Monday, July 23, 2012

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የፓትርያርክነት ማዕርግ የተቀዳጀችበት የነጻነት በዓል - በዓለ ሢመተ ፓትርያርክ - አከባበር የመንፈሳዊ ውርደትና የምዝበራ መንገድ ኾኗል  ሙሉ ዘገባው የደጀ ሰላም ነው::
 በሙስና፣ ብኵንነት፣ ኑፋቄ እና ዐምባገነናዊ አሠራር የነቀዘው የአባ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና 20 ዓመት በዓለ ሢመት ዛሬ ምሽት ለሁለተኛ ጊዜ በሼራተን አዲስ ይከበራል። የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት እና ራእይ ለትውልድ /Vision for Generation/ የተባለው አካል የጥቅም ትስስር የፈጠሩበት የሼራተኑ በዓለ ሢመት ዝግጅት በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ይኹን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት አይታወቅም።

 
 
የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአብያተ እምነት መሪዎች፣ አምባሳደሮችና ታዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ እስከ 1500 እንግዶች ይታደሙበታል በተባለው ይኸው ዝግጅት ከጥቅም ትስስር ባሻገር÷ በግንቦቱ ቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ እና ውሳኔዎች ክፉኛ የተጋለጠውን የአባ ጳውሎስን ማንነት ለማደስ የታሰበበት ‹የሕዝብ ግንኙነት› ሥራ እንደኾነ ተጠቁሟል። በበዓለ ሢመቱ አከባበር የቀደሙት ፓትርያርኮች መልካም ስምና ዝና በተለያዩ ስልቶች እየተንኳሰሰ በምትኩ በሙስና፣ ኑፋቄ እና ዐምባገነናዊ አሠራር የተበሳበሰው የአባ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና የሥራ ክንውን ብቻ “በወደር የለሽነት” /በእንግሊዝኛው የበዓለ ሢመት ኅትመት ላይ እንደተገለጸው - ‘unparalleled efforts/ እንደ ግለሰብ መሞገሱ ብዙዎችን አሳዝኗል።
በበዓለ ሢመቱ ቀን “አንተ የተወገዝኽ ፓትርያርክ ነኽ፤ ሃይማኖት የለኽም!!” ሲሉ አባ ጳውሎስን በመናፍቅነት ያወገዙት ባሕታዊ÷ “ማን ነው የላከኽ?” በሚል ለሳምንት ታስረው ሲደበደቡ ከሰነበቱ አንድ ሳምንት በኋላ ተፈተዋል። በዓለ ሢመቱን በማክበር ሰበብ በሚልዮን የሚቆጠር የአብያተ ክርስቲያን ገንዘብ ወደ ግለሰቦች ኪስ ገብቷል፤ ከመንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም ብቻ ግማሽ ሚልዮን ብር ተወስዷል፤ ምእመናኑና ሙሰኛው የገዳሙ አስተዳዳሪ ከመጪው የሐምሌ 19 ክብረ በዓል ገቢ ጋራ በተያያዘ ፍጥጫ ላይ ናቸው።
በችግር ፈጣሪነታቸውና ሙሰኛነታቸው በሰበካ ጉባኤው እና ምእመናኑ የተከሰሱት የግቢ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ ጉዳይ በቋሚ ሲኖዶስ እንዳይታይ የተከላከሉት አባ ጳውሎስ÷ የአድባራትንና ገዳማትን አለቆችን፣ ጸሐፊዎችንና ቁጥጥሮችን መቀያየርን እንደ ኢንቨስትመንት እንደሚመለከቱት ተነግሯል። ከባሕር ማዶ እየመጡ የአድባራትና ገዳማት እልቅና ከሚሾሙ መነኰሳት ነን ባይ ‹ቆሞሳት› እስከ ብር 200,000 እና ከዚያም በላይ የሚቀበሉት አባ ጳውሎስ÷ ለቤተ መዘክርና የሁለ ገብ ሕንፃ አገልግሎት ዕብነ መሠረት ለማስቀመጥ ሳይቀር እስከ ብር 100,000፣ በግለሰቦች ጸሎተ ፍትሐት ላይ ለመገኘት እስከ ብር 80,000 እንደሚከፈላቸው ተጠቁሟል። ኦዲት የማያውቃቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ የልማት ተቋማት የአባ ጳውሎስ ሙሰኛ አስተዳደር መናኸርያዎች መሆናቸው ሲነገር ለፓትርያርኩ የግል የሕክምና ክትትል የሚውለው ሳምንታዊ የጤና መጠበቂያ ወጪ እስከ ብር 60,000 ደርሷል።

በተያያዘ ዜና የሐምሌው ልዩ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አባ ጳውሎስ ማደርያቸውን ቆልፈው “አልሰበስብም” በማለት ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ጥሪ የእምቢታ መልስ በመስጠታቸው ሳይካሄድ ቀርቷል፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ “የቤተ ክርስቲያን አምላክ ይፍረድ!!” በማለት ሐዘናቸውን ገልጸው ወደ የሀ/ስብከታቸው ተመልሰዋል። የሐምሌውን ጉባኤ መሰረዝ ብቻ ሳሆን የግንቦቱ ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት አባቶች ጋራ ስለሚደረገው የዕርቀ ሰላም ንግግር ውሳኔ ያሳለፈበት ቃለ ጉባኤ መጥፋቱ ተገልጧል፤ በበዓለ ሢመታቸው ቀን “የምንተጋገዝ፣ የምንተማመን፣ ይቅር የምንባባል እንኹን” በማለት የተናገሩት አባ ጳውሎስ÷ ቃለ ጉባኤውን ኾነ ብለው በመሰወር እና ለዕርቀ ሰላም ንግግሩ መቀጠል ጽኑ አቋም የያዙትን አባቶች በመገዳደር ግብዝነታቸውን አሳይተዋል፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ወደ የሀ/ስብከታቸው ከመመለሳቸው በፊት ቋሚ ሲኖዶሱ ጉዳዩን በቅርበት እንዲከታተለው አደራ ሰጥተዋል።
ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ
ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን፡፡

No comments: