Friday, June 15, 2012

የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ካህናት፣ ሰበካ ጉባኤና ሰንበት ት/ቤት በ”ችግር ፈጣሪው” አስተዳዳሪ አባ ሚካኤል ታደሰ ታውከዋል


 READ THIS ARTICLE IN PDF.
·        በአስተዳዳሪነት የተሾሙት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንና ቃለ ዐዋዲውን በመጣስ ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ተገዥ ባለመኾናቸው ማዕርገ ክህነታቸው ተሽሮ በሥልጣነ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ከተወገዙ በኋላ ነው።
·         ሀ/ስብከቱ የሀብት ቁጥጥርን ለማጠናከር ያስተላለፈውን መመሪያ በመጣስ ዘረፋን ያበረታታሉ።
·        ሰንበት ት/ቤቱን ‹ማኅበረ ቅዱሳን ናቸው› በሚል አገልግሎቱን የሚያደናቅፉ ርምጃዎች ወስደዋል።
·        አስተዳዳሪው ከአባ ጳውሎስ የኤጲስ ቆጶስ ሢመት ተስፈኞች አንዱ ናቸው።
  ሙሉ ዘገባውን የወሰድነው ከደጀ ሰላም ብሎግ ነው::
 በማዕርገ ዲቁናቸው በእቲሳ ደብረ ጽላልሽ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም በዐቃቢነት አገልግለዋል፡፡ ያን ጊዜ ስማቸው ዲያቆን ሙሉነህ ታደሰ ይባል ነበር፡፡ በገዳሙ ማዕርገ ምንኵስና ሲቀበሉ ስማቸው አባ ኀይለ ኢየሱስ ታደሰ መባሉን የገዳሙ አስተዳደር በቁጥር 79/05/98 በቀን 16/05/1998 ዓ.ም የሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የግለሰቡን ማንነት አስመልክቶ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጠበት ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

ከ1996 ዓ.ም መጋቢት ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ ጥር ወር አጋማሽ 2000 ዓ.ም ድረስ በሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት የደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤልና የደብረ መንክራት ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ የነበሩት አባ ኀይለ ኢየሱስ ታደሰ በማያውቀው ምክንያት ስማቸውን “አባ ሚካኤል ታደሰ” በሚል ለውጠው ሌላ የምንኵስና እና ቁምስና መታወቂያ ማውጣታቸውን የሚገልጸው ይኸው የገዳሙ ደብዳቤ÷ “አባ ሚካኤል” የተሰኘውን ስመ ምንኵስናና ቁምስና እንደማያውቀው አስታውቋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ አባ ሚካኤልን አስመልክቶ የመነኮሱበትን ገዳም ለመጠየቅ የተገደደው በሁለቱ አድባራት አስተዳዳሪነታቸው ወቅት ለሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ለሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ባለመታዘዝ ቃለ ዐዋዲውን በተደጋጋሚ በመጣሳቸው፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ሰላም በማናጋታቸው ነው፡፡ አባ ሚካኤል ምንኵስናቸውንና ክህነታቸውን በሚመለከት ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ ሀገረ ስብከቱ በቁጥር 2/668/3035/99 በቀን 15/3/99 ዓ.ም በደብዳቤ ቢያዛቸውም ያቀረቡት ማስረጃ ግን የተጭበረበረና በቂ አለመኾኑን በቁጥር 2/2623/3035/2000 በቀን 15/12/2000 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ የተጻፈላቸው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡
“ከማዕርገ ክህነት በመሻር ቃለ ውግዘት ስለማስተላለፍ” በሚል ርእስ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ፊርማ የወጣው ይኸው ደብዳቤ÷ አባ ሚካኤል ታደሰ፡-
·         ቀሳውስትንና ዲያቆናትን፣ መምህራንና ሰባክያነ ወንጌልን ያለበቂ ምክንያት ከመደበኛ ሥራቸው በማባረር ቤተ ክርስቲያንን አገልጋይ አልባ ማድረጋቸውን፤
·         በአስተዳዳሪነት የተመደቡባቸውን አብያተ ክርስቲያን ለብቻ ገንጥለው ከሀገረ ስብከቱ መዋቅራዊ አስተዳደር ውጭ በማድረግና የሀገረ ስብከቱ ፈሰስ (ፐርሰንት) እንዳይከፈል መከልከላቸውን፤
·         ቋሚ ሲኖዶስ ጥር 16 ቀን 2000 ዓ.ም እና የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ግንቦት 16 ቀን 2000 ዓ.ም የአድባራቱን ገንዘብና ንብረት ሀገረ ስብከቱ ለሚወክለው ሰው አስረክበው ወደ መ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት በመቅረብ ሪፖርት እንዲያደርጉ በቁጥር 3778/109/2000 በቀን 29/9/2000 ዓ.ም በተደጋጋሚ ያስተላለፈላቸውን ትእዛዝ “የተጭበረበረ ነው” በሚል አለመቀበላቸውንና በግብረ አበሮቻቸው ማስተቸታቸውን፤ ወደተጠሩበት ቦታ ሄደው ሪፖርት ከማድረግ ይልቅ የሕገ ወጥ ሥራቸው ተባባሪ የኾኑ ግለሰቦችን በማደራጀት ሁከት ማስነሣታቸውን፤
·         በምንኵስና አባ ኀይለ ኢየሱስ፣ በቅስናና በቁምስና አባ ሚካኤል ታደሰ የሚሉ ሁለት ዐይነት ማስረጃዎችን ማቅረባቸውን፤
·         “የሰላም ኮሚቴ” በሚል ሽፋን ባቋቋሙት ቡድን በሰበካ ጉባኤው አስተዳደራዊ ሥራ ጣልቃ ማስገባታቸውን፤ በተፈጠረው ሁከት የአድባራቱን ሰንበት ት/ቤት ጽ/ቤት በማሸግ አገልግሎታቸው እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን፤
·         በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አለመታዘዛቸውን፤
·         በየጊዜው ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የሚተላለፍላቸውን የሥራ መምሪያ እየተቀበሉ ለመሥራት ፈቃደኛ ኾነው ባለ መገኘታቸው የተነሣ ከሀገረ ስብከቱ ጋራ መልካም የሥራ ግንኙነት በመፍጠር በበጀት ድልድል ይኹን በሠራተኞች ቅጥርና በማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ ሁሉ የአሠራር ማእከልነትን ጠብቀው እንዲሠሩ የተላለፈላቸውን መምሪያ በመተላለፋቸው በቁጥር 2/1968/3035/2000 በቀን 21/10/99 ዓ.ም በተጻፈላቸው ደብዳቤ ከሁለቱ አድባራት አስተዳዳሪነትና ከደመወዝ ታግደው የነበረ ቢኾንም በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ እርምት በመስጠት እንዲመለሱ መደረጋቸውን ይዘረዝራል፡፡
ቃለ ዐዋዲውና ሕገ ቤተ ክርስቲያን በሥራ ላይ እንዳይውል ስለማደናቀፍ በአንቀጽ 64 ንኡስ አንቀጽ 6 የተደነገገውን መነሻ ያደረገው ይኸው ደብዳቤ÷ ከላይ የተዘረዘሩት ተግባራት አባ ሚካኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ባለመቀበል ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሃይማኖታችን ያላቸውን ተፃራሪነት የገለጹበት እንደኾነ አመልክቷል፡፡
በመኾኑም ከዲቁና እስከ ጵጵስና ያላቸው መንፈሳዊ ማዕርግ ተሽሮ በሥልጣነ ጴጥሮስ ወጳውሎስ የተወገዙ መኾናቸውን፣ ከነሐሴ 14 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮም አቶ ሚካኤል ታደሰ ተብለው እንዲጠሩ ቃለ ውግዘት የተላለፈ መኾኑን ያስታውቃል፤ ከእርሳቸው መስቀል የተሳለመና ማንኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎት ያገኘ በቅዱሳን ሐዋርያት ሥልጣን በሰማይና በምድር የታሰረ መኾኑንም ይገልጣል፡፡
ከቃለ ውግዘቱ መተላለፍ በኋላ በአባ ሚካኤል ታደሰና በሀገረ ስብከቱ መካከል የተፈጠረውን ችግር በቦታው ተገኝቶ ችግሩን እንዲያጠና መስከረም 10 ቀን 2001 ወደ አርባ ምንጭ የተላከው ሦስት አባላት (ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ የሐንስ እና ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል) ያሉበት ልኡካን ቡድን÷ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ሠራተኞች፣ ከሁለቱ አድባራት ሰበካ ጉባኤ አባላትና ካህናት፣ ከተመረጡ ምእመናንና የአገር ሽማግሌዎች፣ ከጋሞጎፋ ዞን አስተዳደር፣ ፖሊስ፣ ፍትሕና ጸጥታ ዘርፍ ሓላፊዎች እንዲሁም የአባ ሚካኤል ታደሰ ደጋፊዎች ናቸው ከተባሉ አካላት ጋራ ሳይቀር ከተወያየ በኋላ መሰከረም 14 ቀን 2001 ዓ.ም ለመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያቀረበው ባለስድስት ገጽ ሪፖርት በየደረጃው በአባ ሚካኤል ላይ ሲተላለፉ የቆዩ ውሳኔዎችን የሚያጸኑ ናቸው፡፡
ሪፖርቱ እንደሚገልጸው ቋሚ ሲኖዶስና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አባ ሚካኤል ታደሰ የአድባራቱን ንብረት አስረክበው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለመንበረ ፓትርያሪኩ ጠ/ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉ የተላለፉላቸውን ውሳኔዎች ለማድረስ የተላኩ የሀ/ስብከቱን መልእክተኞች በተከታዮቻቸው አስደብድበው የአካል ጉዳት አድርሰውባቸዋል፡፡ ደወል ደውለው የዋሃኑን በመሰብሰብ በከተማው ከፍተኛ ነውጥ ቀስቅሰዋል፡፡ ባልተሰጣቸው ሥልጣን በመጠጥ ኀይል የተጎዱ መንገደኛ ተከታዮቻቸውን “ዲቁና ሰጥቻችኋለኹ፤ ዲቁና የሰጠኋችኹም ሐዋርያት ስለ ክርስቶስ እንደሞቱ ከእኔ ጋራ እንድትሞቱ ነው፤ የቤተ ክርስቲያኑን ማናቸውም ንብረት ለእኔ ካልኾነ በቀር ለማንም እንዳትሰጡ ጠብቁ” ብለው በማደራጀት ቤተ ክርስቲያኑን አዘግተዋል፡፡
በዚህ ድርጊታቸው የሰላም ጠንቅና የወንጀል አቀናባሪ በመኾናቸው በቁጥጥር ሥር ቢውሉም በማረሚያ ቤቱ ኾነው ቤተ ክርስቲያኑን እንዳይከፍቱና ንብረትም እንዳያስረክቡ በሞባይል ስልክ በመቀስቀስ ባደራጁት ሕገ ወጥ ቡድን ቤተ ክርስቲያኑ ለ56 ቀናት ተዘግቶ አገልግሎቱ ተስተጓጉሏል፤ ሕገ ወጥ ቡድኑ “መነኵሴው ካልተፈቱ ቤተ ክርስቲያኑ አይከፈትም” በማለትም ቤተ ክርስቲያኑን መያዣና መደራደርያ አድርጎታል፡፡ ከዚህ ሕገ ወጥ ቡድን ባሻገር አባ ሚካኤል “የሰላም ኮሚቴ” በማለት በሠየሙትና የአድባራቱን ሰበካ ጉባኤ በመተካት የሚንቀሳቀሰው 17 አባላት ያሉት ኮሚቴ÷ የቤተ ክርስቲያኑን ገንዘብ ይኹን ንብረት ያለሞዴል በነጭ ወረቀት በመቀበል አባክኗል፤ ከመነኵሴ ጋራ በአይዞህ ባይነት በመንቀሳቀስ ቤተ ክርስቲያኑን አዘግቷል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔን የማይቀበለው መነኵሴ ነኝ ባዩ አባ ሚካኤል የጥቅም ሰዎች እና ፀረ - ኦርቶዶክስ እምነት አቋም ያላቸው ሰዎች መሣርያ መኾኑን የመሰከረው አጣሪ ኮሚቴው በሪፖርቱ ጨምሮ እንደገለጸው ለችግሩ መባባስ አስተዋፅኦ ያደረጉ ምክንያቶችን ዘርዝሯል፡፡
ከእኒህም መካከል፡- አባ ሚካኤል ታደሰ የቤተ ክርስቲያንን ቋሚ መመሪያና የበላይና የበታች የዕዝ ሰንሰለት አለመጠበቃቸውን፣ በቃለ ዐዋዲው ደንብና መምሪያ የቤተ ክርስቲያኑን ገቢና ወጪ በማእከላዊ ሞዴል አለመያዛቸውን፣ “ሀገረ ስብከቱም ኾነ ቤተ ክህነቱ ገንዘብ ፈላጊዎች ስለሆኑ እነርሱን አንፈልግም” የሚል አቋም በመያዛቸውና በዚሁ መንፈስ የዋሃንን መመረዛቸውን፤ ጥቅመኛ ግለሰቦችና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትን በማዳከም ለራሳቸው ዓላማ ጥቅምን የሚፈልጉ የሌላ እምነት ተከታዮች እጃቸውን እንዲያስገቡ መሣርያ መኾናቸውን፣ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ እያሉ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ጽላቱን በሜሮን ማክበራቸውን፣ በቃለ ዐዋዲው ደንብና መምሪያ መሠረት በማእከል የሚሰበሰበውን የፐርሰንት ክፍያ ሊከፍሉና ሊያስከፍሉ ፈቃደኛ አለመኾናቸውን፣ ሕዝቡን እያታለሉ ሰልፍ በማስወጣት ሁከት መፍጠራቸውን፣ የዞኑ መስተዳደርም ቤተ ክርስቲያኑ ለ56 ቀናት ተዘግቶ፣ መንፈሳዊ አገልግሎቱ ተቋርጦና ዐመፅ ፈጣሪዎች በቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ መሽገው ምእመናን ለጸሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ ሲከለከሉ ዝም ብሎ መመልከቱ አግባብ እንዳልነበር የጠቀሳቸው ይገኙበታል፡፡
ኮሚቴው በሪፖርቱ እንደ መፍትሔነት አቅርቧቸው ከነበሩት ሐሳቦች መካከል “በአንድ ቦታ የተጣሰ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ነገ በሌላ ቦታ ተቀባይነት እንዳይኖረው የሚያደርግ አስተሳሰብ በሚያሰፍን መጥፎ አርኣያነት” ሳይሆን “የሕግን የበላይነት መሠረት ባደረገ መልኩ” መኾን እንደሚገባው ያሳሰበበት አገላለጽ ይገኝበታል፡፡
አባ ሚካኤል ታደሰ ስለፈጠሩት ችግር በጥናት የተደገፈው የኮሚቴው ሪፖርት የቀረበለት ቋሚ ሲኖዶስ መስከረም 20 ቀን 2001 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ከሐምሌ 22 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ ሪፖርቱ እስከተጠናቀረበት ቀን ድረስ የአርባ ምንጭ - ሲቀላ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤልና ደብረ መንክራት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተዘግቶ እጅግ እንዳሳዘነው በመግለጽ ድርጊቱ “በታሪክ አስወቃሽ” መኾኑን በውሳኔ ቃለ ጉባኤው ላይ አስፍሮ ነበር፡፡ የጋሞጎፋ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ጸጥታውን አስከብሮ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ የመሸገው የዐመፅ ግብረ ኀይል እንዲወጣ፣ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲከፈትና አገልግሎቱ እንዲቀጥል እገዛ እንዲያደርግ ለመጠየቅ በቁጥር 334/109/2001 ዓ.ም በቀን 23/1/2001 ዓ.ም ለክልሉ መስተዳድር ጽፎት በነበረው ደብዳቤ መነኵሴ ነኝ ባዩን አባ ሚካኤል ታደሰን የገለጻቸው “ችግር ፈጣሪው እና ልዩ የዐመፅ ሥራ ፈጻሚዎች አስተባባሪ” በሚል ነበር፡፡
የሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት አባ ሚካኤል ታደሰን በቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ መንገድ ብቻ ሳይሆን በከተማው ስለፈጠሩት ሁከት በሕግ አግባብ በፍትሕ አደባባይ እንዲጠየቁም አድርጎ ነበር፡፡ ሀገረ ስብከቱ በቁጥር 2/2593/3035/2000 በቀን 9/12/2000 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መሥርቶት በነበረው ክስ÷ ፍ/ቤቱ በፍ/መ/ቁጥር 06623 በወርኀ ጥቅምት፣ 2001 ዓ.ም ባዋለው ችሎት÷ የቤተ ክርስቲያን የበላይ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት 16 ቀን 2000 ዓ.ም የወሰነውን በማጽናት÷ አባ ሚካኤል ታደሰ የሲቀላ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤልንና ደብረ መንክራት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ንብረትና ገንዘብ የጋሞጎፋ ሀገረ ስብከት ለሚመድበው ሰው በማስረከብ ከአስተዳዳሪነታቸው እንዲለቁ ነበር የወሰነባቸው፡፡
ቀኖናዊ ውግዘቱ፣ አስተዳደራዊ ውሳኔውና ፍትሐዊ ፍርዱ ግን አባ ሚካኤል ታደሰን በሌሎች አድባራት እየተሾሙ ሌሎች ሰበካ ጉባኤያትን፣ ሰንበት ት/ቤቶችን፣ ካህናትንና ምእመናንን እንዳያውኩ አልከለከላቸውም፡፡ ከአርባ ምንጩ ሲቀላ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ኾነው የቆዩት አባ ሚካኤል ታደሰ በዚያ የሰንበት ት/ቤቱን ወጣቶች ሰብስቦ “እናንተ አቋማችሁ ምንድን ነው? ለምን ዝም ትላላችኹ? ወይ ደግፉኝ ወይ ተቃወሙኝ” በማለት ሲያስጨንቋቸው ቆይተዋል፡፡ በደረሱበት ሁሉ በቃለ ዐዋዲው መሠረት የተቋቋመውን ሰበካ ጉባኤ አፍርሰው ዳግመኛ በማስመረጥ ‹በራሳቸው ሰዎች› መሙላትን ሞያ ብለው ይዘውታል፡፡ ከአገልግሎታቸው የተነሣ መልካም ስም ያላቸው ሰንበት ት/ቤቶችና መንፈሳውያን ማኅበራት ስም ያስደነግጣቸዋል፡፡ ከቀሳውስቱ፣ ከዲያቆናቱና ከምእመናኑ መካከል ጥቂቶችን ለይተው በማቅረብ መከፋፈልና በመጨረሻም እነርሱን ከደመወዝና ከሥራ በማገድ መጉዳት የሠርክ ግብራቸው አድርገውታል፡፡
በሥርዐተ ጸሎት የቤተ ክርስቲያንን ድንጋጌዎች እየጣሱ ጸሎተኛ መስለው ለመታየት መሞከራቸውም አልቀረም፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ዐውደ ምሕረት የትምህርተ ወንጌል፣ የሰላምና የፍቅር አደባባይ ሳይኾን ሁከትና ብጥብጥ የሚፈጥሩ ግለሰቦች መፈንጫ በማድረግ የቆዩበትን ልምድ በመቀጠል በተገኙበት ደብር “የዐውደ ምሕረት ጆቢራዎችን” ለመጋበዝ ዳር ዳር በማለታቸው ከስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ጋራ መላተማቸው ተሰምቷል፡፡
ትናንት ደ/ኀ/ቅ/ገብርኤልን ዛሬ መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤልን!!
በልዩ ስሙ ፊት በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን ተጎራብቶ በ1889 ዓ.ም በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የተተከለውና ብፁዕ አቡነ እንድርያስን በመሳሰሉ ደገኛ ብፁዓን አበው ሳይቀር የተመራው መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ ከመጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ እነኾ፣ በ”ችግር ፈጣሪው” አባ ሚካኤል ታደሰ አስተዳደር ሥር እንዲቆይ ተፈርዶበታል፡፡
ከመጋቢት ወር አስቀድሞ መልአከ ሰላም አባ ሳሙኤል ገብረ ጻድቅ በተባሉ አባት ሲመራ የቆየው አስተዳደሩ÷ በተለይም በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ባስመረጣቸው የሰበካ ጉባኤ አባላት አመራር የገቢ አቅሙን በማሳደግ፣ የገዳሙን የራስ አገዝ ልማት የሚያጠናክር፣ በመላው ካህናትና ምእመናን ተሳትፎ ዳብሮ የጸደቀ የሦስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ  ለመተግበር በብርቱ እየተንቀሳቀሰ ነበር፡፡
ሰበካ ጉባኤው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስና በቀድሞው ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም አመራር የሀገረ ስብከቱን አድባራትና ገዳማት ከገንዘብ ዘረፋ ለመከላከል በሙዳየ ምጽዋት ቆጠራና በሞዴል ገቢ ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ያወጣውን መምሪያ በአግባቡ በመተግበሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በወርኀዊና በክብረ በዓል እየሰበሰበ ያለው የገዳሙ ገቢ ከቀድሞው የላቀ ለማድረግ ችሏል፡፡
ለአብነት ያህል÷ በየዓመቱ በታኅሣሥና ሐምሌ ወራት በሚከበረው የሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል በቀድሞው ጊዜ ይቆጠር የነበረው የሙዳየ ምጽዋት አማካይ ገቢ ከብር 110,000፣ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ደግሞ ከብር 300,000 የበለጠ አልነበረም፡፡ በያዝነው ዓመት መስከረም ወር የተመረጠው ሰበካ ጉባኤ መመሪያውን መተግበር ከጀመረ በኋላ ግን ገዳሙ ባለፈው ታኅሣሥ 19 ክብረ በዓል ብቻ ያገኘው ገቢ በአማካይ እስከ ብር 1.4 ሚሊዮን እንደ ነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እንደ ቅርብ ምንጮች ገለጻ÷ ይህ የዕጥፍ ዕጥፍ የኾነ ገቢ በውጭ ምንዛሬ፣ በወርቅና ሌሎች ነዋያት እንዲሁም በመባዕ መልክ ከምእመኑ የሚበረከቱ ስጦታዎችን ገንዘባዊ ዋጋ ሳይጨምር ነው፡፡
ከቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል ማግስት ሙዳይ ምጽዋቱን ባዶ በማድረግ ከወሩ 20ኛ ቀን እስከ ቅዱስ ገብርኤል በዓል ዋዜማ (18ኛ ቀን) በቀድሞ ጊዜ ይገኝ የነበረው ወርኀዊ ገቢ በአማካይ ከብር 60,000 የበለጠ አልነበረም፡፡ ጥቂት የሰበካ ጉባኤው ቀበኞች “ስንት እናስገባ? ስንት ደግሞ እንከፋፈል?” በሚል የምእመኑን የታቦት ብር እንደ ጠላት ገንዘብ መቃረጣቸውን በአዲሱ መመሪያ ለመቆጣጠር ከተቻለ በኋላ ግን የገዳሙ ወርኀዊ የሙዳየ ምጽዋት ገቢ ከብር 170,000 ያላነሰ ኾኗል፡፡
አእምሮ ላለውና የቤተ ክርስቲያናችን እንደማትነጥፍ ጥገት ላም መታለብ ለሚያንገበግበው ሁሉ በቀድሞውና በአሁኑ አሠራር የሚታየውን የገቢ መጠን ልዩነት በማሰብ በገንዘብ ዕጦት ብቻ ከሠራነው ነገር ይልቅ ያልሠራነውን ለማሰብ አይቸገርም፡፡ የመመሪያውን ክፍተቶች እያጠናከሩ ከመሄድ ይልቅ የሚቃወሙ ሁሉ ከገቢያቸው በላይ የኾኑ መኪኖችን የሚነዱቱ፣ መሬት ገዝተው ከአንድም ሁለት ቤት የሠሩቱ፣ ከቤተ ክርስቲያን መዝረፋቸው ሳያንስ ለነጋዴው ይኹን ለምእመኑ በአራጣ የሚያበድሩቱ፣ በዘረፋ ገንዘብ በከፈቷቸው ሁለትና ከዚያም በላይ የቁጠባ ደብተሮች የግፍ ብር የሚያደልቡ፣ ከመነኰሳት ነን ባዮቹም መብል መጠጡንና ሌላ ሌላውን ትተን ትዝህርት የሚያሳዩበትንና አለ የተባለውን የሞባይል ቀፎ የሚለዋወጡቱ፣ የጠዋቱን ለቀትር ሳያቆዩ፣ የቀትሩን ለማታ ሳያውሉ አልባሳቱንና መጫሚያዎችን የሚቀያይሩቱ . . . ብቻ ናቸው፡፡
እንግዲህ አባ ሚካኤል ታደሰ ገና ከመምጣታቸው ያደረጉት ነገር ቢኖር የመመሪያውን አተገባበር በመቀልበስ ቀድሞ ወደ ነበረው የዘረፋ አሠራር መመለስ ነው፡፡ ለዚህም በተለምዶ “አምስቱ ከለባት” የሚል ቅጽል የተሰጣቸውንና ከገዳሙ የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ (ሥራ አስፈጻሚዎች) የዝርፊያ ልማድ ያላቸውን የማስተባበር ሥራ እየሠሩ ነው፡፡
አባ ሳሙኤል በመጋቢት ወር ተሾመው ከመምጣታቸው ቀደም ሲል÷ ከ”አምስቱ ከለባት” የተወሰኑት የድርሻቸውን በመወጣት ላይ የነበሩ የሰበካ ጉባኤ አባላትን በየምክንያቱ ሲያሳጡ የነበሩ ናቸው፡፡ እነርሱ የሚከሷቸው የሰበካ ጉባኤ አባላቱ ግን ከተመረጡበት መስከረም ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መኾን ጀምሮ በነበረው የሦስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅዳቸው መሠረት÷ የገዳሙን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ ኮሌጅ ደረጃ ለማሸጋገር፣ ካህናት አርአያ ክህነታቸውን ጠብቀው ለመኖር የሚያስችላቸውን ማደርያ ሕንፃ ለመሥራት፣ ተግባረ ብዙ የሰንበቴና የስብከተ ወንጌል አዳራሾችን ለመገንባት፣ ከከተማው አስተዳደር መሬት በሊዝ በመውሰድ የገዳሙን ገቢ የሚደጉም ተግባረ ብዙ ሕንፃ ለማቆም፤ በስብከተ ወንጌል ማስፋፋትና በተለያዩ የአቅም ግንባታ ተግባራት ዙርያ ለሌሎች በአርኣያነት የሚጠቀሱ ዕቅዶችን ተልመው የሚታትሩት እንደኾኑ ተገልጧል፡፡ እንግዲህ ከ”አምስቱ ከለባት” ጥቂቶቹ እኒህን የሰበካ ጉባኤ አባላት ነው “የአንድ ብሔር ተወላጆች ናቸው፤ ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰበሰቡ ናቸው፤” የሚሉ ክሶችን ይዘው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋራ እስከ መቅረብ የደረሱት፡፡
‹ክሱ› የቀረበባቸው የሰበካ ጉባኤ አባላት እንዲህ ዐይነቱ ጎሰኛና ከፋፋይ አካሄድ በሰበካው አስተዳደር የድርሻቸውን ከመወጣት ሊከለክላቸው እንደማይችል በመግለጽ፣ ስም አጥፊዎቹ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋቸዋል፡፡ ‹ከለባቱ› ግን ክሳቸውን በማጠናከር “ትግራይ ክልል [ለአኵስም ጽዮን ሙዝየም] የሚካሄደውን ግንባታ ይቃወማሉ፤ ለግንባታው ገቢ ለማሰባሰብ በገዳሙ የተቀመጠውን ሙዳየ ምጽዋት በማይኾን ቦታ ደብቀዋል፤ በዚህም ምክንያት ከሙዳይ ምጽዋቱ የሚገኘው ወርኀዊ ገቢ በግማሽ ቀንሷል፤” የሚሉ ተንኰል የተመላባቸውን ክሶች ለፓትርያሪኩ አቅርበዋል፡፡
የሰበካ ጉባኤ አባላቱም በፈንታቸው ለአኵስም ጽዮን ሙዝየም ግንባታ ቀና አመለካከት በመያዛቸው ገዳሙ የሚጠበቅበትን ክፍያ ቀድሞ ማጠናቀቁን፣ በቀጣይም ተጨማሪ የገቢ ማሰባሰቢያ ዕቅዶችን መያዙን፣ ለ‹ከላባቱ› ክስ መነሻ የኾነው የሙዝየሙ ሙዳየ ምጽዋት ስለተቀመጠበት ቦታ እነርሱ የሰጡት መምሪያ አለመኖሩንና የታኅሣሥ ገቢው ከወትሮው ወርኀዊ መጠኑ ቀንሶ የተገኘው በአጋጣሚ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ነገረ ሠሪዎችን (ሰብቀኞችን) መስማት የሚቀናቸው አባ ጳውሎስ ግን ይህን ተከትሎ የቀድሞውን አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም አባ ሳሙኤል ገብረ ጻድቅንና ጸሐፊውን ከቦታቸው አነሡ፤ በምትካቸውም በብፁዕ አቡነ ኤልያስ የተላለፈባቸው ግዝት ስለመነሣቱ ያልተገለጸውንና በአርባ ምንጩ ተግባራቸው ቋሚ ሲኖዶስ “ችግር ፈጣሪ እና የዐመፅ ሥራ አስተባባሪ” በሚል የገለጻቸውን አባ ሚካኤል ታደሰን በአስተዳዳሪነት ሾመዋል፡፡
አባ ሚካኤል ታደሰ በፓትርያሪኩ ተሾመው ከመጡበት ከመጋቢት ወር መጀመሪያ አንሥቶ ባሉት ሦስት ወራት ውስጥ እስከ አሁን ሰበካ ጉባኤውን የሰበሰቡት ለአንድ ጊዜ ያህል ብቻ ነው፡፡ በዋናነት ሰበካ ጉባኤው ከእግዚአብሔር ቸርነት፣ ከሊቀ መልአኩ ረድኤት ጋራ በስትራቴጂያዊ ዕቅድ በሚመራ ጠንቃቃ አካሄድ ያለው መኾኑ ለአባ ሚካኤል አልተመቻቸውም፡፡ ይልቁንስ ሰበካ ጉባኤውን ሰብስበው እንዲያነጋገሩ በተደጋጋሚ ከሊቃነ መናብርቱ የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች ችላ በማለት በአርባ ምንጭ ሲቀላ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እንደለመዱት በራሳቸው የሠራተኛና አገልጋይ ቅጥርና ዝውውር መፈጸሙን ተያያዙት፡፡ የእርሳቸውን ተግባር ሽፋን ያደረጉት ሒሳብ ሹምና ገንዘብ ቤትም በለቀቀ ሠራተኛ ስም ሳይቀር ደመወዝ እያወጡ መብላቱንና ሌሎችንም የዘረፋ ተግባራት ቀጠሉበት፡፡ ስለሆነም አባ ሚካኤል ከነባሮቹ ከሳሽ ‹ከለባት› ጋራ በማበር ለሰበካ ጉባኤው በዕቅድ የሚመራ አካሄድ ዕንቅፋት ለመፍጠር ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡
በአርባ ምንጭ የአራት ዓመታት ሁከት የተሞላ ቆይታቸው የአድባራቱን ሰንበት ት/ቤት ጽ/ቤት በማሸግ የወጣቶቹን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳስተጓጎሉ ሁሉ በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሚገኘው አንጋፋውን ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት ለተጨማሪ ጉባኤያት የሚገለገልበትን ጥምቀተ ክርስትና ቤት እንዳይጠቀም በመከልከላቸው ለአገልግሎቱ አዳጋች ኹኔታ እየፈጠሩ ነው፡፡ በየጊዜው ተሹመው ለመጡ አስተዳዳሪዎች ደማቅ አቀባበል የሚያደርገው ሰንበት ት/ቤቱ ለአባ ሚካኤልም የልምዱን አልነፈጋቸውም ነበር፡፡ ይኹንና ሰበካ ጉባኤውን በየጊዜው ሰብስቦ በማነጋገርና አብሮ በመሥራት ቤተ ክርስቲያን በካህናትና ምእመናን ዘላቂ አንድነት የቆመ አስተዳደር ያላት መኾኑን ከማረጋገጥ ይልቅ ከጥቅመኞች ጋራ መተባበሩን እንደመረጡ ሁሉ የሰንበት ት/ቤቱን ወጣቶችንም በፈረደበት “ማኅበረ ቅዱሳንነት” በመፈረጅ በየመርሐ ግብሩ ያደረገላቸውን ተደጋጋሚ ጥሪ ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡
በአባ ሚካኤል ታደሰ “ችግር ፈጣሪነት” ሳቢያ የሰበካ ጉባኤው አባላት በዕቅዳቸው መሠረት መሥራት የሚገባቸውን መፈጸም እንዳልቻሉ በደብዳቤ ለሀገረ ስብከቱ አስታውቀዋል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ የሰበካ ጉባኤውን አባላት ፊት ለፊት በማነጋገር አባ ሚካኤል ታደሰ ሰበካ ጉባኤውን በወቅቱ እየሰበሰቡ በውይይት በመወሰን የተቀመጠውን ዕቅድ እንዲያስፈጽሙ፣ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራውና የገቢ አሰባሰቡ ሀገረ ስብከቱ ቀደም ሲል ባወረደው የጥንቃቄ መመሪያ መሠረት እንዲቀጥል ማሳሰቢያ የሰጧቸው ቢሆንም የቃል ማሳሰቢያውን በተግባር ተፈጽሞ ለማየት እንዳልተቻለ እየተገለጸ ነው፡፡
ባለ ራእዮቹ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ምእመናን በ”ችግር ፈጣሪው” አባ ሚካኤል ታደሰ ላይ የሚያቀርቡት አቤቱታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ሰሞኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አጣሪ ኮሚቴ ወደ ገዳሙ እንደሚመጣ እየተነገረ ነው፡፡ አባ ሚካኤል ግን በአርባ ምንጭ ሲቀላ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስትንና ዲያቆናትን፣ ሰባክያነ ወንጌልንና መምህራንን ያለበቂ ምክንያት በማባረር ቤተ ክርስቲያኒቱን ያለአገልጋይ ባስቀሩበት የተለመደ “የዐመፅ ሥራ አስተባባሪነታቸው” ካህናቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አጣሪ ኮሚቴ መረጃ በመስጠት ተባባሪ እንዳይኾኑ “በቅርቡ ይህን ያህል ሰዎች አዘዋውራለኹ” እያሉ እያስፈራሩና በዕድሜ የሚበልጧቸውን፣ በክህነታዊ አገልግሎታቸው የተመሰገኑ አበው ካህናትን ጭምር በሚያሸማቅቅ ቃለ ኀይል እየዘለፉ ይገኛሉ፡፡
መነኵሴ ነኝ ባዩ አባ ሚካኤል ታደሰ ማንንም ባላሳመነው መታወቂያቸው ቁምስናን በሞተ ዕረፍት ከተለዩን ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ መቀበላቸውን ገልጸዋል፤ በጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም በአባ ጳውሎስ ብቸኛ ምርጫ ኤጲስ ቆጶስነት ለመሾም በእጅ በእግራቸው ከተራወጡት ሠላሳ ምናምን ‹ቆሞሳት›ም አንዱ ነበሩ፡፡ አባ ሚካኤል ታደሰ የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን እልቅና ለመሾም ‹የመጡበት መንገድ› (የበቁበት ኹኔታ) ለብዙ ግልጽ ቢሆንም ኤጲስ ቆጶስነቱ ግን የዚያን ያህል ቀላል እንደማይኾንላቸው በወርኀ ጥቅምቱና በታሪካዊው የግንቦቱ ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የታየው የብፁዓን አባቶች ጠንካራ አቋም አረጋግጦት ያለፈው እውነታ ነው፡፡
ይልቁንስ ጥያቄው ወዲህ ነው - ስንት የቤተ ክርስቲያናችን ገዳማትና አድባራት አስተዳደሮች ናቸው በእንደ አባ ሚካኤል ዐይነቱ “ችግር ፈጣሪ፤ የዐመፅ ሥራ አስተባባሪ” አለቆች ከፋፋይ የሁከት ተግባር እየታመሱ ያሉት? ስንቶቹስ ናቸው ገቢያቸው በአልጠግብ ባይ “አምስቱ ከለባት” ቅርጫ ገቢያቸው እየተቀነሰ ከዕለት መንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር የራስ አገዝ ልማታዊና ምሳሌያዊ ተግባራትን ለማከናወን እጅ ያጠራቸው?
አባ ሚካኤል ታደሰ ለመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እልቅና ያደረሳቸው ‹መንገድ› ምንም ይኹን ምን የገዳሙ አስተዳደር፣ ካህናትና ምእመናን የገዳሙን ታላቅነት በሚያስጠብቅ አኳኋን የሚያስታገሥ አብነታዊ ጥረት እንደሚያደርጉ ተስፋ አለን፤ ሌሎችም አብያተ ክርስቲያን የእነርሱን አርኣያ በመንሳት ጊዜው የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር በሁለተናዊ መልኩ ተጠናክሮ ሐዋርያ አገልግሎታችን በብሔራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስፋፋበት እንጂ እንደ አባ ሚካኤል ዐይነቱን “የሰላም ጠንቅና የወንጀል አቀናባሪ” የምንሸከምበት እንዳልኾነ ያረጋግጣሉ ብለን እናምናለን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
ከላይ በዘገባችን የገለጽናቸውን ማስረጃዎች በሙሉ ለመመልከት ይህንን ይጫኑ

No comments: