Tuesday, July 31, 2012

በዝቋላ ገዳም የወተት ላም እርባታ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ ነው፡፡

ለዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የወተት ላም እርባታ ፕሮጀክት ለመተግበር ስምምነት ላይ መደረሱ ተገለጸ፡፡

በገዳሙ በቅርቡ ከፍተኛ የደን ቃጠሎ ተከስቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ገዳሙን ለመርዳት በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የሚገኙ ምእመናን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን ምእመናንን በማስተባበር ከ600,000.00 ብር /ስድስት መቶ ሺህ ብር/ በላይ ለማሰባሰብ መቻሉን የማኅበሩ ዋና ጸሓፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል አስተባባሪነት በአሜሪካ የሚገኙ የማኅበረ በዓለወልድ እና የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ያሰባሰቡት መሆኑ ታውቋል፡፡

የተገኘውን እርደታ ወደ ተግባር ለመለወጥ በታቀደው መሠረት “ለገዳሙ ቋሚ ፕሮጀክት እንደሚያስፈልገው ስለታመነበት ቦታው ድረስ ባሙያዎች በመላክ የዳሰሳ ጥት የተደረገ ሲሆን ከገዳሙ ሓላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱም ለገዳሙ ትልቅ ጥቅም የሚሰጠው የትራክተር ግዢ ቢሆንም ለጊዜው የተሰበሰበው ገንዘብ ይህንን ለማስፈጸም የማይበቃ በመሆኑ ከዚህ በፊት ተጀምሮ የነበረው የወተት ላም እርባታ ፕሮጀክት እንዲተገበር ስምምነት ላይ ተደርሷል” በማለት የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡ በስምምነቱ መሠረት የማኅበሩ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ፕሮጀክቱን እንደሚያስፈጽም ተናግረዋል፡፡

የገዳሙ ደን በተቃጠለበት ወቅት የቀለብ እጥረት በመከሰቱ ማኅበሩ ምእመናንን በማስተባበር 50 ኩንታል ስንዴ 20 ኩንታል ጤፍ፣ 40 ሺህ ብር የሚገመት መጠጥ ውኃ፣ በሶ፣ ስኳር፣ ዳቦ ድጋፍ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ የተወሰደ ዘገባ ነው::

No comments: