Thursday, August 16, 2012

ሕገ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ ምርጫ ምን ይላል???

ምዕራፍ አራት
የኢትዮጵያ ፓትርያርክ
 
አንቀጽ 13
  • ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ ምርጫ
1.    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ ቀኖና በሚፈቅደው መሠረት ተመርጦ ይሾማል፡፡
2.    ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ በሚወስነው ቁጥር መሠረት አስመራጭ ኮሚቴ ይቋቋማል፣
3.    ለፓትርያርክነት የሚመረጡት ዕጩዎች ከሊቃነ ጳጳሳት ከጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳት መካከል ሲሆን ብዛታቸው ከሦስት ያላነሡ ከአምስት ያልበለጡ ይሆናል፡፡
4.    አስመራጭ ኮሚቴው እጩዎችን ጠቁሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀርባል፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ምርጫው እንዲካሔድ ይደረጋል፡፡
5.    መራጮች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ የየመምሪያና ድርጅት ሓላፊዎች፣ የጥንታውያን ገዳማት አበምኔቶች የአድባራት አስትዳዳሪዎች ከየሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያት በዕድሜ ከሠላሳ ዓመት ያላነሱ የካህናትና የምእመናን ተወካዮች እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ22 አስከ 30 ዓመት የሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ሲሆኑ በጠቅላላው በሰበካ ጉባኤው የሚወከሉት ከአንድ ሀገረ ስብከት አሥራ ሁለት ሆነው በሥጋወደሙ የተወሰኑ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የጸኑ መሆን አለባቸው፡፡

6.    የምርጫው አፈጻጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ይሆናል፡፡
7.    የተመረጠው ፓትርያርክ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትንና ቀኖናዋን ሊጠብቅና አድልዎ በሌለው መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊያስተዳድር ቃለ መሐላ ይፈጽማል፡፡
8.    ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ ያወጣል፡፡
 
አንቀጽ 14
  • የፓትርያርኩ የማዕረግ ስምና መንበር
1.    ፓትርያርኩ ከተሾመበት ቀን ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እገሌ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ይባላል፣ ስሙም በመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጸሎት ይጠራል፡፡
2.    ፓትርያርኩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጨ አገር ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን መንፈሳዊ አባት ነው፡፡
3.    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መንበር በአዲስ አበባ ከተማ በቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ነው፡፡
 
አንቀጽ 15
  • የፓትርያርኩ ሥልጣንና ተግባር
1.    ፓትርያርኩ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል፣ ያስጠብቃል፡፡
2.    በዚህ ሕግ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤ በሊቀ መንበርነት ይመራል፡፡
3.    ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 እና በዚሁ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 13 መሠረት ፓትርያርኩ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር ሆኖ ኤጲስ ቆጶሳትን ይሾማል፣ እንዲሁም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ሲስማማበት ለብፁዓን ጳጳሳት የሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ይሰጣል፡፡
4.    በዚህ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 15 መሠረት የተመረጡትን የሥራ ሓላፊዎች ይሾማል፤ በቀደምትነትና በታሪክ የታወቁትን የታላላቅ ገዳማት አበምኔቶችና የከፍተኛ አድባራት አስተዳዳሪዎች በየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት እየተመረጡ ሲቀርቡለት የማዕረግ ስም እየሰጠ ይሾማል፡፡
5.    ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የመንግሥትን ፈቃድ ማግኘት በሚያስፈልግበት ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰነ በተግባር ላይ ያውላል፡፡
6.    ቅዱስ ፓትርያርኩ በዓበይት ጉዳዮች ላይ ሁሉ በቅዱስ ሲኖዶስ አያስወሰነ ይሠራል፡፡
7.    በቅዱስ ሲኖዶስ የወጡ ሕጐች፣ የተላለፉ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ሁሉ በተግባር ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፡፡
8.    በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡትን ሕጐችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በፊርማው ያስተላልፋል፡፡
9.    ከመንግሥታውያንም ሆነ መንግሥታውያን ካለሆኑ መ/ቤቶች ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚቀርቡ ደብደቤዎች ወይም አቤቱታዎችን ደረጃቸውን ጠብቀው በሕግ መሠረት ይፈጸሙ ዘንድ ለጠቅላይ ጽ/ቤት ያስተላልፋል፡፡
10.    በውጭ አገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ለማገልገል ወይም የነፃ ትምህርት ለመማር የሚላኩ ካህናት በዚሁ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 11 መሠረት ተመርጠው ሲቀርቡ እንዲላኩ ያደርጋል፡፡
11.    ከውጭ የሚመጡትን እንግዶች በውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቅራቢነት እየተቀበለ ያነጋግራል፡፡
12.    ፓትርያርኩ በውጭ አገር በሚደረግ በማናቸውም ስብሰባ ላይ ለመገኘትና ጉብኝት ለማካሔድ በሚያስፈልግ ጊዜ ስለተልዕኮው ጉዳይ አስቀድሞ በቅዱስ ሲኖዶስና በቋሚ ሲኖዶስ ያስወስናል፡፡
 
አንቀጽ 16
  • የፓትርያርኩ ከማዕረግ መውረድ
1.    ፓትርያርኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከተሾመ በኋላ የተቀበለውን ሓላፊነት በመዘንጋት፡-
ሀ. የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን የሚያፋልስ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚያሰነቅፍ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ፣
ለ. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ከቁጥር 172 እስከ 208 በተደነገገው መሠረት በደለኛ መሆኑ ከታመነበት፣
ሐ. በቃሉ የማይገኝና በዚህ ሕግ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 7 ድንጋጌ መሠረት በተሾመበት ቀን የፈጸመውን ቃለ መሐላ ያልጠበቀ በአጠቃላይ ታማኝነቱና መንፈሳዊ አባትነቱ በካህናትና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነትን ያጣ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያስነቅፍ መሆኑ በትክክል ከተረጋገጠ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከሥልጣኑ ይወርዳል፤ በምትኩም ሌላ ፓትርያርክ ተመርጦ ይሾማል፡፡
2.    ከዚህ በላይ በተደነገገው መሠረት ከሥልጣኑ የተገለለ ፓትርያርክ በቀኖና ተወስኖ በገዳም ይቀመጣል፡፡
3.    ከሥልጣን የተገለለው ፓትርያርክ በገዳም አልቀመጥም በቀኖናም አልወሰንም በማለት እምቢተኛ ከሆነ ተወግዞ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ይለያል፡፡
4.    ፓትርያርኩ መንፈሳዊ ሥራውን በማካሔድ ላይ እያለ እሥራትና ግዞት ቢደርስበት ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ትመራለች እንጂ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም፡፡
5.    ከዚህ በላይ የተዘረዘረው ሁሉ ፍትሕ መንፈሳዊ በሚያዝዘው መሠረት ይፈጸማል፡፡
 
አንቀጽ 17
  • ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ
1.    ፓትርያርኩ በሞት ሲለይ ወይም በዚህ ሕግ አንቀጽ 16 መሠረት ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫም ይካሔዳል፡፡
2.    የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫ አፈጻጸም እንደጊዜውና እንደሥራው ሁኔታ እየታየ ከ40 እስከ 80 ቀን ባለው ጊዜ ይሆናል፡፡
3.    የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ተግባር
ሀ. ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ጊዜያዊ ጉደዮችን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር እየመከረ ያከናውናል፡፡
ለ. በፓትርያርኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ሆኖ ምርጫውን ያስፈጽማል፤ እርሱ ግን ከምርጫው አይገባም፡፡

ምንጭ፦ ሕገ ቤተ ክርስቲያን 1991 ዓ.ም

2 comments:

Anonymous said...

This is time to practice the regulation of our church. It will be elect the head of our church in the law of church with out the influence of Gov.otherwise we will be ready to pay anything to save our church. It is enough the past distraction. I am personaly too happy to read this key point that provided me information how to elect head of EOTC. God bless all EOTC children particularely Mahiberkidussan leader and preachers. Please work for unity and recancelation this time for us.

Anonymous said...

Good to know the process and my responsibility as a "Memen"!