Wednesday, October 10, 2012

ሰባት ጥንታዊ የዋሻ ቤተ መቅደሶች በቆጠር ገድራ ተገኙ

Kotere 03(ማኅበረ ቅዱሳን):- በጉራጌ ሀገረ ስብከት ቆጠር ገድራ በተሰኘ ስፍራ ጥንታዊ የዋሻ ቤተ መቅደስ እንደተገኘና የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን እንደተተከለ ሰማን፡፡ ቦታው ድረስ ለመሄድ ወስነን የሚመለከታቸው የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎችን ለማግኘት ጥረት አደረግን፡፡ ተሳካልን፡፡ ከአዲስ አበባ ወልቂጤ ያደረግነው ጉዞ የተሳካ ነበር፡፡

ጉዞ ወደ ቆጠር ገድራ መካነ ቅዱሳን ኪዳነ ምሕረት ገዳም

ወደ ቆጠር ገድራ የተጓዝነው መስከረም 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ ወቅቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በተለይም በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ የሆነው የመስቀል በዓል ሲሆን ዋዜማ በመሆኑ ተወላጁ ከተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከአዲስ አበባ እና በሚያስገርም ሁኔታ እየጎረፈ ነው፡፡ “መንገዶች ሁሉ ወደ ጉራጌ አገር ያደርሳሉ” የሚል አስኝቶታል፡፡ የግልና የሕዝብ ማመላላሻ አውቶቡሶች መንገዱ ጠቧቸዋል፡፡ በተለይም ወልቂጤን ይዞ ሌሎችም የገጠር ከተሞች ለየት ባለ የትራፊክ መጨናነቅ ላይ ናቸው፡፡