Wednesday, December 3, 2014

ኢትዮጵያዊቷ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ንጽሕናንን የሚያጎድፍ የሐሰት መረጃ የያዘ ጥናታዊ ጽሑፍ ይፋ ሆነ

ወለተ ጴፕሮስ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የነበረች ከቅዱሳን አንስት ኢትዮጵያውያን መካከል የምትታወቅ ቅድስት ናት። እናታችን ወለተ ጴጥሮስ በተዋሕዶ ሃይማኖት ጸንታ በቅድስና እና በንጽሕና የኖረች፣ ከዚህ ዓለም ገዢ የጥንት ጠላታችንን ዲያቢሎስን ተጋድላ አሸንፋ የኖረች ቅድስት እናት ናት። የዚህ ዜና ዓላማ የቅድስ እናታችን ቅድስናንን ለመዘገብ ሳይሆን፤ ስሟን የሚያጎድፍ መረጃ በእጃችን ስለገባ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ለዚህ ምላሽ እንዲሰጡበት በማሰብ የደረሰንን መረጃ በዚህ ሚዲያ ላይ ይፋ ለማድረግ ተገደድን።

የቅድስት እናታችን ወለተ ጴጥሮስ ገድል ከእውነታው በተቃራኒ ሁኔታ በመተንተን ጥናታዊ ጽሑፍ ዛሬ Dec 2, 2014 (Rutgers State University of New Jersey) በኒው ጀርሲ ግዛት ውስጥ ኒው ብሩዊስክ ከተማ ላይ ፕርፌሰር ዊንዲ ቤልቸር(Wendy Belcher ) ይፋ አድርጋለች። ይህ የእናታችንን የወለተ ጴጥሮስ ንጽሕናን የሚያጎድፍ ጥናታዊ ጽሑፍ በሚቀጥለው የአውሮፓውያን  ዓመት ማለትም በ2015 በዓለም ታዋቂው ዪኒቨርስቲ በፕሪስተን ይታተማል ተብሎ ይጠበቃል።

Thursday, October 16, 2014

"ማኅበሩ አሳዘነኝ ! በላዉ የምር አንጃቴን በላው" ከመምህር ዘመድኩን በቀለ ፌስ ቡክ የተገኘ

ማኅበሩ አሳዘነኝ ! በላዉ የምር አንጃቴን በላው ።
ከዛሬ 2 ዓመት በፊት ዕድሌ ይሁን ወይም ክፉ አመሌ አይታወቅም በሆነ ጉዳይ አንድ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ቁጭ ብያለሁ ። ከእኔ ጋር ደግሞ እድሏ ሆኖ ማረሚያ ቤት ብቻ ከእኔ ጋር መግባት ሲቀርባት ሌላው ጋር ግን በየጊዜው በየቦታው የምትንከራተተው ውዷ ባለቤቴም አብራኝ ነበረች ። የዚያን ዕለት ድርጊት መቸም ቢሆን አልረሳውም ። አንዱ ጥጋበኛ ባለጊዜ ሙሉ ለሙሉ የሚያምረውን የሚሊቴሪ ልብሱን ግጥም አድርጐ ለብሶ በማያውቀው እና በማያገባው ጉዳይ ለእኔ ክብርት በሆነችው በልጆቼ እናት በውዷ ባለቤቴ ፊት በአደባባይ ሕዝብ እያየው ጠፍጥፎ ጠፍጥፎ ወግሮ ወግሮ ይለቀኛል ። በወቅቱ ቦታው ላይ ደንብ አስከባሪዎች ነበሩ ። ህዝቡም ነበረ ። የከተማዋ ማለትም የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትም ነበሩ ። ከባለቤቴ የድረሱለት ጩኸት በቀር ሁሉም ደፍረዉ ከወጋሪዬ እጅ ሊያስጥሉኝ አልፈቀዱም ። ተስፋ ስቆርጥ የሚገላግለኝም ሳጣ ፣ ደግሞስ ባለቤቴም ሆነች በዙሪያዬ ከብቦ በመቆም ትርኢቱን የሚመለከተው ህዝብ ,,,,,,,, ውይ ሲያሳዝን እንዲሁ አንዳች ሳይመልስ ተቀጥቅጦ እኮ ሞተ ብለው የቡና መጠጫ ሳያደደርጉኝ በፊት እርምጃ ወሰድኩኝ ።,,,,,,,,,, እንደው ወጋሪዬ ሳያስበው ድንገት ዝልል ብዬ አባቱን እንደናፈቀ ህጻን እጆቼን አንገቱ ላይ ጠምጥሜ እግሮቼን ደግሞ በወገቡ ላይ አቆላልፌ ጥርሴን ደግሞ በአንገቱ ደምስር ላይ ሰክቼ እንደማስቲሽ ደግሞም እንደመዥገር ከላዩላይ በመጣበቅ ከላዩላይ ልክክ አልኩበት። ሊያወርደኝ ወደላይ ሲል እኔም አቡሬው ወደላይ ወደታች ወደጎን ወደፈለገበት ሲገላበጥ እኔም ግጥም አድርጌ በመያዝና በእጁ ሊመታኝ ሲሞክር ደግሞ በጥርሴ የያዝኩትን የወጋሪዬን ደምስር ጠበቅ በማድረግ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ቢያደርግ ስሩን በጥሼ ከእኔ በፊት የሞትን ፅዋ እንደሚጎነጭ በተዘዋዋሪ መንገድ በጥርሴ መልእክት እያስተላለፍኩ መጨረሻዬን መጠባበቅ ጀመርኩ ። አስቀድሞ ሁሉንም አስፈራርቶ ስለነበር ማን ይገላግለው ። በዚህ ሁኔታ እሱ አፉ ማውራት ስለለሚችል ቢለምነኝ ቢለማመጠኝ ልሰማው? አረ አላበድኩም እንዲያውም በስፖርትና ከእኔ በሚሰበሰበው ግብር ያለ ሐሳብ እየበላ ያፈረጠመው ሰውነቱ ተመቸኝ መሰል ልጥፍ ብዬበት ቀረሁ ። ቆይቶ ፖሊሶቹ ይሁኑ ህዝቡ አላውቅም ብቻ ፌደራል ፖሊሶች ተደውሎላቸው በመኪና መጡ ።

Thursday, April 24, 2014

የብፁዕ አቡነ ዳንኤል የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ተቃውሞ በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ላይየሚከተለውን አስተያየየት መሐሪ Mulugeta Maranatha ከተባሉ ግለሰብ ፌስ ቡክ(facebook) ገጽ ያገኘነው ነው።
+++
ሰሞኑን እንዲያውም በቅርቡ የቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዳንኤል በደብረ ሰላም መድኃኒዓለም ቤ/ክ
ውስጥ ከሚገኙ ከተወሰኑ ምእመናን ጋር እና ከተወገዙት ካሕናት መካከል ከመሪጌታ ቀሲስ ጌታሁን ጋር በአደረጉት የስልክ ንግግር ላይ
የተናገሯቸው ብዙ ስህተቶች እርሳቸውንም ሆነ የቆሙለትን "ሥርዓተ ቤተክርስቲያን" ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። ሲጀመር ከእነዚህ ሰዎች
ጋር ከመነጋገራቸው በፊት በመዓረግም ሆነ በሥልጣን ከሚቀርቧቸው አባት ከብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ጋር መጀመሪያ ቢነጋገሩ መልካም ነበር ያንን ግን የአደረጉ አይመስልም።

+ ሌላው ከስልክ ንግግራቸው እንደተረዳነው የብፁዕ አቡነ ዘካርያስን ርምጃ በተመለከተ ወደፊት ርሳቸው ከብፁዕነታቸው ጋር ተነጋግረው ሊፈቱት እንደሚችሉ
መናገራቸው መልካም ቢሆንም ርምጃው ግን ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን አንፃር ትክክል እንዳይደለ መናገራቸው በዛ በኩል "ስለ እኔ ጠይቃችው" ብሎ ለሌላ
ሰው ሹክ ያሉትን መሪጌታ ጌታሁንን እና ጥቂት ግለሰቦችን ብቻ ለማስደሰት እንደሆነ የሚያስረዳ ነው።

+ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ሀገረ ስብከታቸው ሌላ ቦታ፤ እረኝነታቸው ለሌላ ሥፍራ ሆኖ ሳለ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ በአሉት አብያተ
ክርስቲያናት የሚወስዱትን ርምጃ መከላከልም ሆነ ትክክል እንዳልሆነ መናገራቸው ተገቢ አልነበርም።

+ በመጨረሻም ብፁዕ አባታችን ጥቂት ሰዎችን ለማስደሰት ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን መሻርና መጣስ የሚያስከትለው ችግርና መዘዝ ብዙ እንደሆነ እያወቁ፤
ስለ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን መከበር ግድ ከሌላቸው ሰዎች ጋር የሚነጋገሯቸውን ንግግሮች መጀመሪያ በሚገባ ቢያጤኗቸውና ከሚመለከታቸው አባቶች ጋር መክረውና ተመካክረው ቢያወሯቸው መልካም ነው ብዬ አስባለሁ።

+ ለመሪጌታ ቀ/ ጌታሁን፦ ውግዘቱ የመጣቦ ከብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ነበር። መፍትሔ ማግኘትም የሚችሉት ከርሳቸው ዘንድ ሆኖ ሳለ
በሌላ አቅጣጫ ሌላ ሰውን ሄዶ ፍረድልኝ ማለት እርሶን ሚዛን ላይ የሚጥል በእውነትም ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የወሰዱት ርምጃ ትናንትናም ሆነ ዛሬ አማናዊ የነበረና፤
ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን አስረግጦ ያለፈ ትዝብት ላይ የጣሎት አጋጣሚ ነበር የስልኩ ውስጥ ንግግሮት።

ነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን። አሁንም ሆነ ወደፊት የጥቂት ፓለቲከኞች ፈቃድ ሳይሆን፤ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ለማስከበር የሚደርስብንን
ፈተና ለመቀበል ዝግጁዎች ነን።

Wednesday, April 23, 2014

በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ሥልጣነ ክህነት የተያዘባቸው መልአከ ኃይል ጌታሁን መኮነን በቀድሞ አቋማቸው

የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ መልአከ ኃይል ጌታሁን መኮነን ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ በተገኙበት ውይይት ላይ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲመጣ ያስተላፉት መልዕክት ነበረ። መልአከ ኃይል ጌታሁን መኮነን በአሁን አቋማቸው የሚኒያፖሊስ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን "በገለልተኝነት አሥተዳደር ይቀጥል" ከሚሉ ወገኖች በመሰለፋቸው ብፁዕነታቸው ሥልጣነ ክህነትታቸውን አግደውባቸዋል።

Tuesday, April 22, 2014

ብፁዕ አቡነ ዘካሪያስ የአራት ካህናት ሥልጣነ ክህነት አገዱ

በሰሜን አሜሪካን በሚኒያፖሊስ ከተማ በሚኒሶታ ግዛት የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውዝግብ ከአንድ ዓመት በላይ ፈጅቶ በዘንድሮው በዓለ ትንሣኤ ዕለት አባላቱ ለሁለት ተከፍለው በዓሉን በተለያየ ቦታ አክብረው ዋሉ። ይህ ውዝግብ ከመነሻው ጊዜ ጀምሮ ለአሐቲ ተዋሕዶ በቅርበት መረጃዎች ይደርሱ ነበረ። የቤተ ክርስቲያናችን የውስጥ ችግሮች ለውጭ አካላት አሳልፎ ላለመስጠት ጉዳዪን ላለመዘገብ ተቆጥበን ነበረ። የዚህ አጥቢያ ምእመናን እና ካህናት ለሁለት ተከፍለው ሲወዛገቡ ከአንድ ዓመት በላይ ፈጅቶባቸዋል። ሚኒያፖሊስ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በገለልተኛ አሥተዳደር ሥር ቆይቶዋል። ሦስት አስርተ ዓመታት ለማስቆጠር ጥቂት ዓመታትን የቀረው ይህ አጥቢያ በገለልተኛ የቦርድ አስተዳደር ሥር ቆይቶ ነበረ። 

ሆኖም ግን “የገለልተኛ አስተዳደር ይብቃን እና ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደረ መዋቅር ሥር እንቀላለቅል” የሚሉ ወገኖች አማካኝነት የዛሬ አንድ ዓመት ከሦስት ወር አካባቢ ለአስተዳደር ቦርድ ጥያቄ ቀርቦ ነበረ። በዚህም ምክንያት የአስተዳደር ቦርድ ይህንን ጥያቄ ሁለት አመለካከት ያላቸው ማለትም “ወደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር መዋቅር እንቀላቀል” የሚል አቋም ያላቸው እና “አይ በገለልተኛ የአስተዳደረር እንቆይ” የሚል አቋም ያላቸው ሁለት ቡድኖች ለአስተዳደር ቦርዱ እና ለአባላት ጥናት እንዲቀርብ ኮሚቴ አዋቅሮ ነበረ። ከሁለቱንም ወገኖች ያካሄዱትን ጥናታዊ ጽሑፍ ለአስተዳደር ቦርዱ አቅርበው በመጨረሻም ለቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት በሙሉ በነሐሴ ወር አካባቢ ጥናቱ ቀርቦ ነበረ። ጥናታዊ ጽሑፍ በቀረበት ዕለት “በድምጽ ይወሰን አይወሰን” በማለት አባላቱ ተከራክረው በመጨረሻም ካህናቱ ምእመናን ይከፋፈሉብናል በሚል ፍራቻ “ለጊዜው እንዲሁ እንዳለን በገለልተኝነት እንቆይ” አሉ። የካህናት ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ድምጽ ሳይሰጥ በገለልተኛ አስተዳደር ለጊዜው እንዲቆዪ ተስማምተው ለጥናታዊ ጽሑፍ የታደመ አባላት ድምጽ ሳይቆጠር ተበተነ።