Thursday, October 16, 2014

"ማኅበሩ አሳዘነኝ ! በላዉ የምር አንጃቴን በላው" ከመምህር ዘመድኩን በቀለ ፌስ ቡክ የተገኘ

ማኅበሩ አሳዘነኝ ! በላዉ የምር አንጃቴን በላው ።
ከዛሬ 2 ዓመት በፊት ዕድሌ ይሁን ወይም ክፉ አመሌ አይታወቅም በሆነ ጉዳይ አንድ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ቁጭ ብያለሁ ። ከእኔ ጋር ደግሞ እድሏ ሆኖ ማረሚያ ቤት ብቻ ከእኔ ጋር መግባት ሲቀርባት ሌላው ጋር ግን በየጊዜው በየቦታው የምትንከራተተው ውዷ ባለቤቴም አብራኝ ነበረች ። የዚያን ዕለት ድርጊት መቸም ቢሆን አልረሳውም ። አንዱ ጥጋበኛ ባለጊዜ ሙሉ ለሙሉ የሚያምረውን የሚሊቴሪ ልብሱን ግጥም አድርጐ ለብሶ በማያውቀው እና በማያገባው ጉዳይ ለእኔ ክብርት በሆነችው በልጆቼ እናት በውዷ ባለቤቴ ፊት በአደባባይ ሕዝብ እያየው ጠፍጥፎ ጠፍጥፎ ወግሮ ወግሮ ይለቀኛል ። በወቅቱ ቦታው ላይ ደንብ አስከባሪዎች ነበሩ ። ህዝቡም ነበረ ። የከተማዋ ማለትም የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትም ነበሩ ። ከባለቤቴ የድረሱለት ጩኸት በቀር ሁሉም ደፍረዉ ከወጋሪዬ እጅ ሊያስጥሉኝ አልፈቀዱም ። ተስፋ ስቆርጥ የሚገላግለኝም ሳጣ ፣ ደግሞስ ባለቤቴም ሆነች በዙሪያዬ ከብቦ በመቆም ትርኢቱን የሚመለከተው ህዝብ ,,,,,,,, ውይ ሲያሳዝን እንዲሁ አንዳች ሳይመልስ ተቀጥቅጦ እኮ ሞተ ብለው የቡና መጠጫ ሳያደደርጉኝ በፊት እርምጃ ወሰድኩኝ ።,,,,,,,,,, እንደው ወጋሪዬ ሳያስበው ድንገት ዝልል ብዬ አባቱን እንደናፈቀ ህጻን እጆቼን አንገቱ ላይ ጠምጥሜ እግሮቼን ደግሞ በወገቡ ላይ አቆላልፌ ጥርሴን ደግሞ በአንገቱ ደምስር ላይ ሰክቼ እንደማስቲሽ ደግሞም እንደመዥገር ከላዩላይ በመጣበቅ ከላዩላይ ልክክ አልኩበት። ሊያወርደኝ ወደላይ ሲል እኔም አቡሬው ወደላይ ወደታች ወደጎን ወደፈለገበት ሲገላበጥ እኔም ግጥም አድርጌ በመያዝና በእጁ ሊመታኝ ሲሞክር ደግሞ በጥርሴ የያዝኩትን የወጋሪዬን ደምስር ጠበቅ በማድረግ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ቢያደርግ ስሩን በጥሼ ከእኔ በፊት የሞትን ፅዋ እንደሚጎነጭ በተዘዋዋሪ መንገድ በጥርሴ መልእክት እያስተላለፍኩ መጨረሻዬን መጠባበቅ ጀመርኩ ። አስቀድሞ ሁሉንም አስፈራርቶ ስለነበር ማን ይገላግለው ። በዚህ ሁኔታ እሱ አፉ ማውራት ስለለሚችል ቢለምነኝ ቢለማመጠኝ ልሰማው? አረ አላበድኩም እንዲያውም በስፖርትና ከእኔ በሚሰበሰበው ግብር ያለ ሐሳብ እየበላ ያፈረጠመው ሰውነቱ ተመቸኝ መሰል ልጥፍ ብዬበት ቀረሁ ። ቆይቶ ፖሊሶቹ ይሁኑ ህዝቡ አላውቅም ብቻ ፌደራል ፖሊሶች ተደውሎላቸው በመኪና መጡ ።

ፌደራል ፖሊሶች ሲመጡ ሕዝቡም ፣ ደንብ አስከባሪዎችም ፣ የአዲስ አበባ ፖሊሶችም ፣ ብቻ ምንአለፋችሁ ሁሉም ጥፋተኛው እኔ እንዳልሆንኩ አስረድተው ፖሊቹም እግዚአብሔር ይስጣቸው ተቃቅፈን ወደቆምነው ወደ እኔና ወጋሪዬ ዘንድ በመምጣት እጄን ከአንገቱ እግሬን ከወገቡ ጥርሴንም ከደም ስሩ አላቀው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን ። አሁን ህዝቡም ፖሊሱም አጨበጨቡልኝ ። አቤት የኛ ህዝብ የሚገርም ነው ያሸነፋችሁ ፣ ያገኛችሁ ሲመስለው ማጨብጨብ ሲችልበት ። እኔም ፌደራሎቹ ባይመጡና ባይገላግሉኝ የግዴን ነው እንጂ የምር ድክም ብሎኝ ነበር ።መቸም እንደዚያን ቀን ቀጭን ሆኜ መፈጠሬን ያመሰገንኩበት ቀን ገጥሞኝ አያውቅም ። እየሳቃችሁ ነው አይደል? ሀሀሀሀሀሀሀሀሀሀ ሳቁ እንጂ እንኳን እናንተ እኔም ሆንኩ በወቅቱ እሪ እያለች ታለቅስ የነበረችው ባለቤቴ ሁኔታውን ባስታወስን ቁጥር በተለይ ባለቤቴ ወገቧን እስኪያማት ድረስ ነው የምትስቀው ።
የሆነው ሆኖ በመጨረሻ እራሱን በውጪ ከህግ በላይ ቆልሎ የነበረው ወጋሪዬ በአቃቤ ህግና ፣ በመረማሪ ፊት በፖሊስ ጣቢያ ወስጥ ራሱን ባገኘ ጊዜ ትንኝ አከለ ።እኔም አጥፍቻለሁ ይቅር በለኝ ባለኝ ጊዜ በሁሉ ፊት ክስ እንደማልመሰርትበት ተናግሬ በዕለተ አርብ በቀራንዮ አደባባይ ከአምላኬ የተማርኩትን የይቅርታ ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ በድል አድራጊነት መንፈስ ተሞልቼ በደስታ ከጣቢያው ብዙ ዘመዶች አፍርቼ ወጣሁ ።
የዚያን እለት ደብዳቢዬን ባልከሰውም አስደብዳቢዬ ግን ከቦታው ነበረ ። ከአሁን አሁን እኔን ይከሰኛል ብሎ ቢጠብቅም እኔ መብቴን እንዴት እያስከበርኩ እንደሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እያሳየሁት ሳለ ጉዳያችንን ጨርሰን ልንወጣ ስንል አስደብዳቢዬና አቃቤ ሕጉ ኃይለቃል ይለዋወጣሉ ። አቃቤ ሕጉ አሰደብዳቢዬ የዘረጋለትን 100 ብር እያሳየ በህግ አምላክ ልብ በሉ አላውቀው አያውቀኝ ጉቦ እየሰጠኝ ስለሆነ እከሰዋለሁ ብሎ ሁኔታውን እናይ የነበርውን ሁሉ እማኝ አድርጎ ከሰሰው ። ክሱ የተጀመረው ከ2 ዓመት በፊት ቢሆንም ዛሬ ለምስክርነት ተጠርቼ ሄጄ ያየሁት ነገር ግን ከላይ በርዕሴ ላይ የተጠቀምኩትን ርዕሰ ኃሳብ በውስጤ አመጣውና ጻፍ ጻፍ ብሎ እጄን ቢበላኝ ጊዜና ይኸው ጻፍኩት እና ተንፈስም አልኩኝ ።
በተከበረው ፍርድቤት ምን ዐየሁ መሰላችሁ።
1… ቤቱን ራሱን ። ጣርያና ግድግዳው ወለሉና ወንበሩ ። እንደማንኛውም ቤት ተመሳሳይ ቢሆንም ግን ከእኔ ቤት በተለየ መልኩ ፍርድ ቤት የሚል ማዕረግ ስላለው ያስፈራል ። ሞገስም አለው ።
2, ሦስት ዳኞች ። አቤት ሲያስፈሩ ። ዳኞቹ ወንዶችም ሴቶችም አሉበት።
3, አቃቤ ህግ ። በመንግሥት ወገን ሆኖ ለመንግሥት አንዳንዴም ከግለሰቦች ወገን ሆኖ የሚሟገት ።
4, ጠበቆች ። የከሳሽም የተከሳሽም ተሟጋቾች ።
5, ምስክሮች ። ወንጀል የተባለው ሲፈጸም በቦታው የነበሩ የከሳሽም ፣ የተከሳሽም ወ ገኖች ።
6, ከሣሽ ። ተበድያለሁ ባይ ። አቤቱታውን አቅራቢ ።
7, ተከሳሽ ። ወንጀሉን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረው አካል። እዚህ ለይ ተከሳሽ ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን መረጃዎች መርምሮ ወንጀለኛ እስካላለው ድረስ ወንጀለኛ ያለመባል መብትም አለዉ ። ደስ ሲል ።
8, ተመልካቾች ። ቤተሰብ ፣ ዘመድ አዝማድ ፣ ጓደኞች ፣ ጉዳዩ የብዙሃንን ቀልብ የሚስብ ከሆነ ደግሞ የዲፕሎማቲክ ሰዎችን ፣ አልፎም ተርፎም ከዚህም በላይ የፍርድ ሂደቱን ግልጽና ፍትሃዊ ለማድረግ ሲባል ጋዜጠኞችም ታዛቢዎችም ይጋበዛሉ። አሁንም ደስ ሲል።
እናላችሁ እኔ እዚያ የተከበረው ፍርድ ቤት ቁጭ ብዬ ሰሞኑን የክስ መዓት የወረደበት አንድ ስመጥር ማኅበር ከፊቴ መጥቶ ድቅን አይል መሰላችሁ። " ምስኪን " ስለምን ምስኪን አልከው ብትሉኝ ነገሬን እንዲህ ላስረዳ ።
ማኀበሩ በታላቋ ሀገር የተወለደ ፣ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ። ወላጆቹም ፣አሳዳጊዎቹም ከእኛው ዘንድ ያሉ ። ኮትኩተው በጥሩ ሥነ ምግባር እያደገ ያለ የ3ሺህ ዓመት ዕድሜ ባለፀጋዋ የእማማ ኢትዮጵያ የበኩር ልጅ የሆነችው 2 ሺህ ዘመን ያስቆጠረችው የኮረዳዋ ውቧ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዚህ ያለንበት ክፍለ ዘመን ገና 20ኛ ዓመቱን በቅርቡ ያከበረ የምናውቀው የእኛው ልጅ ነው።
ይህ ልጃችን ታዲያ ለገዳማውያን፣ለአብነት መመምህራንና ተማሪዎች ፣ በአጠቃላይ ለቤተክርስቲያናችን ሁለንተናዊ ለውጥ በዚህ የልጅነት እድሜው ላይም ሆኖ እንኳን ከአቅሙ በላይ ይለፋል። በዚህ ብቻ መች ያበቃል ለዚህች ከጥንት ጀምሮ ሞቷንና ውድቀቷን ምራቃቸውን እያዝረበረቡ ለሚጠብቁና ለሚመኙላት የውስጥም ሆነ የውጭም ጠላቶች አልመች ያለም ነው ። ጡት ነካሾችና የውስጥ ባንዳዎች የሚሠሩትን ህገወጥ ሥራ ሲያሻው በቪድዮ ፣ ሲያስፈልግ በድምጽ ፣ ደግሞ ሲያስፈልግ በዶክመንት እያቀረበ መንገዳቸውን ሲዘጋባቸው ጊዜና እኛና ቅዱስ ሲኖዶሳችን ደስ ሲለን እነ እገሌ እና እነ ግሪሳዎቹ ደግሞ ከፋቸው ። ከፋቸው ከፋቸው እና ቀን ይጠብቁ ገቡ ። ያቀን ታዲያ አሁን የመጣ ስለመሰላቸው ጎበዝ ነገ የሚመጣውና የሚሆነው አይታወቅም በቶሎ ሕይወቱን እንቅጨው ብለው ተነሱ ።
አስቀድመው ግሪሳዎቹን በመላክ ህዝቡ ማኅበሩን እንዲጠላ ። በኦድዮም በቪድዮም ፣በቲቪም በጋዜጣም በግልም በቡድንም ፣በህልምም በውንም በብርቱ ደከሙ ። መንገድ ጠራጊዎቹ ግሪሳዎች የግሪሳዎቹም አባላት አስቀድመው የዛሬውን ትርኢት ፕሮቫውን አሳዩን ። እንዲህም አሉን ። " ማኅበረ ቅዱሳን በራችሁን ይዝጋው !!! እንዲህ እንዳሳደዳችሁን… ቆዩ ታገኙዋታላችሁ… … እንግዲህ ባገኘነው መድረክ ሁሉ እንዋጋችኋለን ብለው ነገሩን። እንደውም በዲላ የማኅበሩን ህጋዊ ቢሮ አንዱ ግሪሳ በአደባባይ ተናግሮ አስዘጋው።
አረ ይህ ነገር አካሄዱ አደጋ አለው ብዬ እኔም በወቅቱ ህገወጥ ነው ብዬ ያመንኩበትን ጉዳይ "አርማጌዶን "ብዬ ባወጣው ለካስ ግሪሳዎቹ የተማመኑትን ተማምነው የተቀመጡ ላታቸውን ከበረቱ ውጪ የሚያሳድሩ ኑረዋል ወስደው 3ወር ቃሊቲ አስከረቸሙብኝ እና ጉልበታቸውን ለማሳየት ተፍጨረጨሩ ። እንዲህ እንዲህ እያልን ነገሮችን እየተመለከትን ከሰሞኑ ደረስን ።
ሰሞኑን ታዲያ ማኀበረ ቅዱሳን መከሰሱን ሰማሁና የወሬ ሱሴ አልለቅህ ቢለኝ የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል እግረመንገዴንም ደግሞስ ማን ያውቃል ስህተትም ሊኖርበት ይችላል በሚል እሳቤ በችሎቱ ታዳሚ የነበሩትን ብጠይቅ ።የችሎቱ ታዳሚ የነበሩት እንዲህ ብለው ነገሩኝ ።
በዕለቱ ዳኞች ተሟልተው አልቀረቡም ፣ ተከሳሽም አልተጠራም ፣ ዐቃቤ ሕግም ጠበቆችም በቦታው የሉም ። የተከሳሽ ወላጆችም ወዳጅ ዘመዶችም ፣ጓደኞችም ፣ ታዛቢዎችም ፣ በቦታው አልነበሩም ። የነበሩት ከሳሾች ብቻ ነበሩ ብለው ሲነግሩኝ ጊዜ በብርቱ ሐዘን ገባኝ ።
ማኅበሩ ሐገር ለቅቆ ሂዶ እንደሆነ ብዬ ብጠይቅም አረ በጭራሽ መኖርያ ቤቱ እኮ እዚያው ችሎቱ ከሚሰጥበት አካባቢ ነው አሉኝ ። እናም ማኅበሩ አሳዘነኝ ። ሆዴንም በላው ። አንጀቴ አልችል አለ ።
የሚገርመው እኔን ጨምሮ ግሪሳዎቹ ሳንቀር ብዙዎቻችን ዛሬ ላይ ሰባኪ መምህር ተብለን ለመጠራታችን ከመንፈሳዊ ኮሌጅ የጥቂት አመታት ቆይታ በተጨማሪ የማኅበረ ቅዱሳን የኅትመት ውጤቶችን እንዴት ልዘንጋቸው። የዲን ዳንኤል ክብረትን የብዕር ትሩፋት የሆኑትን ቬኒስያን፣የታተመ ፍቅር ፣ የነ ቀሲስ ደጀኔን ፣ የብርሃኑ ጎበናን ፣ እሸቱ ወንድማገኘሁን ስብከቶች መቼም ቢሆን አንረሳውም ።
ከእኔ በላይ ግን እግዚአብሔር ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ፣የኢትዮጵያ ገዳማትና ገዳማውያን ። የኢትዮጵያ አድባራት ካህናትና ዲያቆናት ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ፣ መላው ኦርቶዶክሳውያን የተዋህዶ ልጆች የማኅበሩን መልካም ሥራዎች ለትውልድ ስናዘክር እንኖራለን ። የሚታይ የሚዳስስ ሥራ ሠርተዋልና ። አይዟችሁ ወንድሞቼ ።
አሁን ፅጌ ስጦታው ደስ ይበልህ ! እነ አባ ዮናስ ደስ ይበላችሁ ! ግሪሳው ተሃድሶ ኹላ ደስ ይበላችሁ ! እነ ፖልቫሎስኪ ደስ ይበላችሁ ሳትደክሙ ብዙም ኃይል ሳታባክኑ ያ እንደ እሣት የሚፈጃችሁን ማኀበር የሚነቀንቅ አካል ከውስጥ ስላገኛችሁ ።
ማኀበረ ቅዱሳን አሳዘነኝ የገና ዳቦ ስለሆነ ። ከታችም ከላይም እሣት የሚነድበት። በሐገር ውስጥ ያሉት አክራሪ ፣ አሸባሪ ፣ ሲሉት በውጭ ያሉቱ ደግሞ ወያኔ የወያኔ ተላላኪ ሲሉት ። አሳዘነኝ የምር አሳዘነኝ ።
ልብበሉ ማኅበሩ አይሳሳትም አላልኩም ቢሳሳትም ተፈዘጥሮአዊ ነው ። ደግሞም የሰዎች እንጂ የመላእክት ስብስብ አይደለም ። የፈለገ ሺህ ጊዜ ቢሳሳት አሁን ከሳሾች በሚከሱት ክስ ግን 100000000000000000000000000000000000000 ጊዜ እናገራለሁ እጁ የለበትም ።
ይህን ሁሉ የጻፍኩት የማኀበሩ የተመዘገበ አባል ሁኜ አይደለም ። ነገር ግን ህግ ባለበት ሐገር ላይ ተከሣሽ ሳይቀርብ የሞት ፍርድ ለመፍረድ ከሳሾች ሲሯሯጡ ባይ ጊዜ ጨንቆኝ ይህ ነገር ነግ በእኔ ነው ብዬ ብፈራ ጊዜ ነው መጻፌ ። አ
እናንተስ ምን ትላላችሁ Like ማድረጉን ተውት እና Share እና Comment ላይ አተኩሩና የልባችሁን አውጥታችሁ እንወያይ ። የምትሰድቡኝ ሰዎችም ብትሆኑ አደራ ደረጃ የለኝም እንጂ ደረጃዬን የሚመጥን ስድብ ስደቡኝ ። የምታስፈራሩኝም ቢሆን ማስፈፈራራቱን በልክ አድርጉልኝ ። አደራ አደራ አደራ ።
እፎኦኦኦኦይይይይይይይይይ ተገላገልኩት እንዴት ቀለለኝ መሰላችሁ። ለዛሬ አበቃሁ ። ይቆየን።
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
5/2/2007 ዓም
ከፍርድ ቤት መልስ
በመሐል አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ

5 comments:

Anonymous said...

አንት ገዳፈኛ የወሬ አነፍናፊ ደግሞ ከየት መጣህ አንትና ማህበሩ የሰራችሁት መቃብር አፍ ጦሰኛ ዝም ብለህ ተቀመጥ አነንተ ብሎ አዛኝ እንዳት ገባ ደግመህ ዋ

Anonymous said...

ደረት ምታልት

Anonymous said...

Ayi stefeh motehal zemedkun. Casset alshet sileh mk tetgah. Akom yelelh huket balebet bota hulu ejeh yalebt. Yehager, yebetekerstyan endihum yebalebeth ena yeljogh telat malet ant neh.

Anonymous said...

እውነታው ይኸው ነው። የእውነተኛው ተዋህዶ ልጅ ማህበረ ቅዱሳን ጉዳይ ለሹመኛ ፕሮቴስታንት፣ ለመናፍቁ፣ ለተሃድሶ፣ ለፖለቲከኛው፣ ለሃሰተኛ ካባ ለባሽ ሁላ አልመች አለ! እንግዲህ ምን ይደረግ!! ጉዳዩ ከፈጣሪ ጋር ነው።

Anonymous said...

እውነታው ይኸው ነው። የእውነተኛው ተዋህዶ ልጅ ማህበረ ቅዱሳን ጉዳይ ለሹመኛ ፕሮቴስታንት፣ ለመናፍቁ፣ ለተሃድሶ፣ ለፖለቲከኛው፣ ለሃሰተኛ ካባ ለባሽ ሁላ አልመች አለ! እንግዲህ ምን ይደረግ!! ጉዳዩ ከፈጣሪ ጋር ነው።