Friday, May 11, 2012

የቅ/ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ ሁለተኛ ቀን የቀትር በፊት ውሎ

ሙሉ ዘገባውን የወሰድነው ከደጀ ሰላም ብሎግ ነው::  READ THIS ARTICLE PDF
  •       አጀንዳ አዘጋጅ ኮሚቴው 20 ጉዳዮችን በረቂቅነት አቅርቧል
  • ከአቡነ ፋኑኤል ጋራ በተያያዘ በዋሽንግተን የተፈጠረው ችግር በአጀንዳዎቹ ዝርዝር ውስጥ ራሱን ችሎ አልተመለከተም 
  •     ፓትርያርኩ የዕርቀ ሰላም ንግግር አጀንዳን ተቃውመዋል፤ በተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት አጀንዳ አቋማቸው ጸንተዋል
  • “በእኛ ዘመን የተከፈለች ቤተ ክርስቲያን ለቀጣዩ ትውልድ አናስረክብም፤ ሹመቱ ዕርቀ ሰላሙን የሚያደናቅፍ በመኾኑ ወቅቱ አይደለም /ብዙኀኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት/
በትናንትናው ዕለት በቋሚ ሲኖዶስ የቀረቡለትን 15 የመነጋገርያ አጀንዳዎች የተመለከተውና በምልአተ ጉባኤው የተሠየመው ስምንት አባላት የሚገኙበት አጀንዳ አዘጋጅ ኮሚቴ 20 የመነጋገርያ ጉዳዮችን ዛሬ ጠዋት ለምልአተ ጉባኤው አቅርቧል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቲያስን በሊቀ መንበርነት፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስን በጸሐፊነት በመምረጥ ሥራውን የቀጠለው ኮሚቴው÷ ቀደም ሲል በቋሚ ሲኖዶስ ተቀርጾ በቀረበው አጀንዳ ላይ በስፋት በመወያየት ዘመኑን የዋጁና ወቅቱን የተመለከቱ የ20 አጀንዳዎችን ዝርዝር ለምልአተ ጉባኤው አቅርቧል፡፡


እኒህም በተቀመጡበት ቅደም ተከተል መሠረት፡- 1) የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የመክፈቻ ንግግር፤ 2) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ዓመታዊ ሪፖርት፤ 3) ስለ ቤቶችና ሕንጻዎች ጉዳይ፤ 4) በላሊበላ የሰባት ወይራ ሆቴል መመለስ እና ወደ ማእከል ስለሚመጣበት ጉዳይ፤ 5) ስለ ማኅበራት ጉዳይ፤ 6) ማእከልን ጠብቆ አለመሥራት እያስከተለ ስለ አለው ችግር፤ 7) ስለ ሰላም ጉዳይ፤ 8)በላሊበላ ስለተፈጠረው ችግር፤ 9) ስለ ቃለ ዐዋዲው መሻሻል፤ 10) ስለ ልማት ኮሚሽን፤ 11) ስለ ሕፃናት እና ቤተሰብ ጉዳይ፤ 12)በአኲስም ሀገረ ስብከቱና በርእሰ ገዳማት ወአድባራት መካከል ስለ አለው ችግር፤ 13) ስለ ሃይማኖት ሕጸጽ በኮሚቴ የሚቀርበውን ሪፖርት መስማትና መወሰን፤ 14) ስለ ሲዳማ ሀገረ ስብከት ጉዳይ፤ 15) ስለ ሰንበት ት/ቤት እና ማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ፤ 16) ስለ ስብከተ ወንጌል ጉዳይ፤ 17) ስለ አብነት መምህራን ፍለሰት ጉዳይ፤ 18) ስለ ተጀመረው የአሜሪካው ዕርቅ ጉዳይ ሪፖርት መስማት፤ 19) ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በተመለከተ፤ 20) የቋሚ ሲኖዶስ አባላት ምርጫ የሚሉ ናቸው፡፡

አጀንዳ አዘጋጅ ኮሚቴው ዝርዝሩን ለምልአተ ጉባኤው ካቀረበ በኋላ ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በተራ ቁጥር 18 ላይ በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙ አባቶች ጋራ የተጀመረው ዕርቅ ጉዳይ በአጀንዳነት መያዙን ተቃውመዋል፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት “ፖሊቲከኞች ናቸው” በሚልም በዕርቀ ሰላሙ ሂደት መቀጠል ላይ እንደማያምኑበት ተናግረዋል፤ ከመንበረ ፓትርያርኩ ተወክለው ከሄዱት ልኡካን መካከል አንዱን አባል በስም በመጥቀስ “ወደኋላ ቀርተው ከእነርሱ ጋራ ነገር ሲሸርቡብኝ ነበር” በማለት ወቅሰዋል፡፡

በአንጻሩ ፓትርያርኩ በዕርግና እና በሞተ ዕረፍት የተለዩ አባቶችን በመቁጠር ተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት መሾም እንዳለባቸው ከዚህ ቀደም በያዙት አቋም ጸንተዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሚያንጸባርቋቸው አብዛኛዎቹ አቋሞች የብፁዕ አቡነ ገሪማን፣ የብፁዕ አቡነ ማርቆስን፣ የብፁዕ አቡነ ሳዊሮስንና የብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን ድጋፍ ያገኙ ቢኾንም ከብዙኀኑ የመደበኛው ጉባኤ አባላት ግን ጠንካራ ተቃውሞ ነው የገጠማቸው፡፡

አቡነ ጳውሎስ በሰሜን አሜሪካው የዕርቅ አጀንዳ ላይ ስለሰነዘሩት ተቃውሞ ሐሳባቸውን የሰጡ አባቶች÷ “በእኛ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፍላ አትቀርም፤ ለቀጣዩ ትውልድ ለሁለት የተከፈለች ቤተ ክርስቲያን ማስረከብ አንሻም፤ የዕርቅ ሂደቱ መቀጠሉ ግድ ነው፤ በእግራችንም ቢኾን እዚያው ሄደን እናሳካዋለን” የሚሉ ጠንካራ ምልልሶችን ከፓትርያርኩ ጋራ መለዋወጣቸው ተዘግቧል፡፡ ምልአተ ጉባኤው በአጀንዳው እንደተመለከተው የመንበረ ፓትርያርኩ ልኡካንና በስደት የሚገኙት አባቶች ተወካዮች በየካቲት ወር ተደርጎ በነበረው ውይይት ላይ የሚያቀርቡትን ሪፖርት እንደሚያዳምጥ የስብሰባው ምንጮች ተናግረዋል፡፡

አቡነ ጳውሎስ ያለማሳለስ እየተሟገቱበት ያለውንና በብዙዎች ዘንድ “የፓትርያርኩ አዳዲስ የዓላማና ጥቅም ወዳጆች ማፍሪያ ነው” የሚባለውን የተጨማሪ ኤጴስ ቆጶሳት ሹመት ጉዳይንም “ለጊዜው ያለነው እንበቃለን፤ ከተጀመረው ዕርቅ አንጻር ወቅቱን የጠበቀ አይደለም፤ የዕርቁን ሂደት ያደናቅፋል፤ ያለውንም ችግር ያባብሳል” በሚል በሚበዙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በመካከል የወዲያውንም የወዲሁንም ሐሳብ በመዳኘት ለመሸምገል የሞከሩ ብፁዓን አባቶች የነበሩ ቢኾንም ምልአተ ጉባኤው ቀትር ላይ የተነሣው የሚጠቀስ መግባባት ላይ ሳይደረስ ነው፡፡

ከስብሰባው ጋራ በተያያዘ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ገና ባልተወሰነባቸው አጀንዳዎች ሳይቀር መሠረት የሌላቸው አሉባልታዎች እያናፈሱ ይገኛሉ፡፡ ከእኒህም አንዱ በአጀንዳ ተራ ቁጥር 13 “ስለ ሃይማኖት ሕጸጽ በኮሚቴው የሚቀርበውን ሪፖርት መስማትና መወሰን” በሚል የተመለከተው ሲኾን÷ ሊቃውንት ጉባኤው የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተመርቶለት በጥቅምትና ኅዳር ወራት በመረመራቸው ማስረጃዎች “መወገዝ ያለባቸው፣ ከዕውቀት ማነስ የተሳሳቱና ወደ ት/ቤት መግባት ያለባቸው፣ መመከር የሚገባቸው” በሚል የከፈላቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችና አቀንቃኞች መኖራቸው ተዘግቧል፡፡ እንዲህ ዐይነት አሉባልታዎች የሚናፈሱት ምናልባትም ሊቃውንት ጉባኤው የውሳኔ ሐሳቡን ለሊቃነ ጳጳሳቱ ኮሚቴ ከመራ በኋላ በክትትል ማነስ የተፈጠሩ ክፍተቶችን በመበዝበዝ ጠንካራ አቋም በያዙቱ ላይ ጫና ለመፍጠር፣ ጉዳዩን የሚከታተለውን ቀናዒ አገልጋይና ምእመን አስተያየትንም በማዛባት ተስፋ ለማስቆረጥ ከመቋመጥ አያልፍም፡፡

ከቀትር በኋላ ቅዱስ ሲኖዶሱ ወደ አጀንዳው በመግባት መወያየቱን እንደሚቀጥል የጉዳዩ ተከታታዮች ተስፋ አድርገዋል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

4 comments:

Anonymous said...

The holy synod looks more powerless now probably they are intemediated by...., The only solution is to remove the guy the so called " patriarch". And the holy synod is not going to do this. Therefore, we have to take it to our hands. Like the muslims we have to revolt against the patriarch and his gang club members. You may say this is not Godly, but God needs people to do his job and we are the ones to do that. After all, he is not some one anointed by the holy sprit, He is brought to patriarchate position by.... So if the holy synod fail to remove him, we will remove him in any way....you have to know that the Muslims are going to have the people whom they elect. How about us. The holy synod members look afraid. Otherwise, they could have considered the following agendas

1) failure to implement earlier decisions made by the holy synod. This is totaly because of the guy.
2) The issue of north America dioce, the truble maker and the member of the gang club, "aba" Fanuel.

Anonymous said...

cher were yaseman

Anonymous said...

yes we have to do that the early guy discuss. we need to remove him other wise the disaster on our church will be very hard.

Anonymous said...

እውነት ብለሃል፡፡
እኔስ የሚገርመኝ አቡነ ጳውሎስን የመጀመሪያ ታቦት ይዞ በመውጣት የተቃወማቸው የአክሱም ካህናትና ምዕመናን ናቸው፡፡ ብዙ የትግራይ አባቶችም የአባ ጳውሎስን ከሃዲነትና አብደውም እንደሚሞቱ የሚናገሩት ሚስጥሩን ስለተረዱት ነው፡፡ በተጨማሪም አለቃ አያሌው ታምሩ ዘዲማ ጊዮርጊስ ይህን ሁሉ ጉድ ልዑል እግዚአብሔር ቢያመለክታቸው እኮ ነው ሁሉንም ሆዳም ጳጳሳት ያወገዙአቸው፡፡ለማንኛውም ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ምዕመን ይህንን ይወቅ፡፡ ቃለ ውግዘቱን በመጠኑም ቢሆን ያንብቡ፡፡
ቃለ ውግዘት።
«ዛሬ ካለው የቤተ ክርስቲያን አመራር ጋራ ወደ ትግል ሰልፍ እንድገባ ያደረገኝ የኔ ፈቃድ፥ ዐቅምም አይደለም። በ፲፱፻፹፭ ዓመተ ምሕረት ሐምሌ ፭ ቀን ኦፕራሲዮን ሆኜ በሰመመን ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ በሥርዓተ ሙታን ወደ አምላኬ ፊት ቀርቤ የተሰጠኝ ትእዛዝ ነው። በዚያች ሰዓት፤ ከቅዱስ ማርቆስ እስከ ሳድሳዊ ቄርሎስ የነበሩ የእስክንድርያ ፓትርያርኮችና ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከአትናቴዎስ፥ ከሰላማ እስከ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የነበሩ የኢትዮጵያ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትርያርኮች የእሳት ነበልባል በከበበው፥ የእሳት ልሳን ያለው መጋረጃ በተንጣለለበት በዚያ አዳራሽ፥ በዚያ የግርማ ዙፋን ግራና ቀኝ ተሰልፈው ቁመው ነበር። በኤፌሶን ጉባኤ ንስጥሮስን ያወገዘው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ በመንበሩ ፊት ለፊት ቆሟል። ቀድሞ የተወገዘው ንስጥሮስ የማዕረግ ልብሱን ተገፎ በስተጀርባው ቆሟል። አባ ጳውሎስ በማዕረጋቸው እንዳሉ ተከስሰው ከንስጥሮስ ጎን ቁመዋል። በዐጸደ ነፍስ የሚገኙት የእስክንድርያና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አበው፤ «አባ ጳውሎስ ሺ ስድስት መቶ ዓመት የኖረ ውግዘት ጥሰው፥ በሥጋው በደሙ የማሉትን መሓላ አፍርሰው የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የሮም ቅኝ ግዛት ስላደረጉ፤ ፍርድ ይሰጥልን፤» ሲሉ ለኀያሉ አምላክ አቤቱታ አቀረቡ። ከዙፋኑ የመጣው መልስ ግን፤ «እስከ ዕለተ ምጽአት ፍርድ የቤተ ክርስቲያን ነው፤» የሚል ነበረ። ይህ ሁሉ በሚከናወንበት ጊዜ የማላውቀው ኀይል ከዚህ ዓለም ነጥቆ ከቅዱስ ቄርሎስ ጎን አሰልፎኝ ከቆየ በኋላ ከዙፋኑ የመጣው ድምፅ፤ «አንተ ያየኸውን፥ የሰማኸውን ለቤተ ክርስቲያን፥ ለምእመናን ንገር፤» ሲል አዝዞ ወደ ነበርኩበት መለሰኝ። ይህ ትእዛዝ ነው እዚህ ሰልፍ ውስጥ ያስገባኝ። ኢትዮጵያዊ፥ ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ሁሉም ስለ ቤተ ክርስቲያኑ አጥብቆ መታገል አለበት።» አለቃ አያሌው ታምሩ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ የተከሰቱትን የሃይማኖት ትምህርትና የሥርዓት መበላሸት በማስመልከት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ የነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩ ችግሩ ሥር ሳይሰድ ገና ከጅምሩ እንዲታረም ማሳሰቢያና ተማጽኖ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ተደጋጋሚ ተማጽኖ አቅርበው ነበር። ነገር ግን ጥያቄአቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ዘንድ በቸልታ በመታየቱ ምክንያት፤ አለቃ አያሌው ታምሩ ባላቸው ከፍተኛ ሥልጣንና ኀላፊነት፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ ዐመጽ የሚፈጽሙትን ፓትርያርኩንና ተከታዮቻቸውን ለማውገዝ ተገደዋል። ቃለ ግዝታቸው በመጀመሪያ የወጣው ሰኔ ፳፯ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት በ«መብሩክ» ጋዜጣ ላይ ነበር። ይኽም እንደሚከተለው ይነበባል።
« መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ከፓትርያርኩና ተከታዮቻቸው ቃልና እጅ ቡራኬ እንዳይቀበል አገር አቀፍ ጥሪ ቀረበ። የወጣውን ሕግ የተቀበሉ፥ ከሥራ ላይ ያዋሉ እንደ አርዮስ እሱራን ውጉዛን ይሁኑ። አለቃ አያሌው ታምሩ ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ የሆነ ምእመን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቃልና እጅ፥ በሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ በአቡነ ገሪማና በተባባሪዎቻቸው ቃልና እጅ ቡራኬ እንዳይቀበል በአብ፥ በወልድ፥ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን፥ በጴጥሮስ፥ በጳውሎስ፥ በማርቆስ፥ በቄርሎስ፥ በባስልዮስ፥ በቴዎፍሎስ፥ በተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ ቃልና በራሳቸው ማውገዛቸውን አስታወቁ። አለቃ አያሌው ታምሩ ይህን ያስታወቁት የግንቦቱ ሲኖዶሳዊ ጉባኤ አዲስ ያወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡንና ሐምሌ ፭ ወይም ፮ ቀን በሚከበረው የፓትርያርኩ በዓለ ሢመት ላይ የእሳቸው አመለካከት ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገምገም ቃለ መጠይቅ ባደረግንላቸው ወቅት ነው።
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቃልና እጅ፥ በሲኖዶሱ ዋና ጸሓፊ በአቡነ ገሪማ ቃልና እጅ፥ ይህን አሁን የተጻፈውን ሕግ የቤተ ክርስቲያን ሕግ ብለው አጽድቀው በተባባሪነት አሳልፈዋል የተባሉ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ሁሉ እውነት ሆኖ ከተገኘ የበደሉ ተባባሪዎች ናቸውና በነሱ ቃልና እጅ ቡራኬ እንዳትቀበሉ፥ እንዳትናዘዙ፤ ስማቸውን በጸሎተ ቅዳሴ የሚጠሩ አለቆች፥ ቀሳውስት፥ ካህናት ካሉም የአምልኮተ ጣዖት አራማጅ ናቸውና ተጠንቅቁባቸው፤ ምክር ስጧቸው፤ እንቢ ካሉም ተለዩዋቸው። እንዲሁም ሐምሌ ፭ ወይም ፮ ቀን ይከበራል ተብሎ ሽርጉድ የሚባልለት በዓለ ሢመት የአሮን የወርቅ ጥጃ መታሰቢያ ሆኖ በቤተ ክርስቲያን ሊከበር የማይገባው ስለ ሆነ በዓሉ ከመድረሱ በፊት የሲኖዶሱ አባላት በአስቸካይ ተሰብስበው ሕጉን ካልሻሩና በጣዖትነት የተሰየሙትን አቡነ ጳውሎስን ከሥልጣናቸው ካላነሡ ምእመናን ይህንን በዓል እንዳታከብሩ ለቤተ ክርስቲያን ደሙን ባፈሰሰ አምላክ ስም፥ ቤተ ክርስቲያንን በሚመራና በሚጠብቅ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥያቄዬን አስተላልፋለሁ። ምናልባት የሕጉን ጽሑፍ አንብቦ መረዳት የተሳነው፥ ግን በልዩ ልዩ ደጋፊዎቻቸው ተጭበርብሮ በቸልታ የሚመለከተው፤ ከዚያም ዐልፎ በሥልጣናቸው እየተመኩ ለቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ጆሯችንን አንሰጥም ብለው ይህን በደል ያደረሱትን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን፥ በሦስት የሹመት ስም የሚንቀባረሩትን አባ ገሪማን፥ ለነሱ ድጋፍ የሚሰጡትንም ሁሉ፤ ጌታዬ አምላኬ፤ «በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤» ሲል በሰጠው ቃል በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን፤ በጴጥሮስ፥ በጳውሎስ፥ በማርቆስ፥ በቄርሎስ፥ በባስልዮስ፥ በቴዎፍሎስ፥ በተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ ቃል፤ ኃጥእ ደካማም በምሆን በእኔም በቀሲስ ወልደ ጊዮርጊስ ቃል አውግዤአለሁ። ይህን ሕግ የተቀበሉና ከሥራ ላይ ያዋሉ ሁሉ እንደ አርዮስ፥ እንደ መቅዶንዮስ፥ እንደ ንስጥሮስ፥ እንደ ፍላብያኖስ፥ እንደ ኬልቄዶን ጉባኤና ተከታዮቹ እሱራን፥ ውጉዛን ይሁኑ። በማይፈታው በእግዚአብሔር ሥልጣን አስሬአለሁ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን አሜን።
ማስጠንቀቂያ፤ አምላኬ ሂድ ተናገር ያለኝን ትእዛዝ ለእናንተ አድርሻለሁ። ሩጫዬንም ጨርሻለሁ። ከእንግዲህ ተጠያቂነቱ የእናንተ የምእመናንና ታሪክ ተጠያቂ ያደረገው የመንግሥት ነው። ለዚህም ምስክሬ ራሱ እግዚአብሔር፥ ቅዱሳን መላእክት፥ ሰማይና ምድር ናቸው።
አለቃ አያሌው ታምሩ ዘዲማ ጊዮርጊስ። በዚህ ድረ ገጽ ላይ ሙሉ መልዕክቱን ይመልከቱ፡፡
http://www.aleqayalewtamiru.org