Tuesday, December 25, 2012

የ6ኛ ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴው “የተመረጠ” ሳይሆን “የተሰየመ” ነው

  ሙሉ ዘገባው የደጀ ሰላም ነው::
6ኛውን ፓትርያርክ ለማስመረጥ ተቋቁሟል የተባለው አስመራጭ ኮሚቴ በጥቆማ ስም ዝርዝራቸው የተበተነ እንጂ ብዙዎቹ ይስማሙበት ወይም አይስማሙበት እንዳልተጠየቁ ምንጮቻችን ገልጸዋልይህንን ተከትሎ ማኅበረ ቅዱሳን ምርጫው እንዲካሄድ በሾርኔ እንደተስማማ ተደርጎ በድረ ገጾች መዘገቡ አጀንዳው ከምርጫው ወደ ማኅበሩ እንዲዞር ለሚሹ ጥሩ አጋጣሚ ከመፍጠሩም በላይ ማኅበሩ ከቅ/ሲኖዶሱ ጋር ያለውን መልካም የሥራ ግንኙነት ለማጠልሸት ለሚፈልጉ ሰዎች አስደሳች አጋጣሚ እንደፈጠረ እየተነገረ ነው።

ዝርዝሩ እንደሚያመለክተው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስና ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እንዲሁም ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያ ኃላፊዎች መካከል ደግሞ የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ እና የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊው መጋቤ ምስጢር ዓምደ ብርሃን ስማቸው ተጠቅሷል። ታላላቅ ገዳማት እና አድባራትን እንዲወክሉ የተደረጉት ፀባቴ አባ ኀይለ መስቀል ውቤ (የደብረ ሊባኖስ ገዳም አበምኔት) እና ንቡረ እድ አባ ዕዝራ (የአኵስም ጽዮን ንቡረ እድ) ሲሆኑ ዲያቆን ኄኖክ አሥራት - ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፤ አቶ ባያብል ሙላቴ ደግሞ ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰየሙ ናቸው። አቶ ዓለማየሁ ተስፋዬ  (ከኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት)፣ ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ እና አቶ ታቦር ገረሱ ደግሞ ምእመናንን ወክለው የተቀመጡ ናቸው፡፡
ማኅበሩን ወክለው በአስመራጭነት እንዲገቡ የተጠቆሙት አቶ ባያብል ሙላቴ በማኅበሩ እንዳልተወከሉ፣ እርሳቸውም ስለመመረጣቸው ማንም እንዳልጠየቃቸው ታውቋል። ማኅበሩ በአስመራችነት እንዲያገለግል አንድ ተወካዩን እንዲወክል ባልተጠየቀበት ሁኔታ አባሉ ስም ይፋ መሆኑ ከውጪ ለሚመለከቱ ሰዎች የተለየ አንድምታ መስጠቱ እየታየ ነው። ማኅበሩ ‘ጥቆማውን ለመቀበልም ላለመቀበልም አስቸጋሪና አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ ምንጮች ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ማኅበሩም ሆነ በኪሚቴው ውስጥ የገቡት ግለሰቡ ባላወቁበት ሁኔታ ለተደረገው ነገር ማኅበሩን ተጠያቂ ማድረግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች እየተናገሩ ነው።    
ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ የኮሚቴው አባላት መካከል ብፁዕ አቡነ ቄርሎስና አቡነ እስጢፋኖስ በምርጫው አለመስማማታቸውን ተከትሎ ኮሚቴው ተሰይሞ ይፋ ከመደረጉ ውጪ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር የሚያስችለው ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ ምንጮቻችን አብራርተዋል።
ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን።

No comments: