቀን ሰጥተናል፤ ይህ ጥናት አይመለከተውም፤ ለሌሎቹም ቢኾን ሰነዱን በጥንቃቄ መርምረን ፈትሸን ነው የምንወስነው” በማለት 15 ገጾች ያሉት ጥናት ተባዝቶ እንዲደርሳቸው አዝዘዋል፡፡
·         በመንፈሳውን ማኅበራት ምሥረታ ላይ የተደረገው ጥናት በዋናነት የማኅበራትን አፍራሽ ገጽታ በማጉላት “አሁን ባላቸው እንቅስቃሴ በኢትዮጵያም ይኹን በጥንታውያን አኀት አብያተ ክርስቲያን ታሪክ ያልተለመደ በመኾኑ ሊስተካከል ይገባዋል፤ ቤተ ክርስቲያን በቃለ ዐዋዲው የተዘረዘሩ መዋቅሮቿን በማጠናከር ምእመናን ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ ማድረግ ይገባል፤” ብሏል፡፡ ማኅበር የሚለው ስያሜ የማይለወጥ የቤተ ክርስቲያን መገለጫ በመኾኑ አሁን በማኅበራት መልክ ለተደራጁትና ለሚደራጁት አካላት “ኮሚቴ፣ ክበብ” የሚል ስያሜ ብቻ እንዲሰጣቸው ሐሳብ ያቀርባል፡፡
·         በሲዳሞ /ሐዋሳ/ ሀገረ ስብከት “ሊቀ ጳጳሱ ሁሉንም አካላት አቅፈው ለመምራት አልቻሉም፤ ለማኅበረ ቅዱሳን ያደላሉ” በሚል ጥቅመኞችና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች “ተጠሪነቱ ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የኾነ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንዲቋቋምላቸው በአባ ጳውሎስ የቀረበውን ሐሳብ ምልአተ ጉባኤው “የተሐድሶ መንፈስ እንዲህ አድርጎ ቤተ ክርስቲያኒቱን መገነጣጠል ነው፤” በሚል ውድቅ አድርጎታል፡፡ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስነታቸው ለሁሉም ማእከላዊ አባት ኾነው እንዲመሩ፣ ጥያቄ አቅራቢዎቹም ለሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዲገዙ እንጂ ለማንም ተብሎ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደማይሻሻል ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡
·         ቅዱስ ሲኖዶስ በሕገ ወጥ መንገድ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ኾኖ የተሾመው ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተ “መምሪያውን ለመምራት ብቃት የለውም” በሚል በአስቸኳይ ተነሥቶ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው እንዲመለሱ ትእዛዝ ሰጥቷል፤ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ የተነሡበት መንገድ “ሽፍትነትን በቤቱ ያነገሠ” በማለት ባላመኑበት ደብዳቤ ላይ እንዲፈርሙ መገደዳቸውን አጥብቆ ኮንኗል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ስለተጻፈው ደብዳቤም “ሁልጊዜ ይኼን ማኅበር ምክንያት እየፈለጉ በፖቲካና በአስተዳደር መክሰስ፣ ማሳደድ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? መቼስ ነው የሚቆመው? ማኅበሩን ማዳከም ቤተ ክርስቲያንን በድጅኖ የማፍረስ ያህል ነው፤ የመናፍቃን መቀለጃና መጫወቻ ለማድረግ ነው፤” በሚል ክፉኛ አብጠልጥሎታል፡፡
·         የማኅበረ ቅዱሳን ተወካዮች ዛሬ በቅዱስ ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ ፊት ቀርበው ከመምሪያው ዋና ሓላፊ በሕገ ወጥ መንገድ መነሣትና በእርሳቸው ምትክ በሽፍትነት ከተሾመው ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተ ጋራ በተያያዙና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የገጠማቸውን ችግር እንደሚያስረዱ ተነግሯል፡፡ ተወካዮቹ አባ ጳውሎስ ሠርቶ ከማሠራት ይልቅ በአንድ በኩል ማኅበሩን በተለያየ መንገድ እያጠቁና አገልግሎቱ በየምክንያቱ እንዲዳከም በመጣር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዋቅር በቤተ ክርስቲያኒቱ ጠላቶች እንዲወረር የሚያደርጉበት አካሄድ ከቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ህልውና አኳያ ስለሚያደርሰው ጉዳት አቋማቸውን ገልጠው ይናገራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
·         አባ ጳውሎስ በሌላቸው ሥልጣን በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ላይ የጣሉት የፊርማ እገዳ ተነሥቶ የኮሚሽኑ የቁጠባና ተንቀሳቃሽ ሒሳቦች በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት እንደ ቀድሞው እንዲንቀሳቀስ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ አባ ጳውሎስ የኮሚሽኑን ሊቀ ጳጳስ ለምን እንዳገዱ በቤቱ ሲጠየቁ “አልፈርምም፤ አልታዘዝም እያለ፤ በሲኖዶስ እየፈከረ” በሚል ከስሰዋል፡፡ ብፁዕነታቸውም “አዎ! ሕግ ስለተጣሰ፣ ጥያቄው አግባብ ስላልኾነ አልፈርምም ብዬአለኹ፤ በገንዘብ እጦት ከመቶ በላይ ሠራተኞችን በትነናል፤ ኮሚሽኑ የፕሮጀክት ብር ብቻ እንጂ ሌላ ገንዘብ የለውም፤ የፕሮጀክት ብር ደግሞ ለፕሮጀክት ብቻ ነው የሚውለው፤ የፋይናንስ መምሪያ ሓላፊውን ጠይቄ ይህንኑ አረጋግጦልኛል፤ ኮሚሽኑን ከጥፋት ለማዳን ነው ይህን ያደረግኹት፤ ይህ ጉባኤ ገንዘቡ ይውጣ ካለ አይደለም አቶ ወይዘሮም መጥታ ትፈርም! በሕጉ መሠረት ግን ከዋና ሥራ አስኪያጁ ጋራ ኾነን እኔና የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ነው የምንፈርመው፤” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አባ ጳውሎስ እገዳው ለጊዜው ያስተላለፉት እንደኾነ ቢናገሩም “ለጊዜውም ቢኾን ቅዱስ ሲኖዶስ የሾመውን ሊቀ ጳጳስ እርስዎ ሊያግዱ አይችሉም፤ አሠራሩ ባለበት ይቀጥል” በማለት የፊርማ ስረዛ ጥያቄ ላቀረቡባቸው ባንኮች ሁሉ የጻፉት ደብዳቤ በሌላ ደብዳቤ ተሸሮ አሠራሩ በነበረበት እንዲቀጥል ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
·         አባ ጳውሎስ ግፊት በአኵስም ሀገረ ስብከት ከሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ሰላማ ጋራ ስለተፈጠረው ችግር የአኵስም ጽዮን ማርያም ንቡረ እድ በቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ ቀርበው ያስረዳሉ፤ አባ ጳውሎስ “በላሊበላ ጉዳይ ላይ የተያዘው አጀንዳ ከማኅበራት ማቋቋሚያ ጥናት ጋራ ተያይዞ ይታይልኝ፤” በሚል “ማኅበረ ቅዱሳን ሕገ ወጥ ጉባኤ አካሂዷል” ብለው ለመክሰስ አሸምቀዋል፡፡ በስደት ላይ የሚገኙት አባቶች ተወካይ በዕርቀ ሰላም ንግግሩ ሂደት ላይ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ሪፖርት አቅርበዋል፤ ንግግሩን በሚያደናቅፉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተዋል፤ በሪፖርቱ ላይ የሚካሄደው ውይይት ዛሬ ይቀጥላል ተብሏል፡፡
(ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 10/2004 ዓ.ም፤ May 18/ 2012)፦ ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ዘጠኝ ቀን ሰባተኛ ቀን የቀትር በፊት ውሎው ስብሰባውን የጀመረው ቀደም ሲል በንባብ ባዳመጠው ባለ60 ገጽ የሃይማኖት ሕጸጽ አጣሪ ኮሚቴ ባቀረበለት ሪፖርት ላይ በመወያየት የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ነበር፡፡
ይኹንና ኮሚቴው በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች ላይ በየደረጃው ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የተናነቃቸው ርእሰ መንበሩ አባ ጳውሎስ ያንን በመገልበጥ ሌላ የውሳኔ ሐሳብ ይዘው በመቅረብ ያነባሉ፡፡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም አባ ጳውሎስ ያነበቡት ትናንት ካዳመጡት የሚለይባቸውን ነጥቦች በመጥቀስ ቀደም ሲል በቀረበው ወደ ውሳኔ መሄዱ የተሻለ መኾኑን ይናገራሉ፡፡ አባ ጳውሎስ ግን የኮሚቴውን አባላት ሌሎች ተናጋሪዎችን “እናንተ ባቀረባችኹት አላምንበትም፤ ኮሚቴው በትክክል እና በጥራት አልሠራም፤ ሪፖርቱ ችግር አለበት፤ አልቀበለውም” በማለት ፍርጥም ይላሉ፡፡
ይህን ጊዜ ነበር ብፁዕ አቡነ አብርሃም ተነሥተው “አዎ፣ ችግር አለ፤” አሉ “እውነትና ንጋት” በሚል ርእስ አባ ሰረቀ ያሳተሙትን መጽሐፍ መሰል ጥራዝ በማስታወስ ንግግራቸውን ሲጀምሩ፤ “አዎ ችግር አለ፤ ዝምድና ነው፣ ይሉኝታ ነው፣ ወይስ ተመሳስሎ ለመኖር ነው ኮሚቴው እርስዎን ያልጠየቀው? አባ ሰረቀ ከእርዎ ጽሑፍ በመጥቀስ እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት እንደሚሉ አውጥተዋል፤ እውነት ይህ ቃልዎ ነው? እንዲህ ብለዋል? መጽሐፉ ከወጣስ በኋላ ለምን በዝምታ አለፉት? ትክክል ነው ብዬአለኹ፤ ካላሉ ደግሞ አላልኹም ብለው ለምን አልተናገሩም? ኮሚቴውስ ለምን አልጠየቀም?” የሚል ጠንካራ ጥያቄ አንሥተዋል፡፡
የብፁዕ አቡነ አብርሃም ጥያቄ ሰበቡ የአባ ሰረቀ “እውነትና ንጋት” ይኹን እንጂ አባ ጳውሎስ በፕሪንስተን ቴዎሎጂ ኮሌጅ “Filsata: The Feast of the Assumption of the Virgin Mary and the Mariological Tradition of the Ethiopian Othodox Tewahedo Church” በሚል ርእስ እ.አ.አ በ1988 በነገረ ማርያም ላይ የሠሩት የነገረ መለኰት ዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናት ከቀድሞው ጀምሮ ውስጥ ለውስጥ ሲነሣ የቆየ ነው፡፡
በነገረ ማርያም ላይ የኢኩሜኒዝም አንድነት(Ecumenical Unity) ለማምጣት በሚል ዓላማ የተሠራው ይኸው ጥናት በአቀራረቡ ንጽጽራዊ ሲኾን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን (ከገጽ 45 - 306)፣ የሮም ካቶሊክን (ከገጽ 307 - 320)፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክስን (ከገጽ 333 - 348) እና የፕሮቴስታንት አብያተ እምነትን (ከገጽ 321 - 332) የነገረ ማርያም አስተምህሮ የራሱና በንጽጽር የቀረበበት ነው፡፡ ለዚህም በታሪክ የተደረገ የንግግር ጥረቶችን በማስታወስ በቀጣም በክርስትናው ዓለም አንድ የተዋሐደ የነገረ ክርስቶስ አስተምህሮ መደረስ እንደሚቻል ይመክራል፡፡
አባ ሰረቀ በመጽሐፍ መሰል የዶሴ ጥራዛቸው የጠቀሱት ከገጽ 336 - 338 ያለውን የጥናቱን ክፍል ነው፡፡ ይህ ክፍል ግን አባ ጳውሎስ በተለይም የምሥራቅ ኦርቶዶክስን (መለካውያን) የነገረ ማርያም አስተምህሮ ታሪክና ምንነት የዘረዘሩበት ነው፡፡ አባ ሰረቀ እንደነ ቀሲስ አስተርኣየ ጽጌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ነገረ ማርያም ከሌሎች ጋራ ለመቀየጥ ካልፈለጉ በቀር አባ ጳውሎስ የኢትዮጵያን የነገረ ማርያም አስተምህሮ ባቀረቡበት ክፍል ከአንድ በላይ አስረጅዎችን ለመጥቀስ በቻሉ ነበር፡፡
በዚህ ክፍል (በተለይ ከገጽ 45 - 141) ፓትርያርኩ ነገረ ማርያምን በቅዱስ ያሬድ፣ በአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ድርሳናት ውስጥ ደኅና አድርገው የተነተኑትን ያህል በአንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮች ግን “የአስተምህሮ አንድነት አመጣበታለኹ” ለሚለው አካዳሚያዊ ፕሮጀክታቸው ይመስላል ከኢትዮጵያ ምንጮች የማያገኙትን አስተምህሮ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይትበሃል ካልቃኑት ምንጮች ሲጠቅሱ እናገኛቸዋለን፡፡
ለአብነት ያህል በዚሁ ክፍል አባ ጳውሎስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስዋም በሥጋዋም ንጽሕት (በሁለት ወገን ድንግል) የኾነችና በክርስቶስ የማዳን ሥራ ያልተለየች ብትኾንም ከውርስ ኀጢአት ግን ነጻ እንዳልነበረች የጻፉት የቅብጦችን ምንጭ ጠቅሰው ነው፡፡ አባ ጳውሎስ በጥናታቸው ምንጩን ጠሰው እንዲህ ይላሉ፡-
For the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church the Virgin Mary is the example par excellence of obedience and faithfulness to God. She is two-fold virgin; i.e, virgin both in body and soul, who, though not “immaculate” or free from original sin, yet was all-holy, pure, chose to actively participate in the saving work of God, His Incarnation. (p.306) (Amba Alexander, “The Assumption in the Liturgy of the Church of Alexanderia;” Eastern Churches Quarterly, 9 (1951)
በአባ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና (በ1986 ዓ.ም) በቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝና ፈቃድ በተሰበሰቡ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና 11 ሊቃውንት “ወኢረኵሰት በኢምንትኒ እምዘፈጠራ፤ ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ርኵስ ነገር አልተገኘባትም፤ በነፍስም በሥጋም ሁልጊዜም ንጽሕት ናት፤” (ሃይ. አበ 53) በማለት በቅዱሳን አበው የተመዘገበውን መሠረት በማድረግ ያዘጋጁት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ሥርዐተ አምልኮና የውጭ ግንኙነት” መጽሐፍ ግን ስለ እመቤታችን ክብር፣ ንጽሕናና ቅድስና የሚለው የሚከተለውን ነው፡-
“ቤተ ክርስቲያናችን የምታምነውና የምታስተምረው፡- አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) ያላገኛት፣ መርገመ ሥጋ፣ መርገመ ነፍስ የሌለባት፣ ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች፣ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ ሐሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች፣ ከተለዩ የተለየች ንጽሕት ቅድስተ ቅዱሳን ናት፡፡”
አባ ጳውሎስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞተች ስለተባለ “የበደል ውርስ አለባት” ብለው ከሚያምኑ ጸሐፊዎች ጋራም ተባብረዋል፡፡ እነ ቀሲስ አስተርኣየ ጽጌም የሚሉት እንዲሁ ነው፡፡ ስለዚህም ከአበው ድርሳናት ምስክርነት ቢያጡ የጠቀሱት ከቅብጦቹ ምንጭ ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፡-
Like all daughters and sons of Adam, the holy Virgin Mary died as a result of Adam’s sin. “Mary sprung from Adam, died on consequence of original sin; Adam died in consequence of sin, and the flesh of the Lord, sprung from Mary, died to destroy sin.” (p.302) (Malaty, T.Y. St. Mary in the Orthodox Concept, 1978)
ይህን ሐሳብ በተመለከተ አባ ሰረቀን ጨምሮ እነ ቀሲስ አስተርኣየ ጽጌና ሌሎችም “ስሜን (ሥራዎቼን) በመጥቀስ ማታለያ አድርገውኛል” ያሉት ሊቁ አለቃ አያሌው ታምሩ ግለሰቦቹ እሳቸውን በእነርሱ የኑፋቄ ሐሳብ ውስጥ እንዳይጨምሯቸው፣ ለራሳቸው እንዲመለሱና እንዲታገሡ በመከሩበት “ዜና ሕይወት ዘቅድስተ ቅዱሳን እመ አምላክ” በሚል ርእስ ባዘጋጁት የመጨረሻ መጽሐፋቸው፡-
“እነ ቄስ አስተርኣየ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞተች ስለተባለ የበደል ውርስ እንዳለባት አድርገው ሊቈጥት ሞክረዋል፡፡ ክሕደቱ፣ በደሉ ካልቀረ ሰው የኾነ አምላክ ልጇም የመስቀልን ሞት ተቀብሏልና ከአይሁድ ጋራ ቆመው የጲላጦስን ምስክርነት ቢያስተባብሉ ይሻላል፡፡ ከአበዱ ወዲያ በመንገዱ መሄድ መስነፍ ነው ይባል የለ?
በማለት ተችተዋል፡፡
እንግዲህ ትናንት አባ ጳውሎስ በእመቤታችን ክብር፣ ንጽሕናና ቅድስና ላይ “እምነትዎን ይግለጡ፤ ይመኑ ወይም ያስተባብሉ” ሲባሉ ወዲያና ወዲህ በሚላጉ ንግግሮች አንደበታቸው መተሳሰሩ ነው የተዘገበው፡፡ ከዚህ በኋላ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት 60 ገጽ ያለው የኮሚቴው ሰነድ በቁጥራቸው ልክ ተባዝቶ እንዲደርሳቸውና እያንዳንዱን የውሳኔ ሐሳብ በጥንቃቄ እየተመለከቱ ለመወሰን ከመግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ግንቦት 11 ቀን 2004 ዓ.ም የሚከበረውን የማሕሌታይ ቅዱስ ያሬድ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ “ወደ አኵስም እሄዳለኹ” የሚለው የፓትርያርኩ ሐሳብ ያሰጋቸው ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በይደር የተያዘው አጀንዳ በውሳኔ ሳይታሰር እንዳይቀር የሚያስጠነቅቅ ማሳሰቢያ ተናግረዋል - “በሐዋርያት ቃል፣ በሐዋርያት ቃል÷ ይህ የሃይማኖት ጉዳይ ነው፤ ይህ አጀንዳ ሳምንትም ቢፈጅብን እርስ በርሳችን ሳንፈታተሽ አንድ ሰው እንዳይሄድ!”
ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ!!!
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

2 comments:

Mebratu Tegen said...

Amlakachin cherun neger yaseman. Abatochachin le ewnet blew bemegaz ena beseyf yseneteku endeneber metshaf yasredanal.Ezih degmo leala werea ensemalen. ahunim le abatochachin birtatun yesete amlak ahun lalut ye kurt ken lijochm tsinatun ystlin. Aba paulos ¨Aba"blen endnterachew kekhdet menged fetari ymelslin. CHER YASEMAN
WESBHAT LE EGZIABHEA WELE WELADITU DINGL, WELE MESKELU KIBUR

Mebratu Tegen said...

Abatochachin le haymanotachew silu bemegezna beseyf siseneteku endeneber kidus metsihaf ynegrenal. Bezih twlid yalutin abatochim be seyfna bemegaz kemesentek ye mayans fetena newuna yegetemachew lekedemut abatochachin yesetwun birtat ysetlin zend enleminew.