Tuesday, April 22, 2014

ብፁዕ አቡነ ዘካሪያስ የአራት ካህናት ሥልጣነ ክህነት አገዱ

በሰሜን አሜሪካን በሚኒያፖሊስ ከተማ በሚኒሶታ ግዛት የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውዝግብ ከአንድ ዓመት በላይ ፈጅቶ በዘንድሮው በዓለ ትንሣኤ ዕለት አባላቱ ለሁለት ተከፍለው በዓሉን በተለያየ ቦታ አክብረው ዋሉ። ይህ ውዝግብ ከመነሻው ጊዜ ጀምሮ ለአሐቲ ተዋሕዶ በቅርበት መረጃዎች ይደርሱ ነበረ። የቤተ ክርስቲያናችን የውስጥ ችግሮች ለውጭ አካላት አሳልፎ ላለመስጠት ጉዳዪን ላለመዘገብ ተቆጥበን ነበረ። የዚህ አጥቢያ ምእመናን እና ካህናት ለሁለት ተከፍለው ሲወዛገቡ ከአንድ ዓመት በላይ ፈጅቶባቸዋል። ሚኒያፖሊስ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በገለልተኛ አሥተዳደር ሥር ቆይቶዋል። ሦስት አስርተ ዓመታት ለማስቆጠር ጥቂት ዓመታትን የቀረው ይህ አጥቢያ በገለልተኛ የቦርድ አስተዳደር ሥር ቆይቶ ነበረ። 

ሆኖም ግን “የገለልተኛ አስተዳደር ይብቃን እና ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደረ መዋቅር ሥር እንቀላለቅል” የሚሉ ወገኖች አማካኝነት የዛሬ አንድ ዓመት ከሦስት ወር አካባቢ ለአስተዳደር ቦርድ ጥያቄ ቀርቦ ነበረ። በዚህም ምክንያት የአስተዳደር ቦርድ ይህንን ጥያቄ ሁለት አመለካከት ያላቸው ማለትም “ወደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር መዋቅር እንቀላቀል” የሚል አቋም ያላቸው እና “አይ በገለልተኛ የአስተዳደረር እንቆይ” የሚል አቋም ያላቸው ሁለት ቡድኖች ለአስተዳደር ቦርዱ እና ለአባላት ጥናት እንዲቀርብ ኮሚቴ አዋቅሮ ነበረ። ከሁለቱንም ወገኖች ያካሄዱትን ጥናታዊ ጽሑፍ ለአስተዳደር ቦርዱ አቅርበው በመጨረሻም ለቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት በሙሉ በነሐሴ ወር አካባቢ ጥናቱ ቀርቦ ነበረ። ጥናታዊ ጽሑፍ በቀረበት ዕለት “በድምጽ ይወሰን አይወሰን” በማለት አባላቱ ተከራክረው በመጨረሻም ካህናቱ ምእመናን ይከፋፈሉብናል በሚል ፍራቻ “ለጊዜው እንዲሁ እንዳለን በገለልተኝነት እንቆይ” አሉ። የካህናት ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ድምጽ ሳይሰጥ በገለልተኛ አስተዳደር ለጊዜው እንዲቆዪ ተስማምተው ለጥናታዊ ጽሑፍ የታደመ አባላት ድምጽ ሳይቆጠር ተበተነ። 

ከጥናታዊ ጽሑፍ በኋላም በሀገረ ቤት ቅዱስ ሲኖዶስ አስተዳደር መዋቅር ሥር እንተዳደር የሚለው ወገን ውስጥ ለውስጥ ውይይቶች ሲወያዪ ቆይተው ጉዳዪ መፍትሄ እንዲያገኝ ለአስተዳደር ቦርዱ ጥያቄያቸው በተደጋጋሚ ማቅረባቸውን የአሐቲ ተዋሕዶ ምንጮች ገልጸዋልናል። ሆኖም ግን አጀንዳው ወደ ፖለቲካ እየተቀየረ በተቃራኒው ጎን የቆሙ ወገኖች “ቤተ ክርስቲያናችንን ለወያኔ አሳልፈን አንሰጥም” የሚሉ ድምጾች እየጎላ ሄደ። አስተዳደር ቦርዱም ለሁለት ተከፈለ። በገለልተኝነት እንቀጥል የሚሉ እና በኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ አሥተዳደር ሥር እንግባ የሚሉ።

ይህ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ የአስተዳደር ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር እንግባ የሚሉ ወገኖች ውይይቶችን በተለየዪ መድረኮች ሲያካሄዱ ቆይተው እንደነበረ ምንጮጫችን ገለጸውልናል። በመጨረሻም ባሳለፍነው በመጋቢት ወር ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ከኒዮርክ እና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ከኢትዮጵያ ተጋብዘው አዳራሽ ተከራይተው ውይይቶችን አካሄደዋል። ሁለቱንም ሊቃነ ጳጳሳት በዚህ ውይይት ማግስት በዕለተ ሰንበት በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ስነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ነበረ። የቅዳሴ ስነ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስን የአርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ አማኝ ስነ ምግባር የጎደለው ተቃውሞ ከታቦተ ሕጉ ፊት ለፊት ሁለት ጸጉር ያበቀሉ አዛውንት ብፁዕነታቸውን ሲሰድቡ ተሰምቶዋል። አጸያፊ ስድብ በማሰማት ሊቀጳጳሱን ሰድበዋቸውል። ኦርቶዶክሳውያን የተዋሕዶ አማኞች በሌሎች መድረኮች ላይ እንዲህ አይነት አጸያፊ ተግባር እንዳይደገሙ መከላከል እና ምእመናን አባቶቻቸውን እንዲያከብሩ ማስተማር የመምህራኑ ግዴታ ነው። 

በመጨረሻም በገለልልተኛ አስተዳደር እንቀጥል የሚለው ቡድን “ቤተ ክርስቲያናችንን ለወያኔ አሳልፈን አንሰጥም” የሚለውን ድምጽ እያስተጋቡ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ግማሽ ያህል ምእመናን፣ሁለት ቀሳውስት እና ሁለት ዲያቆናት ያካተተ መሆኑን ምንጮጫችን ገልጸውልናል። በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀገር ቤት ያለው ቅዱስ ሲኖድስ አስተዳደር ሥር እንገባ የሚለው ቡድን አስተዳዳሪውን ጨምሮ ሦስት ቀሳውስት፣አራት ዲያቆናት፣መሉ የሰንበት ት/ቤት አባላት እና ግማሽ ያህል ምእመናን እንደሆኑ የአሐቲ ተዋሕዶ ምንጮች ገልጸዋል። በዓለ ትንሣኤ ሁለቱ ወገኖች ተለያይተው በሀገር ቤት ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር እንተዳደር የሚለው ቡድን ከቤተ ክርስቲያኑ ውጪ ሌላ በተከራዪት ቦታ አክብረው ውለዋል። የቤተ ክርስቲያኑ ጉዳይ በፍርድ ቤተ ተይዞ ውሳኔ ለማግኘት በቀጠሮ ላይ መሆናቸውን ምንጮቻችን ገልጸውልናል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ከገለልተኛ አስተዳደር ቡድን የተሰለፉትን ቀሳውስት እና ዲያቆናት ስልጣነ ክህነታቸውን ሽረዋል።የብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ስልጣነ ክህነት የሻሩበት ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። የዚሁ አጥቢያ ጉዳይ ተከታትለን የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዘግባለን ተከታተሉን። 
         
             አምላከ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ያሳየን።

5 comments:

Unknown said...

correction: It was 6 priests and 8 deacons who believe in the Unity of the Ethiopian ORthodox Tewahedo Church.

Unknown said...

Correction: Its 6 priests and 8 deacons who believe in the Unity of the Ethiopian ORthodox Tewahedo Church.

Anonymous said...

ስልጣነ ክህነቱ የተያዘባቸው ካህናት ገብተው እየቀደሱ ነው እግዚኦ ድፍረት ትግሉ ከማን ጋር ነው ከመንፈስ ቅዱስ ወይስ ከሰው ለማንኛውም ልቡና ይስጣቸው። በመጀመሪያም ሊቀ ጳጳሱ በደብዳቤ፣ በስልከ፣ ደጋግመው ከመከሩና ካስጠነቀቁ በኋላ የወሰዱት እርምጃ ነው በተለይ እንደ መንግሥቱ ኃ/ ማርያም ወይም እንደ ቀድሞው ፓትርያርክ በብዙ የማዕረግ ስሞች ካልተጠሩ የሚያኮርፉት " መልአከ ኃይል, ሊቀ ትጉሃን, መሪጌታ, ቀሲስ" የአሁኑ አቶ ጌታሁን መኮንን ተመክረውና ተዘክረው በካህናት ወንድሞቻቸው ተለምነው አሻፈረኝ በማለታቸው የተወሰደባቸው እርምጃ አግባብ ነው እላለሁ ድሮም ስሜታዊ ሆኖ ለጉራና ለጥቅም የሚደረግ ማስተዋል የተለየው እርምጃ የመንፈስ ቅዱስን ሀብት እንደሚያሳጣ የታወቀ ነው ። አሁንም " አቶ ጌታሁን እና ተከታዮቹ ለአሜሪካ ዶላር ክህነታቸውን የሸጡ ካህናት" አቶ አሰፋ ኃይሌ, ቶማስ ወ/ ጊዮርጊስ እና ሰረገላ ኤልያስ የቆሙለት አላማ ስህተት መሆኑን ተረድተው በመፀፀት ሊቀ ጳጳሱን በያነጋግሩ መልካም ነው እላለሁ ካልሆነ እነሱ ያላከበሩትን ስልጣነ ክህነት ተሳዳቢዎቹ / ፖለቲከኞቹ/ እነ አቶ ታዬ, እነ ሻምበል… እነ ኰሎኔር … አክብረው ያኖሩናል ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው። በሰላም ዋሉ!

Unknown said...

'ዘአውገዘ በከንቱ ውጉዝ ውእቱ'

Anonymous said...

ወንድሜ "ከበደ ቦጋለ" ውግዘት እና የሥልጣነ ክህነት መያዝን ለይተው እንዲመለከቱ እመክርዎታለሁ። ወይም ሥልጣነ ክህነት የተያዘባቸው ደብተራ ጌታሁንን ይጠይቁ እርስዎ እንዳሉት በከንቱ አለመሆኑን ይነግሩዎታል የቅዳሜ ሥዑር እለት ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ጋር ደውለው ብቻየን ቀረሁ ይፍቱኝ እያሉ ሲያለቅሱ እንደዋሉ ይነግሩዎታል።በደህና ዋሉ!