Monday, August 20, 2012

ቀጣዩን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ አስመልክቶ ምን ይደረግ?

ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ስርዓተ ቀብር በኃላ ምን ይደረግ?  
ድምጽ ከመስጠት በፊት ሊገናዘቡ የሚገባቸው ነጥቦች
1. የፓትሪያሪክ ምርጫን አስመልክቶ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 13፡5 ላይ እንደተጠቀሰው በፓትርያርክ ምርጫ ላይ የሚሳተፉት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ የየመምሪያና ድርጅት ሓላፊዎች፣ የጥንታውያን ገዳማት አበምኔቶች የአድባራት አስተዳዳሪዎች ከየሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያት በዕድሜ ከሠላሳ ዓመት ያላነሱ የካህናትና የምእመናን ተወካዮች እንዲሁም ዕድሜያቸው 22 አስከ 30 ዓመት የሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ሲሆኑ በጠቅላላው በሰበካ ጉባኤው የሚወከሉት ከአንድ ሀገረ ስብከት አሥራ ሁለት ሆነው በሥጋ ወደሙ የተወሰኑ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የጸኑ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ ከዚህ በፊቱ እንደተደረገው ፓትሪያሪክ የሚሆነውን ለመወሰን የመጨረሻ ወሳኝ አካላት እነዚህ ከሆኑ ቤተክርስቲያን ላለፉት 20 ዓመታት ካየችው መከራ የከፋ እንደማይገጥማት እርግጠኛ መሆን አይቻልም የሚሉ ወገኖች መኖራቸው፡፡

2. ምንም እንኳን በምርጫ የሚሳተፉ የተዘረዘረ ቢሆንም የአመራረጥ ሥርዓቱን አስመልክቶ ሕገ ቤተ ክርስቲያን የምርጫው አፈጻጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ይሆናል ስለሚል ለእጩነት ከሚቀርቡት ሊቃነ ጳጳሳት 3 ወይም 5 ሊቃነ ጳጳሳት የመምረጥ (ነቀፋ እንደሌለባቸው የማጥራት) ድርሻ ከላይ የተጠቀሱት መሆን ያለበት ሲሆን ከ 3 ወይም 5 ሊቃነ ጳጳሳት የመምረጥ ድርሻ ግን የመንፈስ ቅዱስ ድርሻ መሆን አለበት የሚሉ ወገኖች መኖራቸው፡፡ ፓትሪያሪክን ለመምረጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትውፊትን መሠረት አድርጎ በዕጣ ከመሆን ይልቅ በድምጽ ብልጫ መሆኑ የእግዚአብሔር ፈቃድ የራቀው የሰው ሃሳብ የቀረበው ይሆናል ፤ አጽራረ ቤተክርስቲያንም ሆኑ መንግስትም እጁ እንዲኖርበት መንገድ ይከፍታል የሚል ስጋት አለ፡፡

3. ሐዋርያት የይሁዳን ምትክ ቶማስን የመረጡት በዕጣ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል፡፡ “ዕጣም ተጣጣሉላቸው፥ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ” የሐዋርያት ሥራ 1: 26:: በሐዋርያት መንበር የሚቀመጡ ፓትሪያሪኮችም ከዚህ የተለየ አመራረጥ ሊኖራቸው አይገባም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ ነው የሚመራው እንድንል፣ መንፈስ ቅዱስ የመረጠው ሊቀመጥበት ይገባልና፡፡ ለዚህም የእህት አቢያተ ክርስቲያናትን ተሞክሮ መውሰድ በቅርቡ በግብጽ የሆነውን መመልከት ይገባናል፡፡ በተለይም ጾም እና ጸሎት ታውጆ ሱባኤ ተይዞ ሊሆን ይገባል፡፡ ዕጣውም ከማጭበርበር እንዲርቅ በግልጽ በዐውደ ምሕረት የተጠቀለለ እና ነፍስ በማያውቅ ሕጻን የሚወጣ ሊሆን ይገባዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡

4. ላለፉት ሃያ ዓመታት ቤተ ክርስቲያን ሁለት ፓትሪያሪክ እየተባለ ለሁለት ተከፍላ ፤ በመወጋገዝ እና ሁለት የተለያየ ሹመት በማድረግ ምዕመናን ሲያዝኑ ቆይተዋል፡፡ የተፈጠረውን ችግር ሁለቱም ወገን የየራሳቸው ትክክለኛነትን የሚያጎላ ምክንያት የሚያቀርቡ እንጂ መስዋዕት በመሆን መፍትሔ የሚያመጡ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ለዚህ መፍትሔ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ ቀርባላች እና የወደፊቱን አቅጣጫ ማስተካከል የሚገባበት ወቅት አሁን መሆን አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ለዚህም ችግሩን ለመፍታት ዋነኛ ችግር የነበረው ከሁለቱ ፓትሪያሪክ ማን ይመራል የሚለው ነበር፡፡ ስለዚህ ይህንን ዘርፈ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ችግር መፍትሔ ለመስጠት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስን ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ማቅረብ አሊያም ወደ እግዚአብሔር ተጠርተው እስኪሔዱ ድረስ ሌላ ፓትሪያሪክ አለመሾም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
 ዐውደ ምሕረት የተዋሕዶያውያን የመረጃ መረብን ይጎብኙ::
 ድምጽ ለመስጠት እዚህ ላይ ይጫኑ::

1 comment:

Anonymous said...

ያለፉት 20 አመታት የልማት እንጂ የጥፋት አልነበሩም ዝም ብላችሁ አታውሩና አትፃፉ እባካችሁ አስተውሉ
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ሰ/ት/ቤት ተማሪውና አገልጋይ ከመቀለ