Tuesday, September 4, 2012

ቅዱስ ሲኖዶስ ሱባኤ አወጀ

  • ሱባኤው 
    ከጳጉሜን 1/ 2004 - 
    መስከረም 10/ 
    2005 ዓ.ም ድረስ ነው።
  • ቅ/ሲኖዶሱ የአስታራቂ ኮሚቴውን ሪፖርት አዳምጧል::
  • ሦስት የአስታራቂ ኮሚቴው አባላት አዲስ አበባ ናቸው::
  • ቅ/ሲኖዶሱ አካሄዱን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ቡድኖችን እንደማይታገሥ አስታውቋል::
ሙሉ ዘገባው የደጀሰላም ብሎግ ነው::
 READTHIS NEWS IN PDF
  ቅዱስ ሲኖዶስ መጪው ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን ሰላሟንና አንድነቷን የምታረጋግጥበት፣ ዐበይት ተቋማዊ ችግሮቿን በመፍታት ለአገራችንና ለመላው ዓለም ሐዋርያዊ አገልግሎቷን የምታጠናክርበት ይኾን ዘንድ ካህናትና ምእመናን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር የሚያመለክቱበትና ከጳጉሜን 1/2004 - መስከረም 10/2005 ዓ.ም የሚቆይ የሱባኤ ጊዜ ማወጁ ታወቀ፡፡ የሱባኤ ጊዜ እንዲታወጅ የተወሰነው ቅዱስ ሲኖዶሱ ትናንት፣ ነሐሴ 28 ቀን 2004 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ሲሆን ዛሬ ማክሰኞ ባደረገው ስብሰባም ቀናቱን ይፋ አድርጓል። (ዝርዝሩን እንደደረሰልን ለማቅረብ እንሞክራለን።) ሱባኤውን የተመለከተ መግለጫ በተከታዮቹ ቀናት በቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊው በኩል እንደሚሰጥም ተመልክቶ ነበር፡፡ በመንፈሳዊው ትውፊታችን እንደቆየን ወደ አዲሱ ዘመን የምንሸጋገርባትና እንደ 13ኛ ወር የምትቆጠረው ጳጉሜን በበርካታ ክርስቲያኖች ዘንድ የፈቃድ ጾም የሚያዝባት ወቅት እንደኾነች ይታወቃል፡፡


በሌላ በኩል በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥርዐተ ቀብር ላይ ለመገኘት በመዲናዪቱ አዲስ አበባ የተሰበሰቡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በትናንቱ የሲኖዶስ ጉባኤያቸው÷ የቤተ ክርስቲያናችንን ወቅታዊ ኹኔታ በማዘከር መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷን በብቃት ለመወጣት ማነቆ የኾኑባት ውስጣዊ ችግሮቿ በጥልቀት ተፈትሸው ከመሠረቱ ለመፍታት የሚያስችሉ ጥናቶችና ሌሎች ሰነዶች ዝግጅት እንዲደረግ መስማማቱ ተዘግቧል፡፡ ለጥናቶቹ ዝግጅት በሚያግዙ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ ቀርጾ ለጉባኤው የሚያቀርብ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበት ኮሚቴ መቋቋሙም ተነግሯል፡፡
ጠቅላይ ቤተ ክህነቱና በተዋረድ የሚገኙ መዋቅሮች መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚመራባቸው፤ የሰው ኀይል፣ የፋይናንስና ንብረት ሀብቶቿ የሚጠበቁበትና የሚተዳደሩበት፤ ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ጋራ የተጣጣሙ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎች፣ ደንቦችና ዝርዝር አሠራሮች እንደሚመነጩበት የሚጠበቀው ይኸው የጥናት ዝግጅት መጪው የፓትርያርክ ምርጫ የሚፈጸምበትን ደልዳላ መሠረት እንደሚያበጅም ተስፋ ተደርጓል፡፡
የመጪውን የፓትርያርክ ምርጫ የሚመለከቱ በርካታ ጽሑፎች በተለያዩ የብዙኀን መገናኛዎች በመውጣት ላይ እንደሚገኙ የጠቆመው ምንጩ÷ ቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት ሰጥቶ ከሚወያይባቸው የዕርቀ ሰላምና ዘመን ለተሻገረው የቤተ ክህነቱ አሠራር የሚያስፈልጉት የተቋማዊ ለውጥ አጀንዳዎች አኳያ ሚዲያዊ ሥራዎች መሠረታዊ መዋቅራዊ ችግሮቻችንን ከነባራዊ ኹኔታዎች ተመርኩዘው በሚተነትኑ፣ በችግሮቻችን ዐይነትና ስበት ላይ የጋራ መግባባት (ግንዛቤ) በሚፈጥሩ፣ ለተግባራዊ ለውጥም በሚያነሣሱ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩሩ ተመራጭ እንደሚኾን አሳስቧል፡፡
የዋናው ፓትርያርክ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩን የሚያግዙና ቋሚ ሲኖዶሱን የሚያጠናክሩ ስምንት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በምልዓተ ጉባኤው ፈቃድ የመረጠው ቅዱስ ሲኖዶስ÷ በቀደሙት ጉባኤዎቹ ተወስነው የአፈጻጸም የተጓተቱ ውሳኔዎች እንዲፈጸሙ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር ከመሠረቱ በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ በተረጋጋ ኹኔታ በመምከር ለመፍትሔው በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ይህን እንቅስቃሴውን በረብ የለሽ ክሦችና ስም ማጥፋቶች በተጽዕኖ ውስጥ ለማስገባትና ለማሰናከል እየሞክሩ ያሉ ቡድኖችን እንደማይታገሥ መወያየቱም ተሰምቷል፡፡ የግለሰቦቹ ማንነት በሚገባ የሚታወቅ በመኾኑም በሚመለከተው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አካል በሕግ አግባብ ርምጃ የሚወሰድበት መመሪያ እንደሚተላለፍም ተነግሯል፡፡
ቀደም ሲል በተለያዩ ጥቅሞች ዙሪያ ተሰልፈው የግል ፍላጎታቸውን ሲያሳድዱ የቆዩት እኒህ ቡድኖች÷ የቡድንና የግል ጥቅሞቻቸውን አስጠብቀው ለመኖር፣ ቀደም ሲል በፈጸሟቸው የሙስና፣ ብኵንነትና ሌሎች ወንጀል ነክ ተግባራት ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን ያገለግለናል ያሏቸውን ክሦችና አሉባልታዎች ለመንግሥት አካል እስከማቅረብ መድረሳቸውም ተነግሯል፡፡ እንደ መንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ጥቆማ አሉባልታዎቹ ያተኰሩት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩን ለማገዝና ቋሚ ሲኖዶሱን ለማጠናከር በተመረጡት ብፁዓን አባቶች ላይ ነው፤ በቡድን ከሚንቀሳቀሱት ግለሰቦችን ስም ለጊዜው ከማውጣት ተቆጥበናል፡፡
በተያያዘ ዜና ቅዱስ ሲኖዶስ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዐተ ቀብር ላይ ለመገኘትና የዕርቀ ሰላም ንግግሩ በሚቀጥልበት ኹኔታ ላይ ለመወያየት ወደ አገር ቤት የመጣውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና ዕርቅ ጉባኤ ልኡክ ሪፖርትና መግለጫ ማዳመጡ ተዘግቧል፡፡ በይቀጥላል ልኡኩ ባቀረበው ሪፖርት ላይ የሚደረገው ውይይት፣ ቅ/ሲኖዶሱ በሰላምና ዕርቅ ጉባኤው ለቀረቡት ሰባት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት፣ የተከታይ ዕርቀ ሰላም ንግግር የሚካሄድበትን ቦታና ቀን በመወሰን ተወካዮቹን የሚመርጥበትን ስብሰባ በቅርቡ እንደሚያካሂድ እየተጠበቀ ነው፤ እስከ አሁን የዘገየውም በቤተ ክርስቲያንና በሀገር ደረጃ የደረሰው ተደራራቢ ሐዘን መኾኑም ተነግሯል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስን በመወከል በቀጣዩ የዕርቀ ሰላም ንግግር የሚሳተፉት ልኡካን ለመድረኩ (ለጉዳዩ) የሚመጥኑ ይኾኑ ዘንድ ጥንቃቄ እንደሚያሻ፣ በሁሉም ወገኖች በኩል የንግግሩን ሂደት የሚረዱና የሚያቀላጥፉ የቴክኒካል ወይም የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የባለሞያዎች ቡድን አብሮ መሠየም እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል፡፡ ከሰላምና ዕርቅ ጉባኤው አባላት መካከል በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የሚገኙት ቀሲስ ዶ/ር አማረ ካሳዬ፣ ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ እና ዲ/ን አንዱዓለም ዳግማዊ ናቸው፡፡

ዝርዝሩን እንደደረሰልን ለማቅረብ እንሞክራለን።

ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን ሰላምና አንድነት ይጠብቅልን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

No comments: